Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ምላስ አያዳልጠን!

ሰላም! ሰላም! ሩጫው እንዴት ይዟችኋል? ብርዱማ እንደምታዩት ዙር ይደርባል። መደረቡ ሳያንስ አገርና ስሙን በዓለም ያስጠራል። ግን ይኼም አይገርመንም አሉ። “እንዴት?” ብል “መደረብ ብርቅ ነው እንዴ? ይኼ ሁሉ ሰው ደራቢ እኮ ነው። ልዩነቱ ሕጋዊና ሕገወጥ መሆኑ ላይ ነው፤” ተባልኩ። እህ ብላችሁ ስታዳምጡ የማትባሉት የለም። ድሮ ድሮ መደረብ የማውቀው ለካሴትና ለነጠላ ነበር። ታሪክ ግን እንደምታውቁት ዙሩን እያሰፋ መደረብ እንጂ ሌላ አያውቅምና አሁን አሁን ሙላችንን ጨምቆ በሁለት ከፍሎን አረፈው። ደራቢና ተደራቢ። በዘመናት አንዴ እንደመታደል ሆኖ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ ካልጎበኘው በቀር የተደራቢ ዕጣ ምን ሆኖ ይቀራል? እንባ ማዝራት። እዚህ ላይ ያዝ ላድርገውና አንድ ቀልድ ላጫውታችሁ።

በፓርቲ አባልነቱ ብቻ ለግብርና ኤክስቴሽን ፓኬጅ አመራር ታጭቶ ነው አሉ ሰውዬው። የሚያውቃት አንድ ነገር ናት አሉ። በአሉባልታ አገር መቼም ‹ተሳፈጥክ› የሚለኝ የለም። ሲሉ የሰማሁትን ነው። እና ሰውዬው ሲሉ ሰምቶ የቀለባት እንደ ረቂቅ ዕውቀት አክብሮ የያዛት ነገር ምን ትባላለች? በመስመር መዝራት! በየሄደበት አርሶ አደር ሰብስቦ በመስመር ዝሩ ነው ስብከቱ። ታዲያ እንደለመደው አንድ ወረዳ ወርዶ ያቺን የዛገች መስመር የሳተች ስብከቱን ሲሰብክ አንድ አርሶ አደር ተነስተው፣ ‹‹እኛ በመስመር መዝራት መቼ ጠፋን። መስመሩን እኮ ነው ያጣነው። በስማችን እየነገደ ኑሮውን የሚያደላድለውን መስመር ስታስይዙት እኛም እንባ ማዝራታችንን ትተን በመስመር እንዘራለን፤›› ሲሉት፣ መቼም ያለሙያው የገባ ሰው ሙሉ ሀተታ መስማት አይወድም አይደል? የመጨረሻዋን ቃል ሰምቶ ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ ‹‹በመስመር መዝራት ሲባል እንባችሁንም ያጠቃልላል፤›› ብሎ አካሄዱን አሳመረ ይባላል። “እውነቴን መልሱ አፌን በእህል አብሱ” ብሏል ያገሬ ሰው!

ስለሩጫ ሳስብ በቀደም የእኔነቴን አሻራ በምድሪቷ ሳልተክል ብሎ ያቀነቀነው ዘፋኝ ትዝ ይለኝ ነበር። ስለ ነጋቸው አዚመው ሳይጨርሱ ከሩጫው መድረክ የሚሰናበቱ ምድራውያን የበዙባትን ዓለም አንዳንዴ ስም አጣላታለሁ። ጎዳናው በሩጫና በግርግር ተሞልቶ ጨራሹ ጥቂት ነው ተብሎ ለማን አቤት እንደሚባል እንጃ። በተለይ በተለይ በረባ ባረባ የአስተዳደር ችግር ሳይወለድ የሚጨነግፈው ዜጋ አንጀቴን ይበላዋል። አንጀት ተበልቶ የሚያልቅ ቢሆን ማን ይስተካከለን ነበር  አትሉም?  ብላችሁ ሳትጨርሱ ሌላ አንጀት የሚበላ ነገር ላስታውሳችሁ።

መቼም የእኛ ጉድ ለትውስታ እንጂ ለመርዶ አልሆን ብሏል። ምን ትዝ አለህ አትሉኝም ታዲያ? ትዝታ መሰለኝ አፅንቶ ያቆመን። ካላመናችሁ ፌስቡክ አካውንት ክፈቱ፡፡ ፌስቡክ ከደበራችሁ በዘር ፖለቲካ የሚዳኙ ሰዎች የሚጽፉትን መጽሐፍ መግቢያውን ብቻ አንብቡ። ምርጫው የእናንተው ነው። እና ምን ትዝ አለኝ? ያደጉት አገሮች አሻራና ኮቴን የሚጠቀሙባቸው ወጪና ገቢውን ለመቆጣጠር ነው። እኛ ዘንድ ግን ፍዳችንን የሚያበላን አልራገፍ እያለ ነው። ወዲያ በሊቢያ በረሃ ወዲያ በየመን፣ ገፋ ሲል አውሮፓና አሜሪካ ሩጫችን ሁሉ ትኩረቱ አንድና አንድ ነው። አሻራና ኮቴ ማራገፍ ብላችሁ ተቀበሉኛ። ኧረ ቢያንስ ጨዋታ እንቀባበል ተው ግዴለም። ዕውቀት መቀባበል ቢያቅተን፣ ሸክም መጋራት ቢመረን እንዴት ወግና ጨዋታ መቀባበል ያቅተናል? አዚም በተዝረከረከ አመራርና አስተዳደር እየተመሰለ አደነዘዘን እኮ ጎበዝ!

እና ጨዋታም አይደል የያዝነው። ያለፈውን እያሞጋገሱ የያዙትን ከማክፋፋት ምንም እንደማይገኝ የማውቀው እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ‘ወደፊት’ ብዬ ወደ ሥራዬ ተሰማርቻለሁ። ዘመኑን አማነውም አላማነውም፣ መንግሥትን አማረርነው አሞገስነውም መምሸት መንጋቱን መቼ ይተዋል? እንዲያው ነው ኧረ! ታዳያላችሁ አንድ የሚከራየው ቤት ማግኘት የተቸገረ ሰው አላስቆም አላስቀምጥ ብሎኝ እንከራተታለሁ። ይገርማችኋል ይኼ ቤት አጥቶ እረፍት አሳጣኝ የምላችሁ ሰው የተከራየውን ቤት ለቆ እንዲወጣ ምሕረት የለሽ ውሳኔ የተላለፈበት በዚህ ወር ነው። “ምንስ ቢሆን እንኳን ሰላማዊ ሰው ቀርቶ ጠላት በዚህ ክረምት ይሸኛል?” ብላቸው ባሻዬ፣ “ወይ አንተ ድሮና ዘንድሮ አንድ መሰለህ? ድሮ የሰው መድኃኒቱ ሰው ነውና እንዴት ተደርጎ? ያሁኑን ግን ምን እነግርሃለሁ አንበርብር? ያለ ገንዘብ ሰው ዘመድ አላውቅ ብሏል እኮ፤” አሉኝ ከልጃቸው በባሰ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ፊታቸውን ሸፍኖት። እነሆ ይኼን ያህል ዘመን ያስቆጠረ የሰው ልጅ የሥልጣኔ ሩጫ መጨረሻው በአፍቅሮተ ንዋይ ግብግብ ሊቋጭ ያሰፈሰፈ ይመስላል። ‘ትዝታ ታማኝ ነው ወረትን አያውቅም፣ እንደ ሰው ለገንዘብ ቦታውን አይለቅም’ እየተባለ እስከ መቼ ሰው በሰው ትዝታ ይዘልቅ እንደሆነም እንጃ። ‹እኔ አላማረኝም አዲስ ነገር በዝቷል፣ በኪስህ ተማመን ጎበዝ ፍቅር ጠፍቷል› ያለው ሙዚቀኛ ትዝ ሲለኝ ደግሞ ግራ ይገባኝ ይጀምራል። ስንቱ ግራ አጋብቶን እንደምንዘልቀውም በራሱ ግራ ይገባል!

ወዲያው እጄ ላይ ያሉ ሁለት ቪላ ቤቶችን ለማሻሻጥ ወደ ቀጠርኳቸው ሰዎች ደወልኩ። አካባቢውን ስጠቁማቸው ወጣት የመሰሉኝ ደንበኛዬ ሳገኛቸው ዕድሜያቸው ወደ 70 ይጠጋል። “መሬት ቢከሽፍበትም ሰው ቤት ላይ ያለው አቋም አይሏል፤” ያለኝ አንድ ደላላ ወዳጄ ትዝ እያለኝ አንዳንድ ስንባባል፣ ከልጆቻቸው ጋር አሜሪካ 20 ዓመት ኖረው መምጣታቸውን አጫወቱኝ። “ቤቱ ለልጆችዎ ነው ማለት ነዋ?” ስላቸው፣ “ኧረ ለራሴ ነው። እዚያ እንግዲህ ምንም የጎደለብኝ ነገር አልነበርም። ግን በሰው አገር በትንሽ ትልቁ የማያበራ ‘ቢል’ ለመክፈል የሥርዓቱ ባሪያ ሆነው የሚኖሩ ልጆቼን እያየሁ ከምሞት፣ በአገሬ የመብራትና የውኃ ‘ቢል’ እየከፈልኩ ኖሬ በቃሽ ስባል ወገኔ ቢቀብረኝ ይሻለኛል፤” አሉኝ። ጥቂት ዘወር ዘወር ብለው ቤቱን አዩና ለመግዛት መወሰናቸውን ሳያወላውሉ ሲነግሩኝ፣ ማንጠግቦሽና እኔ ከፍልሰታ ፆም በኃላ የምንቆርሰው ሰማይ ጠቀስ ‘ቶርታ’ ፊቴ ላይ ድቅን። ሕንፃማ እንዴት ይታየናል?

ወደ ኋላ ልመለስና ባሻዬ የሠፈሩን ውሪ ሰብስበው ቅዳሜና እሑድ ከሰዓት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀምረዋል። ባሻዬን፣ ‹‹አዲሱ ሥራዎ እንዴት እየሄደ ነው?››  ስላቸው፣ ‹‹ደግ ነው። ልጆች ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ይልም አይደል እንዴ ቃሉ?  እነዚህ ልጆች እኮ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ብዙ ነገር እየከለከልናቸው ነው። ኳስ መጫወቻ የላቸው። መሮጫ የላቸው። ንፁህ አየር መተንፈሻ የላቸው። ምን የላቸው፣ ምን የላቸው። ባይሆን በሰማዩ ሥፍራ ቦታ ይኑራቸው ብዬ እኮ ነው. . .›› ብለውኛል። አይ ባሻዬ? አይታወቃቸውም እንጂ  ይናገራሉ እኮ።

ግን አያችሁ አገሬ እንደ እሳቸው ያሉ ሰዎችን ንግግር መስሚያ የላትም። አገሬ ጆሮዋን የምትከፍተው ለሚያጣብባት፣ ለሚያስተፋፍጋት፣ ለሚያጨናንቃት፣ ወዘተ ወዘተ ነው። ይኼ ምንም ከፖለቲካ ጋር አይገናኝም። እንዴ ተው እንጂ ምን ነካችሁ? ቆይ ለምድነው ሁሉ ነገር ፖለቲካዊ ጥያቄና መልስ የሚሆነው። ለምሳሌ አንዱ ባለፈው ዓመት በአንዱ የተቃውሞ ሠልፍ ውስጥ ተቀላቅሎ እጁን በኪሱ ከቶ ይጓዛል አሉ። እና የሚያውቀው ሰው አገኝቶት፣ ‹‹እንዴ አንተም ተቃዋሚ ነህ?›› ሲለው ምን ቢለው ጥሩ ነው? ‹‹ኧረ እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም። ብቻ ብዙ ተቀማጭ ሰው ስለበዛ ብዙ ጊዜ ወክ የማደርገው ብቻዬን ነው። ዛሬ እስኪ ከሰው ጋር ልጓዝ ብዬ ነው. . .›› አለው አሉ። እኔ ይኼ አሁን ምኑ ፖለቲካ ነው?

በሉ እንሰነባበት። ባሻዬ በድንገት የጀመሩት ፕሮጀክት መስተጓጎሉን ሰማሁ። በበራቸው ሥር ንፋስ ገብቶ መቷቸው ብታዩዋቸው ከአልጋ አይወርዱም፡፡ “እስኪ አሁን ፈጣሪ ያሳይህ ዘመን እንዲህ ሠልጥኖ ‹ብርድ› በሚባል በሽታ እንለቅ?” ሲሉኝ ይቆዩና፣ “የኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ንፋስ የገነደሳቸውን ዛፎች መጨረሻ ሳላይማ አልሞትም፤” ብለው ይፎክራሉ። “ኧረ ጠላትዎን!” እላለሁ ፍም የእሳት ማንደጃ ወደ አልጋቸው እያስጠጋሁ። “እሱ ከሰል ጭሱ አልቋል?” ሲሉኝ ደግሞ፣ “እንጃ ባሻዬ። እኔ አላቀጣጠልኩት። ምነው እርስዎም እንደ መንጋው ባልዋለበት ባልሰማበት ነገር ሰውን በጭስ ያማሉ?” ስላቸው ይስቃሉ። እንዲህ እንዲህ እንባባልና ብዙ እንፖተልካለን። “መቼም አልጋ ይዘው ያወሩት ነገር አያስጠይቅም፤” ይሉኝና በሚመሩት ዕድር ስላካሄዱት ሹም ሽር አስተያየት እንዳለኝ ይጠይቁኛል። “ብዙ የታሙበት ነገር አለ፤” አልኳቸው። “እኮ ምን ተባልኩ? የአምባሰልም ዳገት የዕድገቴ ስርፋ ነው፣ የጦሳም አቀበት የቦረቅኩበት ነው፣ ዛሬስ በቀላሉ ከአፍ አፍ ጣለኝ ምነው? አለ ባህሩ ቀኜ አፈር ልብላለትና፤”  ብለው ቀና አሉ።

“ኧረ ጋደም ይበሉ። ደግሞ ለዘመኑ አፍ ይጨነቃሉ? እንዲያው ነው ሐሜታው። ሹም ሽሩ ለውጥ የለውም። የነገር መጨረሻው እንጂ ጅማሬው አያስመካም ዓይነት ነው ሐሜታው። ብቻ እርስዎ በርትተው ፍፃሜውን ማሳመር ነው፤” አልኳቸው። “እንዴት አድርጌ አንበርብር? ንፋስ ሲጥለን አፍ እየጨረሰን ምኑን ከምን አድርገን ፍፃሜ ማሳመር ይቻላል?” አሉኝና ትክዝ ብለው ቆይተው፣ “ያደላትማ ያገላገላት፣ ምጡን እርሺው ልጁን ሳሚው ነበር የሚባልላት። እኛ እኮ በምጥ ላይ ምጥ ተደርቦ እያቃዠን፣ ባልተጨበጠ መረጃና ትንታኔ አገር በወሬ እየታመሰ፣ አንድ ሳንሆን በየት በኩል አምጠን በምን አፍታ ከመርሳት ደርሰን ወልደን እንሳም? ምጥና ጭንገፋ ሳንጀምር እየጨረሰን፤” አሉኝና ዝም ስላቸው ጊዜ ሸለብ አድርጎ እንቅልፍ ወሰዳቸው። ለባሻዬ ዕድርና ለፓርላማችን ምጡን ረስተው ልጅ የሚስሙበት ዘመን እንዲመጣ እየተመኘሁ፣ ፆም ነውና እኔም ውኃዬን ጠጥቼ ገብቼ ተኛሁ። ማን ያውቃል ስንነቃ ለፍሬ እንደርስ ይሆናል። እስከዚያው ንፋስ እንዳይጥለን ምላስ አያዳልጠን፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት