Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመጀመርያው የሊዝ ፋይናንስ ኩባንያ በ200 ሚሊዮን ዶላር ማሽኖች ሊያስገባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ሊዝ የተሰኘው በኢትዮጵያ የመጀመርያው የፋይናንስ ሊዝ ኩባንያ በመጪው ሁለት ዓመት 200 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የተለያዩ የእርሻ፣ የሕክምናና የማምረቻ መሣሪያዎች እንደሚያስገባ አስታወቀ፡፡

አትዮ ሊዝ አፍሪካን አሴት ፋይናንስ ካምፓኒ በተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ በ400 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ለእርሻ፣ ለሕክምናና አምራች ኢንዱስትሪ የሚውሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች በኪራይ ለማቅረብ የሚያስችለውን የሥራ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አግኝቷል፡፡

ኢትዮ ሊዝ በይፋ ሥራ መጀመሩን ለማስተዋወቅ ነሐሴ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ባዘጋጀው መግለጫ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ግርማ ዋቄ፣ ኩባንያው ለአርሶ አደሮች ዘመናዊ ትራክተሮችና ኮምባይነሮች በኪራይ በማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡ ለሆስፒታሎች እንደ ኤምአርአይና ሲቲስካን የመሳሰሉ ዘመናዊ መሣሪያዎችን፣ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተለያዩ የማምረቻ መሣሪያዎችን በኪራይ እንደሚያቀርብ አክለዋል፡፡ ደንበኞች መሣሪያዎችን በኪራይ ወስደው በሒደት የንብረቱ ባለቤት መሆን እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

በ1990 ዓ.ም. የወጣው የሊዝ ፋይናንስ ሕግ የውጭ ባለሀብቶች በሊዝ ፋይናንስ ዘርፍ እንዲሰማሩ ይፈቅዳል፡፡ ሕጉ በ2005 ዓ.ም. የተሻሻለ ቢሆንም፣ የውጭ ኩባንያዎች በዘርፉ ሳይሰማሩ ቆይተዋል፡፡ ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ኢትዮ ሊዝ የመጀመርያው የሊዝ ፋይናንስ ኩባንያ ለመሆን ችሏል፡፡ ኩባንያው 14 ሚሊዮን ዶላር የመነሻ ካፒታል እንደመደበ፣ በመጪው ሁለት ዓመት 200 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ማሽኖችን ለማስገባት ማቀዱን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ የሊዝ ፋይናንስ አሠራር ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡ አገልግሎቱ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ አክለዋል፡፡

በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር፣ ኢትዮ ሊዝ ለኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ዕድል ይዞ እንደመጣ ተናግረዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ የእርሻ፣ የማምረቻ፣ ግንባታ መሣሪያዎች እንዲሁም አስተማማኝ የፋይናንስ ሞዴል የሚጠቀምና የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና የማይጨምር አሠራር እንደሆነ አምባሳደር ሬይነር አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህ አሜሪካ በኢትዮጵያ የምታደርጋቸው ጥራት ያላቸው ኢንቨስትመንቶች ሁነኛ ምሳሌ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ኢትዮ ሊዝ በውጭ አገር ባለሀብቶች የተመሠረተ የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ ንግድ ተቋም መሆኑን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ትልቅ ተሳትፎ እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡ ኩባንያው ለኢኮኖሚ ዕድገት የራሱን ሚና እንደሚጫወትና ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የገቢ ምንጭ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ ሊዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግሩም ፀጋዬ ኩባንያው የራሱን የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ተጠቅሞ የተለያዩ የግብርና፣ የሕክምና፣ የግንባታ መሣሪያዎች እንደሚያመጣና ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች በብር የሚያከራይ በመሆኑ ለንግዱ ማኅበረሰብ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ኢትዮ ሊዝ እንደ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ተጨማሪ የንብረት ዋስትና እንደማይይቅና በኪራይ የሚቀርበው ማሽን ራሱ በዋስትናነት የሚያዝ እንደሆነ የገለጹት አቶ ግሩም፣ ይህ አሠራር ንብረት ያላፈሩ ጀማሪ ባለሀብቶችን እንደሚያበረታታ ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው ከአገር ውስጥ ምንም ዓይነት ብድር እንደማይወስድ የገለጹት አቶ ግሩም፣ ለባለሀብቶች የሚያቀርበው መሣሪያዎች በረዥም ጊዜ የኪራይ ውል እንደሆነና በውሉ ማብቂያ ባለሀብቱ ማሽኑን በባለቤትነት መጠቅለል የሚችልበት አሠራር እንደሚዘረጋ አስረድተዋል፡፡ በዚህም ዕድል በመጠቀም ባለሀብቶች ለማሽን ግዥ የሚያወጡትን ከፍተኛ ገንዘብ ለመሥሪያ ካፒታል ሊያውሉት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ማሽኑን እኛ በውጭ ምንዛሪ ገዝተን በረዥም ጊዜ በሚከፈል የኪራይ ውል የምናቀርብላቸው በመሆኑ ካፒታላቸው አይታሰርባቸውም፤›› ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የአርኪ ውኃ አምራች ኩባንያ ‹‹ኤስቢጂ››፣ አርሾ ሜዲካል ላቦራቶሪና በአርሲ ዞን በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ባለሀብት ከኢትዮ ሊዝ ጋር ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች