Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየሥነ ሥዕል ዕድገትን የገታው ቅጅ

የሥነ ሥዕል ዕድገትን የገታው ቅጅ

ቀን:

የሰው ልጆች የፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች ከንግግር ባለፈ  በሥዕል፣ በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በቴአትር፣ በጽሑፍ ጥበብ ይገለጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ፖለቲካዊም፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንም ሆነ ሙገሳዎችን በተለያዩ ሥነ ጥበባዊ መንገዶች መግለጽ የተለመደ ሲሆን፣ ዛሬም አሻራቸው ይታያል፡፡

ይሁን እንጂ የጥበብ ዕድገቱን ስንመለከት የራሳቸውን የሥዕል፣ የድርሰት፣ የግጥምና ሌሎች የጥበብ ማንነት ከማፍለቅ ይልቅ በፊት የነበሩትን ወይም የተሠራውን ድጋሚ በመሥራት የእኔ ነው ባይ መብዛቱ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡

- Advertisement -

ሌሎች የዓለም አገሮች ከደረሱበት ትልቅ ቦታ የኢትዮጵያ ጥበብ አዋቂዎች ላለመድረሳቸው አንዱ ምክንያት የቅጅ ጉዳይ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የአፍሪካ አገሮችን ስንመለከት የራሳቸውን ማንነት በማሳየት ረገድ ጥሩ የሚባሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል የሌሎችን አስመስሎ በመሥራት የረሳቸውን ተሰጥኦ ሳይጠቀሙበት የሚቀሩ አሉ፡፡

ቅጅ ወይም መገልበጥ በሥነ ጽሑፍ ፕላጃሪዝም የሚባለው ከሚታይባቸው ሥነ ጥበብ ውስጥ አንዱ ሥነ ሥዕል ነው፡፡

የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ጨምሮ ብዙ ዓለምን ያስደነቁ ሥዕል የሣሉ ባሉበት አገር የሥነ ሥዕል ዘርፍን የራሷ ማንነት (መገለጫ) ከማድረጉ ይልቅ የእከሌ ሥዕል ሽያጭ ላይ ጥሩ ነው በሚል ምክንያት በቅጅ (Copy) የሥነ ጥበብ ዕድገትን ወደ ኋላ የሚጎትቱ እንዳሉ አገር ያወቀው ከሆነ ሰንብቷል፡፡

የሥዕል ቅጅ ወይም ግልበጣን ችግር ለመቅረፍ ከሚንቀሳቀሱ በዘርፉ ከሚሠሩት የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች መካከል ወ/ሮ የእናትፋንታ አባተ ይገኙበታል፡፡

ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ‹‹ነፃ ጥበብ ፍለጋ ማንነት›› (Free Art Felega Identity) በሚል በጀርመን ባህል ማዕከል Copy Kills Creativity? እንዲሁም You Saw One You Know All? በሁለቱ ጉዳዮች ላይ ፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡ በተለይ ማንነት (Identity) ሲባል ከኢትዮጵያዊነት ባሻገር ሠዓሊያን የየራሳቸው መለያ (ማንነት) ላይ ያተኮረ ሥራ እንዲሠሩ በመድረኩ ላይ ከተነሱ ሐሳቦ መካከል ይገኝበታል፡፡

ለምሳሌነት የተነሳው ‹‹ትክክለኛ የበግ እረኛ በግ በግ ነው የሚሸተው›› ስለዚህ አንድ ሠዓሊ መሥራት የሚገባው ራሱን የሚመስል ሥራ ነው፣ ‹‹አርቲስት ማለት ቪዧል ፊሎሰፈር ነው›› ፊሎሰፈር የሚለው ቃል የጥበብ ፍቅር ከሆነ ሠዓሊያን ደግሞ ሥዕል መሣል ያለባቸው አፍቅረው መሆን አለበት የሚሉ ሐሳቦችም ተሰንዝረዋል፡፡

እንደ ማብራሪያ የቀረበው ጽጌረዳ አበባን ከወደድናት ቆርጠን ቤት ውስጥ እናስገባታለን ነገር ግን ካፈቀርናት ቆርጠን እንተክላለን፣ እራሷን ለማሳደግ ግን በእሾህ እንወጋለን ከእርሷ ጋር መከራ ዓይተን እናሳድጋታለን፡፡ የሥዕል ሥራም ልክ እንደ ጽጌሬዳዋ ነው በማለት ተብራርቷል፡፡

በአሁኑ ዘመን እየተሠራ ያለው ሥዕል (Contemporary Art) የአውሮፓውያን እየተባለ በኢትዮጵያ በአንዳንዶቹ ሠዓሊያን ባይወደድም ላሊበላ ላይ ያለውን ‹‹አምሳለ ሲኦል›› ብናይ ከዘመኑ ቀድሞ ህያው የሆነ የኢትዮጵያ አርት ውስጥ አንዱ ነው፣ የሚል ሐሳብ ተደምጧል፡፡

ከሥዕል ሥራዎች ውስጥ ክዋኔ ጥበብ (ፐርፎርማንስ አርት) ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም ሥራዎች ውስጥ በኢትዮጵያ በተረት በተደጋጋሚ የሚነሱት አለቃ ገብረሃና በሠርግ ቤት ያደረጉት ክንውን ከፕርፎማርስ አርት ተጠቃሽ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በተለያዩ ታዳሚያን አስተያየትና ጥያቄዎች የቀረበ ሲሆን፣ ሥዕል ዕውቀትንና ምንጭን ይፈልጋል የሚል አስተያየት ተሰንዝሯል፡፡ ሠዓሊያን አንባቢያንም መሆን አለባቸው፣ ምክንያቱም ስለአካባቢያቸውና ስለማኅበረሰቡ ታሪክ የተለየ ዕይታ እንዲኖራቸው ንባብ ወሳኝ ነው የሚል አስተያየትም ቀርቧል፡፡

መገልበጥ (Copy) ሁል ጊዜ አይሁን እንጂ ለልምምድ መጠቀም ችግሩ ምንድነው? የሚል ጥያቄም ከታዳሚያን ቀርቧል፡፡ በምላሹም ሠዓሊያን ሥዕል ሲጀምሩ የሰው ሥራን ደግሞ በመሥራት ክህሎታቸውን ያዳብራሉ፣ ነገር ግን ትልቁ ችግር በዚያው ከቀጠሉ ነው የሚል ምላሽ ከመድረኩ ተሰምቷል፡፡

በውይይቱ ሠዓሊያን መንገዳቸውን እንዳይስቱ የየራሳቸው የአሣሣል ጥበብና ክህሎት እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ የሰው ሥራን እንደራስ ሥራ አድርጎ የእኔ ነው ማለት ግን ወንጀል መሆኑ ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል ይገኝበታል፡፡

በነፃ ጥበብ ፍለጋ ማንነት ዓውደ ጥናት ላይ እየሠሩ የሚገኙት ወ/ሮ የእናት ፋንታ አባተ እንደተናገሩት፣ የፕሮጀክቱ ዓላማ የኪነ ጥበብ ሰዎች ያላቸውን ዕውቀት እንዲያዳብሩ ማስቻል ነው፡፡ ከሌሎች አገር በቀል ካልሆኑ ሰዎች ጥገኛ ሳይኮን፣ በኢትዮጵያ ሥዕል ማሳያ፣ መገልገያና መጠቀሚያ መሆን እንደሚችል ለማሳወቅ ጭምር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የውጭ አገር የመማር ዕድል እንዲፈጠርና የውጭ አገር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ለማስተዋወቅ ከማስቻል ባሻገር ልምድ ለመለዋወጥ ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህ ዓውደ ጥናት በሦስት ቦታዎች ላይ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል በአርት ስኩል፣ በጎተ ኢንስቲትዩትና በሜቄዶንያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በነዚህ ቦታዎች ላይ የተለያዩ የኤግዚቢሽን፣ የውይይት መድረክና በሜቄዶኒያ የሚገኙትን ሕሙማንንና አዛውንቶችን አንድ አርቲስት እንዴት አድርጎ መርዳት ይችላል? በሚሉ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አክለውም በሥራቸውም ታዋቂነትን እንዲያመጡ ይረዳቸዋል በማለት ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓውደ ጥናት የሚሳተፉት የኪነ ጥበብ ሰዎችም ከሦስት ቦታዎች የተመረጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከአርት ስኩል አሥር ተማሪዎች፣ ከአርት አሶሴሽን አሥር አርቲስቶች፣ ከኦሮሚያ አርት አሶሴሽን ደግሞ አራት አርቲስቶች እንዲሁም በሜቄዶንያ ለሚገኙ አርቲስቶችም ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት ስላላቸው ሁሉንም ማሳተፋቸውን ወ/ሮ  እናትፋንታ ተናግረዋል፡፡

ነፃ ጥበብ ፍለጋ ማንነት የሚለውን ርዕስ የተመረጠበት ምክንያት የራሳቸውን ማንነት የሚያውቁበት የኪነ ጥበብ ሥራዎች ለማየት የሚያስችል ሒደት እንዳለ ለማሳወቅና የየራሳቸውን ፈጠራ ይዘው መሥራት እንዳለባቸው ለማሳየት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ለአራተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ይህ ፕሮጀክት ከዚህ በፊት የነበሩት ሥራዎች በአገሪቷ ለሚገኙም ሆነ ከአገር ውጭ ለሚመጡ የኪነ ጥበብ ሰዎች የተለያዩ ለውጦችን ለመፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ነፃ ጥበብ ፍለጋ ማንነት በውይይት ብቻ ሳይሆን ሥልጠና በወሰዱት የተሠሩ የሥዕል ሥራዎችና የአርት ኤግዚቢሽን ነሐሴ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ተካሂዷል፡፡ በተጨማሪም በመቄዶኒያ የአዛውንቶችና የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል የቡድን ኤግዚቢሽን መክፈቻ ነሐሴ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ተነግሯል፡፡

በሔለን ተስፋዬና ተመስገን ተጋፋው

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...