የ2011 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የ12ኛ ክፍል የፈተና ውጤት ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ ተደረገ፡፡ የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በሰጠው መግለጫ መሠረት፣ ለፈተና ከተቀመጡ 319,264 ተፈታኞች ውስጥ 59 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ ከፍተኛው ውጤት ደግሞ 645 መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡
በኤጀንሲው ገለጻ መሠረት ከ50 በላይ ውጤት ያመጡት ተፈታኞች 48.59 በመቶ ናቸው፡፡ ተፈታኞች ውጤታቸውን በኤጀንሲው ድረ ገጽና በ8181 የአጭር ጽሑፍ መልዕክት የመፈተኛ ቁጥራቸውን በመጠቀም ማወቅ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ኤጀንሲው የፈተና ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራውን ከዝግጅት ጀምሮ እስከ ውጤት ይፋ ማድረግ ድረስ ለማስቀጠል በመሥራት ላይ መሆኑን አስታውቆ፣ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናው በተሰጠበት ወቅት ከቀረቡት ሪፖርቶችና ተያያዥ መረጃዎች የተረጋገጠባቸውን 68 ተፈታኞች ውጤት ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ መደረጉን አስታውቋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በሚገኙ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች 846 ተፈታኞች በተወሰኑ የትምህርት ዓይነቶች ያገኟቸው ውጤቶች ማጣራት የሚጠይቁ መሆናቸውን ኤጀንሲው ገልጿል፡፡
ኤጀንሲው በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የእነዚህ ተፈታኞች ውጤት፣ በተለዩት የትምህርት ዓይነቶች ብቻ ተይዞ ማጣራት እንዲደረግባቸው መወሰኑን አስረድቷል፡፡ ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ግብረ ኃይል የማጣራት ሥራውን ያከናውናል ብሏል፡፡
ኤጀንሲው ባለድርሻ አካላትና መላው ሕዝብ ባደረጉት ርብርብ እጅግ በተረጋጋ የፈተና ከባቢ ፕሮግራሙን በማሳካቱ፣ የዓመቱ የፈተና አስተዳደር ሥራው መሻሻል ማሳየቱን አስታውቋል፡፡ በፈተና አስተዳደሩ ሒደት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ላላቸው ለፌዴራልና ለክልል ተቋማት፣ ለፈተና አስፈጻሚዎች፣ ለመላው ተፈታኞች፣ ለወላጆችና በሒደቱ ለተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ምሥጋናውን አቅርቧል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ የ12ኛ ክፍል ፈተና ሰኔ 6፣ 7፣ 10 እና 11 ቀን 2011 ዓ.ም. መሰጠቱ ይታወሳል፡፡