ላለፉት 17 ወራት ሲጻፉ ሲተነተኑ ከከረሙ የፖለቲካና የማኅበራዊ የለውጥ ፕሮግራሞች በተጨማሪ የኢኮኖሚ ለውጥ ፕሮግራሞችም ይጠቀሳሉ፡፡ መንግሥትም በእነዚህ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ሦስት የማሻሻያ ፕሮግራሞችን እንደነደፈና ከሰሞኑም ለውይይት እንደሚያቀርባቸው ይፋ አድርጓል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የንግድ ተደራዳሪ ማሞ እስመለዓለም ምሕረቱ እነዚህን የሪፎርም ፕሮግራሞች አስተዋውቀዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በኩል በየጊዜው የሚሰናዳው የ‹‹አዲስ ወግ፣ አዲስ ጉዳይ›› ሰሞንኛ መርሐ ግብር ኢኮኖሚ ተኮር እንደሚሆን ሲጠበቅ፣ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መነሻዎችና የወደፊት አቅጣጫዎቹን የሚያመላክቱ እንደሚሆኑ፣ ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. የተካሄደው ውይይት አመላክቷል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ መንግሥት የሚተገብራቸው ሦስቱ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማዕቀፎች በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ፣ በመዋቅራዊ ኢኮኖሚው ችግሮች ላይ እንዲሁም በኢኮኖሚው ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚው መስክ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ተሳትፎ የሚያጠናክሩ፣ ሥራ አጥነትን የሚቀንሱ፣ የመንግሥት የበጀት ጉድለት የሚያስተካክሉ ዕርምጃዎች ታስበዋል፡፡ በዚሁ በማክሮ ኢኮኖሚው መስክ በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚያቃልሉ ዕርምጃዎችን ጨምሮ፣ የውጭ ሐዋላ ገቢን የሚሻሽሉ የመፍትሔ ዕርምጃዎችም ተካተዋል፡፡
በየትኛውም መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ሦስት መሠረታዊ አሳሳቢ ጉዳዮች ትኩረት እንደሚሹ ጸሐፍት ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶቹም ወደ ስድስት ያደርሷቸዋል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሥራ አጥነት እንዲሁም የዋጋ ግሽበት ሦስቱ ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ሥጋቶች እንደሆኑ የሚተነትኑ በአንድ ወገን ይመደባሉ፡፡
እነዚህ ሥጋቶች ላይ ተጨማሪ በማከል የኢኮኖሚውን ዑደት ወይም ‹‹ቢዝነስ ሳይክል›› በመባል የሚታወቀውንና የአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) ውጣውረድን፣ የውጭ ምንዛሪ ችግሮችን ወይም የገቢና ወጪ ንግድ ሚዛንንን እንዲሁም የተባባሰ የዋጋ ግሽበት ከሥራ አጥነትና ከተቀዛቀዘ ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ሲደመር የሚፈጠረው ‹‹ስታግፍሌሽን›› ለአንድ አገር ማክሮ ኢኮኖሚ አሳሳቢ ከሚባሉ መሠረታዊ ችግሮች ውስጥ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ የወቅቱ ሁኔታ ‹‹ስታግፍሌሽን›› በሚባለው መለኪያ ቅንብብ ውስጥ መግባቱን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ቢከብድም፣ ሦስቱን መሠረታዊ ሥጋቶች ግን አሟልቷል፡፡ ይኸውም የተቀዛቀዘ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዋጋ ግሽበትና የሥራ አጥነት በየጊዜው እየተባባሱ የመጡ ችግሮች ስለመሆናቸው መንግሥት ያምናል፡፡ እነዚህን መሠረታዊ የኢኮኖሚው ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ወጥኗል ያሉት አቶ ማሞ፣ የማክሮ ኢኮኖሚውን ችግሮች በመዋቅራዊና በኢኮኖሚው ዘአርፍ ማለትም በግብርናና በኢንዱስትሪው ብሎም በአገልግሎት መስኩ ላይ ትኩረት የሚሰጡ የለውጥ ፕሮግራሞችን መንደፉን አብራርተዋል፡፡
በመዋቅራዊ ኢኮኖሚው ላይ በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ የሚታዩ መሰናክሎችና ማነቆዎችን ለመፍታት የተደረጉ ማሻሻዎች ለአብነትም የንግድ ምዘገባና ፈቃድ አዋጅን ከመቀየር ጀምሮ፣ በሎጂስቲክስ መስክ የመንግሥትን የሞኖፖል ይዞታ የሚቀይር፣ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የ49 በመቶ ድርሻ በመያዝ በዘርፉ መሳተፍ የሚችሉበትን ውሳኔ ማሳለፉ ከዚህ ቀደም ሲገለጹ የሰነበቱ የለውጥ ጅምሮች ናቸው፡፡ በዓብይ ጉዳይ የውይይት መርሐ ግብር ወቅትም እነዚህ ተነስተዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍምዬ የሪፎርም ዕርምጃው ከሚመለከታቸው መካከል ይገኝበታል፡፡ መንግሥት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ከሚያስተላልፋቸው መካከል አንዱ የሆነው ይህ ዘርፍ እንደሆነ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ መስክ ይመደባሉ፡፡
ሲጠበቅ የቆየው የፋይናንስ መስኩ ነበር፡፡ እሱም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ ለውጭ ዜጎች ክፍት እንደሚደረግ በሕግ ተደንግጓል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዕረፍት ከተበተነበት ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን አክሲዮን መግዛት ብቻም ሳይሆን፣ ባንክ ማቋቋም እንደሚችሉ የሚፈቅዱ አንቀጾች የተካተቱበት የባንክ ሥራ አዋጅን በማሻሻል ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ እንዲህ ያሉት ለውጦች መንግሥት እንደቀድሞው በውጭ መንግሥታት እንደ ከዚህ ቀደሙ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ሳይቀርቡለት በራሱ ተነሳሽነት እየወሰዳቸው የሚገኙ ዕርምጃዎች ስለመሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡
ወደ ነገረ ጉዳያችን ስንመለስ በኢኮኖሚው መስክ መንግሥት አሳሳቢ በተባሉት ጉዳዮች ላይ መፍትሔ የሚሰጡ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝና ይህንኑ በማስመልከትም ሕዝቡን ለማወያየት ማሟሻ ያደረገውን ውይይት በጠቅላይ ሚኒስቴር አዳራሽ አንድ ብሏል፡፡ በዚሁ ውይይትም ከመንግሥት ኃላፊዎችና አማካሪዎች የቀረቡ መነሻዎችን በመንተራስ ጥቂት ተጋባዦች በታደሙበት መድረክ የብዙኃኑን ጥያቄዎች በጨረፍታ የጠቃቀሱ ተሳተፊዎች ተደምጠዋል፡፡
የአገሪቱ 80 በመቶ አምራች ገበሬ ምርት ባላቋረጠበት ወቅት፣ የምግብ ዋጋ ጣሪያ እየነካ የመጣበት ጉዳይ ያሳሳባቸው ታዳሚ ካነሱት ጥያቄ ጀምሮ፣ ከአገሪቱ ሕዝብ 48 በመቶውን የሚወክሉት ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ወደ ሥራ ዓለም የሚገቡበት የሽግግር ጊዜ ላይ ተገቢው ሥራ እንዲሠራ፣ ይህ ወቅት በሕይወት አጋጣሚ አንድ ጊዜ ሊገኝ የሚችል ዕድል እንደሆነ ያመላከቱት ‹‹የኢንተርናሽናል ግሮውዝ ሴንተር›› ተመራማሪውና የኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) ናቸው፡፡ መንግሥት የሥነ ሕዝብ ጉዳይን በተለይም ወደ ሥራው ዓለም የሚገቡትንና ሥራ ቀጣሪዎችን የተመለከተ ፖሊሲ እንዲያስቀምጥ የጠቀዩት ባለሙያው፣ እንደ ሥልጠናው ሁሉ በክህሎት ዘርፍ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ምክራቸውን ለመንግሥት አቅርበዋል፡፡
የባንኮች የብድር አሰጣጥ፣ የግል ዘርፉ ተሳትፎ፣ የቡና ዘርፍ ችግሮች፣ በግብርናው መስክ የተዘነጉ ሥራዎች፣ የግንባታው ኢንዱስትሪ ቸል መባል ወዘተ. ከተሳታፊዎች ትኩረት ይሰጥባቸው ተብለው ከተነሱ ሐሳቦች ጥቂቶቹን ይወክላሉ፡፡ ይህም ሆኖ መንግሥት የሕዝቡን ፍላጎትና ሐሳብ በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች ውስጥ በማካተት ችግሮችን ለመቅረፍ ካሰበ፣ ወደ መስክ በመውጣት፣ ገበሬውና የገጠር ነዋሪው፣ ከተሜው፣ ነጋዴው፣ በልዩ ልዩ ሙያ መስክ የተሠማራው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ሲቪል ሠራተኛውንና ሌላውንም ሐሳብ ማጥናት፣ ዝንባሌውንና ችግሮቹን መረዳት እንደሚጠበቅበት ምሁራን ይመክራሉ፡፡
የሲንጋፖር መሥራችና ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሃሪ ሊ ኩዋን ዪው እንደሚሉት፣ አገር ጥቂቶች የበቁና የነቁ ከላይ ያሉትን ብቻም ሳይሆን፣ ‹‹ለራሱ ክብር፣ ጥረት ለማድረግ ፍላጎቱና ተነሳሽነቱ ያለውን ሕዝብ ትፈልጋለች›› በማለት ግለ ታሪካቸውን ‹‹ዘ ሲንጋፖር ስቶሪ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ያሰፈሩትን ሐሳብ ማውሳቱ ሳይበጅ አይቀርም፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሹማምንትም በዙሪያቸው ከከበቧቸው ጎበዛዝት በተጨማሪ ሕዝቡን ማንቀሳቀስ የሚችሉበት የዓላማቸው ተካፋይ ማድረግ የሚችሉበት ማዕቀፍ መፍጠራቸው፣ እንደ ሊ ኩዋን ዪው ሲንጋፖር ከሦስተኛው ዓለም ወደ አንደኛው ባይሆን እንኳ ወደ ሁለተኛው ዓለም ምድብተኞች ለመሳፈር የሚያስችለውን መንገድ እንደሚያሳጥረው የሚያምኑ አሉ፡፡