Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  የሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ትኩረት በተነፈጋቸው ወቅት አገራዊ ጉዳዮችን የዳሰሰው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ከአሁን ቀደም በክፉም ሆነ በደጉ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በምክር ቤትም ይሁን በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ የሚያደርጋቸው ስብሰባዎች፣ ምን አዲስ ነገር ይዘው ይመጣሉ በሚል ጉጉት የታጀቡ ጥበቃዎች የሚደረግባቸው ነበሩ፡፡ እነዚህ ስብሰባዎች አገሪቱ ካለፈው አንድ ዓመት ቀደም ብሎ አገሪቱን ሰቅዘው ይዘዋት በነበሩ ብጥብጦችና አመፆች ወቅት ሲደረጉ፣ አዲስ ለውጥ ሊያስከትሉ ይችላሉ በሚሉ መላምቶች ሳቢያም ስብሰባዎቹ እስከሚገባደዱና በዓይነትም ሆነ በይዘት ከቀደምቶቹ የማይለዩ መግለጫዎች እስከሚወጡ ድረስ አመፆቹና ብጥብጦቹ ረገብ ሲሉም ተስተውሎ ነበር፡፡

  ስብሰባዎቹ ለእንዲህ ዓይነት ጉዳይ ጊዜያዊ መተንፈሻ ጊዜ መስጠታቸው በመታወቁ የኢሕአዴግ ስብሰባዎች ዘለግ እናደርጋቸው እንዴ የሚሉ መጠይቃዊ ተደምሞዎች በስብሰባው ተሳታፊዎች ዘንድ ይስተዋሉ እንደነበር፣ በቅርቡ ‹‹የኢሕአዴግ ቁልቁለት ጉዞ›› በሚል ርዕስ የስብሰባዎቹን ድባብና ውይይት ማስታወሳቸውን በመጽሐፍ ያስቃኙት፣ የቀድሞ የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴዎች አባል የነበሩት አቶ ብርሃነ ጽጋብ አስነብበዋል፡፡

  ሆኖም እጅግ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር የእነዚህ ስብሰባዎች አጓጊነት እንደ ከአሁን ቀደሞቹ አጓጊ ገጽታ እንደሌላቸውና የስብሰባዎቹ ውጤቶች እምብዛም የሚጠበቁ እንዳልሆኑ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ከዚህ ይልቅ መንግሥታዊ ውሳኔዎች የተሻለ ትኩረት እንደሚስቡ አስተያየት ሰጪዎች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከመንግሥታዊ ውሳኔዎች የበለጠ ቦታ ይሰጠው የነበረው የግንባሩ አቅጣጫ፣ አሁን ላይ ይኼን ያህል መንግሥታዊ ውሳኔዎችን ለመቅረፅ  እያገለገለ እንዳልሆነም ያመላክታሉ፡፡

  ምንም እንኳን በፓርቲው መዋቅርና አሠራር ወደ መንበረ ሥልጣኑ የመጡ ቢሆንም፣ ከቀደመው የፓርቲው ልምድ በተለየ ሁኔታ ያለ ፓርቲው ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የሚሰጡ መንግሥታዊ ውሳኔዎችን በመምራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተለየ ባህል እያመጡ እንደሆነ ይነገራል፡፡

  ምንም እንኳን የፓርቲውን ስብሰባዎች ተከትለው በመግለጫ የሚተላለፉት ውሳኔዎች አሁን እምብዛም ትኩረት እየሳቡ ባይሆንም፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሐሙስ ነሐሴ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ ዓርብ ነሐሴ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ያደረገው ስብሰባ፣ በተለይ ከቀጣዩ የ2012 አገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገመት መጠነኛ ትኩረት የተሰጠው ነበር፡፡

  የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ባደረገው የሁለት ቀናት ስብሰባ ‹‹ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ ሕገ መንግሥቱ ባስቀመጠው መሠረት በ2012 ዓ.ም. የመካሄድ አስፈላጊነት ላይ አቋም በመያዝ፣ እንደ ድርጅትም እንደ መንግሥትም ዝግጅት እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጧል፤›› ሲሉ፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ተናግረዋል፡፡

  ይኼ አቋምና ውሳኔ ከአንድ ወር ተኩል በፊት የተላለፈ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሳምንት በፊት የገለጹ ቢሆንም፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እንደ አዲስ አጀንዳ ተመልክቶ ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ አገራዊ ምርጫው ይካሄድ ወይስ ይራዘም ለሚሉና በሁለት ጎራ ለተከፈሉ ክርክሮች ማሳረጊያ ያበጀ እንደበር በወቅቱ ቢገለጽም፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውሳኔ ደግሞ ለዚህ ማሳረጊያ ማጠናከሪያ የሰጠ እንደሆነም ታስቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ያነሱት የግንባሩ ውህደት ጉዳይ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አጀንዳ እንደነበርም ታውቋል፡፡

  ይኼንን ውህደት በሚመለከት በሐዋሳ በተካሄደው የግንባሩ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ በተቀመጠ አቅጣጫ መሠረት በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተካሄደ የነበረው ጥናት ማለቁ የተጠቆመ ሲሆን፣ ጥናቱ ውይይት እየተደረገበት እንደሆነና ሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች መክረውበት ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተወስኗል፡፡

  ነገር ግን ይኼ ውሳኔ የሚመለከተው የግንባሩ አባል ድርጅቶችን ብቻ ነው ወይስ አጋር ድርጅቶችን የሚለው በግልጽ አልተቀመጠም፡፡

  እነዚህ ውሳኔዎች ወቅታዊውንና የፓርቲውን ቁመና የተመለከተ ጉዳይ ቢዳስሱም፣ ግንባሩ ያሳለፋቸው ውሳኔዎችና የግንባሩ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ያስተላለፉት መልዕክት፣ ግንባሩ በሒደት አዳዲስ ባህርያትን እየተላበሰ እንደሆነ ያሳዩ ናቸው ሲሉ ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡

  ለዚህ አንዱ ማሳያ ተደርጎ የሚነሳው ፓርቲው በጽንፈኛ ብሔርተኝነት ላይ የያዘው አቋም ነው፡፡ በብሔር ማንነት ላይ በማተኮር የተሰባሰቡ ፓርቲዎች ግንባር የሆነው ኢሕአዴግ፣ ከአሁን ቀደም ብሔርተኝነትን ከትምክህትና ከጠባብነት አንፃር ከመገምገም ባለፈ ‹‹ጽንፈኝነት›› የሚል መግለጫ ለብሔርተኝነት ሲጠቀም ታይቶ ባይታወቅም፣ በዚህኛው ስብሰባው ላይ ግን ‹‹የብሔር ጽንፈኝነት›› የሚል ሐረግ የታከለበት ገለጻ ተስተውሏል፡፡ ኢሕአዴግ ከአሁን ቀደም ጽንፈኝነትን በዋናነት ለሃይማኖት አክራሪነት የሰጠው መግለጫ ብቻ ነበር በማለትም ለውጡን የገመገሙ አልጠፉም፡፡

  የሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹የብሔር ጽንፈኝነት ለአገራዊ አንድነትና ለፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ተግዳሮት እንደሆነ›› በውይይት ወቅት አንስቶ እንደመከረበት አቶ ፍቃዱ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊ ማንነትን አስታርቆና አቻችሎ ማስኬድ እንደሚገባ›› በአጽንኦት መነሳቱም የተገለጸ ሲሆን፣ አመራሩ ሳይቀር በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚስተዋሉ ጽንፈኝነቶችን መግዛት እንደሚታይበትና ይኼንንም በፅናት መታገል እንደሚገባ ተገምግሟል ተብሏል፡፡

  ኢሕአዴግ እመሠርተዋለሁ ብሎ የነበረውና እምብዛም የጎላ ስኬት ያልተመዘገበበት ነው የሚባለው ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› በተመለከተ፣ የሚያቀነቅነው ብሔርተኝነት ፅንፍ እየያዘ እንደመጣ ሲተች ቆይቷል፡፡ ይኼ ለዜግነት ፓርቲ ሐሳብ አቀንቃኞችና አራማጆች መነሻ ክፍተትም ሆኖ ለክርክር ሲቀርብ ተስተውሏል፡፡

  በዚህ ሳቢያም ኢትዮጵያዊ ማንነት ሥፍራ ያልነበረውና በቂ ዕውቅና ያልተሰጠው እንደነበር፣ ኢሕአዴግ ራሱ በግምገማው መለየቱን በተደጋጋሚ ሲናገር ቆይቷል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያዊ ማንነትና ብሔራዊ ማንነት ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲጓዙ በማድረግ ረገድ ያለውን ክፍተት ለመሙላት መሥራት እንደሚያስፈልግ በኢሕአዴግ በራሱ ሲነገር ቆይቷል፡፡

  የዚህ ጥረት አንዱ አካል በሚመስል ሁኔታም የብሔር ፅንፈኝነት ይንፀባረቅበታል ተብሎ በተለየው የማኅበራዊ የትስስር ገጾች አንዱ በሆነው በፌስቡክ ገጹ ግንባሩ የሚለጥፋቸው ጽሑፎችና የሚያስተናግዳቸው አስተያየቶች፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትና አገራዊ አንድነትን በሚያሳዩ ቅኝቶች እየቀረቡ ነው ያሉት፡፡ ለአብነት ያህልም ዕውቁ የፖለቲካና የዓለም አቀፍ አስተዳደር ባለሙያው ፍራንሲስ ፉኩያማ ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ካደረጉት ንግግርና የሚዲያ ቃለ መጠይቅ፣ ይኼንን ሐሳብ የሚያንፀባርቅ ምልከታ ተመዝግቦ በግንባሩ የፌስቡክ ገጽ ላይ ተለጥፏል፡፡

  ‹‹ብሔርን መሠረት አድርጎ ከመለያየት የአገሪቱን ኅብረ ብሔራዊነት ባስጠበቀና አገራዊ አንድነትን ከግምት ባስገባ መልኩ የጋራ ማንነት መገንባት እንደሚገባ›› እንደተናገሩ በገጹ በማስፈር ባለሙያው፣ ‹‹የጋራ ማንነት መገንባት ላይ የሚያተኩር የፖለቲካ ሥርዓት ያስፈልጋል፤›› እንዳሉና ይኼም፣ ‹‹ለምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትና ለጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል፤›› ይላል፡፡

  ይኼ ጥረትም ኢሕአዴግ አጉድያለሁ በማለት ራሱን ሲኮንን የነበረበትን የፖለቲካ ዘርፍ ለማረም እያደረገ ያለውን ሙከራ እንደሚያሳይ አስተያየት ሰጪዎች ቢናገሩም፣ በምን ያህል ቁርጠኝነትና ውስጣዊ መግባባት ሊያመጣው ይችላል ሲሉ ውጤቱን ከአሁኑ የሚያጠይቁ አልጠፉም፡፡

  አገራዊ ‹‹ለውጡን›› ተከትለው የመጡ አዳዲስ ችግሮችንም ያሳየው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ፣ ለውጡ ወደፊት እንዲካሄድና በሚፈለገው ደረጃ ውጤት እንዲያመጣ የሚታትሩ እንዳሉ ሁሉ፣ ‹‹በለውጡ የቀድሞውን ይዞ የመቆዘም፣ ሕዝበኝነትና ወላዋይነት በአመራር ደረጃ እንዳሉና ይኼም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አንድ ሆነው በአንድ አቅጣጫና በተመሳሳይ ፍጥነት እንዳይሄዱ ማድረጉን በድክመት ገምግሟል፤›› ተብሏል፡፡

  እዚህ ላይ ግን፣ ‹‹ከድርጅት በላይ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ መቀጠል እንዳለባቸው›› መነሳቱ፣ በድርጅቱ አዲስ አቋምና አመለካከት እየመጣ እንደሚገኝ ማመላከቻ ነው ሲሉም የሚመለከቱ አልጠፉም፡፡ ሆኖም ሕዝቡን የመፈረጅ አዝማሚያም እንደሚታይ የሚናገሩ አሉ፡፡ ለዚህ ማሳያ ነው የሚሉትም በመግለጫው፣ ‹‹ሕዝቡ ነፃነቱን›› አጠቃቀም ላይ ከፍተቶች ይታዩበታል ተብሎ መገምገሙ ሲሆን፣ ይኼም የማያስኬድ አዝማሚያ እንደሆነ ያወሳሉ፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም በግንባሩ አባል ድርድቶች መካከል አንድነትን የሚሸራርፉ፣ ‹‹አንድነትን የሚንዱ›› ነገሮች መታየታቸው እንደተገመገመም ተገልጿል፡፡ አንዱ ድርጅት ሌላው ላይ ጣት እንደሚቀስር የተገመገመ ሲሆን፣ ከዚህ ይልቅ ግን እያንዳንዱ ድርጅት ራሱን ከለውጡ አንፃር እንዲመለከት እንደተደመደመ ተገልጿል፡፡

  በተለይ ከሳምንታት ቀደም ብሎ በሕወሓትና በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) መካከል የነበረው የቃላት ጦርነት በመግለጫ የታገዘ መሆኑ መልካም እንዳልነበረና እንዲህ ባይሆን እንደሚመርጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡ የዚህ መደምደሚያም ዋነኛ ማነቆ ይኼ ሊሆን እንደሚችልም ታዛቢዎች ይጠቁማሉ፡፡

  ሆኖም፣ ‹‹በጋራ በመስማማት ድምዳሜ የተደረሱባቸውን ነገሮች በሁሉም ደረጃ መተግበር ላይ ከፍተቶች እንዳሉት ኮሚቴው ተመልክቷል፤›› ሲሉ አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡  

  ከሁሉም በላይ ግን፣ መግለጫው መልስ ያልሰጠበትና ከአሁን ቀደምም የብዙዎች ጥያቄ የነበረው መሠረታዊ ጉዳይ በግምገማው መነሳቱ ተጠቁሟል፡፡ ይኼም የለውጡ ምንነትና ዓላማ ሲሆን፣ በስብሰባው ከመነሳቱ የዘለለ አጥጋቢ ብይን ተሰጥቶታል አልተሰጠውም የሚለው አልተገለጸም፡፡

  አቶ ፍቃዱ ለውጡ በትክክል ምን ማለት እንደሆነና ዓላማው ምንድነው የሚለው ላይ ግልጽነት መፍጠር እንደሚገባ አቅጣጫ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

  የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ከእነዚህ ጉዳዮች በተጨማሪ የዜጎች የመዘዋወርና ንብረት የማፍራት መብቶች አደጋ ላይ መውደቃቸውን የገመገመ ሲሆን፣ ይኼንን ሕገ መንግሥታዊ መብት ለማስከበር የደኅንነትና የነፃነት ሚዛን በተጠበቀ መንገድ የሕግ የበላይነት እንዲከበር አቅጣጫ መቀመጡ ተነግሯል፡፡

  በሌላ በኩልም በደቡብ ክልል እየተነሱ ባሉ የክልልነት ጥያቄዎች ላይ ውይይት መደረጉን፣ በክልሉ መንግሥትና በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) የተጠናውን ጥናት ተመልክቷል ተብሏል፡፡

  የክልልነት ጥያቄዎችን ለመመለስ በተጠናው ጥናት መሠረት ደኢሕዴን ያቀረበውን የክልልነት መዋቅር፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአዎንታ ተመልክቶ ለተግባራዊነቱ ዕገዛ እንደሚያደርግ ተስማምቷል ተብሏል፡፡

  በአጠቃላይ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባዎቹ ትኩረት በተነፈጋቸው ወቅት፣ በዚህኛው ስብሰባ አገራዊ ጉዳዮችን በስፋት በመዳሰሱ ትኩረት ለማግኘት ቢያስችለውም የበለጠ ማድረግ እንዳለበት ማመላከቻ ሆኗል፡፡  

  spot_img
  - Advertisement -

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -