Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከአክሳሪዎቹ ሰፋፊ እርሻዎች ወደ ውጭ የላክነው ምርትም ሆነ ያገኘነው የውጭ ምንዛሪ ገቢ የለም›› አጥቅየለሽ ጂ.ኤም. ፐርሰን (ዶ/ር)፣ የአካባቢ ፖሊሲ አስተዳደርና የበርካታ ሙያዎች ተመራማሪ

አጥቅየለሽ ጂ.ኤም. ፐርሰን (ዶ/ር) ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀ የአካዴሚያ ልምድና ተሞክሮ በማካበት በተለይ በአካባቢ ፖሊሲና አስተዳደር፣ በዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ጤና፣ እንዲሁም በሕዝብ አስተዳደር መስክ በውጭ ተቋማት ትምህርታቸውን የተከታተሉ የበርካታ ሙያዎች ባለቤት ናቸው፡፡ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በዴቨሎፕመንት ስተዲስ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬፕ ታውን ያገኙት አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፣ በዓለም አቀፍ የኅብረሰብ ጤና ሳይንስም ከስዊድን ሉንድ ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በትምህርት ካካበቱት ዕውቀት ባሻገር፣ በርካታ የምርምር ጽሑፎች በዓለም አቀፍ የሳይንስ ጆርናሎች ለማሳተም ችለዋል፡፡ በአካባቢ፣ በድህነት ቅነሳና በልማታዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ የምርምር መጻፍትንም አበርክተዋል፡፡ በትራንስፖርት ዘርፍ በተለይም በመንገድ ደኅንነት መስክ ከጻፏቸው መካከል፣ ከ11 ዓመታት በፊት የጻፉትና በኢትዮጵያ አሽከርካሪዎች ዘንድ በአስገዳጅነት እንዲተገበሩ በሕግ የተደነገጉት የቀበቶ ማሰርና እየነዱ በስልክ አለማውራት ክልከላዎች ላይ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ እንደሚሰማቸው ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡ ምክንያታቸውም ጽሑፉን በጻፉ በዓመቱ ሕጉ መውጣቱ ነው፡፡ በቅርቡ ለንባብ ያበቁትና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በውጭ የታተመው መጽሐፋቸው በኢትዮጵያ የሰፋፊ እርሻዎችን እንቅስቃሴ የቃኘ ነው፡፡ መጽሐፉ በሰፋፊ እርሻ ሥራ ላይ ለመሰማራት ከገቡ የውጭ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች መካከል ዋነኞች የተባሉ ስድስት ኩባንያዎችን በማጥናት የተነሱበትን ሳያሳኩ ስለወደቁበት ምክንያት ይተነትናል፡፡ በግላቸው ተነሳስተው ጥናት ያካሄዱበትን ይህንን ሥራ በተመለከተ ብርሃኑ ፈቃደ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡ 

ሪፖርተር፡– በመጽሐፍዎ በኢትዮጵያ ያሉ ሰፋፊ እርሻዎችን በሚመለከት በተለይ የውጭ ኩባንያዎች ላይ ምርመራዊ ጥናት አካሂደዋል፡፡ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ሰፊውን የእርሻ ሥራ የተቆጣጠሩት አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ገበሬዎች እንደመሆናቸው፣ በሰፋፊ የውጭ እርሻዎች ላይ ማተኮር የፈለጉበትን ምክንያት ቢያብራሩልን?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ ታስታውስ እንደሆነ እ.ኤ.አ. በ2008 እና በ2009 ተከስቶ በነበረው የፋይናንስ ቀውስ፣ እሱን ተከትለው የመጡት የኢኮኖሚና የምግብ ቀውሶች በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ለም መሬት ፍለጋ ወደ አፍሪካ እንዲራወጡ አድርጓቸዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከዒላማቸው ገብታ ነበር፡፡ እንደመጡም ወዲያኑ ወቀሳዎች ይሰነዘሩባቸው ነበር፡፡ ከአካባቢ ከዘላቂ ልማት አኳያ በርካታ ትችቶች ይሰነዘርባቸው ነበር፡፡ በወቅቱ እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ከአካባቢ፣ ከኢኮኖሚ፣ እንዲሁም ከማኅበራዊ ፋይዳቸው አኳያ አዋጭና ተስማሚ ስለመሆናቸው በጥናት የተደገፈ በቂ መረጃ አልነበረም፡፡ በጋዜጣችሁ ስለአንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች የተጻፉትንም አንብቤ ነበር፡፡ በመሆኑም እነዚህ ፕሮጀክቶች ከኢትዮጵያ ፖሊሲዎች አኳያ ያላቸውን ተስማሚነት ለማጥናትና ለመመርመር ወሰንኩ፡፡ ከፖሊሲዎቹ አኳያ ተስማሚ ቢሆኑ እንኳ፣ በመሬት ላይ በተጨባጭ የሚሠሩት ምን እንደሚመስል ማየትና ማረጋገጥ የጥናቴ ዓላማ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡– የጥናት ውጤቶችዎን ያሳተሙበት መጽሐፍ ስድስት የውጭ ኩባንያዎችን እንዳጠኑ ያሳያል፡፡ በአካል ወደ እርሻዎቹ መገኛ ቦታ በመሄድ ምን እየተካሄደ እንደሚገኝ ዓይተዋል፡፡ ነገር ግን ከሌሎች የውጭ ሰፋፊ እርሻዎች ስድስቱን ብቻ የመረጡበት ምክንያት ምንድነው?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ በ2003 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከ5,000 ሔክታር በላይ መሬት በፌደራል መንግሥት እንዲተዳደር የሚያስችል ሕግ አውጥቶ ነበር፡፡ ይህ ከዚህ ቀደም በክልሎች እጅ ሲተዳደር ቢቆይም የሰፋፊ እርሻዎችን መምጣት ተከትሎ የክልሎች የማስተዳደር አቅም ውስን መሆን ማዕከላዊ መንግሥት መሬቶቹን ተረክቦ ለማስተዳደር ያነሳሳው ይመስለኛል፡፡ ስድስቱን ማሳያ ፕሮጀክቶች ለጥናት ስመርጥ መመዘኛ መሥፈርቶችን መሠረት በማድረግ ነበር፡፡ አንደኛው 5,000 ሔክታርና ከዚያ በላይ ይዞታ ያላቸው መሆናቸው ነው፡፡ ሁለተኛው በምግብ ሰብልና እንደ ባዮፊውል ባሉ ምርቶች ላይ የተሠማሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ትንሽ ስለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መለስ ብለን ብናይ፣ አብዛኛው የውጭ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሳተፉ የሚታዩት በማኑፋክቸሪንግና በአገልግሎት መስኮች ነው፡፡ ነገር ግን በግብርና ላይ ያተኮሩት ፕሮጀክቶች በምግብና በኃይል ምንጭ ሰብሎች ላይ በማተኮር ወደ ውጭ ለመላክ የመጡ ናቸው፡፡ ይህ ለምን ሆነ ቢባል በየአገሮቻቸው የሚታየው የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፣ እንዲሁም ዕድገቱን የሚመጣጠን የምግብ አቅርቦት መፍጠር ከባድ እየሆነባቸው በመምጣቱ አገሮች ይህንን ለመፍታት አመቺ ሁኔታዎችን ሲፈልጉ አፍሪካ ላይ ዓይናቸውን አሳርፈዋል፡፡ አፍሪካን ሲመለከቱም ለም መሬት እንደ ልብ የሚገኝባት፣ ዝቅተኛ ወጪ የሚጠይቅ የሰው ጉልበት የተንሰራፋባትና በአነስተኛ ኢንቨስትመንት ብዙ መሥራት የሚችሉባት አኅጉር ሆና ስላገኟት ነው የመጡት፡፡ የምግብ ቀውሱ ዓለምን ከመምታቱ በፊት የውጭ ኩባንያዎች አብዛኛው ትኩረት በማዕድናትና በሌሎች ወሳኝ በሚባሉት የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ እንጂ፣ የእርሻ መሬትን በሚመለከት ፍላጎታቸው እምብዛም ነበር፡፡ ከቀውሱ በኋላ ግን መሬት ስትራቴጂካዊ ሀብት ሆኖ በመገኘቱ በርካቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ጀመሩ፡፡ የአገሪቱ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችም ሰፋፊ የግል እርሻዎችን ስለሚደግፉ ጭምር በርካቶች እንዲመጡ አስችሏቸዋል፡፡ ከኩባንያዎቹ መምጣት አኳያ የፖሊሲዎቹን ጉዳይ ስናይ የተጣጣሙ መሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡ ፖሊሲዎቹ ብቁና ሁሉን አቀፍ ይዘት ያላቸውም ናቸው፡፡ በመሆኑም እኔ ጥናት ላካሂድባቸው የፈለግኳቸው ኩባንያዎች ከሁለት ዓመታት በላይ ቆይታ ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ በዚህ መመዘኛ ጭምር ነው እነዚህን ኩባንያዎች በጥናቴ ያካተትኳቸው፡፡

ሪፖርተር፡– ስለዚህ ስድስቱ ኩባንያዎች ብቻ ናቸው ማለት ነው መሥፈርቶችዎን ያሟሉት?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አኳያ በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት ከታዩ አዎን በትክክል፡፡ አብዛኞቹ ሰፋፊ እርሻዎች ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ ነበር የተከማቹት፡፡ በወቅቱ በቤንሻንጉል ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን በባዮፊውል ላይ የተሰማራውን አንድ ኩባንያ በመሥፈርቱ መሠረት በጥናቴ አካትቻለሁ፡፡ ለእኔ ይህ ተቃርኖ ነበረው፡፡ ስለምግብ ዋስትና ችግር እየተነጋገርን በነበረበት ወቅትና ለምርት በገቡበት አካባቢ የሚገኙ ማኅበረሰቦች የምግብ እጥረት እያለባቸውም፣ ኩባንያዎቹ ምግብ ለማምረትና ወደ ውጭ ለመላክ አንዳንዶቹም ባዮፊውል ለማምረት መምጣታቸው ግራ ያጋባል፡፡ የሥነ ምግባር ጥያቄም አለበት፡፡ መንግሥት በምግብ እጥረት የተቸገረውን ማኅበረሰብ ሊያግዝ ይችላል፡፡ ባዮፊውል አምርተው ለውጭ ገበያ በመሸጥ ከሚገኘው ገቢ ምናልባትም ለማኅበረሰቡ ምግብ ፍጆታና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡– ኩባንያዎቹ ግን ባዮፊውል አምርተው ለመሸጥ ብቻም ሳይሆን እንደ ሩዝ፣ ስንዴ፣ አኩሪ አተርና መሰል የምግብ ሰብሎችንም ለማምረትና ለመሸጥ የመጡ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ኩባንያዎቹ የምግብ ሰብል የምግብ ዋስትናው ባልተረጋገጠ ማኅበረሰብ ውስጥ በማምረት ወደ ውጭ ለመላክ መምጣታቸው ተቃርኖ አለው ሊባል ይችላል?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ የሚመጣው የውጭ ኩባንያ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና ዕውቀት ይዞ እንደሚመጣ ይታመናል፡፡ ኩባንያውን የሚቀበለው አገርም ዓለም አቀፍ ገበያ የማግኘት ዕድል ሊኖረው ይችላል፡፡ በእነዚህ ተስፋ አዘል ሐሳቦች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ብሎም የአገር ውስጥ ቁጠባ አቅሙን ለማሳደግ ሲል በርካታ የውጭ ኩባንያዎች እንዲመጡለት ይፈልጋል፡፡ እንዳለመታደል ግን የመጡት ኩባንያዎች የትኛውንም የመንግሥት ፍላጎትና ምኞች ሊያሳኩ አልቻሉም፡፡ ፕሮጀክቶቹ የታሰበውን ማሳካት ሳይችሉ ስለወደቁበት ምክንያት መጽሐፉ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ አንደኛው ምክንያት ኩባንያዎቹ ስለሰፋፊ እርሻ ልምዱና ዕውቀቱ ሳይኖራቸው ወደ ሥራው መግባታቸው ነው፡፡ እነሱን እንዲያግዙና እንዲደግፉ የተዋቀሩት የመንግሥት ተቋማትም በሚገባ ያልተደራጁና ብቃቱ የጎደላቸው ነበሩ፡፡ በቂ የሰው ኃይልም ሆነ የገንዘብ አቅም አልነበራቸውም፡፡ ሌላኛው የውድቀታቸው ምክንያት የተሟላ መሠረተ ልማት አለመኖሩ ነው፡፡ መንገዶች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የግንኙነት ወይም የተግባቦት አውታሮችና ሌሎችም ለሥራ የሚያግዙ መሠረተ ልማቶቸ አልተሟሉላቸውም ነበር፡፡ እነዚህ ባልነበሩበት ወቅት ነው በርካቶቹ ወደ ሥራ የገቡትና በርካቶቹም ሥራቸውን አቁመው ለመሄድ የተገደዱት፡፡ መጽሐፌ ስድስቱ ኩባንያዎች ሊሠሩ ስላቀዷቸው፣ ነገር ግን ማሳካት ስላልቻሏቸው ጉዳዮች ያትታል፡፡ እናመርታለን ያሉትና ከዓመታት በኋላ በተግባር ያሳዩት ውጤት ትልቅ ልዩነት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡– በጥናትዎ ከጠቀሷቸው የስድስቱ ኩባንያዎች አፈጻጸም ለመታዘብ እንደተቻለው ለዓመታት ያሳዩት የሥራ ውጤት ከሰባት እስከ 28 በመቶ ብቻ ያለውን የዕቅዳቸውን ክፍል ነው፡፡ በመሆኑም ወደ ሥራ ከገቡ ጀምሮ ያስመዘገቡት ይህ አፈጻጸም ከላይ በጠቀሷቸው ችግሮችና አለመሟላቶች ሳቢያ የመጡ ናቸው ሊባሉ ይችላሉ?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ አዎን፡፡ ነገር ግን የፀጥታ ችግርም አጋጥሟቸዋል፡፡ ድርጅቶቹ እንደሚፈልጉት ለመሥራት ያላስቻሉ ግጭቶች ይከሰቱ ነበር፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ዕጦት ትልቅ ጫና በማሳደሩ በናፍጣ የሚሠሩ ጄኔሬተሮች ላይ ጥገኛ ለመሆን ተገደዋል፡፡ በዚህ መንገድ የግብርና ሥራ መሥራቱ ወጨውን በከፍተኛ ደረጃ እንዲንር ያደርገዋል፡፡ አንዳንዶቹ ኩባንያዎችም ለሚያመርቱት ምርት ተስማሚ መሬት አልተሰጣቸውም ነበር፡፡ በጣም ወሳኙ ነገር ግን የአካባቢው ማኅበሰረብ በፕሮጀክቶቹ መምጣት ላይ ተሳትፎ ሳያደርግና በውሳኔ አሰጣጡ ላይ ሳይሳተፍ እንዲገቡ መደረጋቸውም ትልቅ ችግር ፈጥሯል፡፡ ለነዋሪዎቹ ስለፕሮጀክቶቹ መግባትም ሆነ ስለአስፈላጊነታቸው ማንም የነገራቸው የለም፡፡ ከመነሻው ጀምሮ ማኅበረሰቡ ተሳትፎ ቢኖረው ኖሮ አስከፊው የኩባንያዎቹ ውድቀት ብዙም ላያጋጥም ይችል ነበር፡፡ ማኅበረሰቡ ስለአካባቢው ሥነ ምኅዳር ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ምን ዓይነት ሰብል ሊበቅል እንደሚችል፣ የትኛው ውጤት እንደማይሰጥ ምክር ሊሰጥም ይችል ነበር፡፡ የመሬት አጠቃቀም ዕቅዱ አሳታፊ መሆን ነበረበት፡፡ ይህ ግን አልተደረገም፡፡ ይልቁንም ነዋሪዎቹ ማሽነሪዎቹ ሲንጋጉባቸውና ሰፊውን ሁዳድ ማረስ ሲጀምሩ ነው ምን እየተካሄደ እንደሆነ ያወቁት፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝቡ በአካባቢው ስለሚካሄድ የልማት ሥራ የማወቅና መብቱ ተረጋግጥሏል፡፡ ይህ መብቱ ግን ሊከበርለት አልቻለም፡፡

ሪፖርተር፡– እንደ ካሩቱሪና ሳዑዲ ስታር ያሉ ኩባንያዎችን አጥንተዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን እጅግ ዝቅተኛ በሆነ የሊዝ ዋጋ ያገኙ፣ የረዥም ጊዜ የታክስ ዕፎይታና ችሮታ የተሰጣቸው ናቸው፡፡ ይሁንና ኩባንያዎቹ ሲገቡ የሕዝቡ አለማወቅ ብቻም ሳይሆን፣ የካሳና ከአካባቢ የመፈናቅ ጉዳዮች አነጋጋሪ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በጥናትዎ ምን አገኙ?  

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ ጥናቱን ከመጀመሬ በፊት ኢክላንድ ኢንስቲትዩት የተባለው የመብት ተሟጋች ተቋም በርካታ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን በመግለጽ ተቃውሞ አሰምቶ ነበር፡፡ ይሁንና እኔ ግን ይህ ሙሉ እውነታውን ያዘለ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ይልቁንም አብዛኞቹ ኩባንያዎች የተሰጣቸው መሬት ጥቅጥቅ ደን ውስጥ የሚገኝ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ የደኑ ይዞታ የማኅበረሰቡ ንብረትና ከትውልድ ትውልድ ሲቀባበለው የመጣው ሀብቱ ነው፡፡ እነዚህ የማኅረሰቡ ይዞታ የሆኑት የደን ሀብቶች ከኢኮኖሚ ባሻገር ለማኅበረሰቡ ሥነ ልቦናዊ ዋጋም ነበራቸው፡፡ ደኑን እንደ ተቀደሰ ሥፍራ ነው የሚያዩት፡፡ ቀደምት ዘሮቻቸውንም የቀበሩት በደኑ ውስጥ በመሆኑ ልዩ አክብሮት ይሰጡታል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ሳያውቀው እንዲህ ያለ የልማት ሥራ በማምጣት ደኑን ስትነካው ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ትችላለህ፡፡ የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል ከፊል ይዞታም ለሰፋፊ እርሻዎቹ ከሰጡት መሬቶች ውስጥ ይገኝበታል፡፡ የስምምነት ውሎቹ ከመፈጸማቸው ቀድሞ ሕዝቡን ማወያየትና ሐሳቡን መቀበል ቢቻል ኖሮ በርካታ ውድቀቶችን ማስቀረት ይቻል ነበር፡፡ ከቦታ ከማስነሳት አኳያ አንድ ቀበሌ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ዜጎች በባሮ ወንዝ ሙላት ምክንያት እንዲነሱ መደረጋቸውን አረጋግጫለሁ፡፡ የነዋሪዎቹ ከቀዬአቸው መነሳት ከወንዙ ሙላት ሥጋት ጋር በተያያዘ እንጂ፣ በኩባንያዎቹ መምጣት ሳቢያ የተደረገ አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- የሰፋፊ እርሻዎች ውድቀት እንዴት እንደሆነ ዓይተናል፡፡ ግን አሁንም ኢትዮጵያ ለሰፋፊ የውጭ እርሻዎች ምቹ ናት ማለት ይቻላል? የጥናት ውጤቶችዎስ የኢትዮጵያን ምቹነት ይጠቁማሉ?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ እንግዲህ በምክረ ሐሳብ ካስቀመጥኳቸው መካከል መንግሥት አሁንም ሰፋፊ እርሻዎችን የማምጣት ፍላጎቱ ካለው፣ እነዚህን ሊያግዙ የሚችሉ መንግሥታዊ ተቋማቱን ብቃት ባለው የሰው ኃይል መገንባትና በፋይናንስም በሚገባ ማደራጀትና ማስታጠቅ ይኖርበታል፡፡ ተቋማቱ ካላቸው አቅም አኳያ ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸውን የውጭ ኩባንያዎች መቀበል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን ቢያደርጉ የሚመጡትን ኩባንያዎች በአግባቡ ለመከታተል ያስችላቸዋል፡፡ በመጽሐፌ የመንግሥት ተቋማት የአቅም ችግር ብቻ አልነበረም የሚታይባቸው፡፡ ማንም ይምጣ መዝግበው ፈቃድ ይሰጡ ነበር፡፡ የሚመጣውን ሰው ወይም ኩባንያ የኋላ ታሪክና የሥራ ልምድ አያጣሩም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡– መንግሥትም ኩባንያዎቹም የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ማካሔዳቸውን ሲገልጹ ይደመጡ ነበር፡፡ ይሁንና በመጽሐፍዎም እንደጠቀሱት በተግባር ከታዩት መካከል ሌላው ቢቀር የውኃ አጠቃቀም ሥርዓትና ውኃውን መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውሉበት ዘዴ አልነበራቸውም፡፡

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ ጥሩ የሚያሠሩ ፖሊሲዎች ቢኖሩም እሱም ተግባራዊ ማድረጉ ግን የቀን ህልም ነበር የሚመስለው፡፡ የትኛውም ፕሮጀክት በአካባቢና በሕዝብ ላይ ሊያደርስ ስለሚችለው ተፅዕኖ ግምገማ በማከናወን ሥራ ከመጀመሩ በፊት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ይሁንና ያጠናኋቸው ሁሉም ፕሮጀክቶች ግን የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የሠሩት ሥራ ከጀመሩ በኋላ ነበር፡፡ የተፅዕኖ ግምገማውን ያካሄዱት መሥፈርቱን ለማሟላት እንጂ፣ በማኅበረሰቡና በአካባቢ ላይ ሊያደርሱ ስለሚችሉት ተፅዕኖ አስበው አልነበረም፡፡ ይህ በመሆኑም ተፅዕኖን መከላከል የሚያስችሉ አንዳችም ተግባራትን መፈጸም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ያካሄዷቸው የተፅዕኖ ግምገማ ሰነዶችም የትም ተጥለዋል፡፡ ለነገሩ ሰነዶቹ መገኘት የነበረባቸው የእርሻ ሥራቸውን በሚያካሄዱባቸው ጣቢያዎች ቢሆንም አንድም አታገኝም፡፡ ችግር ቢከሰት ከግምገማ ሰነዱ የመከላከያ ሥልቶችና ለመቋቋም የሚያግዙ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ይቻላል ተብሎ ስለሚታመን ሰነዶቹ በሥራ አካባቢ መቀመጥ ነበረባቸው፡፡ የመንግሥት ተቋማትም ቢሆኑ ኩባንያዎቹ ምን እየሠሩ እንደነበር፣ በአካባቢና በማኅበረሰቡ ላይ ስላደረሱት ተፅዕኖም ኦዲት ሳያደርጉ ልቅ ትተዋቸው ነበር፡፡ ነገሩ ሁሉ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ በጠቅላላው የሰፋፊ እርሻ ፕሮጀክቶቹ በኢኮኖሚ፣ በማኅበረሰቡና በአካባቢ ላይ ከጉዳት በቀር ይህ ነው የሚባል ጥቅም ሊያስገኙ አልቻሉም፡፡ 

ሪፖርተር፡– ጥናቱን እንዴት ነበር ያካሄዱት? ኩባንያዎቹስ  ለጥናት እንደ ሄዱ ሲያውቁ አቀባበላቸው ምን ይመስል ነበር? አንዳንዶቹ እርስዎን ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልነበሩ በመጽሐፍዎ ጠቅሰውታል፡፡

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡እኔ ለአገሬ ላበረክት የምችለው አስተዋጽኦ ምርምር በማካሄድ የምርምሩን ውጤቶች ለማሳወቅ በማደርገው ጥረት ነው፡፡ በመጽሐፌም ያደረግኩት ይህንኑ ነው፡፡ መረጃ ፍለጋ ስወጣ የማይታለፍ የሚመስል ከባድ ችግር ነው ያጋጠመኝ፡፡ እንደማስበው ላጠና ይዤ የተነሳሁት ጉዳይ በወቅቱ ፖለቲካዊ ሥጋት ነበረበት፡፡ በርካታ ሰዎች እኔን ለማነጋገር አይፈልጉም ነበር፡፡ ሰዎችን ለማነጋገር ስጥር በርካታ ፈተናዎች ገጥመውኛል፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎችን በቀላሉ ማግኘት አልችልም፡፡ ሳገኛቸውም በርካታ የማጣራትና ቀጠሮዎችን ደጋግመው የመሰረዝ አጋጣሚዎች በሰፊው ይከሰቱ ነበር፡፡ በርካቶች በራቸውን ዘግተውብኛል፡፡ ባሀብቶቹም መጀመርያ ሰሞን ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ እርግጥ ሳዑዲ ስታር ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሰጡኝ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ከብዙ ምልልስ በኋም ቢሆን ካሩቱሪዎች እኔን ለማነጋር ፈቃደኞች ሆነዋል፡፡ ሌሎችም ቀስ በቀስ በራቸውን ገርበብ አድርገውልኛል፡፡ ሒደቱ ግን ያሳምማል፡፡ የትኩረት ቡድን በመፍጠር ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይቶችን አካሂጃለሁ፡፡ የፌደራል መንግሥት ተቋማትና ኃላፊዎች ግን ሲበዛ ዝግ ነበሩ፡፡ ምርምር ለዕድገት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ለራሳቸውም ስለሚበጃቸው ምርምር እንዲካሄድ ማገዝና መደገፍ አለባቸው፡፡ እኔ ካካበትኩት ዕውቀትና ልምድ በመነሳት የበኩሌን ለማበርከት ነበር የምጥረው፡፡ አጥኚዎችንና ተመራመሪዎችን የሚያከብር ባህል ሊኖረን ይገባል፡፡ ብቃቱና ዕውቀቱ ያላቸውን አጥኚዎችና ተመራማዎች ከጎንህ ሳትይዝ በሚገባ የታሸና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ልታወጣ አትችልም፡፡ ታግዬም ቢሆን ማሳካት የቻልኩትን በማየቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ እንደውም የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ መሪ ማንዴላ በአንድ ወቅት ሲናገሩ፣ ‹አንድ ነገር ከመፈጸሙ በፊት ሁሌም የማይቻል ይመስለናል፤› ብለው ነበር፡፡ የማይቻለውን ችያለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡– በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ያካሄዱትን ጥናትና ውጤቶቹን በመጽሐፍ ለማውጣት ከአምስት ዓመታት በላይ ፈጅተዋል፡፡ ረዥም ጊዜ የፈጀ አይመስልዎትም?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ የተወሰኑ ዓመታትን ወስዷል፡፡ አብዛኞቹ የፖሊሲ ሰነዶች ሰፊ ምልከታና ጥናት ይፈልጉ ነበር፡፡ ከግብርና ጀምሮ፣ የገጠር ልማት፣ የትህምርት፣ የጤና፣ የመሬት ፖሊሲዎችንና ልዩ ልዩ አዋጆችን ብሎም ደንቦችና ሌሎችም የሕግ ሰነዶችን መመርመር ነበረብኝ፡፡ የተለያዩ መዛግብትን በማገላበጥ የእርሻ መሬቶቹን የአሁንና የበፊት ማንነት ማጣራት ብሎም እርሻዎቹ ከመግባታቸው በፊት ስለነበረው ሁኔታ የሚያሳዩ ሰነዶችን ማጥናት ያስፈልገኝ ነበር፡፡ ኢንቨስተሮቹን፣ የመንግሥት ኃላፊዎችንና የማኅበረሰቡን አባላት ማነጋገር ግድ ይለኝ ነበር፡፡ ሦስቱን አካላት በማነጋገር ያገኘሁትን መረጃ ከሦስት አቅጣጫዎች ወደ አንድ ማዕከል ማምጣትና ምርምሩን ማካሄድ ያስፈልግ ነበር፡፡ ወደ እርሻዎቹ በመሄድ አሠራራቸውንና እንዴት እንደሚያመርቱ መመልከትም ለጥናቱ አስፈላጊ ሥራ ነበር፡፡ የኬሚካልና መሰል ግብዓት አጠቃቀማቸውንም ማጥናት ነበረበኝ፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ የተጠቀሙባቸውንም ያልተጠቀሙባቸውን ኬሚካሎች በግድየለሽነት በየሜዳው በታትነዋቸው ታገኛለህ፡፡ አደገኛና መርዛማ ኬሚካሎች በየአካባቢው ሲጣሉ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውኃን መበከላቸው ከሚያስከትሉት ጉዳት መካከል ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህን ሁሉ ለማጥናትና በሰነድ ለማስቀመጥ ዓመታትን ጠይቋል፡፡ የሚታየው ክፍተት በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ሕጉ የሚለውን እንዲያስከብሩና እንዲያስፈጽሙ የተመደቡ ሰዎች ሥራቸውን ረስተውታል፡፡ ባለሀብቶቹም ከሕጉ ውጪ ሲሄዱ ምንም አይመስላቸውም፡፡ የኢንቨስትመንት ፖሊሲው ካስቀመጣቸው መካከል ሰፊ የውጭ ኩባንያዎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ማድረግ አንዱ ነው፡፡  በሰፋፊ እርሻዎች በኩል ካየነው ግን ይህ የማይታሰብ ነው፡፡ አብዛኞቹ ሰፊ ካፒታል የሚፈልግ ሥራ በመያዛቸውና አብዛኛው ሥራቸው በማሽን የሚከናወን በመሆኑ ለሰዎች ሥራ ማስገኘታቸው እምብዛም ነበር፡፡ ለሚፈልጓቸው ሥራዎችም ቢሆን ከውጭ በማስመጣት ያሠሩ ነበር፡፡ ምነው ሲባሉም በኢትዮጵያ የምንፈልገውን ሙያና ክህሎት ያለው ሰው ማግኘት አልቻልንም ይላሉ፡፡ የመንግሥት የውጭ ኢንቨስትመንት ፖሊሲ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሊያስገኙ የሚችሉ ኢንቨስትመንቶችን ከውጭ መሳብ እንደሚያስፈልግ አስፍሯል፡፡ ነገር ግን በእርሻዎቹ አካባቢ የሚኖረው ማኅበረሰብ፣ ከጥንት የእርሻ መሣሪያዎችና ከተለመደው የአስተራረስ ዘዴው የተለወጠለት ነገር የለውም፡፡ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር አሻሚና በተግባር ማየትም አዳጋች ነው፡፡ ትልልቅ እርሻዎችን የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማሳተፍ አነስተኛ ገበሬዎች በተለይ በኮንትራት ምርት እንዲያመርቱላቸው የሚያደርጉበት አሠራር እንደሚኖር በግብርና መስክ የሚሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች ፖሊሲ ውስጥ ቢካተትም፣ አንዱም እርሻ አነስተኛ ገበሬዎችን በምርት አብቃይነት አላሳተፈም፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ይህንን ፖሊሲ እንዲያስፈጽሙ በተቋቋሙት መንግሥታዊ ተቋማት አቅም ማነስና ደካማነት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡– መጽሐፍዎ ከመታተሙ ቀድሞ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ስለጥናትዎ ግኝቶች ተነጋግረው ነበር?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ ይህ እንኳ አልሆነም፡፡ በአብዛኛው ሥራዬ ላይ በማተኮሬ ማንንም ስለጥናቱ ውጤት አላነጋገርኩም፡፡ የእኔ ሐሳብ መጽሐፉ ከታተመ በኋላ ፖሊሲ አውጪዎቹ ሊያገኙትና ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል ነው፡፡ ለመንግሥት ተቋማትና ለአካዴሚያን ፍጆታ መዋል የሚችል መጽሐፍ ይመስለኛል፡፡ ለወደፊቱ መንግሥት በውጭ ኩባንያዎች የሰፋፊ እርሻ ሥራዎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ከሆነ፣ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልገው በምክረ ሐሳብነት ያቀረብኳቸውን ጉዳዮች ማየቱም ይጠቅማል እላለሁ፡፡ ከግብርና ባሻገር የኤኮ ቱሪዝም ሥራዎች ላይም ትኩረት ቢደረግ ውጤት ሊገኝ እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች ለኤኮ ቱሪዝም የሚመቹ ናቸው፡፡ ግን ተጨማሪ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡– አብዛኛው የጥናትዎ ክፍል ከአምስት ዓመታት በነበሩ ክስተቶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት ሰፋፊ እርሻዎችን ለማስፋፋት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ አኳያ መጽሐፍዎ የቱን ያህል ወሳኝ ምክር ሊያቀርብለት ይችላል? 

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ መጽሐፉ ፖሊሲ አውጪዎችንም ሆነ ሌላውንም አካል ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት ሊያገለግላቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሰፋፊ እርሻዎች ላይ የውጭ ባለሀብቶችን የማስገባቱ ሥራ ወደፊትም ስለሚቀጥል መጽሐፉ ሊያግዝ ይችላል፡፡ ሰፋፊ እርሻዎችን ዘላቂነት ባለውና አሳታፊ በሆነ መንገድ እንዴት በአግባቡ መጠቀም ይቻላል የሚለው ጉዳይ፣ በርካቶች ትኩረት እንዲሰጡበት ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡– ሳይሳኩ ስለከሸፉት ሰፋፊ እርሻዎች ሲያጠኑ ከደረሱባቸው የጥናት ውጤቶች ሁሉ በጣም ወሳኝ የሚሉት ግኝት የትኛውን ነው?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ የመንግሥት ተቋማት ደካማነት አንደኛው በጥናት ካገኘኋቸው መካከል የሚጠቀሰው እንደሆነ ገልጬያለሁ፡፡ በፕሮጀክቶቹ ላይ ያደረግኩት የረባ ክትትል አልነበረም፡፡ መሬት ሲሰጡም የአካባቢውን ነዋሪዎች ማነጋገር እንዳለበቸው፣ ሕዝቡም ሐሳቡን የመግለጽ መብት እንዳለው አላሰቡም፡፡ ውኃ ገብ መሬቶችንና ብሔራዊ ፓርክን የመሰለ ሀብት ለእርሻ ሥራ ከመስጠት የሚታቀቡትን አሠራር መፍጠር ነበረባቸው፡፡ ተቋማቱ በሚገባ ሊደራጁና በሰው ኃይልም ሊታገዙ ይገባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡– የሰፋፊ እርሻዎቹን በሚያጠኑበት ወቅት ደሃ ተኮር ኢንቨስትመንት ይዘው ስለመምጣታቸው የለኩበት፣ በዚህም ልኬት መነሻነት ኩባንያዎቹን የመዘኑበት ክፍል በመጽሐፍዎ ተብራርቷል፡፡ ኩባንያዎቹ ይህንን መመዘኛ ማለፍ ስላልቻሉበት ጉዳይ ቢያብራሩልን?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ መመዘኛዎቹ ደሃ ተኮርና ለአካባቢ ዘላቂነት ትኩረት የሚሰጡ መርሆዎችን መሠረት ያደረጉ የሰፋፊ እርሻዎች መለኪያዎች ናቸው፡፡ መመዘኛዎቹ ኃላፊነት የሚሰማቸው ባለሀብቶችና ኢንቨስትመንቶች እንዳሉ ለማረጋገጥ ጭምር የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ የምግብ ዋስትናን ሥጋት ውስጥ አለመጣል፣ ነባር ማኅበሰቦችንና ባህሎቻቸውን ማክበር፣ ለአካባቢ ተስማሚነትና መሰል የመመዘኛ መሥፈርቶችን በመጠቀም የሰፋፊ እርሻዎቹን የሥራ እንቅስቃሴ ለመለካት ተሞክሯል፡፡ 

ሪፖርተር፡– ከእነዚህ መሥፈርቶች አብዛኞቹ እርሻዎች ማሟላት ያልቻሉት የትኛውን ነበር?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ እንደ ፕሮጀክቱ ሁኔታ ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ቶረን የተሰኘው አንድ ኩባንያ፣ ለእርሻ ሥራው ተስማሚ ያልሆነ መሬት በመውሰዱ ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡ ሩኪ የተሰኘው ኩባንያ ደግሞ በፀጥታና በኤሌክትሪክ ኃይል ችግሮች ሳቢያ ምርቶቹን ማስፋፋት አልቻለም ነበር፡፡ በፌደራል፣ በክልልና በወረዳ መካከል የአሠራር ከፍተቶች ነበሩ፡፡ ፌደራል መንግሥት የታክስ ዕፎይታ ሰጥቼያለሁ ያለው ኩባንያ በክልል ወረዳ ታክስ አሁኑኑ ክፈል እየተባለ አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ ሲገባም ታይቷል፡፡ ሳዑዲ ስታርን በምሳሌነት ብናነሳ በጋምቤላ አካባቢ በነበረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ሠራተኞቹ ሳይቀር ተገድለውበት ለተወሰነ ጊዜ ሥራ ለማቆም ተገዶ ነበር፡፡ ካሩቱሪን ያየን እንደሆነ፣ ኩባንያው በተሳሳተ መንገድ በገነባው የመስኖ ማጠጫ ሥርዓት የተነሳ ሦስት መንደሮችን በጎርፍ አጥለቅልቆ ራሱም ለጉዳት ተዳርጓል፡፡ ምንም እንኳ የጎርፍ መጥለቅለቅ አልፎ አልፎ ቢኖርም፣ ኩባንያው የገነባው መስኖና ማጠጫ ቦይ ግን ችግሩን አባብሶታል፡፡ ተጨማሪ ጥናቶች እንዲካሄዱ አሳስባለሁ፡፡ ምክንያቱም በጎርፍ በተወሰዱት መንደሮች ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ምን ዓይነት ዘላቂ የጤና ችግር፣ እንዲሁም ሌሎችም የሶሺዮ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች እንደደረሱ በጥናት ማረጋገጥ ስለሚያስፈልግ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- መንግሥት ከሰፋፊ እርሻዎች ተገቢና ዘላቂ ጥቅም ለማግኘት በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ውስጥ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡- ግብርናችንን በሚገባ ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡ ግብርናው መለወጥ አለበት፡፡ ግን እንዴት እንለውጠው የሚለው ላይ በሚገባ መጠየቅና መነጋገር ያስፈልገናል፡፡ ሰፋፊ የንግድ እርሻዎች ያስፈልጉናል ካልን፣ ከፖሊሲዎቻችን ጋር ሳይቃረኑና አዋጭ ሆነው የሚጓዙበትን ዘዴ መቀየስ ይጠበቅብናል፡፡ ተቋሞቻችን ማብቃትና አቅማቸውን መገንባት አለብን፡፡ እኔ ግን ከተፈጥሮ አካባቢያችን አኳያ ኢኮ ቱሪዝምን በትኩረት እንድናየው አሳስባለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡– ሳይሳኩ በቀሩት ሰፋፊ እርሻዎች ሳቢያ በማኅበራዊ፣ አካባቢያዊና ሥነ ምኅዳራዊ ጉዳቶች እንደተከሰቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይሁንና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ በገንዘብ ሲተመን ምን ያህል ሊሆን ይችላል?

አጥቅየለሽ (ዶ/ር)፡ ይህንን የሚያሳይ አኃዝ አላስቀመጥኩም፡፡ ነገር ግን ለዓመታት ሳያሳኩ ከቆዩት ተግባር አኳያ ጉዳቱ ምን ያህል እንደሚሆን ራሱ የሚናገር ይመስለኛል፡፡ ከአክሳሪዎቹ ሰፋፊ እርሻዎች ወደ ውጭ የላክነው ምርትም ሆነ ያገኘነው የውጭ ምንዛሪ ገቢ የለም፡፡ የተነሱበትን አለማሳካታቸው የወጪውን መጠን የሚጠቁም ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ወጪውና ኪሳራው ምን ያህል ነው የሚለውን የሚያሳይ ቁጥር አላካተትኩም፡፡ በፕሮጀክቶቹ አማካይነት የተፈጠረው ኪሳራ ትልቅ መሆኑ አያጠራጥም፡፡ 70 በመቶ የፕሮጀክት ወጪያቸውን በብድር የሸፈኑት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባገኙት ብድር ነው፡፡ 30 በመቶው የእነሱ አስተዋጽኦም አጠያያቂ ክፍተቶች አሉበት፡፡ በተጨማሪም ታክስና የጉምሩክ ቀረጥ አልከፈሉም፡፡ መሬቱም የተሰጣቸው ነፃ በሚባል ሒሳብ ነው፡፡ ምናልባት በአማካይ በሔክታር 20 ብር የሊዝ ዋጋ ቢክፍሉ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጉዳቱና ኪሳራውን ለብቻው ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል ጥናት ማካሄድ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...