Thursday, December 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከሞራልና ከሥነ ምግባር እሴቶች ማፈንገጥ አገርን ዋጋ ያስከፍላል!

የጤናማ ማኅበረሰብ መገለጫ ከሆኑት ወሳኝ ጉዳዮች መካከል የሞራልና የሥነ ምግባር እሴቶች ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ የሞራልና የሥነ ምግባር ደረጃው ከፍ ያለ ማኅበረሰብ ለሰብዓዊ ፍጡራን ክብር፣ ርህራሔ፣ ድጋፍ፣ ታማኝነትና ፍቅር ያሳያል፡፡ ለፍትሕና ለርትዕ ይጨነቃል፡፡ ሰዎችን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቆዳ ቀለም፣ በቋንቋ፣ በባህልና በመሳሰሉት አይለያይም፡፡ ደግና ክፉ ነገሮችን ስለሚለይ ለሚፈጽማቸው ድርጊቶች ይጠነቀቃል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የቀድሞዎቹ ትውልዶች ከፍተኛ የሆኑ የሞራልና የሥነ ምግባር እሴቶች እንደነበሩዋቸው ተደጋግሞ ተወስቷል፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ግን እነዚህ አኩሪና ምሥጉን እሴቶች በመሸርሸራቸው ምክንያት በቁጭት የሚብከነከኑ አሉ፡፡ በተለይ ለአገራቸው ያላቸውን ነገር ሁሉ መስዋዕት ለማድረግ ወደ ኋላ የማይሉ ዜጎች ይህ ጉዳይ ይከነክናቸዋል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፎች የሚስተዋሉ ዝንፈቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ አሉታዊ አሻራዎችን እያተሙ ነው፡፡ የዘመኑን ትውልድ መቅረፅ የሚገባቸው የሃይማኖት ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ ማኅበረሰቡና መንግሥት ጭምር መስነፋቸው ችግሩን እያከበደው ነው፡፡ የአገር የወደፊት ዕጣ ፈንታን የሚፈታተኑ ነገሮች እየበዙ ስለሆኑ መነጋገር ይገባል፡፡

ከሕዝባችን የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር ከሚገናኙ ነገሮች አንዱ የንግድና የግብይት ሥርዓቱ ነው፡፡ የንግድና  የግብይት ሥርዓት ከመዘበራረቁ የተነሳ ባለቤት አልባ ይመስላል፡፡ መንግሥት፣ ሸማቹና የንግዱ ማኅበረሰብ መስተጋብር ውጤት መሆን የሚገባው የንግድና የግብይት ሥርዓት በስፋት የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት ይታይበታል፡፡ በንግድ ሥራ ከተሰማሩት ውስጥ ቀላል ቁጥር የሌላቸው የሚያጋብሱት ትርፍ አስተዛዛቢ ነው፡፡ የዋጋ መነሻና የትርፍ ህዳግ ባለመኖሩ በበርካታ እጥፍ ያተርፋሉ፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ጥራት የሌላቸው ምርቶችን ከውጭ ያራግፋሉ፡፡ በሚዛን ያጭበረብራሉ፡፡ የምግብ ምርቶች ውስጥ መርዛማ የሆኑ ባዕድ ነገሮችን ጭምር እየቀላቀሉ ይሸጣሉ፡፡ ከመድኃኒት ጀምሮ እስከ መዋቢያ ምርቶች ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ያቀርባሉ፡፡ ምርቶችን በመደበቅ ሰው ሠራሽ እጥረት ይፈጥራሉ፡፡ ከእንዲህ ዓይነቶቹ አሳዛኝ ድርጊቶች በተጨማሪ ግብር ያጭበረብራሉ፣ ይሰውራሉ፡፡ በገዛ ወገናቸው ላይ ይህንን ዓይነቱን አሳፋሪ ድርጊት እየፈጸሙ፣ ለደሃ አገር የሚያሳቅቅ የቅንጦት ሕይወት ይመራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ዝቅጠቶች በሕግ ማዕቀፎች ማስተካከል ካልተቻለ መጪው ጊዜ አሳሳቢ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ይታወቁባቸው ከነበሩ አኩሪ እሴቶች መካከል መረዳዳት ይጠቀሳል፡፡ ዕርዳታን ለታይታ ከመጠቀም ባሻገር ተቋማዊ በማድረግ፣ ጎዳና ላይ የወደቁ ሕፃናትና አዛውንቶችን ጭምር ማንሳት ትልቅ ሥራ መሆን ይገባዋል፡፡ ነገር ግን የገዛ ወገንን መፀየፍና የለፋበትን ጭምር መንጠቅ የዘመኑ የአቋራጭ ባለፀጎች መለያ ነው፡፡ በንግድ ሥራም ሆነ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ሰዎች የጋራ ዕድገት እንዴት እንደሚገኝ ሳይሆን፣ አንዱ ሌላውን ጥሎ ለመበልፀግ የሚችሉበትን ዘዴ ይሸርባሉ፡፡ ሁሉም እንደ ሥራውና ልፋቱ የሚያገኝበት የንግድና የኢንቨስትመንት መርህ ተዛብቶ፣ የአየር በአየር ንግድ ላይ መራኮት ተለምዷል፡፡ እንኳንስ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት የወደቁትን ማንሳት ይቅርና የቆሙትን ለመጣል ርብርቡ ከፍተኛ ነው፡፡ ትውልዱን የመቅረፅ ኃላፊነት ለመውሰድ ሳይሆን፣ ብድርና መሬት በአቋራጭ ለመቀራመት የሚደረገው የፍጥነት ውድድር ከኦሊምፒክ ሯጮች ይበልጣል፡፡ ለማኅበራዊ ፍትሕ ሳይሆን ለግላዊና ለቡድናዊ ጥቅም መረባረብ ተመራጭ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ትውልዱስ ከዚህ ምን ይማራል?  አገርስ ምን ትጠቀማለች? የሚሉ ጥያቄዎች ሞኝ ያስብላሉ፡፡ ከዚህ በላይ መዝቀጥ የት ይኖራል?

ሥርዓተ አልበኝነት ተፈጥሮ ያሻቸውን ማድረግ የሚፈልጉ ኃይሎች ደግሞ በየቦታው ግጭት ይቀሰቅሳሉ፡፡ የእነሱ ዓላማ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ ሕገወጥነት እንዲሰፍን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ወጣቱን በፕሮፓጋንዳ እያወናበዱ በገዛ ወገኑ ላይ ያዘምቱታል፡፡ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ወዘተ. በሚባሉት ልዩነቶች ይፈጥራሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን የዓላማቸው ማሳኪያ መድረኮች እያደረጓቸው ነው፡፡ የሞራልና የሥነ ምግባር እሴቶችን በመደፍጠጥ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እናንተ›› በማለት ንፁኃንን ይገድላሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ያፈናቅላሉ፣ ንብረት ያወድማሉ፡፡ የማኅበረሰቡን የዘመናት መስተጋብር ወደ ጎን በማለት ሥርዓተ አልበኝነት ያስፋፋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አገር መሆኗ እየታወቀ በጠባብ ብሔርተኝነት ቀውስ የሚፈጥሩ ኃይሎች፣ ትውልዱን በመበረዝ አገራዊ አንድነትን ያላላሉ፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ለሁሉም ወገኖች እኩል ክፍት ሆኖ የመወዳደሪያ ሜዳው እንዳይዘጋጅ መሰናክል ይሆናሉ፡፡ የዴሞክራሲያዊነት ባህሪ ስለሌላቸው ሁሌም የሚዘጋጁት ለጥፋት ነው፡፡ ትውልዱን ኮትኩቶ ለማሳደግ የሚደረጉ አነስተኛ ጥረቶችን ጭምር በማክሸፍ፣ ለአገር የማይበጁ ድርጊቶችን ያስፋፋሉ፡፡ ይህ የዘመናችን አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

የሞራልና የሥነ ምግባር እሴቶች ጉዳይ ሲነሳ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት አገርን ያጠፋል፣ ሕዝብን ያሽመደምዳል፡፡ የፖለቲካው ልሂቃን ከሴረኝነት ወጥተው በሞራልና በሥነ ምግባር ካልተመሩ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መነጋገር አይቻልም፡፡ የኢኮኖሚ ልሂቃን የአገሪቱን የንግድና የግብይት ሥርዓት ፈር ማስያዝ ካልቻሉ ስለዕድገት መነጋገር ከባድ ይሆናል፡፡ ማኅበረሰቡ ውስጥ የበቀሉ አረሞች በሕግ የበላይነት መስመር ሊይዙ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የጋራ እሴቶች ሲናዱ የሚጎዳው አዲሱ ትውልድ ነው፡፡ ሌብነት፣ አጭበርባሪነት፣ ክፋት፣ ቂም በቀልና ጥላቻ በተሞላባቸው ሰዎች ምክንያት አገር ህልውናዋ ለአደጋ ሊዳረግ አይገባም፡፡ ለአዲሱ ትውልድ ኃላፊነት ያለባቸው ወገኖች በሙሉ በትኩረት ማድረግ ያለባቸው፣ ለሞራልና ለሥነ ምግባር እሴቶች መጥፋት መንስዔ የሆኑ ችግሮችን በመርመር መፍትሔ ማፍለቅ ነው፡፡ አሁን ባለው አያያዝ መቀጠል አይቻልም፡፡ ብዕር መያዝ የሚገባው ጠመንጃ የሚጎመጅ ከሆነ አገር አደጋ ውስጥ ናት፡፡ ሕዝብን በቅንነት ማገልገል ያለበት በቁሙም ሆነ ተኝቶ ዘረፋ የሚያስብ ከሆነ ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጠንቅ ነው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ከሞራልና ከሥነ ምግባር እሴቶች ማፈንገጥ አገርን ዋጋ ያስከፍላል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...