በውብሸት ሙላት
አሁን ሥራ ላይ ያለውን የወንጀል ሕግ ስንመለከት እስረኞችን ለማስተማር ትኩረት የሰጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡
የቅጣት ዓላማ ከአሁን በፊት በነበሩትም ሆነ አሁን ባለው የወንጀል ሕግ ውስጥ በተየያዩ መልኮች የተቀመጠ ነው፡፡ ስለወንጀሎቹና ስለቅጣታቸው አስቀድሞ በግልጽ የሚደነግገው ለማስጠንቀቅ ነው፡፡ አንድ ሰው ሕግ ሲጥስ የሚጠብቀው ቅጣት ምን እንደሆነ ካወቀ ከዚህ ድርጊቱ ይቆጠባል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ምናልባት ትርፍና ኪሳራቸውን አመዛዝነው በማናለብኝነት ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች አይኖሩም ማለት ባይቻልም፣ አብዛኛው ሰው ሕግ ጥፋት ነው ያለውን ነገር ሆነ ብሎ ከመፈጸም ይቆጠባል ተብሎ ግምት ይወሰዳል፡፡ ይህ ዓላማ አስቀድሞ መከላከል የሚለውን የወንጀል ሕጉን ግብ ለማሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የወንጀል ሕግ ካስቀመጣቸው የቅጣት ዓላማ ለማስተማር ትልቅ ትኩረት የሰጠ መሆኑን፣ ከመግቢያው ጀምሮ ያለውን ሐሳብ በማየት መገንዘብ እንችላለን፡፡ የሕጉን ማስጠንቀቂያ በመተላለፍ ወንጀል የሚፈጸሙ ሰዎች ተገቢውን ቅጣት ማግኘት ያለባቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ወንጀል አድራጊዎች ተቀጥተው እንዲታረሙ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
ነገር ግን የሚጣለው ቅጣት ተመጣጣኝ ካልሆነም ሌሎች ወንጀሎችን መፈጸም ለአንዳንዶች አትራፊ ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በሺሕ የሚቆጠር ንብረት የሰረቀ ሰው በቀላል የሚቀጣ ከሆነ በጀመሩት አፀያፊ ሥራ ውስጥ ያሉ እንዲገፉበት፣ ወይም ይህንን ለመፈጸም ፈራ ተባ ይሉ የነበሩ ሰዎችም እንዲሳተፉበት ሊያደርግ ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ቅጣት ውጤታማ የሚሆነው ተመጣጣኝና አስተማሪ ሆኖ የሚጣል ከሆነ ብቻ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ መሠረት መለየትና ማስወገድ በተለያዩ መንገዶች የተንፀባረቁ የቅጣት ዓላማዎች ናቸው፡፡ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ አንድ ላይ እንደተገለጸው ወንጀል አድራጊዎች ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፣ ወይም ተጨማሪ ወንጀል እንዳይፈጽሙ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ የሚል አገላለጽ እናገኛለን፡፡ ለማኅበረሰቡ እጅግ አደገኛ ናቸው ተብለው የሚታወቁ ወንጀል ፈጻሚዎች ከባድ የተባለውን ቅጣት ሊቀጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ አጥፊዎች ለአጭር ወይም ለረጅም ጊዜ ታስረው ከማኅበረሰቡ የሚለዩበት፣ ወይም ሞት ተቀጥተው ሙሉ በሙሉ ከኅብረተሰቡ የሚወገዱበት ሁኔታ የሚያጋጥም ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም መለየትና ማስወገድ የወንጀል ቅጣት ዓላማዎች ተደርገው ተወስደዋል፡፡
ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠና ቅጣት ያረፈባቸው ወንጀለኞች የሚሄዱት ወደ ማረሚያ ቤት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በፌዴራልም ሆነ በክልል ማረሚያ ቤቶች አሉ፡፡ ዋናው የማረሚያ ቅጣት እስር ወይም የእስር ቅጣት ነው፡፡ ማረሚያ ቤቶች ግን ቅጣት ማስፈጸሚያ ብቻ ሳይሆኑ፣ ተቀጪው ታርሞ ጥሩ ዜጋ ሆኖ እንዲወጣበት ሊሠሩ እንደሚገባ የታወቀ ነው፡፡
በእስር መልክ የሚፈጸም ቅጣት እንዲያሳካቸው የሚታሰቡ የተለያዩ ግቦች አሉት፡፡ አንደኛው ወንጀለኞችን ከኅብረተሰቡ በመለየት ድጋሚ ወንጀል እንዳይፈጽሙ መከላከል ነው፡፡ ይሁንና እስራትን የቂም በቀል መወጫና የብቀላ መሣሪያ አድርጎ የሚመለከተው የኅብረተሰብም ክፍል ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታም ኅብረተሰቡ ፍትሕ እንደተደረገ ይቆጥራል፣ ይሰማዋል፡፡
ሌላው ግብ ወንጀለኞች ራሳቸውን አርመውና አስተካክለው ሕግና ሥርዓት አክባሪ ሆነው ለመውጣት ዕድል የሚያገኙበት መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ትምህርትና ሥልጠና፣ የሥራ ዕድል፣ ወዘተ በማረሚያ ቤት ውስጥ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ በሥራቸው ገቢ ያገኛሉ፡፡
እስረኞችን በማረም ረገድ፣ የሃይማኖት ተቋማትም በእነዚህ ማረሚያ ቤቶች በመገኘት መልካም ሥነ ምግባርን ለማስተማር ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ወንጀለኛው በቆይታው መማሩና መሻሻሉ ከታየ በአመክሮ የሚለቀቅበት ሁኔታም አለ፡፡
እስረኞችን በማስተማርና በማረም ረገድ ማረሚያ ቤቶች ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ የታወቀ ነው፡፡ በራሳቸው የሚወስኑት የወንጀል ቅጣት ስለሌለ፣ ፍርድ ቤቶች ወስነው የሚልኩላቸውን በአግባቡ በማስፈጸም ታራሚዎች ተመልሰው ወደ ኅብረተሰቡ በሚቀላቀሉበት ጊዜ፣ የወንጀል መሥራት አስተሳሰብን በመተው ሰላማዊነትን ባህርያቸው እንዲያደርጉ ነው፡፡
ከዚህ ባለፈም በጥቅሉ እስረኞች ከኅብረተሰቡ ተለይተው በማረሚያ ቤት በማሳለፍ የኅብረተሰቡን፣ የአገርንና የመንግሥትን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡ የተፈረደባቸውም ይሁኑ በሌላ ደረጃ ላይ ያሉ፣ በቆይታቸው ታርመውና ተምረው ይወጡ ዘንድ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን ገንቢ የሆኑ ሥራዎች ላይ እንዲያውሉ ማመቻቸት የማረሚያ ቤት ኃላፊነት ነው፡፡ የሥነ ልቦና ምክርም ሊመቻች ይገባል፡፡ መልካም ዜጋ ሆነው እንዲወጡ የሚያግዙ ተግባራት ማድረግ የግባቸው አካል ነው፡፡ ስለሆነም ማረሚያ ቤቶች ተልዕኳቸው አጥፊዎች በቂ በሆነ የተሃድሶ አገልግሎት አግኝተው ከጥፋታቸው ተፀፅተው መልካም ዜጋ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ደጋጋሚ ወንጀለኝነትን (Recidivism) በመቀነስ የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ ነው፡፡
በጥበቃ ሥር ያሉና የታሰሩ ሰዎች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 እና ከተረጋገጠላቸው ሥነ ሥርዓታዊ መብቶች በተጨማሪ፣ የአካል ደኅንነት መብቶቻቸው ከማንኛውም ኢሰብአዊና ጭካኔ ከተሞላበት አያያዝ የመጠበቅ መብት አላቸው፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 21 ላይ እንደተገለጸው ከትዳር አገራቸው፣ ከጓደኛና የቅርብ ዘመድ ጋር፣ እንዲሁም ከሃይማኖት አማካሪና ከጠበቃቸው ጋር የመገናኘትና የመጎብኘት ዕድል ሊመቻችላቸው እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ከሕገ መንግሥቱም ባለፈ፣ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ላይም ለታራሚዎች በርካታ መብቶች ጥበቃ ተሰጥቷቸው እናገኛለን፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የተለያዩ ውሳኔዎችን በተለያዩ ጊዜያት አሳልፏል፡፡
የታራሚዎች መብት ብዙ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ትኩረት የሆነው የመጎብኘት መብት ስለሆነ ወደ እሱ እንሻገር፡፡ ከላይ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 21 (2) ላይ ታራሚዎች ከትዳር አጋራቸው ጋር የመገናኘትና የመጎብኘትም ዕድል ሊመቻች እንደሚገባ ጠቅሰናል፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ነጥብ “መጎብኘት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ምንን ነው? ይዘቱ እስከምን ድረስ ነው? በእርግጥስ የእስረኛ መብት ነውን? እስረኛ የትዳር አጋርን በሚመለከት ያልታሰረው/ችው የትዳር አጋርስን ምን መብት አላት? ትዳር መያዝ ለቤተሰብ ምሥረታ ከፍተኛ ሚና ስላለው ቤተሰብን በመጠበቅ ረገድ የመንግሥትስ ግዴታ ምን ሊመስል ይገባል? እስረኛን ታርሞና ተምሮ ወደ ኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲቀላቀል በተለይ በትዳር አጋር የሚረገው ጉብኝት ምን ሊሆን ይገባል? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡
እዚህ ላይ መገናኘት የሚለውን የተውነው በእንግሊዝኛው ‹‹Communicate›› የሚለውን ለመግለጽ ጥቅም ላይ ስለዋለ ነው፡፡
እስረኛን በሚመለከት መጎብኘት የሚለው የሚያመለክተው በሌሎች ሰዎች መጠየቅን ነው፡፡ ጥየቃው በተለያዩ ሰዎች ሊሆን ይችላል፡፡ ጥየቃ ማግኘት፣ መወያየት፣ ማውራትና የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡ አንድ እስረኛ በማን በማን ሊጎበኝ ይችላል? ወይም የመጎብኘት መብት አለው? የሚለውን እንደየአገሮቹ ሕግ የተለያየ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በጓደኛ፣ በትዳር አጋር፣ በሃይማኖት አማካሪ፣ በቅርብ ዘመድና በሕግ አማካሪ የመጎብኘት መብት መኖሩን ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡ እነዚህ ዝርዝሮች በዝቅተኛ መሥፈርትነት የተቀመጡ ናቸው፡፡ መንግሥት ዝርዝሩን ሊጨምረው ይችላል፡፡
ጉብኝቱ አሁን አሁን በአካል ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ዕገዛም ይከናወናል፡፡ በስልክ፣ በይነ መረብን (ኢንተርኔት) መሠረት ያደረጉ የቪዲዮ ግንኙነትና ጉብኝትም ይደረጋል፡፡
አንድ እስረኛ ከላይ በተጠቀሱት ሲጎበኝ፣ በአካል ሳይነካካ፣ ለሰላምታ ያህል በመሳሳምና በመጨባበጥ፣ በአንድ ቦታ ከሌሎች ተነጥሎ በመነጋገር፣ ወዘተ ሊከናወን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ የተለመደው ከሕግና ከሃይማኖት አማካሪ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች በተለየ ቦታ (ክፍል) ይፈጸማሉ፡፡ ሌሎች ጋ ሲሆን ከሌሎች እስረኞች ጋር በኅብረት ወይም ለብቻ በአካል መነካካት በሚቻልበት ሁኔታም ይደረጋል፡፡ ከሃይማኖትና ከሕግ አማካሪ ጋር ከሚደረገው ግንኙነት ውጪ በአገራችን ያሉ ማረሚያም ይሁኑ ማረፊያ ቤቶች ወጥ የሆነ አሠራር የላቸውም፡፡
ታራሚው ወይም ታራሚዋ ባለትዳር በምትሆንበት ጊዜ፣ እስረኛ የትዳር አጋርን የሚጠየቅበት ሁኔታም ቢሆን በኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም ጎብኚ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ግን ሁኔታው እየተለወጠ መጥቷል፡፡ የትዳር አጋር የሚጎበኝበት ሥርዓት እየተሻሻለ ነው፡፡ የትዳር አጋር ጋር በተለየ ክፍል ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ፣ የአዳር ጉብኝትም የሚፈቀድባቸው አገሮች በርካታ ናቸው፡፡
በዋናነት ለምን ያህል ሰዓት (ጊዜ) ይገናኙ የሚለውን አገሮች በሕጋቸው ይወስናሉ፡፡ እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስረኛ የሆነው ሰው ትዳርና ልጆች ካሉት ቤተሰቡ በአንድ ጊዜ ለአዳር ወይም ለ24 ሰዓት አብረው የሚያሳልፉበትን ክፍል የሚያመቻቹ አገሮች አሉ፡፡ እንዲህ ሲሆን ለክፍሎቹና ለሌሎች ወጪዎች ማካካሻ የሚሆን ክፍያ ጎብኚዎች ወይም ታራሚው መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጉብኝት ቀደም ብሎ ለማረሚያ ቤት በማሳወቅ ክፍል እንዲመቻች በማድረግ የሚከናወን ነው፡፡
ታራሚዎችን ከትዳር ጓደኛ ጋር በተለየ ክፍል እንዲገናኙ ማድረግ በፌዴራል ሥርዓት በሚከተሉ አገሮችና በክልሎች የሚተዳደሩ ማረሚያ ቤቶች በሚኖሩበት ጊዜ፣ ሥልጣኑ የክልሎቹ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ የሚሲሲፒን ግዛት ብንወስድ፣ ይህን ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች 100 ዓመት አልፏታል፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ግዛቶቹ ተግባራዊ እያደረጉት ነው፡፡
እስረኛ ከትዳር አጋር ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለመፈጸም በሚያስችል አኳኋን ግላዊነቱ ተጠብቆለት የመጎብኘት መብት አለው ወይ? የሚለውን በሚመለከት በእኛ አገር ግልጽ መልስ አናገኝም፡፡ ይሁን እንጂ ከተለያዩ ሕግጋት ድንጋጌዎች በመነሳት ከአሉታ ይልቅ ወደ አዎንታዊው የሚያደላ መልስ መስጠት ይቀናል፡፡ በሌላ አገላለጽ መብት ነው የሚያሰኙ አስረጂዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
በቀዳሚነት የምናገኘው ከላይ በመንደርደሪያችን ላይ እንደ ገለጽነው፣ አንድ እስረኛ በማረሚያ ቤት ቆይታው ተምሮ መልካም ዜጋ ሆኖ እንዲወጣ የሚደረግበት አሠራር እንጂ የበቀል፣ ሌላ የተወሳሰበ አዕምሮና የሥነ ልቦና ችግር እንዲፈጠርበት አይደለም፡፡ ከትዳር አጋሩ ጋር ግንኙነት እንዳያደርግ በመከልከል ትዳር እንዲናጋ፣ ቤተሰብ እንዲፈርስ፣ የትዳር አጋርንም አብሮ የሚቀጣ አሠራር የማስፈን ግብ የለውም፡፡ ይልቁንም መልካም ዜጋ እንዲሆን እንጂ፡፡
እንዲህ ዓይነት ክልከላዎች ከማኅበረሰባዊ ልማድ ያፈነገጡ ድርጊቶችን ወደ መለማመድ ሊወስድ ይችላል፡፡ ስለሆነም፣ መልካም ዜጋ ሆኖ መውጣት ለአገርም ለኅብረተሰብም አስፈላጊ ስለሆነ፣ በትዳር አጋር የሚደረግ ጉብኝትም ክልከላም ሊመዘን የሚገባው ከዚህ አንፃር ነው፡፡
ሌላው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 34 (3) ቤተሰብ የኅብረተሰብ ተፈጥሯዊ መነሻ እንደሆነ ዕውቅና ስለተሰጠው፣ ለቤተሰብ ኅብረተሰብም መንግሥትም ጥበቃ ሊያደርግሉት እንደሚገባ ስለተደነገገ ባለትዳር የሆነ/ች እስረኛን በሚመለከት በትዳር አጋር የሚደረግ ጉብኝት ቤተሰብን ከመፍረስ ሊጠብቅ በሚችል መንገድ መሆን አለበት፡፡ የትዳር አጋር ጋብቻውን የሚያስፈርስ ፈተና ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ የእስረኛ አጎበኛኘት ሊኖር አይገባም፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የትዳር አጋር መታሰርና ግንኙነት እንዲያደርጉ የሚያደርግ አሠራር በሌለባቸው አገሮች፣ ለትዳር መፍረስ (ፍቺ) አንዱ ምክንያት እንደሆነ ነው፡፡
የትዳሩ መጠበቅ ለቤተሰብ መኖርና መጠበቅ መሠረት ስለሆነ፣ በትዳር አጋር የሚደረገው የጉበኝት ሁኔታ ፍቺን የሚያባብስ እንዳይሆን መንግሥት ግዴታ አለበት ማለት ይቻላል፡፡ ከእዚህ አንፃር በትዳር አጋር የሚደረግ ጉብኝት ግንኙነት የማድረግ መብትን (Conjugal Right) ታሳቢ ሊደርግ ይገባዋል ማለት ነው፡፡
የቤተሰብ ሕጉም ቢሆን ባለትዳሮች በጋብቻ ፀንተው እስከኖሩ ድረስ፣ “መደበኛውን የግብረ ሥጋ ግንኙነት ያደርጋሉ” የሚል ማስገንዘቢያ የሰጠው ግንኙነት ማድረግን እንደ መብት ወይም ግዴታ ባይሆንም እንኳን፣ ለቤተሰብ መፅናት መሠረት በመሆኑ ነው፡፡ ከእዚህ አንፃር ስንመለከተው ደግሞ ያልታሰረች/ው ባለትዳር በእስር ላይ የሚገኝ ባሏን ወይም ሚስቱን በሚጎበኝበት ጊዜ፣ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች እንዲሟሉ በመብትነት መጠየቅ እንደሚያስችልም የሚከራከሩ አሉ፡፡ ክርክሩ ሰምሮ በፍርድ ቤት የተፈቀደባቸው አገሮች ያሉትን ያህል ውድቅ የተደረገበትም ጊዜያት ብዙ ናቸው፡፡
በጥቅሉ ሲታይ እስረኛን በማረም መልካም ዜጋ ለማድረግ፣ ለኅብረተሰብ መሠረት የሆነውን ቤተሰብን ከመጠበቅ ረገድ፣ የባለትዳሮችን የጋብቻ ሁኔታ ከማፅናትም፣ በፍቺ ምክንያት ልጆችም እንዳይቀጡ ብሎም የሕገ መንግሥቱም የሰብዓዊ መብቶች ሰነድና የቤተሰብ ሕጉም መንፈስ የባለትዳሮችን ግንኙነት የማድረግ መብት (Conjugal Right) እንዳላቸው የሚያጠናክር ስለሆነ መንግሥትም ትኩረት ሊያደርግበት ይግባል፡፡
አዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡