በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ
ገና ስንወለድ ኢትዮጵያችንን ያገኘናት በሃውርታዊና የባለ ብዙ ዘርፍ ማኅበረሰቦች አሰባሳቢና አቃፊ አገር ሆና ነው፡፡ እርሷም ብትሆን ከማህፀኗ የወጣነውን ልጆቿን ሁሉ ያለ ልዩነት ተቀብላና የአቅሟን ያህል ተንከባክባ እንዳቆየችን አንድና ሁለት የለውም፡፡ ውድ አገራችን ኢትዮጵያ በዓለማችን ላይ በሚገኝ ማንኛውም አገረ መንግሥት ምሥረታ፣ ልምድና ሒደት እንደሚያጋጥመው ሁሉ በመካከላችን ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ቋንቋን . . . መሠረት ያደረገ ቤተሰብዓዊ አለመግባባት፣ አምባጓሮና ግጭት ቢፈጠር እንኳ ከእዚህ የተነሳ ብቻ ዘላቂ ቂም ቋጥረንና በኃይል ተበጣብጠን በማያባራ ሁከትና የወንድማማቾች ትርምስ እንድንተላለቅባትና እርስ በርስ ተበላልተን እስከ ወዲያኛው እንድንጠፋባት ፈፅሞ አትፈቅድም፡፡ የቱንም ያህል ብናማርራትና ብናስከፋት እናት ናትና በልጆቿ መካከል የምታደርገው ልዩነት ቢኖር እንኳ እርሱ ቴክኒካዊና ጊዜያዊ ነው፡፡ በዕውን ለዘለቄታው ከተፈላለግንና በሰከነ አኳኋን ከተነጋገርን በቀላሉ ሊታረም የሚችል ነገር ነው፡፡
የብሔር አከላለልና መዘዙ
የረዥም ጊዜ የአገርነት ታሪክ ያላት እምዬ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገጠማት ከባድ ፈተና ለዘመናት አብረውና በአመዛኙ ተሰበጣጥረው የኖሩት፣ ማኅበረሰቦቿ ፍላጎታቸው በውል ሳይታወቅና የቅድሚያ ፈቃዳቸው ሳይጠየቅ የበቀሉበት ዘውግና የሚናገሩት የአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቻ እየተጠቀሰ በየሰፈሩበት መልክዓ ምድር ያላግባብ እንዲከለሉ ከመደረጋቸው ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፡፡ ይኸው አላስፈላጊ አጥር የተሠራው በአደገኛው ሕገ መንግሥታዊ ‘ትሬኮላታ’ መሆኑ ደግሞ፣ ሁኔታውን ይበልጥ የተወሳሰበ እንዳደረገው በሒደት ያስተዋልን ይመስለኛል፡፡ ለመሆኑ ክልል ማለት ምን ማለት ነው? መከለልስ? ዕውቁ የአገራችን የታሪክ ተመራማሪና የሥነ ጽሑፍ ሰው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ በቅርቡ ማለትም ሐምሌ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ለዘንድሮ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን አጭር ቃለ ምዕዳን እንዲያስተላልፉ በተጋበዙበት ወቅት ንግግራቸውን ለመጀመር ሲንደረደሩ፣ ክልሎችን በስያሜያቸው መጥራት እንደሚያስጠላቸው በአደባባይ ሲገልጹ ታዝበናል፡፡ ተመራማሪው ለዚህ አቋማቸው በዕለቱ የሰጡት ምክንያት ባይኖርም፣ ሰውየው ካላቸው የፀና ኢትዮጵያዊነት አኳያ በስያሜው ያደረባቸውን ቅሬታ መገንዘብ አዳጋች አይሆንም፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ‘ክልል’ የሚለው የአማርኛ ቃል አሁን አሁን አዘውትረን በምንጠቀምበት ልክ ‘Region’ የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል በትክክል የመመለስ ወይም የመተካት አቅም ያለው ስለመሆኑ ያን ያህል እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ መደበኛ ያልሆነው የአደባባይ ትርጓሜው ግን እምብዛም አደናጋሪና አሻሚነት ያለው እንዳልሆነ በበኩሌ እረዳለሁ፡፡
እንግዲህ ከዚህ ስንነሳ ‘ክልል’ ማለት በአንድ በተወሰነ ማኅበረሰብ ይዞታ ወይም ባለቤትነት ሥር እንዲውል ወይም አንድ የተወሰነ ተግባር እንዲከናወንበት ወይም አገልግሎት እንዲሰጥበት፣ በሕግም ሆነ በአካባቢያዊ ልማድ ዋቢነት ተለይቶ በይፋ የተመደበ ሥፍራ ስለመሆኑ ብዙ መመራመር የሚያሻው ጉዳይ ሆኖ አይታይም፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ በሕግ ወይም በታወቀ ልማድ ባለመብት መሠረት ከሆነው ማኅበረሰብ ወይም ከተፈቀደው ተግባር ወይም አገልግሎት በስተቀር ሥፍራው ለሌሎች ማኅበረሰቦች ወይም ተግባራት አስቀድሞ የተከለከለና አይነኬ መሆኑን ለመገመት አያዳግትም፡፡ በሌላ አነጋገር ክልል ማለት በቁሙ ክልክል መሆኑን በቀላሉ ይገነዘባል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ጥሎብን አገራችን መላዋ ኢትዮጵያ መሆኗን አጥብቀን ስለምናምን በአመዛኙ የምንኖረው አብረንና እርስ በርስ ተሰበጣጥረን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ተፈጥሯዊ ኩነት አስገድዶት በአንድ የተወሰነ መልክዓ ምድራዊ አካባቢ ሰፍሮ በወጥነት የሚኖረው ወገናችን ከስንት አንድ ቢሆን ነው፡፡ በመሬት ላይ ያለው እውነታ እንዲህ ከሆነ ታዲያ ብዙኃኑ አንደኛው ከሌላው ጋር ተሰበጣጥረው ብቻ ሳይሆን፣ በደምና በሥጋ ሳይቀር ተዋህደው በሚኖሩበትና እንደ ኢትዮጵያ ባለ አንድ አገር ውስጥ የሚኖር አንድ ማኅበረሰብ አብረውት ከሚኖሩ ሌሎች ማኅበረሰቦች ተለይቶ፣ እንዴትና በምን ዓይነት ሁኔታ ለብቻው ሊከለል ይችላል? ከዚህ የቃሉ አሉታዊ አጠቃቀም አንፃር መከለል እኮ በቁሙ የተወሰደ እንደሆነ ከሌላው ተለይቶ ለብቻ መታጠር፣ መጋረድ፣ መዘጋት ወይም መገደብ ማለት ነው፡፡ ቀድሞውኑ ለዚህ አስተሳሰብ ከታመኑት ጥቂት ቡድኖችና የእነርሱ አጫፋሪዎች በስተቀር የትኛውም ጤናማ ማኅበረሰብ ይህንን ዓይነት ሰው ሠራሽ አጥር ይመኛል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ (ሦስት) ድንጋጌ መሠረት በብሔርም ተደራጀ፣ በሃይማኖት ወይም በሌላ በማናቸውም ሁኔታ የትኛውም ቡድን ወይም ስብስብ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የእኔ የብቻዬ ነው ሊለው የሚችለው የመሬት ክፍል የለውም፣ ሊኖረውም ከቶ አይችልም፡፡
ለጉዳዩ አግባብነት ያለው የእዚህ ሕገ መንግሥት ድንጋጌ እንዲህ ይነበባል፡፡ ‹‹የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥና የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው፤›› ይላል፡፡ እንዲያ ከሆነ ታዲያ የጋራ የሆነውን መሬት ወይም ሌላ የተፈጥሮ ሀብት ሌላውን ባገለለ መንገድ የቡድን ይዞታዬ ነው በማለት ለብቻው ሊከልል የሚችለው ማነው ጎበዝ? በእርግጥ የዚሁ ጉራማይሌ ሕገ መንግሥት ሌላው አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ (አንድ) ድንጋጌ ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን ኃይለ ቃል የሚቃረን በሚመስል አቀራረብ መቀረፁን በተጨማሪ እንታዘባለን፡፡ እርሱም እንደሚከተለው ይነበባል፡፡ ‹‹ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው፤›› ይላል፡፡ ከዚህ ግልጽ ተቃርኖ በቀላሉ የምንገነዘበው ዓብይ ቁምነገሮችና ዴሞክራሲያዊው ሕገ መንግሥታችን ‹‹የምትኖሩት አብራችሁ ነው፣ መላው የአገሪቱ መሬትና የተፈጥሮ ሀብትም የጋራችሁ ነው፤›› በማለት ካንቆለጳጰሰን በኋላ፣ ብዙም ሳይቆይ ‹‹ካሻችሁ ግን ልትገነጣጠሉና ልትከፋፈሉት ትችላላችሁ፤›› ሲል ለማያባራ የእርስ በርስ ብጥብጥ የሚዳርግ ሌላ ጨካኝና አፍራሽ ድንጋጌ የሰነቀረልን መሆኑን ነው፡፡ ኧረ ጭራሹን ተለይተንና አገር ሆነን ከፌዴሬሽኑ ብንወጣም ጉዳዩ አይደለም፡፡
‹‹እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው›› መሆኑ ይመስላል፡፡ ቀድሞ ነገር ከጠባብ የቡድን ፍላጎት እንደመነጨና በአንድ ድርጅታዊ የፖለቲካ ፕሮግራም ተቃኝቶ እንደ ተዘጋጀ የሚነገርለት ይኸው የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ (አንድ) ሥር እንደተደነገገው፣ የአዲስ አበባ ከተማን ሳይጨምር መላ አገሪቱን በዘጠኝ ክልሎች እንደ አዲስ ሸንሽኖ ያደራጀ ሲሆን፣ የድሬዳዋ ከተማንና ድሬዎችን ከእነ ጭራሹ ዘሏቸዋል፡፡ አብዝቶ የሚያስገርመው ግን ዘጠኙን ክልሎች ራሳቸውን በወጉ አጥርቶ ሳያዋቅር በእነዚሁ ክልሎች ውስጥ የተካተቱት ሌሎች ህዳጣን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች እንደ ገና በማናቸውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል መመሥረት ቢያስፈልጋቸው እንኳ፣ ይኸው መብት ሳይቀር ከወዲሁ እንደተረጋገጠላቸው ሌላ ደላይና ሸንጋይ ንዑስ አንቀጽ በተጨማሪነት በማካተት አገሪቱን እስከ ወዲያኛው በመገነጣጠሉ አደገኛና ዘላቂ ፕሮጀክት አጥብቆ የገፋበት ሆኖ መታየቱ ነው፡፡ የራስን ዕድል በራስ በመወሰን ስም ይህንኑ መብት ገቢራዊ ለማድረግ እንዲቻል አስቀድሞ በተቋቋመ በየትኛውም ክልል ውስጥ የሚኖር ማናቸውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱን አዲስ ክልል የመመሥረት መብቱን በሥራ ላይ የሚያውልባቸው ዋና ዋና መሥፈርቶች ደግሞ በዚሁ ሸፋፋ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ (ሦስት) ድንጋጌ ሥር ተዘርዝረው እናገኛቸዋለን፡፡
አዲስ ክልል የመመሥረት ጥያቄና አቀራረቡ
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ‘ብሔር’፣ ‘ብሔረሰብ’ እና ‘ሕዝብ’ የሚሉትን የተለያዩ ቃላት የሚጠቀምባቸው እንዲያው በደመነፍስ ነው ቢባል መሳሳት አይሆንም፡፡ ሌላው ቀርቶ አንደኛውን ከሌላው የሚለይበት ይህ ነው የሚባል አስተማማኝ መለኪያ እንኳ የለውም፡፡ ይህ ቁልፍ ችግር ከመነሻው ሳይፈታ ነው እንግዲህ በአንድ ክልል ውስጥ ራሱን ችሎና መሬት ነክሶ የሚኖር ማናቸውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱን ክልል ለመመሥረት ይፈቀድለት ዘንድ ለታቀፈበት ክልል ምክር ቤት በጽሑፍ ጥያቄ የማቅረብ መብት እንዳለው በዘፈቀደ የተደነገገው፡፡
እንደ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ (ሦስት) ፊደል ተራ ቁጥር፣
ሀ. ድንጋጌ ከሆነ የተባለው ጥያቄ ወደ ክልሉ ምክር ቤት መተላለፍ ያለበት በቅድሚያ ለአነሳሹ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ምክር ቤት በተዋረድ ቀርቦ በይፋ ከተመከረበትና በዚሁ የበታች ሸንጎ አባላት ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ድጋፍ ተቀባይነት ያገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር የራሱ የበታች ምክር ቤት የሌለው ወይም ይህንኑ ምክር ቤት ያላቋቋመ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ቢኖር እንዲህ ያለ ጥያቄ ማቅረብ አይቻለውም ማለት ነው፡፡ ያም ሆኖ የክልል ምሥረታ ጥያቄውን በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ ጉዳዩ ለሚመለከተው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ምክር ቤት የመጀመርያ ደረጃ ምርመራና አስተያየት በቀጥታ ስለሚያቀርበው አካል ማንነት ሕገ መንግሥቱ በግልጽ አይናገርም፡፡ ይኸው ጉዳይ በመጠኑም ቢሆን ተብራርቶ የምናገኘው ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ ከስድስት ዓመት በኋላ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባራቱን ለመዘርዘር ታስቦ በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/1993 ዓ.ም. አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ (አንድ) ላይ ነው፡፡ በተጠቀሰው የአዋጁ ሥነ ሥርዓታዊ ድንጋጌ መሠረት የክልል ምሥረታን ጨምሮ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን አስመልክቶ የሚነሳ ማናቸውም ጥያቄ የሚቀርብበት ጽሑፍ፣ የጥያቄውን ይዘት በዝርዝር የሚያሳይና ጥያቄው እውነትም የነዋሪው ሕዝብ ወይም የብሔር፣ ብሔረሰቡ መሆኑን ለመገመት ያመች ዘንድ እንዳስፈላጊነቱ ከነዋሪው ሕዝብ ወይም ከብሔር፣ ብሔረሰቡ አባላት መካከል ቢያንስ አምስት ከመቶ የሚሆኑትን ወገኖች ስም ዝርዝር፣ ፊርማና ቋሚ አድራሻ የያዘ ወይም እንዳስፈላጊነቱ ጥያቄውን ባቀረበው የመስተዳድር አካል ባለሥልጣን የተፈረመና ማኅተም ያረፈበት መሆን ይገባዋል፡፡
እዚህ ላይ ‘ነዋሪው ሕዝብ እና ‘የብሔር፣ ብሔረሰብ አባላት’ የሚሉት ሐረጎች እየተወያየንበት ባለው አዋጅ ውስጥ የተቀመጡት በአማራጭነት እንጂ፣ በጣምራ ቅድመ ሁኔታነት አለመሆኑን ስንመለከት የክልል ምሥረታ ጥያቄን አግባብ ካለው ብሔር ወይም ብሔረሰብ አባላት ውጪ ያሉ፣ ወይም ከእነርሱ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ሌሎች ዜጎች ጭምር የአምስት ከመቶ መሥፈርትን አሟልተው እስከተገኙ ድረስ፣ የማንቀሳቀስ ዕድል ጨርሶ እንዳልተነፈጋቸው እንረዳ ይሆናል፡፡ ሆኖም በመጠኑም ቢሆን፣ ተስፋፍቶ የተቀረፀ የሚመስለው ይኸው የማስፈጸሚያ ድንጋጌ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39ና አንቀጽ 47 ድንጋጌዎች ጋር ተጣምሮ ሲነበብ ራሱን ሕገ መንግሥቱን የተከተለ ነው ለማለት ያዳግታል፡፡
በመሠረቱ የሕገ መንግሥቱ ገዥ ፍላጎት ክልል እመሠርታለሁ የሚለውን ብሔር ወይም ብሔረሰብ አባላት እንጂ፣ ከእነርሱ ውጪ ያሉ ወይም አብረዋቸው የሚኖሩ ሌሎች ዜጎችን ጥያቄ ማስተናገድ ወይም የእነርሱን የልብ ትርታ ማዳመጥ አይደለም፡፡ እንዲያም ሆኖ ታዲያ አንድን የአፍ መፍቻ ቋንቋ በመናገራቸው ወይም በሆነ ዘውግ ስም ተዘጋጅቶ በተሰጣቸው የመንደር ነዋሪነት መታወቂያ ካልሆነ በስተቀር፣ የጥያቄ አቅራቢውን ብሔር ብሔረሰብ አባላት ማንነት እንዴት ባለ ምትኃታዊ ዘዴ አጥርቶ መለየትና መመዝገብ እንደሚቻል ግልጽ አይደለም፡፡
ለ. የክልሉ ምክር ቤት ኃላፊነት ጥያቄው በጽሑፍ የቀረበለት ክልል አቀፍ ምክር ቤት ይኸው ጥያቄ ከደረሰበት ዕለት አንስቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ጥያቄውን ላቀረበው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ የማደራጀት ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ በእርግጥ የተጠቀሰውን ሕዝበ ውሳኔ ምክር ቤቱ እንደሚያደራጀው በሕገ መንግሥቱ ይደንገግ እንጂ፣ ወደ መሬት አውርዶ የሚያስፈጽመው ቴክኒካዊ ባለ አደራ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ እዚህ ላይ ሕገ መንግሥቱ ያለበቂ ቅድመ ጥንቃቄ ‘ሕዝበ ውሳኔ’ ሲል የሚገልጸው ‘Referendum’ የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል በአማርኛ ቋንቋ አቻው ለመተካት በማሰብ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ እንዲያ ከሆነም’ ‘ውሳኔ ሕዝብ’ ወይም ‘የሕዝብ ውሳኔ’ እንጂ ‘ሕዝበ ውሳኔ’ ብሎ ነገር የለምና የተወላገደ አተረጓጎም ስለመሆኑ እግረ መንገዴን ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ ብላክስ ሎው ከተሰኘው የሕግ መዝገበ ቃላት ለመገንዘብ እንደሚቻለው፣ ይኸው ቃል በሥራ ላይ የሚውለው አንድ የተወሰነ ሕዝብ ወይም ክፍለ ሕዝብ እንደ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ባለ አንድ ታላቅ ሕዝባዊ ኩነት ላይ በነቂስ ወጥቶ የነፍስ ወከፍ ድምፁን በመስጠት ውሳኔ የሚያሳልፍበትን ሒደት ወይም የሚደረገውን ምርጫ ለመግለጽ ነው፡፡ (Brian A, Garner) እ.ኤ.አ. በ1999 ያዘጋጀውን የዚህኑ መዝገበ ቃላት ሰባተኛ ዕትም በዋቢነት ይመለከቷል፡፡ “Referendum is the Process of Referring a State Legislative Act, a State Constitutional Amendment, or an Important Public Issue to the People for Final Approval by Popular Vote or the Vote Taken by This Method”.
ሐ. በሕዝበ ውሳኔው የሚሳተፈው ማነው? እንግዲህ የክልል ምሥረታ ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ የተባለው ሕዝበ ውሳኔ ቢደራጅ የድምፅ ሰጪዎች ማንነት በወጉ ተለይቶ ከወዲሁ መታወቅ ቁልፍና አከራካሪነት የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ሆነ የማስፈጸሚያ አዋጁ ዝርዝር ድንጋጌዎች አንዳች ፍንጭ አይሰጡም፡፡ አንድ ነገር ግን በጣም ግልጽ ነው፡፡ ከጅምሩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሕጉ የሚጠይቀውን የአምስት ከመቶ መሥፈርት አሟልተው ያንቀሳቅሱት እንጂ፣ ማናቸውንም የክልል ምሥረታ ጥያቄ ለታቀፈበት ክልል ምክር ቤት በጽሑፍ የማቅረብ መብት ያለው በዚያ ክልል ውስጥ የሚኖር ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ መሆኑ አስቀድሞ የተደነገገ በመሆኑ ይህንኑ በሥራ ላይ ለማዋል በሚደራጀው ሕዝበ ውሳኔ የመመዝገብና ድምፅ የመስጠት መብት የሚኖራቸው የዚያ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ አባላት ብቻ ስለመሆናቸው እምብዛም ልንከራከር አንችልም፡፡
ይህንኑ ኩነት ተከትሎ እንደ አዲስ የሚፈጠረው ክልል በዚያ ሕዝበ ውሳኔ ተሳታፊ በሚሆነው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ አባላት የአብላጫ ድምፅ ተደግፎ እንዲቋቋም ከተደረገ ሌላ ተጨማሪ ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የፌዴሬሽኑ አባል እንደሚሆን የተተነበየለት በመሆኑ፣ እምዬ ኢትዮጵያ ከስንት ቦታ የመሸንሸንና ክፉውን ያርቀውና ከእነ ጭራሹ የመበታተን ዕጣ ሊገጥማት እንደሚችል ከወዲሁ ለመገመት አይከብድም፡፡ ለምሳሌ የሲዳማ ብሔር በቅርቡ እንደተረዳነው ከአምስት ወራት በኋላ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካይነት ይዘጋጅለታል የተባለው ሕዝበ ውሳኔ ተሳክቶለት የሚካሄድ ቢሆን፣ ‘ሲዳማ ክልል ይሁን ወይም አይሁን?’ ብሎ ለመወሰን በነቂስ ወጥተው የሚመዘገቡትና ድምፃቸውን በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ የሚሰጡት ሲዳማዎች ብቻ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ በእርግጥም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ (ሁለት) ፊደል ተራ ቁጥር ድንጋጌ የሚነግረን ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡
አዳጋቹ ነገር ሲዳማ ውስጥ ከሲዳማ ብሔር ጋር ተቀላቅለው መኖር ብቻ ሳይሆን፣ በአንዳንድ የዞኑ አካባቢዎች በቁጥር የሚልቁ የሌላ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ተወላጆች መገኘታቸውና በእንዲህ ያለው ሕዝባዊ ኩነት የእነርሱ ድምፅ ሊሰማ የሚችልበት ዕድል የሌለ መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ ይህንን ዓይነቱን ግዙፍ ሕገ መንግሥታዊ ህፀፅ ሳያርሙ ዘጠኙም ክልሎች ያረገዟቸውን ትልልቅና ትንንሽ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በገዛ አባሎቻቸው የአብላጫ ድምፅ ድጋፍ ብቻ ከዛሬ ጀምሮ ክልል ሆናችኋል እያሉ ለማወጅ መንደርደሩ፣ የዜጎችን ዘላቂ አብሮ የመኖር እሴት መናድና ጠባብ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች አለን የሚሉትን ሕገ መንግሥታዊ መብት በማስከበር ስም አገራዊ አንድነትን ማፍረስ ይሆናል፡፡ ማንም እንደሚያስታውሰው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እስከ ዛሬም ድረስ ጭንብሉ ሆኖ በዘለቀው በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አማካይነት አገሪቱን በተቆጣጠረ ማግሥት፣ ከተገቢው በላይ ተረባርቦ ባፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ውስጥ በተለይ የአንቀጽ 39 እና አንቀጽ 47 ድንጋጌዎችን እስከ ማካተት የደረሰው ለሁለት ዓበይት ዓላማዎች ነበር፡፡ አንደኛው በመሬት ላይ አስቀድሞ የተከናወነ ቢሆንም፣ የቀድሞዋን የኤርትራን ክፍለ ግዛት ከኢትዮጵያ መገንጠል ቅቡልነትና ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ ሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ይከበርልን ስም ዘላቂ የትርምስ አጀንዳ ሰጥቶ የወደፊቷንና የታላቋን ትግራይ ሪፐብሊክ ምሥረታ መፃኢና ድንቅ ፕሮጀክት ከወዲሁ ለማመላከትና የምሥረታዋን ራዕይ ለማቀላጠፍ ነበር፡፡
በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችና ሌሎች ህዳጣን ቡድኖች በተፈጥሮ ያላቸው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አከባበር ጥያቄ ለዓለም አቀፍ ሕግ ያን ያህል እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ጭምር ተቀብላ ያፀደቀችውና እነሆ ደጋግመን አበሳውን በምናሳየው ሕገ መንግሥት አንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ አራት መሠረት፣ የብሔራዊ ሕጎቿ ሥርዓት ክፍልና አካል ያደረገችው እ.ኤ.አ. 1966 ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ውል በአንቀጽ 27 ሥር የሚከተለውን ደንግጎ እናገኘዋለን “In Those States, in Which Ethnic, Religious or Linguistic Minorities Exist, Persons Belonging to Such Minorities Shall not Be Denied the Right, in Community with the Other Members of their Group, to Enjoy their Own Culture, to Profess and Practise their Own Religion, or to Use their Own Language.” ወደ አማርኛ ሲመለስ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹የራሳቸው የሆነ ዘውጋዊ ወይም በሕገ መንግሥታችን መጠሪያ ብሔረሰባዊ፣ ሃይማኖታዊና የቋንቋ ማንነት ያላቸው የተለያዩ ቡድኖች በሚኖሩባቸው አገሮች፣ በእነዚሁ ቡድኖች የታቀፉ አባላት ከመሰሎቻቸው ጋር በመሰባሰብ ባህላዊ ሥርዓቶቻቸውን በአደባባይ እንዳይገልጹ ወይም እንዳይከውኑ፣ በአንድነት ሆነው አምልኮ እንዳይፈጽሙም ሆነ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይጠቀሙ አይከለከሉም፡፡››
በተጨማሪም ይኸው ዓለም አቀፍ ስምምነት ገና በመክፈቻው አንቀጽ አንድ ንዑስ አንቀጽ አንድ ሥር የሚከተለውን ደንግጓል “All Peoples have the Right of Self-Determination. By Virtue of that Right, they Freely Determine their Political Status and Freely Pursue their Economic, Social and Curtural Development.” እርሱንም እንዲህ ተርጉሜዋለሁ፡፡ ‹‹ሕዝቦች ሁሉ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት አላቸው፡፡ ከዚሁ በመነጨ ምክንያት የየራሳቸውን ፖለቲካዊ አቋም በነፃነት ሊወስኑና የፈለጉትን ዓይነት ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ የልማት አቅጣጫ በራሳቸው ምርጫ የመከተል መብት አላቸው፡፡›› ከዚህ አልፎ ሉዓላዊነቱ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በተረጋገጠ በየትኛውም አገር ውስጥ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች የራሳችን ድርሻ ነው የሚሉትን አካባቢ በራሳቸው ጊዜ ለብቻቸው እየከለሉ አብረዋቸው የሚኖሩትን ሌሎች ወገኖች በመጤነትና በባይተዋርነት የሚገፉበት፣ ሲያሻቸውም ነፃ አገር ሆነናል በማለት እየተገነጠሉ የሚወጡበት የዘፈቀደ ሥርዓት በዓለም አቀፍ ሕግ ውስጥ አልተደነገገም፣ ጨርሶ አይታወቅም፡፡ በብሔራዊ የሕግ ሥርዓቶች ደረጃም ቢሆን፣ ለዚህ ያልተቀደሰ በገዛ ራስ የመከለልም ሆነ የመገንጠል መብት ሙሉና ያልተገደበ ዕውቅና የሚሰጠውና የሚንከባከበው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ብቻ ነው ቢባል ከእውነታው እንደ መራቅ አይቆጠርም፡፡ ቀድሞ ነገር መታጠርም ሆነ መገንጠል ወይም መገነጣጠል ከሥነ ሕግ እሳቤ በመብትነት ሊረጋገጥና ተፈላጊው ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ መብት እኮ በፀባዩ የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተረጋገጠለትና የተሟላ ደስታን ለመሻት ሲል ይህንኑ ሊያከብርለት ወይም ሊያስከብርለት ከሚገባው አካል አጥብቆ የሚጠይቀው እንጂ፣ ሌሎች ወገኖችን ወደ ጠርዝ ገፍቶ ለብቻው የሚሠለጥንበት ጉዳይ አይደለም፡፡
የሲዳማ የክልልነት ልምምድና የደኢሕዴን ግራ መጋባት
ለመሆኑ የሲዳማ ሕዝብ ለምን፣ እንዴትና ከማን ነው የሚከለለው? የአቀንቃኞቹ ፍላጎት ሰምሮ ሲዳማ የራሱን ክልል ካበጀስ የጌዴኦ ብሔረሰብ እንዴት ይሆን የሚተዳደረው? እርሱም በማን አንሼ ሒሳብ ክልል ልሁን ይላል? ወይስ አዲስ የሚፈጠረውን የሲዳማ ክልል ጨምሮ ከአጎራባች ክልሎች አንደኛውን በመምረጥ ይካለላል? እነዚህን ተደራራቢ ጥያቄዎች በመንተራስ በመጣጥፎቼ ውስጥ አዘውትሬ ባነሳቸው የማይሰለቹኝን ብልኋን መነኩሴ እማሆይ ትርፌን ሰሞኑን በለሆሳስ አወያይቻቸው ነበር፡፡ የመለሱልኝን ብነግራችሁ በሳቅ ፍንድት ነው የምትሉት፡፡ ‹‹አበስኩ ገበርኩ››፣ አሉ እማሆይ፣ በአንገታቸው ላይ የተንጠለጠለውን መቁጠሪያ በግራ እጃቸው ጣቶች ያለማቋረጥ እያፍተለተሉ፡፡ ‹‹መከለል አልከኝ ልጄ? መከለል እኮ መታጠር ነው፡፡ ቀድመው ለተከለሉትም ከልቤ አዝንላቸዋለሁ፤›› ነበር ያሉኝ እማሆይ፡፡
የዛሬውን አያድርገውና ከደርግ ውድቀት ማግሥት ኢሕአዴግ ፈጠርኳት በሚላት የሽግግር ወቅቷ ኢትዮጵያ፣ የሲዳማ ብሔር ያኔ ይጎራበቱት የነበሩትንና እንደ ጌዴኦና ቡርጂ ያሉትን ብሔረሰቦች አቅፎ ክልል ስምንት በሚል የቁጥር መጠሪያ ተደራጅቶ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ እንግዲህ ምን ያህል እንደጠቀመው ባይታወቅም ይህ መነሻ ሬከርድ ከነበረው ዛሬ ሲዳማ ተመልሼ ልከለል ብሎ ቢነሳሳ እምብዛም ላይገርም ይችል ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩን በፊታውራሪነት የሚያንቀሳቅሱት አንዳንድ የብሔሩ ተወላጆችና አጃቢዎቻቸው ከሚንቀለቀለው እቶነ እሳት በብዙ ማይሎች ርቀው በሚያስተጋቡት ከፋፋይ ፕሮፖጋንዳና ያለ ገደብ በሚረጩት የጥላቻ መርዝ ልክ መከለል፣ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ያን ያህል አንገብጋቢና የሚያጓጓ ነገር አይደለም፡፡ ጥያቄው በእርግጥ የምልዓተ ሕዝቡን ትክክለኛ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ስለመሆን አለመሆኑ ለመገመትም ቢሆን ሁለት ጊዜ ማሰብ በተገባ ነበር፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ከዘጠኙ ክልሎች አንዱ የሆነውንና ሲዳማ ጭምር የታቀፈበትን የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በገዥነት ተረክቦ የሚያስተዳድረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን)፣ ለተራዘመ ጊዜ ማወዛገቡን በቀጠለው የሲዳማ ብሔር የክልልነት ጥያቄ ላይ የወሰደው አቋም ሰፊ ብዥታና ግራ መጋባት ተስተውሎበታል፡፡ ‘እኛም ክልል እንሁን’ የሚሉ ተጣማሪ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጉዳዩን በየአካባቢ ምክር ቤቶቻቸው እያስወሰኑ ንቅናቄው ሙሉ በሙሉ ለሚቆጣጠረው ክልል አቀፍ ምክር ቤት ሲያቀርቧቸው የቆዩት ተመሳሳይ ጥያቄዎች መበራከት ክፉኛ ስለተገዳደረው፣ የትኛውን ተቀብሎ የትኛውን እንደሚነፍግ በጉልህ ተስኖት ታይቷል፡፡ ይህንን በውል ለመረዳት የንቅናቄው ማዕከላዊ ኮሚቴ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ አኳኋን ለአሥር ተከታታይ ቀናት ሲያካሂደው የሰነበተውን ውጥረት የነገሠበት ስብሰባ እንዳጠናቀቀ ሐምሌ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ያወጣውንና ለሕዝብ ያሠራጨውን ድርጅታዊ መግለጫ መመልከት ይበቃል፡፡ ስድስት ዓበይት ነጥቦችን በያዘው በዚህ የንቅናቄው የአቋም መግለጫ አራተኛ አንቀጽ ላይ የሚከተለውን አንኳር ነጥብ እናገኛለን፡፡ ‹‹በክልል የመደራጀት ጥያቄን በተመለከተ የሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ በክልል የመደራጀቱ ጥያቄ ሲነሳ የነበረው ከአንድ አካባቢ ብቻ ባይሆንም፣ ጥያቄው በጥናት ላይ ተመሥርቶ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ድርጅታችን በአሥረኛ ጉባዔው በወሰደው አቋም መሠረት ሕዝቡን ያሳተፈ ዝርዝር ጥናት ሲያካሄድ ቆይቷል፡፡ በጥናቱ የቀረቡትን አማራጮች በጥልቀት በመመርመርና የሕዝቡን የጋራ ዘላቂ ጥቅም የሚያረጋግጠውን አማራጭ በመውሰድ፣ የክልል አደረጃጀት ጥያቄዎች በሚመለሱበት አግባብ ላይ አቋም ተወስዷል፡፡ በክልላችን መላው ሕዝብ ምክክርና ውይይት የሚያደርግበት ሆኖ በአንድ በኩል በጥናቱ የተገኘውን የክልሉን ሕዝቦች አብሮ የመቀጠል ፍላጎት ባከበረ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጉባዔውን ውሳኔ ተግባራዊ በሚያደርግ መንገድና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የመምራት ግዴታውን ለመወጣት ማዕከላዊ ኮሚቴው ተስማምቷል፤›› ይላል፡፡
እነሆ የመከለል ጥያቄ የሚያቀርብ ማናቸውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ጥያቄው በወቅቱ ባይመለስለት እንኳ ተዋረዱን ጠብቆ ቅሬታውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል እንጂ፣ የራሱን ኃይል ወይም ጉልበት ያላግባብ ተጠቅሞ የእኔ ነው የሚለውን አካባቢ በክልልነት እንዲያውጅ በእናት ሕገ መንግሥቱም ሆነ በማስፈጸሚያ አዋጁ አልተፈቀደለትም፡፡ ይህንኑ የቀን ቅዠት ወደ አደባባይ ወጥተው በሥርዓተ አልበኝነት ገቢራዊ ያደርጉላቸው ዘንድ ኤጀቶዎችን በጭዳነት ያሠማሩ የጥፋት ኃይሎች ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በተከታዮቹ ቀናት ለደረሰው የንፁኃን ወገኖቻችን ሕይወት መቀጠፍ፣ የአካል መጉደልና የሀብት ውድመት የመብት ጥያቄ አንቀሳቃሾች ሳይሆኑ የወንጀል ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ በደቡብ ክልል ፖሊስ መረጃ መሠረት እንኳ ከፍ ብሎ ከተጠቀሰው ዕለት አንስቶ በሐዋሳና በሌሎች የሲዳማ ዞን ከተሞች ውስጥ ኤጀቶዎች በዋነኝነት የመሩትን ሁከትና ግርግር ተከትሎ 53 የሚደርሱ ሰዎች የሞት አደጋ አጋጥሟቸዋል፡፡
በአካል የተጎዳውንም ሆነ በላቡ ጥሮና ግሮ ያፈራው ሀብትና ንብረት በእሳት ቃጠሎና በድንጋይ ውርጅብኝ የወደመበትን ወገን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ከእነዚህ ተጎጂዎች መካከል ሲዳማዎች ራሳቸው እንደሚገኙበት ፈፅሞ መጠራጠር አይቻልም፡፡ እንግዲህ ‘የአህያ ባል ሚስቱን ከጅብ አያስጥል’ ነውና ከርቀት ሆነው ቃጠሎው እንዳይበርድ ቤንዚን በማርከፍከፉ ዕኩይ ተግባር አብዝተው የተጠመዱት ፅንፈኛ የብሔሩ ተወላጆችና አራጋቢዎቻቸው ቆመንላችኋል የሚሏቸውን ወገኖች፣ በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ፈጥነው ሊደርሱላቸውና ለይተው ከጥፋት ሊታደጓቸው ከቶ እንደማይቻላቸው ዕውን ሆኗል፡፡
የሕወሓት ወላዋይ አቋምና የኦሮሞ አክራሪዎች ጫና
እንደ እውነቱ ከሆነ ደቡብን ለማተራመስ ድንጋይ የሚያቀብሉ ኃይሎች ቁጥር ሥፍር የላቸውም፡፡ ከእነዚህ አንደኛው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ነው፡፡ ሕወሓት ሐምሌ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በማዕከላዊ ኮሚቴው አማካይነት ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫ በስድስተኛው ነጥብ ላይ እንዲህ ብሎ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ‹‹በደቡብ ክልል የተነሱ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ ጥያቄዎቹን በኃይል ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት አይኖረውም፤›› ይህ የሕወሐት ጥብቅ ማሳሰቢያ የተስተጋባው በኤጀቶዎች እንቅስቃሴ እየታገዘ ባለፈው ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የራሱን ክልል በራሱ ጊዜ አውጃለሁ በማለት ሲያስጠነቅቅ የከረመውን የሲዳማ ዞን አመራር የአገሪቱ መሪና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በፓርላማ ተገኝተው ለማስፈራራት፣ ወይም ለማስታገስ በሞከሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እንደ ጃዋር መሐመድ ያሉ ፅንፈኛ የኦሮሞ ኃይሎች በበኩላቸው የሲዳማ ወጣቶችን ትኩሳት በማናርና የራስን ዕድል በራስ በመወሰን መብት አከባበር ስም ለዕኩይ ተግባር እንዲሠማሩ በማድረግ ረገድ የተጫወቱት አፍራሽ ሚና የሚናቅ አልነበረም፡፡ በተለይ በስም የተጠቀሰው ግለሰብ በዘንድሮው የፍቼ ጨምበላላ በአል ላይ በአካል ተገኝቶ ‹‹ጉልበታችሁን ተጠቅማችሁም ቢሆን ሲዳማን ከልሉ›› ሲል ደመ ሞቃቶቹን ኤጀቶዎች በአደባባይ የቀሰቀሰበትና ስሜቶቻቸውን ለጥፋት ያነሳሳበት ንግግር፣ ከሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በኋላ በተከታዮቹ ቀናት የደቡብ ክልል መዲና በሆነችው በሐዋሳ ከተማና በሌሎች በርካታ የሲዳማ ዞን አካባቢዎች ለተከሰተው ነውጥ፣ ለጠፋው ሕይወትና ለደረሰው የሀብት ውድመት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ለመገመት ከባድ አይሆንም፡፡
በዚህ ጸሐፊ አስተያየት የመልዓከ ሞት ምሳሌ የሆነው ጃዋር መሐመድ በተገኘበት ሥፍራ ሁሉ እርሱ ዕውቅ የፖለቲካ ሳይንስ ጠቢብ በመሆኑ አያሌ የዓለም መንግሥታትን እንዳማከረ ሲለፍፍና ማለቂያ የሌለውን ቱሪናፋውን ሲረጭ አብዝቶ መስማቱ ክፉኛ ያታከተው አንድ ወዳጄ፣ የቱን ያህል ተማሮ እንደ ወረፈው ያጫወተኝን በዚህ አጋጣሚ ላጋራችሁ ወደድኩ፡፡ ምን እንዳለው ታውቃላችሁ? ‹‹ወንድሜ ሆይ የምትለው ሁሉ እውነት ወይም ሐሰት ሊሆን ይችላል፡፡ እውነት ከሆነ ግን አማከርኳቸው የምትላቸው የዓለም አገሮች እንደ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ወዘተ. ያሉ መሆን አለባቸው፡፡›› ነው ያለው፡፡
ዳተኝነት የተጫጫነው የፌዴራል መንግሥቱ ምላሽ
ይህ ሁሉ ሲሆን የፌዴራሉ መንግሥት ምላሽ በጣሙን ቀዝቃዛና ያለቅጥ በበዛ ቅድመ ጥንቃቄ የተሞላ ሆኖ እንመለከተዋለን፡፡ መደበኛ ባልሆነው የኤጀቶዎች ሁከት ሲታመስ የቆየውን ምልዓተ ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ አብዝቶ ችላ ማለቱ፣ የደቡቡን ወገናችንን ብዙ ዋጋ ማስከፈሉ አልቀረም፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸው የአካባቢ ባለሥልጣናት በራሳቸው የቡድን ታጣቂዎች እየታገዙ አብረዋቸው የሚኖሩትን የሌላ ብሔር ብሔረሰብ ተወላጆች ሲያንገላቱ በፍጡነ ረድኤት ደርሶ የእርምት ዕርምጃ መውሰድና መድህን መሆን የነበረበት የፌዴራሉ መንግሥት በዚህ ረገድ ፍፀም ዳተኝነት ታይቶበታል፡፡ መወሰን ያለበትን መወሰን ባለበት ጊዜ ባለመወሰኑ ሳቢያ የንፁኃን ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ሀብትና ንብረታቸው በወሮበላ ተዘርፏል፣ በእሳት ቃጠሎ ወድሟል፡፡
አሁን አሁን እንደ አገሪቱ ቁጥር ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትር እየተቆጠረ የመጣው ጃዋር መሐመድም ይህንን አጋጣሚ ከሕግ በላይ ሆኖ ያሻውን ጥላቻና ፀብ አጫሪነት ያለገደብ እየገፋ ሃይ የሚለው አካል በመጥፋቱ ይመስላል፣ ለፌዴራሉ መንግሥት ሳይቀር ያለውን ግልጽ ንቀት ለማሳያነት ሲጠቀምበት ማየትና መታዘብ በእጅጉ ተለምዷል፡፡ የሕዝብ ሰላምና ፀጥታን የሚያናጋና የአገሪቱን የግዛት አንድነት ለማፈራረስ የተቃጣ እንደ መሆኑ መጠን የምሬን ነው የምላችሁ፣ የፌዴራሉን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ትኩረት የሚያገኝ ከሆነ ጃዋር በተወዳጁና በሰላማዊው የፍቼ ጨምበላላ በዓል ላይ ተገኝቶ በአደባባይ ያደረገው ቅስቀሳ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 241 ድንጋጌ መሠረት፣ የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት የሚደረግ ከባድ ወንጀል ሆኖ መደንገጉ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ተጠቃሹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ እንደሚከተለው ይነበባል
‹‹ማንም ሰው በኃይል ወይም በሌላ በማናቸውም ሕገ መንግሥትን የሚፃረር መንገድ በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር የአገሪቱ ሕዝቦች አንድነት እንዲፈርስ፣ ወይም ፌዴሬሽኑ እንዲከፋፈል፣ ወይም ከፌዴሬሽኑ ግዛት ወይም ሕዝብ ከፊሉ እንዲገነጠል የሚያደርግ ተግባር የፈጸመ እንደሆነ ከአሥር ዓመት እስከ 25 ዓመት ለመድረስ በሚችል ፅኑ እስራት፣ ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ በዕድሜ ልክ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል፤›› ይላል፡፡ በሥራ ላይ ባለው በዚሁ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ አንድ ሥር እንደተደነገገው ደግሞ ታስቦ የሚፈጸም ማናቸውም የወንጀል ድርጊት በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በአነሳሽነት ወይም በአባሪነት አቋም በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር ሊፈጸም ይችላል፡፡ እንግዲህ ራሱ በቀጥታ ባይፈጽመው እንኳ ወንጀሉን የራሱ ያደረገው በመሆኑ፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት መያዝና መጠየቅ የሚገባው ይህ አደገኛ ግለሰብ በነፃነት እንዲመላለስ የተፈቀደበት አድራጎት፣ የፌዴራሉን መንግሥት ዳተኝነት ወይም ደንታ ቢስነት ከማሳየት ያለፈ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?
መደምደሚያ
ድህረ ደርግ ኢትዮጵያ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞችን ሳይጨምር በጠቅላላው ዘጠኝ ትልልቅና ትንንሽ ክፍለ ግዛቶች አሏት፡፡ እነዚህን ክፍለ ግዛቶቿን ‘ክልል’ እያለች ነው የምትጠራቸው፡፡ ክልሎች የሚቋቋሙት ‹በሕዝብ አሰፋፈር፣ በቋንቋ፣ በማንነትና በሚመለከታቸው ማኅበረሰቦች ፈቃደኝነት› ላይ ተመሥርተው እንደሆነ፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 46 ንዑስ አንቀጽ (ሁለት) ሥር የተደነገገ ቢሆንም፣ በዚሁ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ አንድ መሠረት ተፈጠሩ የተባሉት ዘጠኙም ክልሎች፣ የተጠቀሱትን መሥፈርቶች የሚያሟሉ ሆነው አናገኛቸውም፡፡ የክፍለ ግዛት ሽንሸናው በአመዛኙ እንዲሠራ ታቅዶ የነበረው የነዋሪዎችን ብሔራዊ ማንነትና የሚናገሩትን የአፍ መፍቻ ቋንቋ መነሻ በማድረግ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ዕቅድ በተለይ ደቡብ ላይ ሲደርስ የጨነገፈ ይመስላል፡፡ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የየራሳቸው ክልል እንዲኖራቸው ሲደረግ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙት አያሌ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ግን ጠቀመም ጎዳም ይህ አማራጭ አልተሰጣቸውም፡፡ ለነገሩ ክለላው ሕገ መንግሥቱ እንደሚደነግገው የተከላይ ማኅበረሰቦች የቅድሚያ ፈቃድ ጨርሶ የተጠየቀበት እንዳልነበር ከዚሁ ጋር አያይዞ ማስታወሱ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ እንግዲህ በዓይነት ብዙኃን ሆነው ሳለ ለአያሌ ዘመናት በአንድነት ተሳስረው የኖሩትን ዜጎችና ማኅበረሰቦች በብሔርና በቋንቋ እየለያዩ የማጠሩ አደገኛና ከፋፋይ ፕሮጀክት ያኔ ገና ተጀመረ እንጂ፣ በዘጠኙ ክልሎች ውልደት ብቻ አልተጠናቀቀም፡፡ ይልቁንም ‹‹በዕንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ›› እንዲሉ በእነዚሁ ቀደምት ክልሎች ውስጥ የታቀፉ ሌሎች ህዳጣን ‹‹ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወደፊት እንዳስፈላጊነቱ የየራሳቸውን ክልሎች ሊመሠርቱ እንደሚችሉ፤›› በዚያው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ሥር ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ እነሆ እንደ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ከንባታ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ. ያሉት ደቡብ በቀል ብሔረሰቦች በአሁኑ ወቅት እያከታተሉ የሚያነሱት ጥያቄም፣ ከዚሁ አክራሪ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ነው የሚመነጨው፡፡
እነሆ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዕድሜ ከ25 ዓመት አይበልጥም፡፡ እምዬ ኢትዮጵያ ግን በፖለቲካዊ ህልውናዋ አንጋፋ ከሚባሉት መንግሥታት ተርታ ነው በዓለም ታሪክ የምትመደበው፡፡ ስለሆነም በዕድሜው ገና ለጋ የሆነውና ዘርፈ ብዙ ህፀፅ የሚስተዋልበት ሕገ መንግሥታችን እንደ አገር የመቀጠላችንን ወርቃማ ዕድል በሚያጨልም መንገድ፣ በብሔርተኝነት ምርቃና በተነሳሱ ሰዎች መሣሪያነት የጻፈውን ሁሉ በዘፈቀደ ገቢራዊ ማድረግ ፈፅሞ አይበጃትም፡፡ ሕገ መንግሥት እኮ በአንድ አገር ውስጥ የሠለጠነ ማኅበረሰብ የጋራ መተዳደሪያ ሕግ እንጂ ራሱ አገር አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥት የሚከበረው አገር ፀንታ ስትቆም ብቻ ነው፡፡ የእርሱ መከበር በተቃራኒው አገር እስከ መበተን የሚዘልቅ ከሆነ ግን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ስለመሆኑ አንድና ሁለት አይኖረውምና እዚያው ላይ ተቸክሎ ከመቆዘም ይልቅ፣ ያለ ዕውቀት የተሠራ ስህተት ቢኖር እንኳ በተደረሰበት ጊዜ ፈጥኖ ማረሙ ብልህነት ይሆናል፡፡
በጨረፍታ ለማስታወስ ያህል የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አቶ ክፍሌ ወዳጆ ይመሩት በነበረው የወቅቱ አርቃቂ ኮሚሲዮን አማካይነት ተዘጋጅቶ ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. በሕገ መንግሥታዊ ጉባዔ ከመፅደቁ በፊት፣ ረቂቅ ሰነዱ በያዛቸው አንዳንድ አንኳር ጽንሰ ሐሳቦች ላይ የተካሄዱ የውይይት መድረኮች ነበሩ፡፡ ይህ ጸሐፊ ለይስሙላ ያህል በየሠፈሩ ተዘጋጅተው ከነበሩት ከእነዚያ የውይይት መድረኮች በአንደኛው ተገኝቶ ለመሳተፍና የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ሞክሯል፡፡ ሆኖም በሰሞነኛ ሥልጠና ለብ ለብ ተደርገው በረቂቅ ሰነዱ ላይ እንዲያወያዩን የተመደቡት ካድሬዎች ውይይቱን በነፃነት ከመምራት ይልቅ፣ በድርጅታቸው ተቆጥሮና ተለክቶ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ያላንዳች ይሉኝታ በማስፈጸሙ ተግባር ላይ በማተኮራቸው በሰፊው ስንነታረክ ከቆየን በኋላ ነገሩ ‹‹ጨዋታ ፍርስርስ ያደረ እንጀራ ቁርስርስ›› ሆነና ያለ መቋጫ ስምምነት ነበር የተበታተንነው፡፡
ለምሳሌ ያህል የዚያ ውይይት ታዳሚዎች ሐሳብና አስተያየት እንድንሰጥባቸው ከቀረቡልን ጥያቄዎች አንዱ፣ ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበትን ሥነ ሥርዓት ይመለከታል፡፡ የተባለው የማሻሻያ ሥነ ሥርዓት የከበደ ይሁን ወይስ የቀለለ ሲሉ እንድንወስንላቸው የመድረኩ አወያዮች ለሚያቀርቡት ጥያቄ፣ ይህ ነው የሚባል ማብራሪያ የመስጠት አቅም አልነበራቸውም፡፡ ከመካከላችን አንዳንድ ተሳታፊዎች እጃችንን አውጥተን ጽንሰ ሐሳቡን በመጠኑ ለማብራራት ዕድል ይሰጠን ዘንድ መድረኩን በምንጠይቅበት ጊዜ፣ አስቀድመው ከያዙት ድርጅታዊ ተልዕኮ የምናዘናጋቸው እየመሰላቸው አጥብቀው ሲፈሩና ሲጨናነቁ ተስተውለዋል፡፡ እንግዲህ ከዚህ የተወናበደ አቀራረብ የተነሳ ሥነ ሥርዓቱ ለምን እንደሚከብድ ወይም እንደሚቀል ሳንተማመንበት ነበር በጥያቄው ላይ ወስደነዋል የተባለው አቋም፣ በካድሬዎቹ አማካይነት ተመዝግቦ ወደ በላይ አካል የተላለፈው፡፡ በብሔር፣ ብሔረሰቦች ልየታና ፍረጃ ላይ አተኩሮ የተዋቀረው ፌዴሬሽን የዚሁ ሕገ መንግሥት ቀጥተኛ ውጤት ነው፡፡ ቀድሞ ነገር የእኛ የሐበሾች አኗኗር ጨርሶ ልንለያይ በማንችልበት አኳኋን የተዋደደና የተጋመደ በመሆኑ፣ ከዚያ በፊት ሰምተነው በማናውቀው መንገድ ብሔራችን እየታየና የአፍ መፍቻ ቋንቋችን እየተቆጠረ ያላንዳች አስተማማኝ መለኪያ ከዘጠኝ የተከፋፈልንበትን አመክንዮ በውል አልተረዳነውም፡፡ ለምን በዘጠኝ ክልሎች እንደተከፋፈልን እንኳ እስካሁን አይገባንም፡፡ በዚህ መልክ መከለሉም ቢሆን፣ በማያባራ የድንበር ገፋኸኝ፣ ገፋሽኝ አተካራ እርስ በርስ ከመናቆር በስተቀር ያመጣልን ይህ ነው የሚባል ትሩፋት የለም፡፡
እንግዲህ በተጨማሪ መከለል አያጓጓንም የምለው ከዚህ ሀቅ በመነሳት ነው፡፡ ለአስተዳደራዊ ምቹነት ሲባል በተለያዩ ክፍለ ግዛቶች መዋቀራችን ያን ያህል ነውር ባይሆንም፣ ሕገ መንግሥቱ በሚደነግገው መሠረት ‹‹እንደገና በብሔር ከመከለል ያድነን›› ብርቱ ምኞቴ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን አሻሽለን ወይም ከናካቴው በአዲስ ተክተን ለአገራችን መፃኢ ዕጣ ፈንታ የሚበጀውን እስክንመክርና በጋራ እስክንወስን ድረስ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ራሱ ሲዳማ ላይ ይጀምረው እንጂ፣ በደቡብ ክልል ብቻ እንኳ ልቀጥልበት ቢል ሊጨርሰው የማይችለውን አደናጋሪ የሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት ብሎ ነገር ባይገፋበት ይመረጣል፡፡ ሌላው ቀርቶ በታቀደው ሕዝበ ውሳኔ ለመሳተፍ ሊመዘገቡ የሚችሉትን ባለመብቶች አጥርቶ መለየቱና ድምፅ ማሰጠቱ ኃይለኛ ራስ ምታት ስለሚለቅበት፣ በአካባቢው ጊዜያዊ የፖለቲካ መረጋጋትን ያመጣ መስሎት የደመነፍስ ዕርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ ከወዲሁ ይመከራል፡፡ አበቃሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋከልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡