Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዋስትና የተፈቀደላቸው ብርጋዴር ጄኔራል በየ48 ሰዓታት ለፖሊስ ሪፖርት እንዲያደርጉ ግዴታ ተጣለባቸው

ዋስትና የተፈቀደላቸው ብርጋዴር ጄኔራል በየ48 ሰዓታት ለፖሊስ ሪፖርት እንዲያደርጉ ግዴታ ተጣለባቸው

ቀን:

በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የሆሚቾ አሙኒሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ሐድጉ ገብረ ጊዮርጊስ በ50 ሺሕ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ብይን ተሰጥቶ፣ በየ48 ሰዓታት  ለፌዴራል ፖሊስ እየቀረቡ ሪፖርት እንዲያደርጉ ግዴታ ተጣለባቸው፡፡

በብርጋዴር ጄኔራል ሐድጉ ላይ ዋስትና ፈቅዶ ግዴታ የጣለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው፡፡ ችሎቱ በብይኑ እንደገለጸው፣ ተጠርጣሪው በ50 ሺሕ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱና ከአገር እንዳይወጡ ለኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ እንዲጻፍ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በአዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀጽ 6 (ሀ እና ሐ) መሠረት ብርጋዴር ጄኔራል ሐድጉ ከሚኖሩበት አዲስ አበባ ከተማ ክልል እንዳይወጡ፣ በየ48 ሰዓታት በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እየቀረቡ ሪፖርት እንዲያደርጉ ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ሐድጉ ዋስትና የተፈቀደላቸው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተሻሻለ ክሱ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ)፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 (1ሀ እና ለ) እና (2) ድንጋጌ በመተላለፍ  30,000 ‹ኢራ ቦክስ አሴምብልና ሎወር ፕሌት ካፕ› ግዥ ጋር በተያያዘ፣ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከ1.9 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው በተመሠረተባቸው ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ፣ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ ሊያስቀጣቸው የሚችለው እስራት ከአራት ዓመታት በታች በመሆኑ ነው፡፡ ከላይ በተጠቀሰው የሕግ ድንጋጌ ክስ ቢቀርብባቸውም፣ ክሱን በማየት ላይ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው ብይን፣ ተከሳሹ ሊጠቀሰባቸው የሚችለው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 113(2) ድንገጌ መሠረት አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1ሀ እና ለ) በመሆኑና ይኼ ደግሞ በፀረ ሙስና ልዩ ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 282/2007 ድንጋጌ መሠረት፣ ዋስትና የሚከለክለው የቅጣት መነሻቸው ከአራት ዓመት በላይ በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በዓቃቤ ሕግና በተከሳሹ መካከል የነበረውን ክርክር ሲሰማ የነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ከላይ እንደተገለጸው በሰጠው ብይን የተከሰሱበትን የሕግ አንቀጽ የቀየረ ቢሆንም፣ ተደራራቢ ክስ ስላለባቸው ዋስትና ነፍጓቸው ነበር፡፡ ተከሳሹ በጠበቃቸው ሕይወት ሊላይ አማካይነት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቅርበው ተከራክረዋል፡፡ ክርክሩን የሰማው ይግባኝ ሰሚው ችሎት ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ሰጥቶ ነበር፡፡      

በሰጠው ፍርድም የሥር ፍርድ ቤት አዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ (4) ጠቅሶ ተከሳሹን ዋስትና ቢከለክልም፣ የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 3(1)  የሕጉ አገላለጽ በግልጽ እንደሚታየው፣ ‹‹ከአራት ዓመት በላይ›› የሚለው አገላለጽ ‹‹አራት ዓመትና ከዚያ በላይ›› መሆኑ የሚያሻማ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡

ተደራራቢ ወንጀሎት ሲኖሩ ተደምረው ከአሥር ዓመታት በላይ የሚያስቀጡ በሆነ ጊዜ ዋስትና የሚከለክል ቢሆን ኖሮ፣ ‹‹ከአራት ዓመት በላይ›› የሚለው አገላለጽ እንደማያስፈልግም ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ገልጿል፡፡ በመሆኑም የአዋጁ ዓላማ ከአራት ዓመት በታች ያሉትን ቅጣቶች እንደሚያካትት በማብራራት ይግባኝ ባዩ ብርጋዴር ጄኔራል ሐድጉ በ100,000 ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ውሳኔ በመስጠት፣ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ብይን ውድቅ አድርጎት ነበር፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በ100,000 ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ውሳኔ የሰጣቸው ተከሳሹ ከእስር ሳይፈቱ ከሦስት ቀናት ቆይታ በኋላ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ነሐሴ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሥረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ይዟቸው ቀርቦ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸዋል፡፡

ተጠርጣሪው ብርጋዴር ጄኔራል ሐድጉ የሜቴክ ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው በሚሠሩበት ወቅት፣ ከኮርፖሬሽኑ የግዥ መመርያ ውጪ ጄሆአኪን ቴክኖን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከሚባል ድርጅት ግዥ እንዲፈጸም በማድረግ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከ1.9 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ እንደጠረጠራቸው ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በመሆኑም ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቃ ባቀረቡት ክርክር ፖሊስ ለጊዜ መጠየቂያ ያቀረበው ጉዳይ በተመሳሳይ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 225176 ቀርቦና ክርክር ተደርጎበት፣ በጥር ወር 2011 ዓ.ም. የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ መዘጋቱን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም አስቀድሞ በተመሳሳይ ችሎት ቀርቦ የታየና የተዘጋ ጉዳይ በመሆኑ፣ በድጋሚ የማይቀርብና የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑን አክለዋል፡፡

በተመሳሳይ ጉዳይ የሥር ፍርድ ቤት ዋስትና ከልክሏቸው በይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብለው ዋስትና የተፈቀደላቸው ቢሆንም፣ ማረሚያ ቤቱ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝና ያለ በቂ ምክንያት ሁለት ቀናት አቆይቶ ተጠርጣሪውን ከእስር ሲፈታቸው፣ ፖሊስ ከማረሚያ ቤቱ መውጫ በር ላይ ጠብቆ አስሮ እንዳቀረባቸውም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ምርመራ ተጠናቋል ተብሎና ከጥር ወር 2011 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ማጠናቀቅ እየተቻለ አቆይቶ ማቅረቡ ሕግን መሠረት ያላደረገ፣ እንዲሁም የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔን ላለመፈጸም የተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ክርክር ተደርጎበት ተዘግቷል የተባለውን ጉዳይ መዝገብ 225176 አስቀርቦ በማረጋገጡ የፖሊስን ማመልከቻ ውድቅ በማድረግ ከላይ በተጠቀሰው አግባብ በ50,000 ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ፣ ከአገር እንዳይወጡ ለኢምግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ እንዲጻፍ፣ ተጠርጣሪ ከአዲስ አበባ ከተማ እንዳይወጡና በየ48 ሰዓታት  ለፌዴራል ፖሊስ ሪፖርት እንዲያደርጉ ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...