Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለአዲስ አበባ ስፖርት የከንቲባው ማስጠንቀቂያ

ለአዲስ አበባ ስፖርት የከንቲባው ማስጠንቀቂያ

ቀን:

የአዲስ አበባ ስታዲየም ለከተማ አስተዳደሩ እንዲሰጥ ስምምነት ላይ ተደርሷል ተብሏል

“የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርት ዘርፉን ከለውጥ ዕርምጃዎቹ የትኩረት መናኸሪያ ብቻ ሳይሆን ከእንግዲህ በስፖርቱ በነበር መቀጠል አይቻልም፡፡ ለከተማዋ ወጣቶች ተገቢውን ቦታና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ አሠራሮች ይዘረጋሉ፣ ወጣቶች ለስፖርቱ ባላቸው ፍቅር የተነሳ የሚሰባሰቡባቸው ማዘውተሪያዎች የተመልካቾችን ስሜት መግዛት የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ወጣቶች የሚፈጠሩበት መሆን ሲኖርባቸው፣ በተቃራኒው ወጣቶች የሚደበደቡበትና የሚቆዝሙበት እንዲሆኑ አንፈልግም፤” በማለት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ለከተማ አስተዳደሩ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ማስጠንቀቂያ አዘል ጥሪ አቀረቡ፡፡

የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ሰኞ ሐምሌ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. የከተማዋን የስፖርት እንቅስቃሴ በሚመለከት በሸራተን አዲስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የታደሙት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ፣ በስፖርቱ የነበሩ ግን ደግሞ ውጤታማ ያላደረጉ አደረጃጀቶችና አካሄዶች እንዲስተካከሉ፣ የጎበጡ እንዲቃኑ፣ ወጣቱን የሚያሳትፉ፣ ለዘርፉ የሚመጥኑ በስፖርት ሳይንስ ሙያተኞች የተቃኙ ሥርዓቶች እንዲፈጠሩ መሥራት እንደሚገባ፣ ካልሆነ ግን የከተማ አስተዳደሩ ዕርምጃ መውሰድ ብቻ ሳይሆን፣ ተቋማቱ ፈርሰው እንደገና የሚዋቀሩበት አካሄድ እንደሚከተል አስጠንቅቀዋል፣ ተግባራዊ እንደሚያደርጉትም ለታዳሚው ቃል ገብተዋል፡፡

ከንቲባው፣ “የከተማ አስተዳደሩ አቋም የከተማዋን ወጣት እንደ ዝንባሌው ማገልገል ነው፡፡ ወጣቱ መከፋት ብቻ ሳይሆን ስፖርት ለመከታተል ወጥቶ ድብደባ እንዲደርስበት በግሌ አልፈልግም፡፡ ማዘውተሪያዎቻችን ወጣቶች በውጤት ማጣት የሚቆዝሙባቸው የሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው፣ ሕዝባችን ስፖርት በተለይም እግር ኳስን የሚከታተለው በፍቅር ነው፣ ዘርፉ ከዚህም በላይ የልማቱ አንድ አካል ነው፣ ብታምኑም ባታምኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ስፖርቱን ለመለወጥ ተዘጋጅቷል፣ እናደርገዋለንም፤” በማለት ያስተላለፉት መልዕክት የብዙዎቹን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡

 “የስፖርቱ ተቋማት መሪዎችና ኃላፊዎች በዚህ ሒደት ከተባበራችሁን እሰየው፣ ካልተባበራችሁን መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ፣” በማለት ስለአዲስ አበባ ስፖርት ቀጣይ ሕልውናና ዕጣ ፈንታ በሚመለከት ጠንከር ያለ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ከንቲባው፣ “በአደረጃጀትና የአሠራር ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋለው ዝባዝንኬ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፤” ብለው የስፖርት ሚዲያዎች በዚህ መድረክ የሰሙትን ሙሉ በሙሉ ለኅብረተሰቡ እንዲያደርሱ፣ የከተማ አስተዳደሩ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ፍላጎትና እርካታ ውጪ ተቋማዊ አሠራሮች ሊኖሩት እንደማይገባ፣ ቀደም ሲል በነበረው ዓይነት አካሄድ የመቀጠል ፍላጎት ያላቸው ካሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

“እያንዳንዳችን ባለን የኃላፊነት መጠንና ልክ ተጠሪነታችን ለወጣቱና ለሕዝባችን ነው፤” ያሉት ከንቲባው፣ በቅርቡ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ከደንብና መመርያ ጋር ተያይዞ ያልተግባቡት ሁለቱ ክለቦች አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የሚሳተፉበት የሊግ ስያሜ ፌዴራልም ይሁን የተፈለገው ሊሆን ይችላል፣ “አካሄዱ ለአዲስ አበባ ወጣት የማይጠቅም ከሆነ ማፍረስ በጣም ቀላል ነው፣ እንደገና እናደራጀዋለን፣ እዚህ ያላችሁ ክለቦችም ሆናችሁ ሌሎች ባለድርሻዎች አቋማችንን በደንብ እወቁት፤” በማለት የከተማ አስተዳደሩ የማይናወጥ አቋም ስለመሆኑ ጭምር አስረድተዋል፡፡

ከንቲባው፣ “ፖለቲካ ስፖርቱ ውስጥ መግባት የለበትም፣ አሁን የምናገረው እንደ ፖለቲከኛ ሆኜ አይደለም፣ ነገር ግን እንደ አንድ ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ስፖርት መልካም ሆኖ የዓለም አቀፉ መርህም እንደሚለው ስፖርት ለአንድነት፣ ለሰላምና ለወንድማማችነት የሚለውን ሕግጋት መጠበቅ ስላለበት ነው፤” ብለዋል፡፡

“የዓለም አቀፉን ሕግጋት መጠበቅ ከቻልን በጣም ቀላል ነው፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሕግጋቱን ብቻ ማስፈራሪያ እያደረጉ 20 ሺሕ ወጣት በተሰበሰበበት ጩቤ፣ ቆንጨራና ዱላ ይዞ የሚወጣ ከሆነ አያስኬድም፤” ያሉት ከንቲባው፣ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይን ጨምሮ በሌሎችም ጎዳናዎች ከ50 ሺሕ እስከ 70 ሺሕ ወጣቶች ማስ ስፖርትና በሌሎችም ፕሮግራሞች ሲታደሙ አንዳች ኮሽታ ሳይፈጠር የተጠናቀቁ ሁነቶችን በማሳያነት አንስተዋል፡፡ በተጓዳኝ በስታዲየሞች ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች ታዲያ የችግሩ መንስኤ የስፖርቱ አደረጃጀትና አመራሩ እንደሆነና የተቋማቱ መሪዎችም ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጭምር አሳስበዋል፡፡

እንደ ከንቲባው ከሆነ የስፖርቱ ሰላማዊ እንቅስቃሴና ውጤታማነት አደረጃጀቱ ሲስተካከልና ለዚያ ተቋም የሚመጥን፣ ኃላፊነት የሚሰማው ሙያተኛንና ሙያን ማጣጣም ሲቻል ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ማን የቱ ጋ ቢቀመጥ ለሚለው ጥያቄና ኅብረተሰቡም የሚጠብቀውንና የሚመኘውን ውጤት ለማስመዝገብ ብዙም እንደማይከብድ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ሌላው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት ምክትል ከንቲባ ታከለ፣ መጠሪያውን በአዲስ አበባ ስም ያደረገው የአዲስ አበባ ስታዲየምና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተጠሪነት ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡ እንደ ከንቲባው ከሆነ፣ የአዲስ አበባ ስታዲየም ለከተማ አስተዳደሩ እንዲሰጥ ለሚመለከተው አካል በደብዳቤ ተጠይቋል፡፡

ለዚህ ምሳሌ አድርገው ያነሱት ከንቲባው፣ “የስፖርት ኢንዱስትሪው በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍ እንዲል ማሰብ አስፈላጊ መሆኑ፣ አሁን ባለው የሁላችንም ኩራት በሆኑት አትሌቶቻችን ካልሆነ በእግር ኳሱ የለንበትም፣ ሕዝባችን ደግሞ የሚወደው እግር ኳስ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አዲስ አበባ ላይ መሥራት ከተቻለና ወጣቶቻችንን እንደየ ዝንባሌያቸው ማንቀሳቀስ ከቻልን ስኬታማ የማንሆንበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፤” ብለው ለዚህ የአዲስ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ ማዘውተሪያዎች በባለቤትነት ይዞ ማዘመንና ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡

ስፖርቱን በአደረጃጀት ለማዘመንና በሥርዓት ለመምራት፣ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በኢትዮጵያ በርካታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስፖርት ሳይንስ ዲፓርትመንት እንዳላቸው ያወሱት ከንቲባው፣ “ዩኒቨርሲቲዎቻችን የስፖርቱን ጉዳይ እንደ አንድ ትልቅ የአገር ጉዳይ ተመልክተው መሥራትና ለዚያ የሚጠቅሙ በጥናት የተደገፉ የምርምር ሥራዎችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥት ለዚያ የሚሆነውን በጀት መመደብ ይችላል፣ የከተማ አስተዳደራችን ለዚህ ሙሉ ፈቃደኛ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ፣ እንደ ዜጋም ሁላችንም ሊሰማን ይገባል፤” በማለት የደረሱበትን ድምዳሜ ጭምር ተናግረዋል፡፡

“ፌዴራል መንግሥት ስታዲየም ማስተዳደር ይኖርበታል የሚል እምነት የለኝም፣ ሥራውም አይደለም፡፡ ከዚህ በመነሳት ብቻ ሳይሆን እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ስታዲየም ለባለቤቱ እንዲመለስ በይፋ ጠይቀናል፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም ከስያሜው ጀምሮ የአዲስ አበባ ነውና መልሱ ብለናል፣ መመለስም እንዳለበት እናምናለን፤” ያሉት ከንቲባ ታከለ፣ በጉዳዩ ከኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) ጋር ተጋግረው ሚኒስትሯም ፈቃደኛ ስለመሆናቸው ጭምር ነው የተናገሩት፡፡

እንደ አዲስ አበባ ስታዲየም ሁሉ ከንቲባው ሌላው በንግግራቸው ያካተቱት፣ የፌደራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስን ጉዳይ ነው፡፡ “ፌዴራል ፖሊስ የሁላችንም ኩራት ነው፣ በመሆኑም ሁለት ቡድኖች በተጫወቱ ቁጥር ስታዲየም ቆሞ መጠበቅ የለበትም፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተገኝቶ ስያሜውን በሚመጥን መልኩ ሥራውን መሥራት ይጠበቅበታል፤” ብለዋል፡፡

ፌዴራል ከስያሜው መረዳት እንደሚቻለው በአገር አቀፍ ደረጃ ማዕቀፎችን ማለትም ከሕግ አኳያ መመሪያዎችንና ፖሊሲዎችን የሚያወጣና የሚቀርፅ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ እንደ ከንቲባው፣ “ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የከተማችን ክለቦች ናቸው፡፡ አስተዳዳሪዎቻቸው ከምሥረታቸው ጀምሮ እዚህ አድረሰዋቸዋል፣ ሁለቱም የከተማዋ ቡድኖች እንደመሆናቸው የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍና እገዛ ሊያደርግላቸው ይገባል፡፡ ክለብም ሆነው በአኅጉራዊና ኢንተርናሽናል ውድድሮች ላይ ተሳትፈው የከተማችንን ስም እንዲያስጠሩ እንፈልጋለን፣ ለዚያ ደግሞ መደገፍ፣ ማገዝና ማብቃት ስንችል ነው፤” ብለዋል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ፖሊስ አንድ የሜትሮፖሊታን ፖሊስ ማሟላት ያለበት ቁመና ላይ እንደሚገኝ ያከሉት ከንቲባው፣ “ተቋሙ ቀደም ሲል በነበረው አሠራር ፌዴራል ቢወስደውም፣ እንደገና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲመለስ ጠይቀናል፤” ብለው ከዚህ በፊት በፌዴራል ስር ቆይተው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተመለሱት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣንን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

በመድረኩ የታደሙ ሙያተኞች በበኩላቸው ከስፖርቱ የኋላ ታሪክና ከከንቲባው አስተያየት በመነሳት ያላቸውን ሥጋት ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በማሳያነትም ስፖርቱን በሚመለከት አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ተመሳሳይ መድረኮችን በማዘጋጀት ሙያተኞችና ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ውይይቶችንና ክርክሮችን አድርገዋል፣ እያደረጉም ናቸው፡፡ ይሁንና ሁሉም ውይይቶችና ክርክሮች መድረክ ከማድመቅ ያለፈ ሚና ሳይኖራቸው የቀሩበት አጋጣሚ ብዙ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...