Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቡና ንግድ ተጠቃሚው ማን እንደሆነ ባነጋገረው መድረክ ላኪዎችና ምርት ገበያ ወቀሳ ተሰነዘረባቸው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ላኪዎችን የሸለመው መንግሥት የቡና ብራንድ ማዘጋጀቱን አስታውቋል

ለሁለት ቀናት በቢሾፍቱ ውይይት በማካሔድ፣ ችግኝ በመትከልና ለከፍተኛ ላኪዎች ዕውቅና በመስጠት መንግሥትና ቡና ነጋዴዎች ተመሠጋግነው ባሳረጉት ቆይታቸው የቡና ወቅታዊና አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡ የቡናው ዘርፍ የገጠሙት ፈተናዎች በመስኩ የተሠማሩትን ብቻም ሳይሆን፣ ኢትዮጵያንና በቡና የሚተዳደሩ 28 ሚሊዮን ሕዝቦችን የሚያሳስብ ደረጃ ላይ ስለመድረሱም አውስተዋል፡፡

ለውይይትና ለዕውቀና የተጠራው መድረክ ላይ በየጊዜው እየነቀሰ የመጣው የቡና የወጪ ንግድ ጉዳይ ትኩረት ስቧል፡፡ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር በኩል የውይይት መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ነበር፡፡ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጽሑፍ ከጠቀሷቸው አንኳር ጉዳዮች አንዱ የቡና የዓለም ገበያ ዋጋ መውደቅ ያስከተለው ጫና ነው፡፡

በመሆኑም ዘንድሮ አንዱ ኪሎ ወይም 2.2 ፓውንድ ቡና በ24 ብር አልያም በ80 የአሜሪካ ሳንቲም ተሸጧል፡፡ ባለፈው ዓመት ግን አንድ ኪሎ ቡና ይሸጥ የነበረው ከ90 ብር አልያም ከሦስት ዶላር ባላነሰ ዋጋ በመሆኑ ትልቅ የዋጋ ማሽቆልቆል ዘንድሮ አጋጥሟል፡፡ ምንም እንኳ በዋጋ ደረጃ የዘንድሮው የቡና አፈጻጸም ዝቅተኛ ይሁን እንጂ ለውጭ ገበያ በዋለው ምርት ላይ ትልቅ ውጤት እንደታየበት ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ እስከ 230 ሺሕ ቶን የሚጠጋ ቡና ለውጭ ገበያ መቅረቡን አውስተዋል፡፡

እንዲህ ያሉ እውነታዎችን በማውሳት የተሟሸው የቢሾፍቱ ስብሰባ፣ ቀስ በቀስ እየጠለቀ በአንዱ የቡና ንግድ መስመር የተሠማራው ሌላውን እየኮነነ፣ መንግሥትንም እየሸነቆጠ፣ መንግሥትም ላኪውን እያስጠነቀቀ ተገምዷል፡፡ በስብሰባው ወቅት አምራቾችን የወከሉ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየኖች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረዋል፡፡  በተለይ ላኪዎች ከአምራቾችና ከመንግሥት የሰላ ቅሬታ ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ ከአንዳንዶቹም ‹‹ከአምራቹ የተሻለ ገቢ ስለምታገኙ የዋጋ ጭማሪ አድርጉለት›› የሚል መማጠኛም ቀርቦላቸው ነበር፡፡

በላኪዎች ላይ ለተሰነዘረው ቅሬታ መነሻው አብዛኞቹ ወደ ውጭ የሚልኩትን ቡና በዓለም ዋጋ መቀነስ ምክንያት እየከሰሩ እንደሚሸጡ መግለጻቸውን ተከትሎ ሲሆን፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመርን ጨምሮ በርካቶች፤ ‹‹ላኪዎች ካልተጠቀሙ፣ አምራቹም ካልተጠመቀ፣ መንግሥትም አልተጠቀምኩም ካለ ታዲያ በቡና የተጠቀመው ማን ነው?›› የሚለውን በርካቶች በጥያቄዎቻቸው ውስጥ መላልሰው አሰምተዋል፡፡ ከላኪዎች ባሻገር ብዛታቸው 5,500 እንደሆነ የተገለጹ የቡና ገዥና ሻጮችን አገናኞችም ዋጋ በማዛባት ተኮንነዋል፡፡ ይሁንና መደበኛ ሥራቸው ዕቃ አስመጪ የሆኑ ቡና ላኪዎችን የተቀላቀሉም ጣት ተቀስሮባቸዋል፡፡

የአልፎዝ ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓሊ ሑሴን በበኩላቸው፣ ‹‹3,000 ዶላር የገዛነውን ቡና በ2,000 ዶላር የምንሸጥ አለን፡፡ ይህንን የምናደርግ ሰዎች መታየት አለብን፤›› ያሉት አቶ ዓሊ፣ የሚያጠፋ ሰው መጠየቅ ብቻም ሳይሆን፣ መመከር እንደሚገባው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ቡናን ከዋጋ በታች የመሸጡ አባዜ ትልቅ ችግር እየሆነ እንደመጣም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በኮንቴይነር አሽገው የላኩት ቡና እየተሰረቀ እንደተቸገሩ ያሳሰቡ ላኪዎችም፣ መንግሥት ችግሩን እልባት እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡

በላኪዎች ላይ ከተሰነረዘው ወቀሳ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ምርት ገበያም የድርሻውን ቀምሷል፡፡ ምርት ገበያው ጥራቱ የወረደ ነው ተብሎ ማረጋገጫ ተሰጥቶት ለአገር ውስጥ ገበያ ይቅረብ የተባለ ቡና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው እያለ አስቸግሮናል ያሉ ተደምጠዋል፡፡ አንዳንዶችም ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የደረጃ ቡና ገዝተው፣ በምርት ገበያው ግን ጥራቱን ያልጠበቀ እየተባለ ውድቅ እንደሚደረግባቸው በመግለጽ ብሶታቸውን አሰምተዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ የኤሌክትሮኒክ ግብይቱን በመኮነን፣ ‹‹ምርት ገበያው የኮምፒውተር ጫና ሆኗል›› በማለት በኦንላይን ግብይት ይፈጸማሉ ያሏቸውን የግብይት ችግሮች ነቅፈዋል፡፡ በሰላሳ ሰኮንድ ውስጥ የሚጠናቀቀው የኤሌክትሮኒክ ግብይት፣ በርካቶች በምን አግባብ እንደሚገበያዩ ለማወቅ ያላስቻለ፣ ሆነ ተብሎ የሚፈጸም የተዛባ የግብይት ሒደትን ለመግታት ያላስቻለ የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ተችቶችን አስተናግዷል፡፡

የግብርና ሚኒስቴርን መምራት ከጀመሩ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ከቡናው ዘርፍ ተዋንያን ጋር በመድረክ የተገናኙት፣ ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሑሴን ከአብዛኛው ተወያይ ያደመጡት የችግር መብዛትን ሳይሆን ያልተፈቱ ያደሩ ችግሮችን እንደሆነ ገልጸው እግረ መንገዳቸውን ወረፍ አድርገዋቸዋል፡፡ ‹‹በዘርፉ ከችግር ጋር መኖር ባህል ሆኗል፡፡ ስትናገሩ እንደ ነጋዴ እንደ አትራፊ ተናገሩ›› በማለት ነጋዴው መንግሥትን ሳይሆን ራሱን መስሎና ሆኖ እንዲከራከር አሳስበዋል፡፡

የቡና ሥርቆት መልኩን ቀይሮና ተራቆ መምጣቱን ተከትሎ በርካታ ላኪዎች ችግሩ እያሳሰባቸው መምጣቱን፣ ተጎጂዎችም ከራሳቸው ባሻገር ኢትዮጵያን ችግር ላይ ሊጥል የሚችል አዲስ አደጋ መደቀኑን በመግለጽ ማሳሰባቸውን በመንተራስ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ መንግሥት ለችግሩ ትኩረት በመስጠት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን የሚመራ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ማቋቋሙንም አቶ ዑመር አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና ቡናውን የሚሠርቁት አካላት ከነጋዴው የተወሰሩ እንደማይሆኑ ሲገልጹም፣ ‹‹የሠረቀውን ቡና አብሮ የሚያፋልግ መቼም ለማግኘት አያስችልም›› በማለት የመንግሥት የምርመራና የተሠረቀውን ቡና የማፈላለግ አቅጣጫ እንዴትና በምን አኳኋን እየተካሄደ እንደሚገኝ ለነጋዴዎቹ ጠቆም አድርገዋል፡፡

እንዲህ መሰል ምላሾችና ጥያቄዎችን ያስተናገደው የቡና ነጋዴዎችና የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መድረክ፣ ለቡና ዘርፍ ድጋፍ የሚሰጥ የቡና ፈንድ ማቋቋምን ጨምሮ ከመንግሥት ጋር በመደራደር መብቱን የሚያስከብር ጠንካራ ማኅበር እንዲሆን፣ ሚኒስትሩም በቡናው መስክ ወሳኝ የሚባሉ ዕቅዶች በሚገባ ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ፣ ፕሮጀክቶች እንዲቀረፁ ለዚህም ነጋዴዎቹ በራሳቸው መንገድ ተባብረው ወደ መንግሥት እንዲመጡ አሳስበዋል፡፡

እንዲህ ያሉትን ጨምሮ ‹‹በቢሾፍቱ መወያየቱ የተፈለገው ወጣ ብለን እንዲዋጣልን ነው›› በማለት ቡና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሑሴን አግራው የስብሰባውን ዓላማ ቢገልጹትም፣ ሚኒስትሩ ግን በዓመት ሁለት ጊዜ የቡና ነጋዴዎች እንደሚያገኙ በመጠቅስ ነጋዴዎቹ የልባቸውን እንዳልተናገሩ፣ የውስጣቸውን ችግር እንዳላወጡ ወረፍ አድርገዋቸዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን ያስተናገደው የሁለት ቀናቱ የቡና ነጋዴዎችና የመንግሥት አካላት የውይይት መድረክ የላኪዎች ማኅበር የቦርድ አባላትን ምርጫ በማካሄድ፣ የዛፍ ችግኞችን በመትከልና በዓመቱ ለተገኘው የ760 ሚሊዮን ዶላር የቡና ወጪ ንግድ ገቢ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለነበራቸው ላኪዎችና አምራቾች ዕውቅና በመስጠት ስብሰባውን አጠናቆ ተመልሷል፡፡ ከሁለት ቀናቱ ስብሰባ ማግሥት በአዲስ አበባ የተገናኙት ቡና ነጋዴዎችና የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን እንደ አዲስ ባዘጋጀው የቡና መለያና ብራንድ ላይ መወያየታቸውም ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች