Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ተነስተው ወደ ቢሮ ሊሄዱ እየተዘጋጁ ከትልቁ ልጃቸው ጋር እየተነጋገሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከውጭ አገር የመጣ የቀድሞ ወዳጃቸውን እቤታቸው ምሣ ጋብዘውት እያወሩ ነው]

  • ከረዥም ጊዜ ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያን እንዴት አገኘሃት?
  • ክቡር ሚኒስትር መንገዱም፣ ሠፈሩም ሆነ ሰው በጣም ተለውጧል፡፡ ከተማው ደግሞ ሕንፃ በሕንፃ ሆኖ ተቀያይሯል፡፡ ለውጥ አለ፡፡
  • ልክ ነህ ብዙ ነገሮች ተለዋውጠዋል፣ ወደፊት ከዚህ የበለጠ ለውጥ ታያለህ፡፡
  • ግን ክቡር ሚኒስትር. . .
  • ገና ከመምጣትህ አቃቂር ላውጣ እንዳትል ብቻ፡፡
  • አቃቂር ሳይሆን እውነቱን እንነጋገር፡፡
  • ምን ይሆን እውነቱ?
  • ክቡር ሚኒስትር ለውጡ ሰውን ያማከለ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡
  • እንዴት ማለት?
  • ለምሳሌ አዲስ አበባ በሕዝብ ተጨናንቃለች፡፡
  • ልክ ነህ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ከሚሠራው ይልቅ ሥራ አጡ ይበዛል፡፡
  • አሁንም ልክ ነህ፡፡
  • ከመንገድና ከሕንፃ ግንባታ በፊት ግን ሥራ ፈጠራ ላይ ቢተኮር ይመረጣል፡፡
  • መንግሥት ለዚህ ከፍተኛ ዝግጅት አድርጓል፡፡
  • ምን ዓይነት ዝግጅት ክቡር ሚኒስትር?
  • በአዲሱ በጀት ዓመት ለሦስት ሚሊዮን ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ነው ዝግጅቱ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ይህ ዝግጅት ግን በጥናት ላይ ሊመሠረት ይገባል፡፡
  • ያለ ጥናትማ ዝግጅት አይደረግም፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ብዙ የዘመቻ ሥራ ውስጥ ስላላችሁ ይህም ዘመቻ እንዳይመስል ብዬ ነው፡፡
  • ካሁን በኋላ የኢኮኖሚ ዕድገታችን የሚለካው በሚፈጠረው የሥራ መጠን መሆኑን እኮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ታዋቂ ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት የሥራ ፈጠራ አንዱ የዕድገት አካል እንጂ ለብቻው ወሳኝ አይደለም፡፡
  • ሰማህ ወዳጄ ካሁን በኋላ ገንዘብ እየተረጨ ጥቂቶች የሚከብሩበት ኢኮኖሚ አይደለም ትኩረታችን፡፡
  • እኔም ይህንን እደግፋለሁ ክቡር ሚኒስትር፣ ነገር ግን ጂዲፒውን የሚያሳድጉ የምርትና የምርታማነት ጉዳዮች ላይ በማተኮር የሥራ ፈጠራን ማጠናከር ይበጃል፡፡
  • ሌላስ?
  • ሌላው ደግሞ ሁልጊዜም በጥናት ላይ የተመሠረቱ የዕድገት ዘዴዎች ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡
  • በል እስቲ እየበላህ ሌላ ጉዳይ እናውራ፡፡
  • ሥራ እንዴት ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ከበድ ቢልም ሕዝብን ማገልገል ደስ ይላል፡፡
  • ልክ ነዎት ግን. . .
  • ግን ምን?
  • ሕዝብን ማገልገል ሲሉ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡
  • ምን ይሆን?
  • መንገድ ላይ የለማኙ ብዛት ያስደነግጣል፣ በዚህ ላይ የትራፊክ መብራት ላይ የተጎሳቆሉ ሕፃናት ያሳቅቃሉ፣ በምሽት ጎዳና ላይ  ታዳጊ ሴቶች ለወሲብ ንግድ መሰማራታቸው ያሳዝናል. . .
  • ይህም  ትልቁ ፈተና ነው፡፡
  • ወደ ኋላ ልመልስዎትና ከእነዚህ ወገኖች በተጨማሪ በየጥጋጥጉ ያለ ሥራ የተቀመጡ ወጣቶች ጉዳይ ደግሞ ያስፈራል፡፡
  • ምኑ ነው የሚያስፈራው ሥራ ልንፈጥርላቸው እኮ ነው፡፡
  • እስከዚያው ድረስ ግን እኔን በጣም ያሳስበኛል፡፡
  • ሥራ ፈጥረን ሁሉንም ነገር እናስተካክላለን፡፡
  • እስኪስተካከል ግን እንደ አንድ ነገር ያስፈራኛል፡፡
  • እንደ ምን?
  • እንደ ቦምብ፡፡
  • የምን ቦምብ?
  • የሚፈነዳ!

[ክቡር ሚኒስትር ከአማካሪያቸው ጋር ቢሮ ውስጥ እየተነጋገሩ ነው]

  • አንተ ሰውዬ ሪፖርቱን ጨርሰሃል ወይ?
  • ትንሽ ይቀረኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምንድነው የሚቀርህ?
  • ሪፖርቱ ውስጥ መካተት ያለባቸው ቁጥሮች ይቀራሉ፡፡
  • ቶሎ አሟልተህ አምጣ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ቁጥሮች በሚገባ መሠራት አለባቸው፡፡
  • ቁጥሮቹ ከእኛው መሥሪያ ቤት አይደል እንዴት የሚገኙት?
  • ክቡር ሚኒስትር ልክ ነዎት፣ ነገር ግን መሠራት ያለባቸው ቁጥሮች ስላሉ ነው፡፡
  • ለምሳሌ?
  • ሥራው ግማሽ ሳይደርስ 80 በመቶ የሚሉ መረጃዎች እየደረሱን ነው፡፡
  • በምን ምክንያት?
  • ቁጥር ከፍ ማድረግ የሥራ ተነሳሽነትን ይጨምራል እየተባለ ነዋ፡፡
  • ከየት የመጣ ልምድ ይሆን?
  • መጨማመር የቢሮክራሲው መለያ እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኛ ግን መታገስ የለብንም፡፡
  • አልሰሙም ለካ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምኑን?
  • የበላይ አካልም ቁጥር ሲያንስ ደስ አይለውም እኮ?
  • በዚህ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ነገር የሚፈለግ አይመስለኝም፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ሪፖርት ሲቀርብ ጨመርመር ማድረግ እንደ ማጣፈጫ ነው ይባላል፡፡
  • አንተ ይህንን ወሬ ከየት አመጣኸው?
  • የቀድሞ አማካሪ ነው የነገረኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሌላስ ምን ነገረህ?
  • ቁጥሮች ተጋነው ሲጨመሩ ከበጀት ላይ ለመቦጨቅም ይረዳሉ ብሎኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አገሪቱን በአጥንቷ ያስቀሯት እንዲህ እየዘረፉ እኮ ነው፡፡
  • እሱ እንደነገረኝ ባይሰርቁም ስም መውጣቱ አይቀርም፡፡
  • በቃ ከሌብነት ውጪ ሥራ አልነበራቸውም?
  • ቦጨቅ እያደረጉ በቴሌቪዥን የኢኮኖሚ ዕድገቱን በማጋነን ማውራት ራሱን የቻለ ሥራ ነበር ብሎኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አንተ ምን አልከው?
  • እኔማ ምን እላለሁ ልምድ በነፃ ሲገኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • ልምዱን ምን ልታደርገው አሰብክ ታዲያ ክቡር አማካሪ?
  • እኔማ ባይበዛም ትንሽ ግነት በመፍጠር አለቃን ማስደሰት ጥሩ ነው እላለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • በዚህ መሠረት ሪፖርትህ ይቀርባል ማለት ነው?
  • ልክ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ወቀሳ ቢቀርብብንስ?
  • ማሳለፍ ነው፡፡
  • እንዴት ተደርጎ?
  • እንዳልሰሙ በመሆን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ ጋር የስብሰባ ሻይ ዕረፍት ላይ እየተነጋገሩ ነው]

  • እንዴት ነህ እባክህ?
  • አለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ፖለቲካው እንዴት ይዞሃል?
  • ልክ እንደ ሰሞኑ ቅዝቃዜ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ነው ምን ተፈጠረ?
  • ምርጫ ቦርድ ካቅማችን በላይ አሥር ሺሕ የፓርቲ ጉባዔ አባላት አምጡ የሚል ሕግ ያወጣል፣ ሌላው ደግሞ ስማችንን ይቀማል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ ለመገኘት እኮ የአባላት ቁጥርና ጥራት ወሳኝ መስሎኝ፡፡
  • ይህች የሴራ ፖለቲካማ አትጠፋንም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ማለት?
  • ለምሳሌ አንድ ፓርቲ ዕጩዎችን ለምርጫ እንዲያቀርብ የሚፈለገው የድጋፍ ፊርማ በሚሊዮኖች ይቆጠራል፡፡
  • ታዲያ አቅምን መጥኖ መዘጋጀት ነዋ፡፡
  • ይህንን እኮ ነው ሴራ የምንለው ክቡር ሚኒስትር?
  • እናንተ ሴራ ጉንጎና ውስጥ ከምትገቡ ሰብሰብ ብላችሁ ለምን አትጠናከሩም?
  • መጀመርያ ኢሕገ መንግሥታዊ የሆኑ የአዋጁ አንቀጾች ሊሻሻሉ ይገባል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • በተናጠል ስትሆኑ እኮ የገንዘብ፣ የሰው ኃይል፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ችግር ስለሚኖርባችሁ እንጂ አዋጁ ለጠንካራ ፓርቲዎች መፈጠር ትልቅ ዕድል ይሰጣል፡፡
  • አዋጁ በዚህ መንፈስ ከሄደ ሕገ መንግሥታዊ የመደራጀት መብትን ይጋፋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኔና አንተ የተነጋገርንበትን ጊዜ ያህል ተገናኝታችሁ ብትነጋገሩ ግን ረዥም ርቀት ትጓዙ ነበር፡፡
  • እንዴት አድርገን ነው ተገናኝተን የምናወራው?
  • ምን ችግር አለ?
  • ፋታ አትሰጡንማ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ከዚህ በላይ መቼ ፋታ አግኝታችሁ ታውቃላችሁ?
  • ክቡር ሚኒስትር በረቂቅ ሴራ ግራ ታጋቡናላችሁ፡፡
  • ወዳጄ ፖለቲካው አልገባችሁም ማለት ነው?
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • ሁልጊዜ በትንሽ በትልቁ ከምታለቃቅሱ አንድ ነገር አድርጉ፡፡
  • ምን እናድርግ ክቡር ሚኒስትር?
  • ሰብሰብ በሉ፡፡
  • ከዚያስ ክቡር ሚኒስትር?
  • በኅብረት ማጥቃትና መከላከል ተማሩ፡፡
  • እኛ ጦርነት አንፈልግም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ማን ተዋጉ አላችሁ?
  • ምን እያሉ ነው ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
  • ሕዝብ ፊት ይዛችሁ የምትቀርቡት ነገር ፈልጉ፡፡
  • ምንድነው እሱ ክቡር ሚኒስትር?
  • የምርጫ ማኒፌስቶ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከባለቤታቸው ጋር እራት እየበሉ እያወሩ ነው]

  • የሚጠጣ ነገር የለም እንዴ?
  • ምን ይምጣልህ?
  • ወይን ይሻለኛል፡፡
  • ወይን ስትል አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡
  • ምንድነው እሱ?
  • የጓደኛህ ሚስት ወይን ከውጭ ማስገባት ጀምራልሃለች አሉ፡፡
  • ከየት አገር?
  • ከአንዱ የአውሮፓ አገር ነው አሉ፡፡
  • የውጭ ምንዛሪ ከየት አገኘች እባክሽ?
  • ለባሏ እኮ ሁሉም ነገር ክፍትፍት ብሎሎታል፡፡
  • በምን አወቅሽ?
  • ወሬ ይደበቃል እንዴ?
  • እሱ እኮ እንዲህ ዓይነት ነገር አያውቅም፡፡
  • ኧረ እባክህ? እሱ እኮ ካሽ እንጂ ማቴሪያል አይቀበልም፣ ዶላር እንጂ ብር ንክች አያደርግም፣ የውጭ አገር እንጂ የአገር ውስጥ አካውንት የለውም፣ በሌላ ሰው እንጂ በእጁ አይቀበልም አይደል የሚባለው?
  • አንቺ ይህንን ያልተረጋገጠ ወሬ ከየት ነው የምታመጪው?
  • አንተ መቼ ይሆን አካባቢህን በንቃት የምትከታተለው?
  • ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
  • ማለት የፈለግኩት ፈዛዛ ነህ፡፡
  • ምን?
  • ፍሌቨሩ አልገባህም፡፡
  • የምኑ ፍሌቨር?
  • የጥቅማ ጥቅሙ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይህንን ሁሉ ፀባይ ከመቼ ወዲህ ነው ያመጣሽው?
  • ዕድሜ ለዘመኑ! ለመረጃ በጣም ቅርብ ሆኛለሁ፡፡
  • ይህ ሁሉ ዳርዳርታ ምን ይሆን?
  • አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡
  • ምን?
  • የሥራ ዕድል ፈጠራ፡፡
  • ለማን?
  • ለእኔ ነዋ!
  • ሥራ ላጡ ወጣቶች ለመፍጠር ነው ላይ ታች የምንለው፡፡
  • ሲባል አልሰማህም?
  • ምን ተባለ ደግሞ?
  • ደግነት ከቤት ይጀመራል ነዋ!

[ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ተነስተው ወደ ቢሮ ሊሄዱ እየተዘጋጁ ከትልቁ ልጃቸው ጋር እየተነጋገሩ ነው]

  • አንተ የክረምት ማጠናከሪያ ተማር ብዬህ አልነበር?
  • ኧረ ዳዲ ትንሽ ልረፍበት ደክሞኛል፡፡
  • ይልቅ ለኮሌጁ ትምህርት ብትዘጋጅ ይሻልሃል፡፡
  • ዳዲ አንድ ነገር ልጠይቅህ ብዬ ነው፡፡
  • ምንድነው እሱ?
  • ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ብር እየተሰጠ ነው አሉ፡፡
  • አንተ አርፈህ ብትማር ይሻልሃል ገና ነህ፡፡
  • እኔም መንቀሳቀሻ ያስፈልገኛል እኮ?
  • ምን ልትሆንበት?
  • አንዱ ሞል ውስጥ በክረምቱ ከጓደኞቼ ጋር ለመነገድ፡፡
  • ምንድነው የምትነግዱት?
  • የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፡፡
  • ሁሉም ነጋዴ ሆኖ ማን  ገዥ ይሆናል ብለህ ነው?
  • ከጎን እኮ ሌላ ቢዝነስ ይሠራል፡፡
  • ምን ዓይነት ቢዝነስ?
  • ዶላርና ዩሮ፣ እንዲሁም. . .
  • ብለህ ብለህ ብላክ ማርኬት ውስጥ ልትገባ?
  • ከፍተኛ ትርፍ እኮ ነው ያለው ዳዲ፡፡
  • በል አርፈህ ተቀመጥ፡፡
  • ዳዲ እባክህ ተባበረኝ፡፡
  • ለመሆኑ ከዶላሩ ሌላ ምን ሥራ አለ?
  • ለሀብታሞችና ለባለሥልጣናት ቅምጦች ማዘጋጀት፡፡
  • ምን አልክ አንተ?
  • ዳዲ የተለመደ ሥራ እኮ ነው፡፡
  • ይኼ የምትለው ነገር በእርግጥ አለ?
  • ኧረ ሌላም ሞልቷል ዳዲ፡፡
  • ምንድነው እሱ?
  • እንቡጥ ልጃገረዶችን. . .
  • ዝም በል ብዬሃለሁ፡፡
  • ዳዲ እኔም ሲባል ነው የሰማሁት፡፡
  • አሁን ከአጠገቤ ጥፋ፡፡
  • እሺ ዳዲ ግን. . .
  • ግን ምን?
  • አንድ ነገር ልንገርህ፡፡
  • ምንድነው እሱ?
  • ይህንን የምልህን ብዙዎች ያውቁታል፡፡
  • ካሁን በኋላ አንተ ስትናገር እንዳልሰማህ፡፡
  • እሺ ዳዲ ግን. . .
  • ግን ምን?
  • እኔ ምን ልሥራ?
  • አርፈህ ተማር፡፡
  • ጓደኞቼ ግን በአጭር ጊዜ ሊከብሩ ነው ዳዲ፡፡
  • ይህንን ክፉ አቋራጭ መንገድ በቅርቡ እናፈርሰዋለን፡፡
  • ከዚህ ቀደም የሞከሩት አልተሳካቸውም ዳዲ፡፡
  • ምን ስለሆነ ነው ያልተሳካላቸው?
  • እነሱም ስለገቡበት ነዋ!
  • ምን?
  • ተዘፈቁበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ ነው? እንዴት? አለቃዬ ዕረፍት የለው፣ እኔንም አላፈናፍን ብሎኛል። ታድለሽ። ታድለሽ? ሥራ ገደለኝ ዕረፍት አጣሁ እኮ ነው ያልኩሽ? ገብቶኛል። ምነው እኔንም...

[ክቡር ሚኒስትሩ የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለተከበረው ምክር ቤት ካቀረቡ በኋላ ከምክር ቤቱ አባላት የሚነሱ ጥያቄዎችን እየተቀበሉ ማብራሪያ በመስጠት ላይ ናቸው]

ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ለሕዝብ ይፋ ያደረገው ነገር ከምን እንደደረሰ ቢያብራሩልን? ምንድነው ይፋ ያደረገው? ጥያቄውን ትንሽ ቢያብራሩት? ከአራት ዓመት በፊት በኦጋዴን አካባቢ ነዳጅ መገኘቱን ለሕዝብ በቴሌቪዥን አብስሮ...

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የካቢኔና የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባል የሆኑ ከፍተኛ አመራር የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያደመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል አግኝቼ ላነጋግርዎት የፈለግኩት። ጥሩ አደረግህ፣ ምን አሳሳቢ ነገር ገጥሞህ ነው? ክቡር ሚኒስትር ተወያይተንና ተግባብተን ያስቀመጥናቸው አቅጣጫዎች፣ በተለይም...