- Advertisement -

የነገው ሰው ትምህርት ራዕይ በመቀጨቱ ከልብ አዝናለሁ

በሉልሰገድ ዓለማየሁ (ዶ/ር)

የአሻራዬን ማኅተም፣ የነገውን ሰው ትምህርት ቤት፣ ፈጥሬ ዳር ሳላደርስ አርቆ ማስተዋል በተሳናቸው ከአቅሜ በላይ በሆኑ ተቀናቃኝ ወገኖች ስለተሰናከለብኝ እጅግ በጣም አዝኛለሁ፡፡ ለምን? እንዴት?

ለሃያ ዓመታት ያህል በተባበሩት መንግሥታት፣ በዩኔስኮ ለትምህርት ሒደት መሻሻል በልዩ ባለሙያነትና በዋና የትምህርት አማካሪነት በጋና፣ ናይጄሪያና ስዋዚላንድ ያገለገልኩ ሲሆን፣ መታመን ባልተቻለ ጥራት የስዋዚላንድን ትምህርት ካሽቆለቆለበት ውድቀት መልሼ አንስቻለሁ፡፡ ለዚህም አገልግሎቴ ከጠቀስኳቸው አገሮች የትምህርት ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተበረከቱልኝ በርካታ ምስክር ወረቀቶችና እማኞች በእጄ ይገኛሉ። እንግዲህ ቀድሞ በአገሬና ቀጥሎም በነዚህ አገሮች የካበተውን ልምዴን ሰንቄ ነው የነገውን ሰው ትምህርት ቤት በማቋቋም ልረዳና ለሌሎችም ምሳሌ ለመሆን 28 ዓመታት በፊት ወደ አገሬ የተመለስኩት፡፡

የነገው ሰው ምህርት ቤት የተሰየመው 1954 .ም. ተወልዶ ለዓመታት በቆየ የሬዲዮ ላይ የልጆች ጊዜ ፕሮግራሜ ነው፡፡ የሬዲዮ ፕሮግራሙ በወቅቱ አዲስና ልዩ የነበረ ሲሆን፣ በአገራችን ባልተለመደ ሁኔታ ከአሜሪካ ድምፅ ባገኘሁት ልምድ ላይ የተመሠረተ አዝናኝ አስተማሪና ፈር ቀዳጅ ዝግጅት ነበር። በዚሁ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ በአገራችን ራስን ማስተዋወቅ የጀመርኩት እኔ ነበርኩ፡፡ ለተወዳጁ ፕሮግራሜ መታሰቢያ ይሆን ዘንድም የነገው ሰውስያሜ ትምህርት ቤት አቋቋምኩ፡፡ ራዕዬ ለትውልድ የሚዘልቅ የነገውን ትውልድ ገንቢ ሆኖ የሚያገለግልና የተማሩ የሰው ልጆች መፍለቂያ ማዕከል እንዲሆን ነበር።

በትምህርት ሥርዓት ሙያ እንኳን ለአገሬና ለሌሎችም አገሮች በተትረፈረፈ ልምድ ክህሎትና ዕውቀት የተጠመቅኩ ነኝ፡፡ ከአገሬ የማስተማር ምስክር ወረቀትና ከአሜሪካ በትምህርት ሙያዎች የባችለርስ ዲግሪ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኮሎራዶ፣ የማስትሬትና በኤዱኬሽን የፕራክቲሺነር ዶክትሬት ዲግሪዎቼን ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዘርን ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ ያገኘሁ ሲሆን፣ ከዩኤስ ዲፓርትመንት ኦፍ ሔልዝ ኤጁኬሽን ኤንድ ዌልፌር (አንደኛ) በትምህርት መጻሕፍት ዝግጅት፣ (ሁለተኛ) በሥርዓተ ትምህርት ግንባታና (ሦስተኛ) በትምህርት አስተዳደር የልዩ ዝግጅቶች ሦስት የምስክር ወረቀቶች አሉኝ፡፡ ቀድሞ በአገሬም ውስጥ ይሁን በኋላ ዩኔስኮ በመደበኝ አገሮች በትምህርቱ ዘርፍ ያልተጠበቁ ውጤታማ ስኬቶች አስመዝግቤአለሁ፡፡

አድጌ በተጠመቅኩበት የትምህርት ሙያዬ ጠንካራው እምነቴ ትምህርት መማር የሁሉም የሰው ልጆች መብት መሆኑ ነው፡፡ በየደረስኩበትም የማውጀውና ሌሎችም እንዲያደርጉት የምገፋፋው መምህር የልጆቹን ሁለንተና ዕድገት ወደ ጎንና ወደ ላይ እንዲመጥቅና ያለምንም እንከን እንዲምዘገዘግ በመስዋዕትነት መሥራት እንዳለበት ነው፡፡ በመምህርነቴም ጽኑ ሃይማኖታዊ ራዕዬ ይህንኑ ዳር ለማድረስ ሲሆን፣ መምህር ሆኜ ከተመረቅኩበት ከሰኔ 24 ቀን 1944 ዓ.ም. ጀምሮ በቅንነትና ሙያዊ ፍቅር የኖርኩለት ግብ ነው፡፡ ዛሬም እንደ ትናንትናና እንደ ነገው መማር የማይችል ልጅ እንዳልተወለደ በአደባባይ ለፋፊ ነኝ፡፡

- Advertisement -

እምነቴ መምህር በማይቆጠበው መስዋዕትነቱለሚበረው ክንፍ ለሚራመደው ድጋፍ ለሚያዘግመው ምርኩዝ ነው” መምህር፣ በዕውቀት እንዲወለዱ ሁሉንም ልጆች ሊደርሱ የሚችሉበት ሥፍራ ሁሉ የሚያደርስና ሕይወትን እንዲሸንፉ እንጂ እንዳይሸነፉ የሚያደርግ ሌላው የሰው ልጆች ፈጣሪ ነው፡፡ ለእኔ መምህርነት መለኪያና መስፈርያ የሌለው የመስዋዕትነት ሥራ ነው፡፡ ደርግ እንደገባ ከአገር ከመልቀቄ በፊት ለራሴ በፈጠርኩት የማዕረግ ስም ርዕሰ መምህር በኮተቤ እንዲከተሉኝ የኮተኮትኳቸው የኮተቤዎቹ ዕጩ መምህራኖቼ በእኔው ዓይነት፣ ሙያዊ እምነት ቀና ያሉ፣ አንጋጠው፣ አሻግረውና አሻቅበው የሚመለከቱ የመምህርን መስዋዕትነት የተገነዘቡ ወጣቶች መሆናቸውን በጊዜው አብስረውኛል፡፡ ከየአቅጣጫው ይጽፉልኝም በነበሩት ደብዳቤዎቻቸው እንደገለጹልኝ በየተመደቡባቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ የሚደነቁ ተዓምራትን ያደርጉ እንደነበር እየተረዳሁ ረክቻለሁ፡፡ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ እንደተላክሁ 1950 .ም. በጥቢው ወራት በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የትምህርት መጻሕፍት አዘገጃጀት ጥበብ ኮርስ ለመውሰድ ዋሽንግተን ዲሲ ተመደብኩ፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም አገሬ በነበርኩ ጊዜ ዘወትር ሰዓቱን በጉጉት እየጠበቅኩ አዳምጠው የነበረውን የቮይስ ኦፍ አሜሪካኑን መርሊን ስቶሪ ቴለር፣ ያለበት ከተማ በመምጣቴ ተደስቼ ወደ ቮይስ ኦፍ አሜሪካ (VOA) ቢሮ ሄድሁ፡፡ እዚያም እንደደረስኩ ወደ ዋናው ኃላፊ ወሰዱኝ፡፡ እሱም በመደነቅ በክብር ተቀብሎኝ ፕሮግራማችን ይህን ያህል ካስደሰተህ ለምን አንተው ራስህ ለአገርህ ሰዎች በቋንቋህ ተርጉመህ አታስተላልፈውም አለኝ፡፡ ይህን ያላሰብኩትን ዕድል በማግኘቴ ፈንድቄ በአገራችን የመጀመርያው የነበሩትን ከ30 በላይ በአማርኛ ቋንቋ በሬዲዮ ላይ የቀረቡ ፕሮግራሞችን ከዋሽንግተን ዲሲ፣ ቮይስ ኦፍ አሜሪካ ወደ አገሬ አስተላልፌያለሁ፡፡ ከዚህና ከበጋው ወራት በኋላ ከአገሬ ለተላኩበት ቀጣይ መደበኛው ሥልጠናዬ ከጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኮሎራዶ ቦልደር ኮሎራዶ ተዛወርኩ።

አሜሪካ ሳለሁ ለአገሬ የሚጠቅም መስሎ የሚታየኝን ሁሉ፣ ያየሁትን፣ የሰማሁትንና ማግኘት የቻልኩትን ይዤ ለመመለስ ማንኛውንም ነገር ከየትም ሥፍራ ተስገብግቤ ከመሻማት አቁሜ አላውቅም ነበር፡፡ ከአሜሪካ ትምህርት ቤቶችም ለአገራችን ሥርዓተ ትምህርት ጥራትና ዕድገት እንዲሁም የተሻለ አወቃቀር የሚረዱ አሠራሮችን ለመቅሰም በየደረስኩባቸው ስቴቶች ሁሉ ሥራ ጉዳዬ ብዬ ትምህርት ቤቶችን ጎብኝቻለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲዬም ያልጠበኩት ዕድል አጋጥሞኝ ትምህርት በሬዲዮና ቴሌቪዥን ኮርስስጃለሁ፡፡ በዚህም ዕውቀት ነው ወደ አገሬ እንደተመለስኩ ዛሬ በአገራችን የሚካሄደውን ትምህርት በሬዲዮ የማቋቋሚያ ዕቅዱን ያወጣሁትና ምናልባት በአየር ላይ ማዋሉን እቀጥል ይሆናል ስል ያልጠበኩት ሌላ አዲስ ነገር የጠበቀኝ፡፡ ያኔ ከውጭ አገር ትምህርት የምንመለስ ሁሉ መንፈሳችን የተነሳሳ ልበ ሙሉ፣ ምርጫችን የተትረፈረፈ፣ ምኞታችን የመጠቀ፣ ልሳናችን ያልተሸበበና የሾረ፣ ካወቅንበት አስበን፣ ፈጥረን፣ ሠርተን፣ ለማደር የምንችልና በሮች ሁሉ የተከፈቱልን ዕድለኛ ትውልድ ነበርን፡፡

ጊዜው በታላቁ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ በገፍ የተላኩልን ፒስ ኮር መምህራን የአገራችንን ትምህርት ቤቶች ያጥለቀለቁበት ወቅት ነበር፡፡ አብሮም ተያይዞ በርከት ያሉ ባለዲግሪ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር የተመለሱበት ጊዜ በመሆኑ የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ በማለት፣ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ክቡር አቶ ገብረ መስቀል ክፍለ እግዚእ፣ ታሪካዊ ዕርምጃ በመውሰድ በውጭ አገር ሰዎች ሥር ይተዳደሩ የነበሩትን ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያውያን እንዲተኩ ያደረጉበት ዓመት ነበር፡፡ ከጣሊያን ወረራ በኋላ የትምህርቱን በአገራቸው መስፋፋት ለማረጋገጥና ዕድገቱንም በቅርብ ለመቆጣጠር በጊዜው ዋናው የትምህርት ሚኒስትሩ ራሳቸው ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነበሩ፡፡

አዲሱን የክቡር አቶ ገብረ መስቀልን ሹመት በመቀበል አሥር ፒስ ኮሮች፣ ከአንድ ሌላ፣ አቶ መላኩ ምሕረቴ ከተባለ እንደእኔው ከአሜሪካ የተመለሰ የቴክኒካልና ሜካኒካል ትምህርት ምሩቅ ጋር ሆነን የቀድሞውን የሚያዝያ 27 ትምህርት ቤቴን ጅማ፣ በአዲሱ አሜሪካዊው አወቃቀር በአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትነት (Comprehensive Secondary School) ለማደራጀት በዳይሬክተርነት ሄድኩ፡፡ ጅማም እንደደረስኩ የጃንሆይ ማረፊያ የነበረውን ግቢ ለማስፋፊያ በመረከብ የቀድሞውን የሚያዝያ 27 ትምህርት ቤት በከፍተኛ ደረጃ በመጠቀ አወቃቀር ጀመርኩ፡፡ ትምህርት ለእኔ በክፍል ውስጥና በጊዜ ገደብ የተወሰነ አይደለም፡፡ ስለዚህ በተጨማሪ ከዘረጋኋቸው በርካታ የመማር ማስተማር ማበልፀጊያ ዘዴዎች አንዱ ከዩኤስአይኤስ አዲስ አበባ ትምህርታዊ፣ አዝናኝና አበልፃጊ ፊልሞችን በመምረጥ እያመጣሁ ዘወትር ረቡዕ ማታ ለተማሪዎቼና እነሱን ተከትሎ በመምጣት የኳሱን ሜዳ ለሚያጥለቀልቀው የጅማ ሕዝብ አሳይ ነበር፡፡ ከጅማ ሕዝብ ያገኘሁት መወደድ ባስከተለብኝ እንቅፋት ሳቢያ ከጥር 1 ቀን 1954 .ም. ጀምሮ አዲስ አበባ እንድዛወር ተደረገ፡፡ ወዲያውም ውሎ ሳያድር በ15ኛው ቀን በትምህርት ባለሥልጣናት ይወደድ የነበረው እንግሊዛዊው የመድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሚስተር ላስት፣ ለመጻሕፍት ዝግጅት ሥራ በጊዜያዊነት በዋናው መሥሪያ ቤት ስለተመደበ እስከ ትምህርቱ ዓመት መጨረሻ ድረስ በቦታው ላይ በተጠባባቂ ዳይሬክተርነት ሾመው ጉለሌ ላኩኝ፡፡

ተልዕኮዬም እንዳለቀ እዚያ በቆየሁበት ጊዜ ያየሁት በማስተማር ላይ የተሸረበ ደባና ወንጀል አልዋጥልህ ስላለኝ በራሴ ጥያቄ ከሐምሌ 30 ቀን 1954 .ም. ጀምሮ ችግሮቹን በማጋለጥ፣ በኃላፊነቱ እኔው እንድቀጥል ጠይቄ ከፋሺስት ጣሊያን ወረራ በኋላ ለትምህርት ቤቱ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ዳይሬክተር ሆኜ ተሾምኩ፡፡ ይህን ዕርምጃም ለመውሰድ ካነሳሳኝ ዋናው ምክንያት መካከል በትምህርት ቤቱ የአንደኛ ደረጃው ትምህርት ቤት ኢትዮጵያውያን መምህራን አብዛኛዎቹ ድጋፍ ዕርዳታና ቁጥጥር ያልነበራቸውና አንዳንዶቹ ጨርሶ እዚያ መገኘት የሌለባቸው ነበሩ፡፡

በሁለተኛ ደረጃው ያሉት የውጭ አገር ዜጎች መምህራን በተለይ እንግሊዛውያኑ ጉዳቱን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ፣ ተማሪዎችን በክህሎት በመለያየት ዕድላቸውን የሚያሰናክል ሒደት የሚከተሉ ነበር፡፡ ከተለያዩ አገሮች የመጡ እነዚህ የውጭ አገር መምህራን የሚበረውንና ያለብዙ ድካም ብሔራዊ ፈተና ያልፍልን ይሆናል የሚያሰኛቸውን ተማሪ ታቅፈው በመኮትኮት ዝቅተኛ የመረዳት ችሎታ ያለውን ተማሪ ግን በክህሎት አለያይተው ብርቱው ይበልጥ እየበረታ ሲሄድ፣ ደካማው ይበልጥ እየደከመና የጠዋት ዕድሉን ረጋሚና በአጭር ተቀጭቶ የሚቀር ነበር።

እኔ ከተሾምሁ በኋላ ግን የእያንዳንዱ ክፍል አመዳደብ ላይ ሁሉም ተማሪዎች ሳይለያዩ አንድነት እየተማሩ እንዲያድጉ ማዘዜን የተቃወሙና ይህ እንዳይሆንና በድምፅ ብልጫ እንዲወሰን የጠየቀው የሁለተኛው ደረጃ ዩኒት መሪ ሚስተር ሬልተን በማን ሕይወት ላይ ነው የድምፅ ብልጫ የምታስወስደው? ባልኩትና ሁሉም ተደባልቆ አብሮ እየተማማረ ይራመድ ቀላቅላችሁ መዝግቧቸው በማለቴ ተበሳጭቶ በማግሥቱ ወደ አገሩ ተሳፈረ፡፡

ብዙም ዝርዝር ሳልገባ በሁሉም መንገድና አቅጣጫ የተማሪው መብት እንዲጠበቅ በማድረግ ተማሪው መምህሩና ድጋፍ ሰጪዎቹ ሁሉም የነቁና በየደረጃው ለትምህርቱ ጥራት የሚደክሙበትን መድረክ አሰፈንኩ፡፡ አስተዳደሩ መልክ ስምና ዝና የተጎናፀፈ እንዲሆንም አደረግኩ፡፡ ከተማሪው እስከ ጠቅላላው መምህራኑና የአስተዳደር ሠራተኞቹ የሚካፈሉበት የአስተዳደርና የግንባታ መረብ ዘረጋሁ፡፡ ከአገር ውስጡም ሆነ ከውጭ አገር መምህራን ጋር ባደረግነው ከፍተኛ ሙያዊ መግባባት የትምህርቱን ጥራት ለሁሉም ተማሪዎች ዕውን በማድረግ ደካማና ማማር የማይችል ወይም በክህሎት ደረጃ በሚል ሰበብ ከሌሎች ተለይቶ የሚሸማቀቅ ልጅ የሌለበት የሁሉም ልጆች ድል ማድረጊያ ትምህርት ቤትነቱን አሳመንኩ፡፡

የተማሪው የደም ሥር የሆነውንም መማር ማስተማር በምንም ምክንያት የዛሬው ወደ ነገ እንዳይተላለፍ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ታጠቅኩ፡፡ እንደ ምመኘው  በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች እንዳየሁትና እንደፈለኩት ትምህርቱን ማበልፀግ ግን አልቻልኩም፡፡ በወቅቱ የትምህርት መሣሪያ እጥረት ስለነበር በዚሁ ሳቢያ የመማር ማስተማሩ ሒደት እንዳይስተጓጎልና እንዳይሰናከል ዕርዳት ፍለጋ በየቦታው መሯሯጥ ጀመርኩ፡፡ ሆኖም ከአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ጽሕፈት ቤት፣ ከትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ላገኝ እችል ከመሰለኝ ሥፍራ ሁሉ በልመና፣ በግዥ፣ በዕርዳታና በተገኘው መንገድ ሁሉ በቂ የማስተማሪያ መርጃ ቁሳቁሶችን የማባዣ ወረቀቶችን፣ ስቴንሲሎችና ቀለሞችን አመጣ ነበር፡፡ ለየዕለቱም ትምህርት በተለይ ለብሔራዊ ፈተና ለሚዘጋጁ ስድስተኛ፣ ስምንተኛና በተለይ 12 ክፍሎች መምህራኑ ጊዜ ወስደው እንዲያዘጋጁና የየዕለቱ ዝግጅቶቻቸውን በማራቢያ እስቴንሲሎች ላይ እየቆረጡ እንዲያመጡልኝ እያደረግኩ፣ ከቀን ሥራ የዘለለውን ራሴ ሌሊቱን በጌስቴትነር ማሽን ለተማሪዎቼ እያራባሁላቸው በማደር ጠዋት ጠዋት ለቀኑ ትምህርት አደርስላቸው ነበር፡፡

ለተማሪዎቼ በክፍል ውስጥ ብቻ የሚሰጠው ትምህርት በበቂነት አርክቶኝ አያውቅም ነበር፡፡ ዘወትር ጠዋት ትምህርት ከመጀመሩ በፊት 15 ደቂቃ የተወሰነ ጸሎት ተደርሶ የሰንደቅ ዓላማ ማውጣት ከተከበረ በኋላ፣ተማሪዎቹ ልቦና መልካም ሥነ ምግባርን የማስረጽ ዓላማ አንግቤ ተማሪዎቼን በምክር አንጽ ነበር፡፡ የሃይማኖት ሰዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱን፣ የዩኒቨርሲቲ ባለ ሥልጣናትና መምህራን፣ ታዋቂ ሰዎች እንደነ ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ከመልካም ግጥሞቹ ጋር፣ ዲፕሎማቶች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ነጋዴዎች ወዘተ. እየመጡ የተማሪዎቼን አስተሳሰብ የምኞታቸውን አድማስ ለማስፋት ትምህርታዊ ንግግር ያደርጉ ነበር፡፡

ትምህርት ቤቱን በልዩ ልዩ ክበቦችና የተማሪዎች መልካም አስተዳደር ያጎለበተ ተማሪው ነግቶ ጠዋት ትምህርት ቤት እስኪደርስ የሚናፈቅና ማታ ግቢውን መልቀቅ እንዲጠላ ያደረገ፣ የመድኃኔ ዓለምን ዕድገት፣ ስምና ዝና የገነባ በአገራችን የመጀመርያውን ፈር ቀዳጅ የተማሪዎች መማክርት (Student Government) በምርጫ አቋቁሜያለሁ፡፡ እነዚህ መማክርት ከሌሎች ለትምህርት ቤቱ ካበረከቱት ብዙዎች አገልግሎቶች እጅግ በጣም ምስጉን በኃላፊታቸው 70 በላይ ረዳትና ወገን የሌላቸውን ልጆች አልብሰው፣ ክብራቸው ተጠብቆ፣ ተመግበውና መጠጊያ አግኝተው የሀብታሙ ልጅ የደረሰበት እንዲደርሱ ዕድል የሰጡ ትናንትና፣ ዛሬና ነገም የምኮራባቸው ልጆቼ ነበሩ፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥት እኔ በአገር ውስጥ ባልኖርም ከነዚህ ተረጂ ልጆች መካከል ከፍተኛ ሥልጣን ላይ በመድረስ እስከ ሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የበቁ እንደነበሩ ሰምቻለሁ፡፡ ወደ አገሬም በተመለስኩ ጊዜ አንዳንዱን በሥልጣን ላይ አግኝቻቸው አንከባክበው ረድተውኛል፡፡

በጠመኔና ጥቁር ሰሌዳ ከማስተማር አልፎ በትምህርት ቤት ደረጃ የተማሪዎች የግል ማኅደር እንኳን መቋቋም ጨርሶ ባልታሰበበት ዘመን፣ የተማሪዎችን የግል ማኅደር መፍጠሩ፣ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ተለምነው በመጡ ሦስት ፋይሊንግ ካቢኔቶችና አስፈላጊዎቹን ፎርሞች ፈጥሬ ኃላፊ መድቤ ለዘለዓለም ሊቀጥል በሚችል የተማሪዎች ግላዊ መረጃ አመዘጋገብ ሥርዓት በደዊ (Dewey System) አቋቁሜያለሁ፡፡

በአገራችንም በቅድሚያ ተማሪዎቼን ዩኒፎርም ያለበስኩ፣ ተማሪዎቼ ጠዋት ጠዋት ወደ ምህርት ቤት ሲመጡና ማታ ወደ ቤት ሲመለሱ የመኪናዎችን አመጣጥ ከፊት ለፊታቸው እያዩ እንዲጓዙ በመምከር፣ ተከታትየም በማስፈጸም፣ የመጀመርያውን ሕይወት አዳኝ የትምህርት ቤት ትራፊክ ያቋቋምኩና የመድኃኔዓለሞቹ ብዬ በመሰየም በአገራችን የመጀመርያውን ዓመታዊ የትምህርት ቤት መጽሔት ማሳተም የጀመርኩ ነኝ፡፡ ብሔራዊውን የኢኤስኤልሲ ፈተናን ማለፍ ወይም አለማለፍ ሳያስጨንቃቸውና የማለፉ ዋናው አገልግሎት ውስኑን የአገር ውስጥ ከፍተኛ ትምህርት ቦታዎች ለማግኘት ብቻ መሆኑን እንዲገነዘቡ ሆኖ ሁሉም ልጆቼ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ለመፈጸማቸው በአገራችን የመጀመርያው የሆነውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መልቀቂያ የምስክር ወረቀት ሰጥቼ ያስመረቅኩ ነኝ፡፡ ልጆቼም በዚሁ በሰጠኋቸው የምስክር ወረቀቶቻቸው ተጠቅመው  በግል ወጪያቸው ከአገራችን ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አሜሪካን ተሻግረው ሌላ ፈተናና የምስክር ወረቀት ሳያስፈልጋቸው በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን መከታተል ችለዋል፡፡

እግረ መንገዳችንን ቀደም ብዬ አንስቼው እንደነበረው በአሜሪካ የማያቸውን እጄን ላሳርፍባቸውና በመማር ልቀስም የምችላቸውን ነገሮች ሁሉ ወደ አገሬ ይዣቸው ለመመለስ የምጥር እንደነበርኩ ቀደም ብዬ ጠቅሻለሁ፡፡ በዚሁ አደኔ ለመድኃኔዓለም ምህርት ቤት አምጥቼ፣ ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ የተዳረሰው ‹‹ከዚህ ከማይሞተው የሰው ልጅ ማደጊያ ሥፍራ ግቡ›› የሚለውን ጥቅስ፣ ያገኘሁት፣ ለመጀመርያ ዲግሪዬ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኮሎራዶ ጥናቴን ስከታተል፣ አዘወትር ከነበረው የዩኒቨርሲቲው ኖርሊን መጻሕፍት ቤት መግቢያ ላይ ከተጻፈው ‹‹Enter Here the Timeless Fellowship of the Human Spirit›› ከሚለው ጥቅስ ነው፡፡

በዚህ ዓይነት የመድኃኔዓለምን ትምህርት ቤት ካገለገልኩ በኋላ ከነባለቤቴ ለድኅረ ምረቃ ዲግሪዎቻችን ወደ አሜሪካ ተመልሰን እንድንሄድ ስለተፈቀደልን ጥር አጋማሹ ላይ 1957 .ም. የትምህርት ቤቱ ኅብረተሰብ ተማሪዎቼ በተለይ የትምህርት ሚኒስትሩን ክቡር አቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ፣ ሚኒስትር ዴኤታውን አቶ ሚሊዮን ነቅንቅ፣ ረዳት ሚኒስትሩን አቶ ታደሰ ተረፈንና ሌሎችም የትምህርት ባለሥልጣናትን እንዲሁም የአዲስ አበባውን ትምህርት ቤቶች ዋና ዳይሬክተር አቶ ወርቄ ደምሴንና ለትምህርት ቤቱ ትምህርት መሻሻል ይደክሙ የነበሩትን የትምህርት ሱፐርቫይዘሮቻቸውን ጋብዞ ተተኪው ዳይሬክተር አቶ ኃይለ ጊዮርጊስ ጣሰው በተገኙበት በግቢው ውስጥ ታላቅ አሸኛኘት ተደርጎልናል፡፡ የአገር ልብሶችና የወርቅ ጌጣጌጥ አብራን ለተጓዘችው ለሁለት ዓመቷ ልጃችን ሳይቀር ሸልመው ሸኝተውናል፡፡

ቀደም ባለው ሕይወቴ ከየትና ከምን ተነስቼ እዚህ እንደደረስኩ ወደ ኋላ መለስ ብለን ብናይ ከመምህራን ማሠልጠኛ እንደተመረቅኩ ከመስከረም 1945 እስከ ሐምሌ 1947 .ም. ድረስ በመምህርነት ሦስት ወር አለታ ወንዶና ሁለት ዓመት በራስ ደስታ ትምህርት ቤት ይርጋለም አስተምሬያለሁ፡፡ በራስ ደስታ ትምህርት ቤት ይማሩ የነበሩት ልጆች በአብዛኛው ለመንግሥት ሥራና ለንግድ ወዘተ. ከልዩ ልዩ የአገራችን ክፍሎች ወደ ይርጋለም የመጡ ቤተሰቦች ልጆች እንጂ በአብዛኛው የሲዳማ ልጆች አልነበሩም፡፡ ከወላይታ ግን በቡድን መጥተው ገብተው የሚማሩና በመቀራረብ የተለያዩ በትምህርትም በማኅበራዊ ኑሮም ስንረዳዳ የነበሩ ብርቱ ታታሪና ጎበዝ ልጆች ነበሩ፡፡

አንድ ቀን 1946 .ም. አንድ 35 ዓመት ግድም የሲዳማ ገበሬ፣ ከከተማ ወጣ ብሎ ከሚኖርበት የእርሻው ሥፍራ ዘጠኝ ዓመት ልጁን አምጥቶ ትምህርት ቤት አስገባ፡፡ ልጁ እንደ አጋጣሚ በዚያን ሰዓት እኔ አስተምርነበረበት አንደኛ ሲ ከፍል ተመድቦ ተላከ፡፡ ልጁ ክፍል ሲገባለት ለማየት የተከተለውን አባት አንተስ ለምን አብረህ አትማርም? ተመልከት እዚህ ከፍል ውስጥ አምስት ዓመት ትንሽ ልጅ ቢኖርም 13 14 15 እ ከዚያ በላይም ልጆች አሉ፡፡ እባክህ አንተንም ላስተምርህ ብየው አባትየውም ከልጁ ጋር መማር ጀመረ፡፡ በጣም የሚገርመው በመምህርነቴ ዘመን ሁሉ ከእሱ በፊትም ሆነ ከእሱ በኋላ እስከ ዛሬ እንደ እሱ ያለባት ትንሽ ነገር ላይ እየተንደረደረ መምህሩን ቀድሞ የሚገኝ ተማሪ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡

በሲዳማ ከቆየሁባቸው ሦስት ዓመታት የመጨረሻውን ሰባት ወር በአቤላ ወንዶና ለኩ ምህርት ቤት በሥራ መሪነት አገልግያለሁ፡፡ እዚያም ፊታቸውን ገና ወደ ትምህርት ያላዞሩትን ሲዳማዎች በልዩ ልዩ ዘዴ ባለመማራቸው በማስቆጨትና በማማለል ወላጆች የፈቀዱላቸው ወንዶች ልጆቻቸውን ብቻ እያመጡ በማስገባት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተማሪውን ቁጥር እጥፍ በማድረግ የሲዳማውን ድርሻ ከነባሮቹ ከከተሜዎቹ ተማሪዎች ጋር እንዲስተካከል አድርጌያለሁ፡፡ በተማሪዎቼ ላይ የቆላ ቁስል ችግር ስለነበረም መድኃኒት ከዋናው መሥሪያ ቤት በማምጣት ብዙዎችን በዚያች አጭር ጊዜ ቆይታየ ለማዳን ችያለሁ፡፡ በዓመቱ መጨረሻ ግን ከመስከረም ወር 1946 .ም. ጀምሮ አዲስ አበባ ደጃዝማች ወንድራድ ትምህርት ቤት ተዛወርኩ፡፡ እዚያም ምንም ያህል ሳልቆይ ከመጋቢት 1 ቀን 1948 .ም. ጀምሮ በትምህርት መጻሕፍት አዘጋጅነት ተቀባይነት በማግኘት ፖይንት ፎር በትምህርት ድርጅት ውስጥ ሥራ ጀመርኩ፡፡ እዚህም፣ ከጠላት ወረራ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በአገራችን በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረቱ በዕድሜ፣ በክፍልና በደረጃ የተዘጋጁ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን መጻሕፍት ከመጋቢት 1947 .ም. ጀምሮ እያዘጋጀሁ ሥራ ላይ አውያለሁ፡፡

እነዚህም አንደኛ ክፍል ለገባ ትምህርት ጀማሪ ሕፃን፣ ትምህርቱን በጀመረ በሦስተኛው ወሩ ፊደልን ለይቶ አማርኛን ማንበብ የሚችልበትን ‹‹አረንጓዴው ጓደኛዬ›› የተባለውን መጽሐፍ፣ ሁለተኛው የንባብ መጽሐፌን ለሁለተኛ ክፍል፣ ሦስተኛው የንባብ መጽሐፌን ለሦስተኛ ክፍል፣ ዛሬ የአማርኛ ፊደላት (ሆሄያት) የእጅ አጻጻፍ አሥጊና መለየት በማይቻሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው እንደገና አሁን 60 ዓመት በኋላ መልሼ ያሳተምኩት ከሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታና ከአሜሪካዊው የቋንቋዎች ሊቅ፣ ሚስተር ኦወን አር ላቭሌስ ጋር በመቀናጀት ያዘጋጀሁት የጽሕፈት ፋና መጽሐፍ ለቀላል ፈጣንና ቀልጣፋ የአማርኛ ፊደላት አጻጻፍ አንዲረዳ የተዘጋጀ (አሁን 60 ዓመት በኋላ እንደገና ያሳተምኩት) እንዲሁም ለኅትመት ተዘጋጅቶ የቀን ብርሃን ለማየት መጠባበቅ ላይ ያለውን የጅማው ምንባቤን አዘጋጅቻለሁ፡፡ ይህ መጽሐፍ አሁን ዝግጁ ሆኖ ለአራተኛ ወይም ለአምስተኛ ክፍል ማገልገል ስለሚችል ፈላጊ ለማሳተም መጠየቅ ይችላል።

ምን ይደረጋል እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ነገር እነዚህ ለዓመታት ያገለገሉ መጻሕፍት ያለአግባብ ተቀጭተዋል፡፡ ምክንያቱም በእያንዳንዱ መጻሕፍት ውስጥ ባሉት እንደ ሌሎቹ የዚያን ዘመን የነበሩ መጻሕፍት ሁሉ ርዕሰ ብሔራችንና የትምህርት ሚኒስትራችን የነበሩት የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ይለ ሥላሴ ፎቶግራፍ ስለነበረ ብቻ የደርግ ጊዜ የትምህርት ሙያ ማይማን ባለሥልጣናት በቀላሉ ጃንሆይ ያሉባቸውን ገጽ ብቻ ቀዶ በማውጣት ፋንታ እነዚያን በጥናትና ምርምር ተደክሞባቸውና ከፍተኛ የአገሪቱ ሀብት ፈሶባቸው በደረጃ ተመጥነውና ተሰልተው የተዘጋጁትን የማስተማሪያ መጻሕፍት ሁሉ አቃጥለዋቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ይሆናል ለብዙ ጊዜ የትምህርቱ ሒደት ቀኝ ኋላ ዞሮ የትምህርት ጥራት አሥጊ ደረጃ ላይ ደረሰ የተባለው፡፡

ለዚሁም ይሆናል ከደርግ ዘመን በኋላ የትምህርቱ ጥራት ማሽቆልቆሉና በጠበቁት ጊዜ የልጆቻቸው ፊደልን ለይቶ ማንበብ አለመቻል ወላጆችን በተለይም የገበሬዎችን ቤተሰቦች አስጨንቆ የነበረው፡፡ ይህንኑ አሳሳቢ ጉዳይ ይዤ ነው 1993 .ም. በአገሪቱ የየክልሉ የትምህርት ሁኔታ እንዲገመገም በዓለም ባንክ በተዋቀረው ቡድን ውስጥ የኔዘርላንድን ኤምባሲ ወክዬ ወደ አማራና ትግራይ ክልል ተጉዤ የነበረው፡፡ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ወቅቱ የአማራው ክልል ክልል አቀፉን የትምህርት ኮንፈረንስ እያካሄደ የነበረበት ጊዜ ስለነበር ዕድሉን በመጠቀም አንድ ልጅ ትምህርት ቤት ገብቶ ፊደልን ለይቶ ማንበብ የሚችለው መቼ ነው በማለት ጠቅላላ ጉባዔውን ጠይቄ ሊቀመንበሩ ያለማመንታት ሦስተኛ ክፍል ላይ ነው የሚል መልስ የሰጠኝ፡፡ ከተልዕኮዬም እንደተመለስኩ ለዚህ ችግር መፍትሔውን ዘርዝሮ በማሳየት ለመርዳት፣ መፍትሔውንና ዘዴውን ከመስከረም 1994 .ም. ጀምሮ የትምህርት ሚኒስቴርን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዩኔስኮ ሥር ለስዋዚላንድ መንግሥት የትምህርት አማካሪ ሆኜ አምጥቼ የነበረውን ዕፎይታ እንዲሁም ቀደም ብሎ ካበረከትኳቸው የትምህርት ሙያ አስተዋጽኦዎቼ መካከል ጠቃሚ መረጃዎቹን በማቅረብ በአገራችን ላይ ለመድገም ደጋግሜ ጠይቄ የነበረው፡፡

ያም ሆነ ይህ የነገውን ሰው ትምህርት ቤት ሳቋቁም መምህራኖቹን ያዘጋጀሁትና ያደራጀሁት ርዕሰ መምህርነትየኮተቤዎቹ ልጆቼን ባሠለጠንኩበት የማስተማር ዘዴ ልዩና ሃይማኖታዊ በማድረግ በዚያው የማስተማር ጥበቤ ሁለንተናቸውን ለሚያስተምሩት ለነገው ሰው ልጆቹ ለሚያቅዱት ሁሉ ድል ለሚፈጽሙት ሁሉ ሊቅነት እንዲያጎናፀፉ አድርጌ ኮትኩቻቸው ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል በማንኛውምና በሆነው መንገድ ሁሉ የመበልፀግ አቀበት ብቻ በታያቸው ተቀደምኩና ተገፍቼ “የነገው ሰው ልጄንተነጠቅኩ፡፡ ነጣቂዎቹ ልጄን ግጠው አጥንት ሲቀረው ጥለውት ወጡ፡፡ የተከተሏቸው በጎ አሳቢዎች ምንም ያህል ገንዘብ አፍሰው መልሰው ለማንሳት ቢጥሩም፣ ሙያዊው የትምህርት ሒደት በቀላሉ በቀለም ታድሶ ተመልሶ እንደሚያበራ ቁሳዊ ነገር ስላልሆነላቸውየነገው ሰው” ተጣድፎ መቃብር ገብቷል፡፡

ይኸው እንግዲህ እንደነአሜሪካኑ የል ወይም ሐርቫርድ ወይም እንደ እንግሊዙ ኦክስፎርድ ወይም ኬምብሪጅ ይሆናል ብዬ የጀመርኩት የነገው ሰው ተክሌ ድርቅ በልቶት በሚያሳዝን ሁኔታ ከመሬት ሳይነሳ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ከመጀመርያው ጀምሮ ወዳጆቼም ሆኑ ጓደኞቼ ለምን ከሰህ መብትህን አታስከብርም በማለት ሊገፋፉኝ ሞክረው ነበር፡፡ ምንም እንኳን የተወለድኩት ጥቃትን እምቢኝ ከሚሉ ንፁህ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ቢሆንም፣ ተቀናቃኝ ቀማኞቼን ከነክፉ ሥራቸውና እኩይነታቸው እያወቅኩና እየተጎዳሁነገር ትደር/ሀቡልቱ ዱቢን” በሚለው ባደግኩበትና ከሁሉ በላይ ሰላምን በሚወደው የጅማ ታላቅ ሕዝብ መላ ሁሉን ትቻለሁ። ነገሩን መለስ ብዬ ሳስበውም ከወለድኩትና ከምወደው ልጄ ከነገው ሰው ጋር እንዴት ፍርድ ቤት እቆማለሁ?

ከላይ የዘረዘርኩት የተብራራ ሐተታ በትምህርቱ ዘርፍ ያካበትኩትን ልምድና ያለፍኩበትን ውጣ ውረድ ለማሳየት እንደ መንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ ነው። ከኢትዮጵያም ዘልቆ በአኅጉራችን የመማር ማስተማር ሒደት ውስጥ የምኮራበትን አስተዋጽኦ ያበረከትኩት ገንዘብንማካበት ሳይሆን ለሙያው ባለኝ ጥልቅ ፍቅርና አክብሮት ነው። አሁንም ከምሥረታው አንስቶ በነገው ሰው ትምህርት ቤት ላይ ያዋልኩትን ጊዜ መዋዕለ ንዋይና ዕውቀት እንዲሁም የደረሰብኝን በደል እንደሚከተለው አብራራለሁ።

የነገው ሰው እንዴት ተቋቋመ?

  1. ፕሮጀክቱን ነድፌ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በስሜ አውጥቼ ዕቅዱ የሚያዋጣ መሆኑን ከሰኔ 1988 እስከ ጥቅምት 1989 .ም. ድረስ የታዋቂና ታላላቅ ሰዎች ኮሚቴ አባላት አዋቅሬ በማስጠናት ዘላቂና አዋጭነቱን በጋራ ሆነን በመምከር በጥቅምት ወር 1989 .ም. በተጠራና በስኬት በተከናወነ የምሥረታ ጉባዔ በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አቋቋምነው፡፡ የነገው ሰው ሲቋቋም የወጣውን አጠቃላይ ወጪ ያወጣሁት በግሌ ሲሆን፣ አብረውኝ ለደከሙት የኮሚቴ አባላትም ይሁን ለእኔ በአክሲዮን መልክም ይሁን በጥሬ ገንዘብ ያሰብነው ጥቅም አልነበረም፡፡ በወቅቱ ነዋሪነቴ በእንግሊዝ አገር ስለነበር ቤተሰቦቼን እንግሊዝ ጥዬ ለወራት ጥናቴን ሳካሂድ የቆየሁት በዋቢ ሸበሌና በሆቴል ዲአፍሪክ በግሌ ወጪ ሲሆን፣ ወጪውን ከሒሳብ አላስገባሁትም፡፡ ጠቅላላ ድካሙበገንዘብ መተመን አይቻልም
  2. ገና ሐሳቡ ሲጠነሰስ ጀምሮ ሥራውን በአክሲዮን ማኅበርነት ለማዋቀር መፈለጌን የነገርኳቸው ቤተሰቦቼ ፍላጎቴን የሰሙ ወዳጆቼና ጓደኞቼ ኧረ ተው ዛሬ በአገራችን ‹‹አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አያዋጣም››፣ በአነስተኛ ደረጃም ቢሆን በራስህ ጀምረህ ብትስፋፋ ይሻላል ሲሉኝ ሐሳባቸውን ባለመቀበልና ደርግ ሲገባ የተባበሩት መንግሥታትን ለማገልገል አገር ከመልቀቄ በፊት በወገኖቼ ላይ የነበረኝን ተስፋና እምነት በመሰነቅ በዋናነት የቀድሞ ተማሪዎቼንና የትምህርት ሙያ ባልደረቦቼን የዕድሉ ተካፋይ እንዲሆኑ በመፈለግ ማኅበሩን በአክሲዮንነት በማቋቋሙ ጸናሁ፡፡  ሲጀመር ድርጅቱ የተቋቋመበት፣ ምሥረታው የተካሄደበትና ትምህርት ቤቱ ሥራ የጀመረው በስሜ በነበረው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሲሆን፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በራሴ ገፋፊነት የድርጅቱ ደንብ የሚፈቅደውን የፈጣሪነቱን ጥቅምና ካሳ ሳልፈልግ ከግሌ ስም ወደ አክሲዮኑ ስም እንዲዛወር ሳደርግ ተዛውሮ ምንም ያህል እልፍ ሳይል ይቸረኝ የነበረው ምክር ሁሉ በብዙ እጥፍ ምን ያህል እውነታ እንደነበረው መረዳት ጀመርኩ፡፡

 ድርጅቱ በብዙ ድካም ወጪና ሙያዊ ድጋፍ እያበበና መልክ እየያዘ ሲመጣ የአክሲዮን አባላት የሆኑም ያልሆኑም ትምህርት የራሱ የሆነና የተለየ መመሥረቻ፣ መገንቢያና መጠንከሪያ ሙያ ያለው መሆኑን ያልተገነዘቡ፣ ድርጅቱን ቢረከቡት ዛሬ ያደረሱበት የውድቀት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ጨርሰው ያላለሙ በጭፍናቸው ሲያስቡት ግን ሙያው የሚበለፅግበት የወርቅ ማዕድንና ገንዘብ ተትረፍርፎ የሚታፈስበት ቢዝነስ ነው ብለው ያመኑ ግለሰቦች ገና በእንቡጥነቱ ሊቀሙት  ብድግ አሉ፡፡

ሁኔታው አስከፍቶኝና ዛሬ የደረሰበት ውድቀት በሩቁ ቢታየኝም፣ የመጠላለፉና የመቀዳደሙ የተንኮል ባህሪ የማላውቀውና ከአስተዳደጌ፣ ከግል ባህሪዬና ካለኝ የሙያ ክብር ጋር የሚፃረር በመሆኑ የእነሱን ተንኮልና ሸር መቋቋም በሄዱበትም የክፋት ጎዳና መጓዝ አልቻልኩም፡፡ በዚህም ሳቢያ እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 4 Dec. 1998 ለቦርድ ሊቀ መንበሩ ለክቡር አቶ ሺመልስ አዱኛ የስንብት ደብዳቤ አቀረብኩ፡፡ ከመልቀቄ በፊት ግን ለመጨረሻው ጠቅላላ ጉባዔ ያደረግኩት ሁለመናዬን ሰጥቼው የነበረውን ድርጅቴን ቀሚ ስለመጣበት በደል እንዳይደርስበት በመጸለይና የተሸረበበትን ተንኮል ውጤት በመፍራት በትንቢት የአደራ ጥሪዬን ለጠቅላላ ጉባዔው በንባብ አሰምቻለሁ።

በዚሁ ማስጠንቀቂያዬ ውስጥ ያቀረብኩት ዋናው ፍሬ ነገር ድርጅቱን ከተሰናበትኩ በኋላ እኛን ለመተካት የሚመረጠው ተተኪ ቦርድ ቢያንስ፣ የድርጅቱን ህልውና የሚጠብቅ፣ ዝናውን፣ ዕድገቱንና ዘላቂነቱን የሚያረጋግጥ አባላትና በኃላፊነት የሚመሩ ሰዎች ያቀፈ እንዲሆን አደራ ብዬ የነበረበት መልዕክቴ ነበር፡፡ እንደተመኘሁት ሳይሆን ቀርቶ እንደፈራሁት ማኅበሩ ዛሬ የተቋቋመለት ዓላማና ግብሩ እስከነራዕዩ ሞተ፣ የስሙ ሰሌዳ ብቻ አልባሌ ስርቻፍራ ላይ ተወሽቋል፡፡ የተለያዩ ሰዎች የድርጅቱን ሙያዊ አቋም ተጓዳኙን የተገልጋይ ቁጥርና ሁለንተናዊ የሙያ ኃይልና የአገልግሎት ሙያዊ አቅሙን ሸርሽረው ለውድቀት አደረሱት፡፡

እንደዚሁም የተያያዘውን ተጓዳኝ የገቢ ኃይሉን በራስ ወዳድነት በማያስፈልግ ወጪ እንዲሟጠጥ በማድረግ ድርጅቱን አሽቆልቁለው ካወረዱት በኋላ ሲለቁ የናዱት ዋናው የሙያ ግንባታ በመምህራን፣ በተማሪዎች የማስተማር መማሩ ሙያዊ ጥበብ ተመልሶ ታድሶ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል እንደ መርካቶ ንግድ ቤት ስላልሆነ ውድቀት መከራና ዕዳ ዕጣ ፈንታው ሆኗል። 

ለዚህ ነው ሀብታቸውን ጭምር በማፍሰስ የወደቀውን የነገውን ሰው ተረክበው ከዕዳ ለማውጣትና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ እነ አቶ ጴጥሮስ ተክሉና ሐጂ አቡበከር ሳቢት የደከሙት፡፡ ለዕዳው ጊዜያዊ መፍትሔ ቢያገኙለትም ከላይ በተሰጡት ምክንያቶች ሙያዊ ሥሩ ስለ ደረቀ ማገገም አልተቻለም፡፡ የገንዘብ ኪሳራው በዚህ ዓይነት በገንዘብ ቢታገምም ዋናው የተናደው ሙያዊ አገልግሎቱ በመምህራንና በመማር ማስተማር ሒደት የተናደው ስምና ዝናው በቀላሉ የሚመለስ አልሆነም፡፡  

  1. መለስ እንበልና እንይ፤ ከመነሻው ጀምሮ የጽሕፈት መሣሪያና ማንኛውም የጸሐፊ አገልግሎት ክፍያ እንዲሁም የመስተንግዶዎች ወጪ ይከፈል የነበረው ከእኔው ኪስ ነበር፡፡ ቤቴን ከተረከብኩ በኋላ ከገንዘብ ወጪውም በተጓዳኝ መኖሪያ ቤቴ በጽሕፈት ቤትነትና ለቦርድ መሰብሰቢያነት አገልግሏል፡፡
  2. የነገውን ሰው ትምህርት ቤት ለማቋቋም በስሜ አውጥቼ የነበረውን የኢንቨስትመንት ፈቃድ ቁጥር ኢአባ-ኢፈ1827/89 ሐምሌ 30 ቀን 1989 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረው ፈቃድ ተሰርዞ ወደ ማኅበሩ እንዲዘዋወርልኝ፣ መሥራች የቦርድ ሊቀ መንበር ከነበሩት ከክቡር አቶ ሺመልስ አዱኛ ጋር ሆነን ለኢንቨስትመንት ባለሥልጣን አመልክተን፣ ድርጅቱን ለማቋቋምህ ቢያንስ በስምህ 30 በመቶ ድርሻ ካልተያዘ በስተቀር እስካሁን በስምህ የቆየውን ፈቃድ ወደ አክሲዮን ማኅበሩ ማዘዋወር አይቻልም ተባልን፡፡ እኔም ይህን ባለመፈለጌና እንደ ማንኛውም አባል አንደኛው ሰው ብቻ መሆንና ዓላማዬ ከሌሎች አባላት የተለየ ጥቅም እንዳይኖረኝ በገዛ ፈቃዴ በንፁህ ልብና በቀና መንፈስ ከክቡር አቶ ሺመልስ አዱኛ ጋር በመመካክር የፕሮጀክት ጥናቱን እንደገና አሻሽዬ አዲስ ማመልከቻ ለኢንቨስትመንት ቢሮ በማቅረብ ፈቃዱ የእኔ ተሰርዞ አዲስ ፈቃድ በማኅበሩ ስም እንዲተካ ተደረገ፡፡
  3. እንዳለ ሆኖ የነገውን ሰው ለመፍጠር ለፕሮጀክት መቅረፅና ማዘጋጀት፣ መምህራንን ቀናት ከፈጀ በእጅ ልቅም (Hand Picked) ምልመላ በኋላ በተለየ መስዋዕትነትና የማስተማር ፍቅርን በማሠልጠን፣ ማኅበሩን ለማቋቋም፣ የወጣውን ወጪ እንዲሁም የነገው ሰው ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ ያፈሰስኩትን መዋዕለ ንዋይ በመጠኑ እንደሚሸፍን ታምኖ፣ ማኅበሩ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ በባጀትነት እየተንከባለለ የቆየውና ይከፈልሃል ተብሎ የነበረው 1990ዎች መግዣ ዋጋ ብር 250,000 በቸልተኝነት ሲንከባለል ቆይቶ እስከ ዛሬ ሳይከፈለኝ ኖሯል፡፡
  4. የነገው ሰው ስሙ ከጽንሰ ሐሳቡ ጀምሮ እስከ ማጎልመሻውና ማጎልበቻው ድረስ ማለትም መመሥረቻው፣ ድርጅቱን ማቋቋሙ፣ የማደርጀቱና ለሙያዊ አገልግሎት የማብቃቱ ወጪ በሥነ ሥርዓት ተማሪዎችንና መምህራንን የማሠልጠን ድካሙ፣ የድርጅቱ ዓርማ፣ ማኅተሙና ከዚያ ሥር የተቀመጡት በሁለቱም ቋንቋዎች የተጻፉት ጥቅሶች፣ የመምህራንና የተማሪዎች የሙያና አስተዳደር ሕጎች ደንቦችና ፎርሞች እንደዚሁም የመዝገብ አያያዙ ሥነ ሥርዓት (The Making of an Institution) ወዘተ. በእኔ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ዋጋቸው በድርጅት ማቋቋም ዋጋ ተመን ቢሰላ ምን ያህል ይሆን?
  5. ቀደም ሲል እንደገለጽኩት በእጅ ልቅም በብዙ ጥንቃቄና ድካም የተመረጡትን መምህራን የተለዩና ለሙያቸው መስዋዕት የሚሆኑ በማድረግ ድርጅቱን እንዲገነቡ፣  “The Making of a Master Teacher” የተባለውን የማሠልጠኛ ልዩ መጽሐፍ አዘጋጅቼ ኮርስ በመስጠት አሠልጥኛቸዋለሁ፡፡ ኮርሱን አደራጅቶ ለማሠልጠን ሆነ ለመጽሐፉ ዝግጅት ለተበረከተው ሙያዊ አገልግሎት የታሰበልኝም ይሁን የተከፈለኝ ምንም ነገር የለም፡፡ መለስ እንበልና ድርጅቱን  ተረክበው የነበሩት የትምህርትን ሙያዊ ሒደትና አወቃቀር የማያውቁ ሰዎች የሥልጡንና ዕንቁ መምህራኖቼን አያያዝ ባለማወቃቸው ምክንያት መምህራኑ ተደናግጠው እየተጣደፉ ከሥራ መልቀቃቸው የመጀመርያውንና በቀላል የማይታገመውን የድርጅቱን ውድቀት አስከትሏል።
  6. በክቡር አቶ ሺመልስ አዱኛ የሚመራው ቦርድም ሆነ እኔ የነገውን ሰው መሥርተን በእግሩ ለማቆም መስዋዕትነት ከፍለን ድርጅት ገንብተናል፡፡ ለቀን በምንወጣበት ጊዜ ያለምነውና የፈጠርነው ልዩ ምርጥና ዝነኛ የማይሞት የሰው ልጆች ማደጊያ የትምህርት ማዕከል ሆኖ ለምዕት ዓመታት ያለማቋረጥ እንዲቀጥል ነበር እንጂ እንደዚህ በአጭሩ በራስ ወዳዶች እንዲቀጭ አልነበረም፡፡
  7. ቀደም ሲል እንዳወሳሁት ሰዎቹ ልጆቻቸውን ምህርት ቤት ካደረሱ በኋላ በማሳደም በተለየ ጥራትና ምጥቀት ለነገው ሰው ሠልጥነው የነበሩትን የትምህርቱ ጎምቱ ባለሙያ መምህራን እንደ ተራ የቢሮ ጸሐፊዎች በማንገላታታቸው ሥልጡን መምህራኑ በደልና ማዋከቡን መቋቋም ባለመቻላቸው እየለቀቁ ወጡ፡፡ ሌሎችም እየተፈራረቁ በመተካካት ትምህርት ቤቱ ወደ ላይና ወደፊት ማደጉ ቀርቶ፣ በሁለንተናው ወደ ታች እያቆሽለቆለ በመሄዱ ዛሬ በሌላ ምህርት ቤት ተወርሶ በታላቅ ተስፋ ጀምረነው የነበረው የማይሞተው የመማሪያ፣ ማደጊያና መጎልመሻ ሥፍራ እንዲሆን የፈጠርነው ትምህርት ቤታችን በአጭሩ ተቀጭቷል፡፡ በለቀቅንበት ጊዜ ይህ እንዳይመጣ እኛን የሚተካው አዲስ ቦርድአባላቱ በአመራረጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግበት ጉባዔውን ተማጽኜ ነበር። የምክሬ አለመከበርና የአዲሱ ቦርድ በአበል ከመጠንከር ውጭ በትምህርት ሙያ አቋም የሌለው በመሆኑ በመዝለፍለፉ፣ ሐምሌ 10 ቀን 1992 .ም. በወጣው የዩኒቲ ኮሌጅ ዕለታዊ አዲስ ጋዜጣ፣ ‹‹የነገው ሰው አክሲዮን ማኅበር ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› በተባለው ሪፖርት፣ የታተተው እንዳይከሰት ስጸልይ የነበረው ሳይሆን ቀርቶ የነገው ሰው ወደ ውድቀት ማሽቆልቆሉን በመቀጠል አሁን እስከነጭራሹ ህልውናው ለጊብሰን አካዳሚ መሸጡ አሳዝኖኛል፡፡

በእኔ ላይ ከደረሰው በደል እጅግ የሚያሳዝነው ከፈጠርኩት ማኅበር ስሜን ጨርሶ ለመፋቅ፣ የተፈጸመው ሕገወጥ ደባ ነው። እንደ ተራ ማኅበርተኛ እንኳን ተራ አባል በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ አሟልተን ውልና ማስረጃ ከእነ ባለቤቴ ቀርበንና  በአባልነታችን በሕግ ፊት ፈርመን የያዝነውን ኢምንት የሆነችውን ከዋጋ የማትገባ አክሲዮናችን ያለምንም ሕጋዊ መሠረት ተሰርዟል፡፡ ይሆናልም ብለን፣ እንኳንና በዕውን በህልም ያልጠረጠርነው ከማኅበሩ ውስጥ የስማችን መጠበቂያ ትሆናለች ያልናት በሕግ ፊት ፈርመን የያዝናትና የተሰረዘችብን አክሲዮናችን ጉዳይ በጣም አሳዝኖናል፡፡ አሁን ያለው ቦርድ መብታችንን በመጠበቅ ማኅበርተኝነታችንን መልሶ በማክበር ለኛም ያለውን ውክልና ቢያሳየን መልካም ነው።

ሕጋዊነታችንን በቀላሉ ለማገናዘብ እንዲቻል የመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ተራ ቁጥር 88 እና 89 የባለቤቴና የእኔ ስሞች ሲሆኑ፣ የመመሥረቻው ጽሑፍም ውስጥ በተራ ቁጥር 88 እና 89 ላይ መሥራቾች ሆነን ገብተናል፡፡ እዚያው ውስጥ ገጽ 3 ላይ ለተከፈለበት አክሲዮኖች ዝርዝር ውስጥ ተካተናል፡፡ በሕግና ሥነ ሥርዓት አባል የሆኑትን ሰዎች ከአባልነት መሰረዝ ወንጀል አይደለምን

በደላችንን በሰብዓዊነትና ማስተዋል በሰፈነበት ፍርድ የሚመለከተው ሁሉ እንዲያጤንልን እንዲሁም የነገውን ሰው በታላቅ ሙያዊ ሥነ ምግባርና ኃላፊነት በመፍጠርና በማጎልመስ ያደረግነው ውለታ ሌላው ቢቀር በአክሲዮናችን መመለስ ስማችን ከማኅበሩ ጋር ተያይዞ እንዲቆይ ፍትሕ እንዲፈጸምልን እንጠይቃለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

- Advertisement -

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

ከ ተመሳሳይ አምዶች

አገሬ ምንተባልሽ – ልብ ያለው ልብ ይበል

በቶማስ በቀለ ይቺ አገራችን ብዙ ተብሎላታልም፣ ብዙ ተወርቶባታልም፣ አገሪቱ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አገር (ላይቤሪያን ጨምሮ) ከመሆኗ አኳያ የሚነገርላት ብዙ ጥሩና የሚገርሙ ነገሮች ያሉትን ያህል፣ ከረሃብ...

‹‹አክሱም የአፍሪካዊ ሥልጣኔ በጨረፍታ››

በሽብሩ ተድላ ይህች ጽሑፍ መጠነኛ አስተያየት የምታቀርበው "AKSUM A glimpse into an African civilization by Hailu Habtu/Zamra Press.2024" (እኔ ርዕሱን "አክሱም የአፍሪካዊ ሥልጣኔ በጨረፍታ" ብዬ...

የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ ከቋንቋ አንፃር

በተሾመ ብርሃኑ ከማል  በአሜሪካ በ2018 ለንባብ ካበቁት አካዴሚያዊ መጻሕፍት ተጠቃሹ ‹‹ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ›› የሚል ርዕስ ያለው የግርማ አውግቸው ደመቀ (ዶ/ር)...

‹‹ከድጡ ወደ …?

በሉልሰገድ ኃ. ዓለማየሁ (ዶ/ር) አስታውሱ ቀደም ብሎ በሪፖርተር ጋዜጣ ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ታትሞ የነበረውን ‹‹መቼ ነው? አልመረረንም እንዴ? እንቅልፉስ አደበንን እንዴ?›› የሚለውን እሮሮዬን...

ዘርፈ ብዙው የጥምቀት ክብረ በዓል

ዩኔስኮ የሚባለው የመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ተቋም የጥምቀት ክብረ በዓልን ‹የሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ› አድርጎ የመዘገበው በ2012 ዓ.ም. ነበር፡፡ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን...

የህልውና አባዜ እና የሰው ልጅ በጨረፍታ

በሽብሩ ተድላ መግቢያ ሳይንሳዊ አስተሳሰብን፣ ብሎም የሳይንስ ዕውቀትን በማኸዘብ (ብዙ ሰው በቀላል መንገድ እንዲገነዘበው ማድረግ)፣ በምክንያት ላይ የተመሠረቱ፣ ብዙ ጠቃሚ ተግባራትን የሚያከናውን ኅብረተሰብ ለመገንባት ያስችላል፡፡ ለሰው...

አዳዲስ ጽሁፎች

የጤናው ዘርፍ ባለፉት ስድሥት ወራት

የወባ በሽታ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ዋነኛ የጤናና የማኅበራዊ ቀውስ መንስዔ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2024 ያወጣው መረጃም 263 ሚሊዮን ሰዎች የወባ...

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በባለሙያ ዓይን

(በጎ ጎኖችና እርምት የሚፈልጉ ጉዳዮች) በዮሐንስ መኮንን በጥር ወር 2016 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዋና ዋና ኮሪደሮችን በማዘመን ከተማዋን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ ምቹ ያደርጋታል የተባለ ፕሮጀክት በ43 ቢሊዮን...

በልዩነት ውስጥ ሆነንም እስኪ እንነጋገር

በገነት ዓለሙ ዴሞክራሲ መብቶችና ነፃነቶች የሚሠሩበት የሕዝብ አስተዳደር ነው፡፡ ሰብዓዊ መብቶችንና ነፃነቶችን መኗኗሪ ያደረገ ሥርዓት ነው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በተፈጥሮ የተገኙ፣ ሰው በመሆናችን ብቻ...

ለጤናማ የትራፊክ ፍሰትና ለመንገድ ደኅንነት ቅጣት መጣል ብቻውን መፍትሔ አይሆንም!

በአዲስ አበባ ከተማ ለተሽከርካሪዎች ምቹ የሆኑ መንገዶችን እየተመለከትን ነው፡፡ ከአዳዲሶቹ መንገዶች ባሻገር አንዳንድ ነባር መንገዶች የማስፋፊያ ሥራ ታክሎባቸው አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡ ከኮሪደር ልማቱ ጋር...

የግጭት አዙሪት ውስጥ ሆኖ የአፍሪካ ማዕከል መሆን ያዳግታል!

የአፍሪካ ኅብረት 38ኛው የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ሲካሄድ ብዙ ትዝ የሚሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ እጅግ በጣም አሰልቺ፣ ውጣ ውረድ የበዛበትና ታላቅ ተጋድሎ ተደርጎበት ከከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ...

አገሬ ምንተባልሽ – ልብ ያለው ልብ ይበል

በቶማስ በቀለ ይቺ አገራችን ብዙ ተብሎላታልም፣ ብዙ ተወርቶባታልም፣ አገሪቱ በቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አገር (ላይቤሪያን ጨምሮ) ከመሆኗ አኳያ የሚነገርላት ብዙ ጥሩና የሚገርሙ ነገሮች ያሉትን ያህል፣ ከረሃብ...
[the_ad id="124766"]

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን