Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከቀድሞ የብሔራዊ ደኅንነት ተከሳሾች አንዱ ወንጀል ሠርተው ሳይሆን ታስረው በተፈለገባቸው ወንጀል መከሰሳቸውን...

ከቀድሞ የብሔራዊ ደኅንነት ተከሳሾች አንዱ ወንጀል ሠርተው ሳይሆን ታስረው በተፈለገባቸው ወንጀል መከሰሳቸውን ተናገሩ

ቀን:

ዓቃቤ ሕግ በስልክ የጠራቸው ምስክሮች ሳይቀርቡ ቀሩ

‹‹ምስክሮች እየቀረቡ ያሉት በዓቃቤ ሕግ ፈቃድ ነው ማለት ስህተት ነው››

ፍርድ ቤት

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው የክስ መዝገብ ተካተው የተመሠረተባቸውን ክስ ከማረሚያ ቤት እየቀረቡ በመከታተል ላይ የሚገኙ ተከሳሾች ክስ የተመሠረተባቸው ወንጀል ሠርተው ሳይሆን፣ ታስረው በተፈለገባቸው ወንጀል መሆኑን አንድ ተከሳሽ ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

ተከሳሹ ለፍርድ ቤቱ የተናገሩት ዓቃቤ ሕግ ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ለስድስት ምስክሮች ስልክ በመደወል በዕለቱ ቀርበው እንደሚመሰክሩ የገለጸ ቢሆንም፣ አለመቅረባቸውን ለፍርድ ቤቱ በተናገረበት ጊዜ ነው፡፡

ተከሳሹ ፍርድ ቤቱን አስፈቅደው በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፣ ምስክርነት ከተጀመረ ጀምሮ ያለው ውጣ ውረድ ብዙ ነው፡፡ ከታሰሩ አንድ ዓመት እንደሆናቸውና የሠሩት ወንጀል ተጣርቶ መታሰር ሲገባቸው፣ ወንጀል የተፈለገባቸው ታስረው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ያሰራቸውና የመረመራቸው ዓቃቤ ሕግ ሆኖ ሳለ፣ የማያውቃቸው ፖሊስ ምስክሮችን አፈላልጎ እንዲያቀርብ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምስክሮቹ ተጠቂዎች ናቸው ስለተባለ መጥሪያ እንደማያስፈልጋቸውና የተጠቀሰው ሰው ያለ ምንም ጥሪ ቀርቦ እንደሚመሰክር ጠቁመው፣ አብዛኞቹ ምስክሮች አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታና በአማራ ክልል በተፈጠረው ችግር የሸሹ በመሆናቸው ሊቀርቡና ሊመሰክሩ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዕረፍት ጊዜውን ጭምር መስዋዕት አድርጎ ጉዳያቸውን በማየቱ ክብር እንዳላቸውና እንደሚያመሠግኑ ገልጸው፣ ዓቃቤ ሕግ ስለምስክሮቹ እያቀረበ ያለው ምክንያት አሳማኝ ያልሆነና ከእውነት ያፈነገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ እያቀረባቸው ያሉት አንዳንዶቹ ምስክሮች ተከሳሾቹን ስለማያውቋቸው በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ወዲያና ወዲህ እየተንቀሳቀሱ፣ እነሱ ወደ ፍርድ ቤቱ ሲገቡ እንዲለዩዋቸው እየተደረገ መሆኑንም ተከሳሹ ተናግረዋል፡፡

ሌሎቹም ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካይነት ባቀረቡት ክርክር፣ ዓቃቤ ሕግ 131 ምስክሮች እንደሚያሰማ በክሱ መግለጹን ጠቁመዋል፡፡ የክሱ መነሻ ያደረገውም ምስክሮቹን ነው ብለዋል፡፡ በፍርድ ቤትም ገደብ ስላልተደረገበት የፈለገውን ምስክር በፈለገው ተጠርጣሪ ላይ እያቀረበ ነው ብለው፣ በተሰጠው ጊዜ ምስክሮቹንም ማቅረብ ካልቻለ አካሄዱ ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑም ገልጸዋል፡፡

የፍርድ ቤቱን ጊዜ ከመውሰዱም በተጨማሪ ተከሳሾችም የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታቸውንም እየተጋፉ በመሆኑ፣ ዓቃቤ ሕግ ‹‹ምስክሮች ከመጡ ይምጡ ካልመጡም ይቀጠራል›› በማለት እየሠራ ያለው አካሄድ በፍርድ ቤቱ መዝገብ አመራር ላይ ችግር ይፈጥራል የሚል ሥጋት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ ብዙ ምስክሮች ያለው መዝገብ ቢሆንም እስካሁን መጥሪያ አለመውጣቱ ዓቃቤ ሕግ ሥራውን በአግባቡ አለማከናወኑን የሚያሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ችሎት ለፖሊስ ትዕዛዝ መስጠቱን በማስታወስ፣ ዓቃቤ ሕግ ፖሊስን የማዘዝ ሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 943 ተሰጥቶት እያለ ለምን ተከታትሎ እንደማያስፈጽም፣ ፍርድ ቤቱ ሊጠይቀው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ለማሰማት ዝግጁ ነው? ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን መቅረብ ካረጋገጠ በኋላ (በሌሉበት ክሳቸው እየታየ ከሚገኘው አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ አቶ አጽብሀ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሽሻይ ልዑል በስተቀር) ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ስለማቅረቡ ጠይቋል፡፡ በዕለቱ የቀረቡት ዓቃቤ ሕግ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፣ በስልክ ደውለው ስድስት ምስክሮች እንደሚመጡ ነግረዋቸው ነበር፡፡ ግን አልመጡም ብለዋል፡፡ ይኼንንም የሚያደርጉት በግል ጥረታቸው እንጂ ፖሊስ እስከ ዕለቱ ድረስ ምላሽ እንዳልሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

እስከ ነሐሴ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ያሰሟቸው ዘጠኝ ምስክሮችም በስልክ እየነገሯቸው ቀርበው ስለመሰከሩ፣ በዕለቱም እንደሚመጡ የነገሯቸው ምስክሮች እንደሚመጡ እምነት ቢኖራቸውም ሳይቀርቡ መቅረታቸውን ለፍርድ ቤቱ ካስረዱ በኋላ ነው፣ ከላይ የተገለጸውን አስተያየት ተከሳሹና ጠበቆቹ ያቀረቡት፡፡

በድጋሚ ለምስክሮች መጥሪያ አለመውጣቱን ጠቁመው ቀደም ብሎ በተሰጠው ትዕዛዝ ፖሊስ ምን ላይ እንደደረሰ ምላሽ እንዳልሰጣቸው ዓቃቤ ሕጉ ተናግረው፣ እስከ ነሐሴ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ቀጠሮዎች ግን በግል ጥረታቸው በሚያቀርቧቸው ምስክሮች እያሰሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጠሮ ቀናት ምስክር ያልቀረበበትና ያልተሰማበት ቀን እንደሌለ ጠቁመው በዕለቱ ምስክር ያልቀረበበት የመጀመሪያ ቀን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአዋጁ መሠረት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ከጠየቁት ጋር 160 ምስክሮች እንዳሉ፣ በመዝገቡ ምስክሮችን በማቅረብና ባለማቅረብ የተለየ ጥቅም የሚያገኝ አካል እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

ምስክሮቻቸው ብዙዎቹ ክልል መሆናቸውን ገልጸው፣ በቅርብ የሚገኙትን በስልክ እየጠሩ እንደሚያስመሰክሩና ይኼም ጥረታቸውን የሚያሳይ እንጂ በቸልተኝነት የሚታይ አለመሆኑን ዓቃቤ ሕጉ ተናግረዋል፡፡

ተከሳሾች ‹‹ምስክሮች በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ እንዲለዩን ይደረጋል›› ማለታቸው ‹‹አሉባልታ ነው›› ያሉት ዓቃቤ ሕጉ፣ ‹‹እኔ እንደ ባለሙያ ይኼንን ያህል የወረደ ሥራ አልሠራም፡፡ እስካሁን የፈጸምነውም ነገር የለም፡፡ አሉባልታ ነው፡፡ ምስክር ስላልመጣ የተለየ የምንይዘው ጥቅም የለም፤›› ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመሀል አብዛኞቹ ምስክሮቻቸው በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ በመሆናቸው፣ ፌዴራል ፖሊስ እንዲያቀርብ በአዋጅ በተሰጣቸው ሥልጣን ማስገደድና ማዘዝ እንደሚችሉ ጠቁሞ፣ በግላቸው ብቻ ጥረት ማድረጉም አደጋ እንዳለውም አሳስቧል፡፡

ዓቃቤ ሕጉም በመቀጠል በስልክ እንዲቀርቡ የሚያደርጉት በማግባት መሆኑንና ፍርድ ቤቱም እንዳለው አደጋ እንዳለው እንደሚገነዘቡ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ የሰጠውን ትዕዛዝ ምላሽ እየጠበቁ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመጨረሻ እስከ ዕለቱ ድረስ ይቀርቡ የነበሩት ምስክሮች፣ በዓቃቤ ሕግ በጎ ፈቃድ እንደሆነ መታሰቡ ስህተት መሆኑን አስረድቷል፡፡ በዓቃቤ ሕጉ እስካሁን ዘጠኝ ምስክሮች ሊሰሙ የቻሉት ፍርድ ቤቱ በሰጠው ግልጽ ትዕዛዝ እንጂ፣ በዓቃቤ ሕግ ፈቃድ አለመሆኑንም አስምሮበታል፡፡

በዕለቱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ከሰዓት በኋላ የሚቀርቡ ከሆነ በማለት መዝገቡን ቢያቆየውም፣ በዓቃቤ ሕግ በኩል ከሰዓትም የተለየ ነገር ባለመኖሩ፣ ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ምስክሮች የሚቀርቡ ከሆነ አንድ ላይ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ በማስታወቅ ችሎቱ አብቅቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...