Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማዕድን ዘርፍ በታሪኩ ዝቅተኛ ገቢ አስመዘገበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በ2011 በጀት ዓመት በኩባንያዎችና በባህላዊ አምራቾች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የተለያዩ ማዕድናት 48.938 ሚሊዮን ዶላር እንደተገኘ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ይህም በመስኩ ባለፉት ዓመታት ከተመዘገበው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ዝቅተኛው እንደሆነ ታውቋል፡፡

ከማዕድናት ወጪ ንግድ በዓመት ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይገኝ የነበረ ሲሆን፣ ወርቅ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ከማዕድናት ኤክስፖርት ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ እያሽቆለቆለ መጥቶ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 766 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም፣ ማሳካት የተቻለው ግን 48.9 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ለመጣው የማዕድን ወጪ ንግድ በዋነኝነት የሚጠቀሱት ምክንያቶች፣ የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋትና የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ ናቸው፡፡

የሚድሮክ ጎልድ ለገንደምቢ ወርቅ ማውጫና ንብረትነቱ የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን የሆነው የቀንጢቻ የታንታለም ማዕድን ማውጫ ሥራ ማቆም፣ ለማዕድን ዘርፍ የወጪ ንግድ መዳከም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገለጻል፡፡

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን የሕገወጥ የማዕድናት ዝውውር ምክንያት ያስረዳሉ፡፡ በባህላዊ አምራቾች የሚመረቱ ማዕድናት በዋነኝነት ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ከመቅረብ ይልቅ፣ ድንበር ተሻግረው በጎረቤት አገሮች ገበያዎች ላይ መቅረቡ ለወጪ ንግድ ገቢ መዳከምን እንደ ምክንያት ይጠቅሳሉ፡፡

በአገሪቱ ከተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በተለያዩ ክልሎች የተከሰቱ ግጭቶች፣ በማዕድን ዘርፍ ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደሩ ኃላፊዎቹ ያምናሉ፡፡

እየተዳከመ የመጣውን የማዕድን ዘርፍ ለማንሰራራት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው ዘርፉን የሚታደግ የቴክኒክ ኮሚቴ መዋቅሩ ነው፡፡

በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን ለይቶ መፍትሔ መስጠትና ምርታማነትንና የወጪ ማዕድናት ንግድ እንዲያንሰራራ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለበት ብሔራዊ ኮሚቴ ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይና ከማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን የተውጣጡ 12 ባለሙያዎች ተመድበውለታል፡፡

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አገሪቱ ከተያያዘችው የለውጥ እንቅስቃሴ፣ የማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንዳገኘ አስታውቋል፡፡ ‹‹ዋነኛው ምክንያት የአገራችን የዕድገት ግስጋሴ ከባድ ፈተና የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመፍታት የአንበሳውን ድርሻ የመውሰድ አቅም ያለው መሆኑ ግንዛቤ በመፈጠሩ ነው፤›› ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡

ዘርፉን ወጥ በሆነ መንገድ ለመምራትና ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የማዕድን ፖሊሲ፣ የነዳጅ ሥራዎች ፖሊሲ የማዘጋጀት፣ እንዲሁም የተለያዩ አዋጆችንና ደንቦችን የማሻሻል ሥራዎች እንዳከናወነ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ ተቋማዊ አሠራርን የሚያሻሽልና የማዕድን ፈቃድ አስተዳደር ዘመናዊና ግልጽ የሚያደርግ የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አምስት የማዕድን ምርትና 19 የምርመራ ፈቃዶች መስጠቱን ገልጾ፣ የተመዘገበው የኢንቨስትመንት ካፒታል መጠን 4.95 ቢሊዮን ብር እንደሆነ አመልክቷል፡፡ የወርቅ ማዕድን፣ የእብነ በረድ፣ ብረት፣ የከበሩ ጌጣ ጌጦችና ሌሎች ማዕድናት ፍለጋና ልማት ሥራ ላይ የዋለው ኢንቨስትመንት ካፒታል 1.124 ቢሊዮን ብር፣ በነባር 11 የነዳጅ ፍለጋና ልማት ሥራ ስምምነቶች የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ለማካሄድ ከ1.96 ቢሊዮን ብር፣ በአጠቃላይ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት እንደተደረገ ተገልጿል፡፡

እስካሁን በኦጋዴን የተገኘውን 6.3 ትሪሊዮን ኪዮቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለማልማት የማስተላለፊያ ቧንቧ ዝርጋታ ስምምነት መፈረምና ወደ ሥራ መግባት፣ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድገው ገልጿል፡፡

‹‹በ2011 ዓ.ም. ባጋጠሙት የፀጥታ ችግሮች አልሚ ኩባንያዎች ከፍተኛ ፈተና የሆነባቸው ከባለድርሻ አካላት ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎቶችን ሳያገኙ፣ ከአንድ ዓመት በላይ የተጓተቱ በርካታ ጉዳዮች በመኖራቸው ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድና መስፋፋት ዋነኛ ችግሮች ነበሩ፤›› ብሏል፡፡

በወለጋ በማዕድን ሥራ የተሰማራ ሰንራይዝ በተባለ ኩባንያ ሠራተኞች ላይ ግድያ መፈጸሙ፣ ቱሉኮፒ በተሰኘ አካባቢ በወርቅ ምርት ላይ የተሰማራ ከፊ ሚኒራልስ በተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ላይ የዘረፋ ወንጀል መፈጸሙ የሚታወስ ነው፡፡ የፀጥታ ጉዳይ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነት ውጪ የሆነና ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚፈልግ ውስብስብ ችግር እንደሆነ፣ አንድ የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች