Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ70 ቢሊዮን ብር ዕዳ ከተያዙ የስኳር ፕሮጀክቶች ስድስቱ በዚህ ዓመት ይሸጣሉ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ የተሰናዳው ብሔራዊ ሰነድ ለሕዝብ ውይይት ይቀርባል ተብሏል

መንግሥት እያካሄዳቸው ከሚገኙ የለውጥ ፕሮግራሞች መካከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወሩ ሒደት አንዱ በመሆኑ፣ 70 ቢሊዮን ብር ዕዳ ካለባቸው 13 የመንግሥት የስኳር ፕሮጀክቶች ስድስቱ በተያዘው በጀት ዓመት ለጨረታ እንደሚቀርቡ ተገለጸ፡፡ የተቀሩት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ገና አልተጠናቀቀም ተብሏል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አማካይነት በየጊዜው የሚሰናዳው የ‹‹የአዲስ ወግ አዲስ ጉዳይ›› ውይይት መድረክ፣ ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስብሰባ አዳራሽ ‹‹የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ሪፎርም መነሻና አቅጣጫ›› በሚል ርዕስ ከግሉና ከመንግሥት አካላት ተወካዮች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱም መንግሥት እየወሰዳቸው የሚገኙ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተወስተው፣ የዚህ ማሻሻያ አካል መሆኑ በተገለጸው በፕራይቬታይዜሽን ማዕቀፍ ውስጥ ትኩረት ከተደረገባቸው የልማት ድርጅቶች ውስጥ የስኳር ኢንዱስትሪው አንዱ እንደሆነ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

የስኳር ፕሮጀክቶች ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር ዕዳ እንዳለባቸው ያስታሰወሱት ከፍተኛ አማካሪው፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባለባቸው የዕዳ ጫና፣ የአቅምና የብቃት ውስንነት፣ እንዲሁም የአስተዳደርና መሰል ችግሮችና ጫናዎች ሳቢያ እንደሚፈለገው ውጤታማ መሆን ባለመቻላቸው ለግሉ ዘርፍ ክፍት ቢደረጉ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኙ በመታመኑ ወደ ግል የማዘዋወር ሥራ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡

አብዛኞቹ የስኳር ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት ሥራ ከመጀመር አልፈው የአገር ውስጥ ፍጆታን ሸፍነው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡ ይታሰብ ነበር፡፡ ይሁንና አዳዲሶቹ ብቻም ሳይሆኑ ነባሮቹም ቢሆኑ የአቅማቸውን ግማሽ እንኳ ማምረት እንዳልቻሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በ42 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተፈቀደ ካፒታል በ2003 ዓ.ም. የተመሠረተው የስኳር ኮርፖሬሽን፣ በ2003 ዓ.ም. እንደሚኖር ከሚጠበቀው የ2.2 ሚሊዮን ቶን የስኳር ምርት በ2007 ዓ.ም. ወደ 3.7 ሚሊዮን ቶን፣ እንዲሁም በ2013 ዓ.ም. ወደ አምስት ሚሊዮን ቶን የሚያሻቅብ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ከ2007 ዓ.ም. ወዲህም 1.3 ሚሊዮን ቶን ስኳር ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ሲገልጽ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በስኳር ምርት ብቻም ሳይወሰን በትንሹ ከ180 ሺሕ ሜትር ኪዩብ በላይ ኢታኖል፣ ከ138 ሺሕ ሜትሪክ ኪዩብ በላይ የኬሮሲን ምርት በአገር ውስጥ በመተካት፣ የራሱን የኤሌክትሪክ ኃይል ከስኳር ተረፈ ምርቶች በመጠቀም ለመንግሥት ብሔራዊ የኃይል ቋት በመሸጥ ጭምር ፈርጀ ብዙ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በስፋት የተነሳው የስኳር ኮርፖሬሽን፣ በሰባት ዓመታት ጉዞው አገሪቱን ለ70 ቢሊዮን ብር ዕዳ የዳረጉ ፕሮጀክቶችን ሲያንቀሳቅስ በመቆየቱ አብዛኞቹ የስኳር ፋብሪካዎች ተሸጠው ለዕዳ መክፈያነት እንዲውሉ ማደረጉ የውዴታ ግዴታ እንደሆነበት መንግሥት አስታውቋል፡፡   

በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ግል እንደሚዛወሩ ከሚጠበቁት የስኳር ፕሮጀክቶች ባሻገር፣ መንግሥት አትራፊና በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙትን እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርጅት ለመሸጥ መነሳቱ አግባብ አይደለም የሚል ቅሬታ በተሳታፊዎች ተነስቷል፡፡

‹‹ሁሉም አንድ ዓይነት ችግር ስላለባቸው አይደለም ወደ ግል የሚዛወሩት፤›› በማለት ምላሽ የሰጡት ብሩክ (ዶ/ር)፣ በተለይ እንደ ምድር ባቡርና ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ድርጅቶች ላይ ስለሚታየው ችግር ከፍተኛ አማካሪው የመንግሥትን አቋም ገልጸዋል፡፡ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ዕዳ የተሸከመ በመሆኑ፣ ‹‹የትኛውም ዓይነት ብቃት እንዲኖረው ቢደረግ ይህንን ዕዳ መክፈል ስለማይችል፣ ወደ ግል እንዲዛወር በማድረግ ወይም አዳዲስ ካፒታል ከግሉ ዘርፍ በማምጣት ድርጅቱን ማሻሻል እንደሚቻል ታምኖበታል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዕዳ ያውም ከአገር ውስጥ ምንጮች የተበደረው ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ተቋማቱ የሚያገኙት ገቢ ከተሸከሙት ዕዳ በላይ በመሆኑና በዚህ አግባብ መቀጠል ስለማይችሉ፣ ወደ ግል መዛወራቸው አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ምንም እንኳ በአትራፊነቱ የሚጠቀስ የልማት ድርጅት ቢሆንም፣ እንደ ልቡ ብድርም ሆነ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻሉ 49 በመቶ ድርሻው ለግል ኩባንያዎች ቢሸጥ፣ እንዲሁም በቴሌኮም መስክ ሌሎች ሁለት አገልግሎት ሰጪዎች ገብተው ቢሳተፉ በውድድር ገበያ ይሰፋል፣ የሥራ ዕድል ይፈጠራል ብሎም ተጨማሪ ካፒታል እንደሚገባ ታምኖ የፕራይቬታይዜሽን እንቅስቃሴው እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም በስብሰባው የተሳተፉት የማኅበራዊ ጥናት መድረክ ዋና ዳይሬክተር የራስ ወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ መንግሥት በሕዝብ ሀብትና ጥረት የተገነቡና የሕዝቡ ቅርስ የሆኑ ተቋማት ወደ ግል የሚዛወሩበትን መንገድ ሕዝብ እንዲያውቀውና በሚገባ እንዲሳተፍበት ማድረግ እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡ ከፍተኛ አማካሪውም ሕዝብ እንዲሳተፍ ማድረጉ ተገቢ እንደሆነ ተቀብለው እንሠራበታለን ብለዋል፡፡ በጠቅላላው አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚያስገኙ የልማት ድርጅቶች ለጨረታ እንደቀረቡ በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡

በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ ይሻሉ ባላቸው የኢኮኖሚው መሠረታዊ ማነቆች ላይ ማለትም በዋጋ ግሽበት፣ በውጭ ምንዛሪ ዕጦት፣ እንዲሁም በብድር ዕዳ አከፋፈል ላይ የነበሩ ችግሮች ላይ ሲሠራ መቆየቱንና አሁንም በሥራ ዕድል ፈጠራና በውጭ ምንዛሪ ችግሮች ላይ ትኩረት መደረጉን ያስገነዘቡት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪና የኢትዮጵያ የንግድ ጉዳዮች ብሔራዊ ተደራዳሪ አቶ ማሞ እስመለዓለም ምሕረቱም ኢኮኖሚያዊ፣ መዋቅራዊና ዘርፍ ተኮር የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ሰነድ ዝግጅት መጠናቀቁንና ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ሕዝባዊ ውይይቶች እንደሚደረገቡት አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች