Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያን ከዋጋ ንረትና የሥራ ቅጥር አዙሪት ማውጣት ይቻላል

ኢትዮጵያን ከዋጋ ንረትና የሥራ ቅጥር አዙሪት ማውጣት ይቻላል

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ግለሰቦች የሚፈልጉትን ሸቀጥ ለመሸመት ወይም የመግዛት አቅም እንዲኖራቸውና ገቢ ለማግኘት ጉልበታቸውን ይሸጣሉ፡፡ ስለሆነም የግለሰቦች የኑሮ መጀመርያ የምርጫ ውሳኔ ሠርቶ ገቢ በማግኘት (Employment) እና ሳይሠሩ ዕረፍት በማድረግ (Leisure Time) መካከል ነው፡፡ ሥራ ለመሥራት የሚከፈለው የዕጦት ዋጋ (Opportunity Cost) ለሥራው የተሰዋው የዕረፍት ጊዜ ነው፡፡ የውሳኔ ምርጫው በእያንዳንዱ ሰው ስሜት ጉልበትን ለሥራ ሸጦ በሚገኘው ደመወዝ ከሚገዛው ሸቀጥ የሚገኘው ጥቅምና ዕረፍት ከማድረግ የሚገኘው ዕፎይታ መካከል የተሻለው ነው፡፡

በቀድሞ ጊዜ በአሥራ አምስት ሣንቲም ይሸጥ የነበረ የሆቴል ሽሮ ወጥ ምግብ ዋጋ ሃምሳ ብር ከገባ ጊዜ ጀምሮ፣ ሃምሳ ብር ለማግኘት የምለፋው ልፋት ረሃቡን ከመታገስ አይበልጥብኝም ብሎ ተስፋ የቆረጠው ወጣት በዝቷል፡፡ የአንድ ብልቃጥ ክኒን ዋጋ ሦስት ሺሕ ብር ከገባ ጊዜ ጀምሮ ሦስት ሺሕ ብር ለማግኘት ከመልፋት፣ አርፌ ተኝቼ በሽታዬን በዕረፍት ከማስታመም አይበልጥብኝም የሚለው ጎልማሳ ሰው በዝቷል፡፡ ጎጆ ቀልሶ ለመኖር የሚያስፈልገው የደመወዝ መጠን መብዛት ሥራ መሥራትን ተስፋ ቢስ አድርጓል፡፡ መብራትና ውኃ በሌለበት ገጠር ሄዶ ሠርቶ አሥር ሺሕ ብር ከማግኘት፣ ከተማ ዘመድ ዘንድ ተጠግቶ መኖርን የሚመርጥ ሰው ብዙ ነው፡፡ ሀብታሙ ያለኝ ይበቃኛል ለምን እሠራለሁ ያለበትና ደሃው ምንም ያህል ብሠራ ምንም ልገዛ አልችልም ብሎ ተስፋ የቆረጠበት ሁኔታ ውስጥ ገብተናል፡፡ የኑሮ ከመጠን በላይ መክበድ የሥራ ተነሳሽነታችንን አላሽቋል፡፡

በአሥራ አምስት ሣንቲም ትሸጥ የነበረችውን ሽሮ ለመብላት የሃምሳ ብር ሥራ መሥራት ካለብኝ ባይበላስ፣ ባይጠጣስ፣ ባይኖርስ፣ መኖር ወደሚቻልበት አገር ብሰደድስ፣ ወደሚል ተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ወጣቱ ገብቷል፡፡ ከቅርብ ዓመታት በፊት ከዩኒቨርሲቲ በዲግሪ የተመረቀው በአምስት መቶ ብር ደመወዝ ለመቀጠር በደስታ ፈቃደኛ የነበረበትን ሁኔታ እናስታውሳለን፡፡ ዛሬ በአምስት ሺሕ ብር ለመቀጠርም ደስተኛም ፈቃደኛም አይሆንም፡፡ ዘመድ ጋ ተጠግቶ መኖሩ ይመረጣል፡፡ ለመሥራት አለመፈለግና የሥራው አለመኖር በኢትዮጵያ ውስጥ እየተጋጩ ያሉ መሆናቸው በእኩል ደረጃ ሊታዩ የሚችሉ ችግሮች ናቸው፡፡

ለመሥራት አለመፈለጉ፣ ሥራን መናቁና ዕረፍትን መሻቱ የግለሰቦች ግላዊ ባህሪ ብቻ ሳይሆን ጥቅሙን ከፍተኛ ለማድረግ ከሚፈልግ አዋቂ (Rational) የገበያ ኢኮኖሚ ሰው የሚጠበቅ የወል ባህሪ ቢሆንም፣ ብዙ ሰዎች ግን ባለማወቅ ትውልዱን በሰነፍነት ይፈርጃሉ፡፡ ኢኮኖሚስቶች ስለሥራ ቅጥርና የዕረፍት ጊዜ ምርጫዎች ከገቢ መጠንና ከኑሮ ሁኔታ ጋር አገናዝበው የተነተኗቸውን ጽንሰ ሐሳቦች መረዳት ለጣምራ ችግሮቻችን መፍትሔ ይሆናል፡፡

የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መጠናት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ የሥራ ቅጥር የአንድ ማኅበረሰብ ቀዳሚ የፖሊሲ ግብ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ የጥንቶቹ ሊበራል ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች በማይክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት ደረጃ የሥራ ቅጥርን ከደመወዝ መጣኝ ጋር አስተሳስረው አጥንተዋል፡፡ የተዛምዶ ጽንሰ ሐሳብም ነድፈዋል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚክስ አባት የሆነው ኬንስና ተከታዮቹ የሥራ ቅጥርን ከጥቅል አገራዊ ገቢ ጋር አስተሳሰረው አጥንተዋል፡፡ ኬንስ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነበት ሥራውም ‹‹የሥራ ቅጥር፣ የወለድና የጥሬ ገንዘብ አጠቃላይ ጽንሰ ሐሳብ›› ተብሎ የሚጠራው መጽሐፉ ነው፡፡ የልማት ኢኮኖሚስቶችም የሥራ ቅጥርን የልማት ፕሮጀክቶች ከሚፈጥሯቸው የሥራ ዕድሎች ጋር አስተሳስረው ያጠናሉ፡፡ ሆኖም በልማት ኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ከገበያ ኢኮኖሚ አንፃር፣ በተለይም ከሚፈጥሩት የዋጋ ንረት የጎንዮሽ አሉታዊ ተፅዕኖዎች አኳያ ስለማይተነተኑ የዋጋ ንረትና የሥራ ቅጥር  አዙሪት ውስጥ ይከታሉ፡፡

ኢትዮጵያ በደርግና በኢሕአዴግ አስተዳደሮች በልማት ኢኮኖሚክስ የሥራ ፈጠራ ዕድሎችን ከልማት ፕሮጀክቶች ጋር አስተሳስራ ስታቅድና ስትተገብር በመኖሯ፣ የዋጋ ንረትና የሥራ ቅጥር አዙሪት ውስጥ እንደ ወደቀች ሁላችንም የዓይን ምስክሮች ነን፡፡  የሥራ ቅጥሮች የዋጋ ንረት ምክንያቶች እንዳይሆኑ በገበያ ኢኮኖሚ ጥናት የዋጋ ንረትና የሥራ ቅጥር አዙሪት ውስጥ ላለመውደቅ ማቀድ ትችል ነበር፡፡ የጥቅል ምርት ፍላጎት ዕድገት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚክስ (Demand Side Economics)፣ ወይም የፍላጎት አስተዳደር (Demand Management) የዋጋ ንረትና የሥራ ቅጥር አዙሪት ውስጥ ሳይገባ በማክሮ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማቀድ ይቻላል፡፡   

በማክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት የፍላጎት አስተዳደር ማለት ምን ማለት ነው? የፍላጎት አስተዳደር ማለት በብሔራዊ ኢኮኖሚ ሒሳብ መዝገብ ውስጥ የሚመዘገቡትን ከጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን ጋር እኩል የሆኑ ሦስት የወጪ ዓይነቶች የቤተሰቦች የፍጆታ ሸቀጥ ፍላጎት ወጪዎች፣ የመንግሥታዊና የግል ድርጅቶች የመዋዕለ ንዋይ ሸቀጥ ፍላጎት ወጪዎች፣ የመንግሥት መደበኛ ወጪዎች ድምር አስተዳደር ጥናት ነው፡፡ ይህም እስከ ዛሬ ከተጓዝንበት በመንግሥት ድጋፍ ግብርናንና የኢንዱስትሪ አገልግሎትን በመደገፍ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ የአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚ ፖሊሲ የተለየ ነው፡፡ ‹‹አቅርቦት የራሱን ፍላጎት ይፈጥራል›› የሚለውን የሊበራል ኢኮኖሚስቶች የአቅርቦት ጎን ፍልስፍና፣ ኬንስ ‹‹ወጪ የራሱን ገቢ ይፈጥራል›› በሚል የፍላጎት ጎን ፍልስፍና የገለበጠበት አስተምህሮ ነው፡፡

ጠቅላላ የአገር ሸቀጥ ሸመታ ወጪ አድራጊ የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚ አስተዳደር ሦስት አካላት የሆኑትን ቤተሰብን፣ ድርጅቶችንና የመንግሥትን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚገዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ የዋጋ ንረትና የሥራ ቅጥር አዙሪት ውስጥ ላለመውደቅ፣ እነዚህን ገዥ ምክንያቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ አድርጋ መውሰድ የምትችልባቸውን መንገዶች በጥቂቱ እንመልከት፡፡

ቤተሰቦች የፍጆታ ወጪዎቻቸውን የሚወስኑት ከገቢያቸው ወይም ከገቢያቸው ዕድገት ውስጥ ምን ያህሉን ለፍጆታ እንደሚጠቀሙና ምን ያህሉን እንደሚቆጥቡ የሚወስኑት ውሳኔ የፍጆታ መርሐ ግብር (Consumption Function)፣ ወይም የፍጆታ ዝንባሌ (Propensity to Consume) ይባላል፡፡ በእያንዳንዱ የገቢ መጠን ላይ ሸማቾች የተለያዩ የፍጆታና የቁጠባ መርሐ ግብሮች ወይም ዝንባሌዎች ይኖሯቸዋል፡፡ መጣኞቹ በሥሌት የሚለኩ ናቸው፡፡ በሒሳብ ሥሌት የለውጥ ተዛምዶ መጣኝ (Rate of Change) ወይም በግራፍ የተዛማጅነት መስመርን ግድለት (Relationship Line Slope) በመለካት ለእርግጠኝነት የቀረበ መልስ ማግኘት ይቻላል፡፡ መለካት ካልተቻለ፣ ባይለኩም አቅጣጫውን የማወቅ አጠቃላይ ግንዛቤ ብቻም ይበቃል፡፡

በኅብረተሰቡ ዘንድ የገቢ መመጣጠንና አለመመጣጠን በምርት አቅርቦት ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ አውቆ ገቢን ማሳደግ ወይም የገቢ ክፍፍልን ፍትሐዊ ማድረግ፣ ዋናው የሥራ ዕድል ፈጠራ መንገድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከልክ በላይ የሆነ የሀብት ክፍፍል ስላለ የሀብታሙን ገቢ ማሳደግ የውጭ ሸቀጦችን ማበረታታት ሲሆን፣ የደሃውን ገቢ ማሳደግ ግን የውስጥ ሸቀጦች አምራቾችንና የሥራ ዕድል ፈጠራን ማበረታታት ነው፡፡ የመንግሥት መዋዕለ ንዋይ ፍላጎት የሚወሰነው በመሠረተ ልማት ግንባታና መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በማስፋፋት ፖሊሲው ላይ ተመርኩዞ ሲሆን፣ የግል ድርጅቶች መዋዕለ ንዋይ ፍላጎት ግን የሚወሰነው በወለድ መጣኝ ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡ በገበያ ኢኮኖሚ የወለድ መጣኝ የሚወሰነውም በገበያ ውስጥ በተሠራጨው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት መጠን ነው፡፡ የወለድ መጣኙ ዝቅተኛ ሲሆን መዋዕለ ንዋይ ስለሚበረታታ ድርጅቶች በብዛት ለማምረት ተጨማሪ ሠራተኞችን ይቀጥራሉ፡፡

የመንግሥት መደበኛ ወጪ የሚወሰነው በመንግሥት አገልግሎት ለሕዝብ ተፈላጊነት መጠን ነው፡፡ የመንግሥት አገልግሎት ለሕዝብ ተፈላጊ ሆኖ ሲገኝ መንግሥት የሥራ አጥነትን ለማስወገድ መዋቅሩን አስፋፍቶ ምርታማ በሆነ የሥራ መደብ  ብዙ ሠራተኞችን ይቀጥራል፡፡ የኬንስ የበጀት ጉድለት (Deficit Financing) ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሚስጥር የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ ኬንስ የቤተሰቦች የፍጆታ ወጪና የግል ድርጅቶች የመዋዕለ ንዋይ ወጪ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ፣ ወይም ለማስፋፋት በቂ ካልሆነ መንግሥት ክፍተቱን ለመሙላት የበጀት ጉድለት ውስጥ መግባት አለበት ይላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የበጀት ጉድለት ውስጥ የሚገባው በምን ቀመር እንደሆነ አይታወቅም፣ ጠያቂም የለም፣ መላሽም የለም፡፡ ማን ይጠይቃል? የፓርላማ አባላት ወይስ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች? ወቸው ጉድ፡፡

ከዚህ በላይ የተገለጹትን የሥራ ቅጥር የማክሮ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ሁኔታዎች በማክሮ ኢኮኖሚክስ ሳይንስ ሳይተነትኑ፣ በልማት ፕሮጀክቶች ጋጋታ በገበያ ፍላጎትና ዋጋ መለኪያ ተፈላጊነታቸው ያልተመሰከረላቸው የሥራ ዕድል ፈጠራን ማቀድ የሥራ ቅጥርና የዋጋ ንረት አዙሪት ውስጥ መውደቅ ነው፡፡

በገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ ላለች አገር የመጀመርያው የቱ ለገበያውና ለግሉ ኢኮኖሚ ውሳኔ ይተው? የቱ በማዕከላዊ ደረጃ ይታቀድ? የሚለው ምርጫ ነው፡፡ በልማት ኢኮኖሚ ፍልስፍና መንግሥት እኔው ዕቅድ አውጥቼ እኔው ለወጣቱ ሥራ ላፈላልግ  ቢልም እንኳ፣ በቀጥታ ፕሮጀክቶች ስለሚፈጥሩት የሥራ ዕድል ዝርዝር ጥናት ውስጥ ከመግባቱ በፊት የዋጋ ንረት የጎንዮሽ ችግር እንዳይገጥመው የማክሮ ኢኮኖሚ ማዕቀፉን መተንተንና ማዘጋጀት ይገባል፡፡ ከማክሮ ኢኮኖሚ የገበያ ኢኮኖሚ አመራር አስተምህሮ አንፃር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ሥራ ለመፍጠር ቀርፋፋ ነው የሚባለው፣ በገበያ የሚመራው የግል ኢኮኖሚና በፍጥነት አድጓል የሚባለው፣ በዕቅድ የሚመራው ብሔራዊ ኢኮኖሚ ያልተግባቡበት ያላቻ ጋብቻ ቁርኝት፣ ወይም እያንዳንዱ ድርሻውን አለማወቅ የኃላፊነት መደበላለቅ ተቃርኖ የሰፈነ መሆኑን አውቆ መንግሥት መፍትሔ ሊሻ ስለሚገባው፣ የሁለቱን ልዩነት አጠር አድርጌ አቀርባለሁ፡፡  

የሊበራል ኢኮኖሚስቶች የገበያ ኢኮኖሚ ማይክሮ ኢኮኖሚክስ አመለካከት ምንም እንኳ ለጥቂት ጊዜ የምርትም ሆነ የሥራ ገበያ ፍላጎትና አቅርቦት እኩል ሳይሆኑ ቀርተው ዋጋዎች ቢዋዥቁም፣ የተመረተው ምርትና ለገበያ የቀረበው ሁሉ እንዲሸጥ የማጣሪያ የገበያ ዋጋ (Market Clearing Price) ባይፈጠርም፣ በረዥም ጊዜ ውስጥ ፍላጎትም ሆነ አቅርቦት ከዋጋ ውጣ ውረድ ጋር በመጨመርና በመቀነስ ተለዋውጠው እኩል በመሆን፣ የተመረተው ምርት ሁሉ እንዲሸጥ የረጋ ቋሚ ማጣሪያ የገበያ ዋጋ ይፈጥራሉ፡፡ ይህም የሥራ ዕድልን ይፈጥራል የሚል አመለካከት ነው፡፡

በሌላ በኩል የኬንስ ማክሮ ኢኮኖሚክስ አስተምህሮ በክላሲካል ኢኮኖሚስቶቹ የገበያው ብቃት አስተምህሮ አለመስማማቱን የሚገልጸው በረዥም ጊዜማ ሁላችንም እንሞታለን በማለት፣ የገበያ ማጣሪያ ዋጋ እስከሚፈጠር ረዥም ጊዜ ከምንታገስ በማክሮ ኢኮኖሚ የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚክስ ወይም የፍላጎት አስተዳደር ፖሊሲ መንግሥት ገበያውን በዕቅድ መግራትና መምራት አለበት የሚል ነው፡፡

በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የገበያ ኢኮኖሚ ዳብሮ፣ የገበያ ኢኮኖሚ ሰው ባህሪን ተላብሰን፣ ፍላጎትና አቅርቦት በራሳቸው ውስጣዊ ሒደት ተመጣጥነው፣ ትክክለኛው የሸቀጦች ማጣሪያ ዋጋ በገበያ ውስጥ ተተምኖ፣ ገበያዎቻችን ይስተካከሉ የሚለውን የሊበራል ኢኮኖሚስቶች አመለካከት የሩቅ ጊዜ ውጥን ወደ ጎን ትተን መንግሥት መቼ ነው ገበያውን መርቶ ገበያዎቻችን የሚያስተካክለው ብለን የምንጠይቅበት ጊዜ ላይ ነን፡፡  በልማት ፕሮጀክቶች ለምንፈጥራቸው የሥራ ቅጥር  ዕድሎች የማክሮ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ በመተንተን የዋጋ ንረትና የሥራ ቅጥር አዙሪት ውስጥ እንዳንገባ እንጠንቀቅ በማለት ሙያዊ ምክሬን እለግሳለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...