Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናክልሎች የማያስፈጽሟቸውን ሕጎች በማውጣታቸው ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ከአቅም በላይ መሆናቸው...

  ክልሎች የማያስፈጽሟቸውን ሕጎች በማውጣታቸው ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ከአቅም በላይ መሆናቸው ተገለጸ

  ቀን:

  በመሬት ላይ የሚወጡ ሕጎች ሕገ መንግሥቱን ያልተከተሉ መሆናቸው ተጠቁሟል

  ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች የሕገ መንግሥት መሠረት እንዲኖራቸው ተጠይቋል

  የከተማና የገጠር የይዞታ መብት ወጥና ተመሳሳይ እንዲሆን ተጠይቋል

  ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት የሚቀርቡ አቤቱታዎች እጅግ በጣም እየበዙና ከአቅም በላይ እየሆኑ የመጡት፣ ክልሎች ሊያስፈጽሟቸው የማይችሏቸው ዝርዝር ሕጎች በመኖራቸው እንደሆነ ተጠቆመ፡፡

  የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ነሐሴ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል ለአንድ ቀን አዘጋጅቶት በነበረው ዓውደ ጥናት ላይ ከመሬት ጋር በተያያዘ ማብራሪያ የሰጡት የሕግ ባለሙያው አቶ አበበ ሙላት እንደተናገሩት፣ የመሬት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 456/97 አፈጻጸም በከተማ አስተዳደሮች አካባቢ ሕጉን ለመከተል ከሚሞክሩ ባለፈ በአግባቡ እየተገበሩት አይደለም፡፡ በገጠር መሬት ይዞታዎችም ላይ ሕጉ በአግባቡ እየተተገበረ አይደለም፡፡ ሕግና ተቋማት ጎን ለጎን መሄድ ቢገባቸውም እየተደረገ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤትም የሚቀርቡ በርካታ አቤቱታዎች ሕጉ ተጥሶና ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም አስፈልጎ ሳይሆን፣ ሕጉን በተግባር ላይ የማዋል ወይም የማስፈጸም ችግር መሆኑን አስምረውበታል፡፡

  መሬትን መሸጥ ሕጉ እንደማይፈቅድ እያወቀ ሰው ግን በተግባር ሲፈጽመው እንደሚታይና ይኼንን በሚመለከት ክልከላ ሲመጣበት ክርክር የሚገጥመው ሕጉን መሠረት አድርጎ ሳይሆን፣ የከለከለውን አካል በመሆኑ ይኼ የሚያሳየው የክልል አመራሮች የማስፈጸም አቅም አለመኖሩን እንደሆነ አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡

  ተቋማት ተቀናጅተውና ተናበው ስለማይሠሩና በአንድ ይዞታ ላይ ተደራርበው ማስረጃዎች ስለሚሰጡ፣ ፍርድ ቤቶች የሚቀርብላቸውን ተመሳሳይ ማስረጃ በማየት ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ በማንሳት ለጉዳዩ ዕልባት ለመስጠት፣ ወይም የተፋጠነ ፍትሕ ለመስጠት እንደሚቸገሩም አስረድተዋል፡፡ ክልሎች ያወጧቸውን ዝርዝር ሕጎች እንዴት ማስፈጸም እንዳልቻሉ በምሳሌ ያስረዱት አቶ አበበ፣ የኪራይ ውል መመዝገብ ቢኖርበትም ‹‹‹ማን እንደሚመዘግበው›› እንደማይታወቅ ጠቁመዋል፡፡ አንድ አርሶ አደር መሬቱን ማከራየት፣ በስጦታ መስጠት፣ ማውረስና የመጠቀም መብቱን መሸጥ ቢችልም፣ እንዲመዘገብበት የተደራጀው ከአካባቢው እጅግ በጣም ርቀት ባለው ቦታ ላይ በመሆኑና ሊያከራየው የሚፈልገው የመሬት ስፋት 0.25 ካሬ ሜትር ከመሆኑ አንፃር በዚያ ርቀት ላይ ተጉዞ የሚከራከረው ኢንቨስተር ስለማይኖር፣ በአካባቢውና በቅርበት ለሚገኝ ሌላ አርሶ አደር ምርቱን እኩል ለመጋራት (ለመካፈል) እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡

  በአካባቢው ውል የሚዋዋልበት ዘዴ ባለመዘርጋቱ፣ መሬቱን ለእኩል የወሰደው አካል ትንሽ ጊዜ ቆይቶ ማካፈሉን ትቶ ለራሱ ብቻ መጠቀም ሲጀምር ጉዳዩ ወደ ክስ እንደሚሄድና እስከ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እንደሚደርስ ጠቁመዋል፡፡ ይኼንን መፍታት ያለበት ክልሉ ሲሆን፣ ይኼንንም ለማስፈጸም ሕገ መንግሥቱንና አዋጅ ቁጥር 456/97 መሠረት አድርጎ ማስፈጸሚያ ዝርዝር ሕግ በማውጣትና በአግባቡ በመፈጸም እንደሚኖርበትም ተናግረዋል፡፡ የመሬት አስተዳደር አዋጁ በራሱ ችግር እንዳለበት የጠቆሙት አቶ አበበ፣ የገጠር መሬት ተመዝግቦ የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ቢሰጠውም መዝጋቢው ማን እንደሆነ፣ መሰረዝ የሚችለው ማን እንደሆነና የሕግ ውጤቱ ምን እንደሆነ ምንም እንደማይል ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ነጥቦች ብዙ ጊዜ ለፍርድ ቤት እንደሚቀርቡና እንደሚያከራክሩም አክለዋል፡፡

  የፌዴራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የመሬት አስተዳደር ሕግን ያወጣ ቢሆንም፣ ትንሽ አንቀጾች ማለትም ከ12 አንቀጾች ያልበለጡ ድንጋጌዎችን ከመያዝ ውጪ ስለአተገባበሩ ዘርዘር ያለ ነገር ባለማውጣቱ፣ ለችግሩ መባባስም የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

  ገበሬው መሬቱን የማከራየት መብት እንዳለው ቢደገነግግም  ለስንት ዓመትና ስንት ስንተኛውን ማከራት እንዳለበት እንደማያውቅ፣ ለቤተሰብ አባል ማውረስ እንዳለበት ቢደነግግም፣ ‹‹የቤተሰብ አባል እነ ማን ናቸው? ስንት ጊዜ አብሮ የቆየ ነው ቤተሰብ አባል የሚባለው?›› የሚሉትንና ሌሎች ዝርዝር ነገሮችን ባለማካተቱ፣ ለግጭትና ለመካሰስ በር የሚከፍት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

  የፌዴራል መንግሥት ዋና ዋና ድንጋጌዎችን በማስቀመጥ የማስተዳደር ሥልጣን የተሰጣቸው ክልሎች ዝርዝር ሕግ እንዲያወጡ እሳቤ የተደረገ ቢሆንም፣ ክልሎች ግን የፌዴራሉን ሕግ ወስደው ዝርዝር ሕግ ማስቀመጥ (ማውጣት) እንዳልቻሉ በተግባር መታየቱን አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡ አንዱ ክልል የሌላኛውን ክልል ሕግ እንዳለ ከመገልበጥ ባለፈ ዘርዘር ያለ ትርጉም እየሰጡ የራሳቸውን ሕግ ማውጣት እንዳልቻሉ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የአማራ ክልልን እንዳለ መገልበጡን በመጠቆም በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች የተሻለ ነገር ቢኖርም፣ እነሱም ዘንድ ችግሮች እንዳሉ አክለዋል፡፡

  የፌዴራሉ መንግሥት ያወጣው ሕግ የሚሰጠው መብት በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች ብቻ የመጠቀምና የይዞታ መብት እንዳላቸው መሆኑን የጠቆሙ አቶ አበበ፣ ይኼንን ክልሎች በደንብ ስላልተረጎሙት ከሕገ መንግሥቱ ጋር መጣጣም እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ መሬትን ከማውረስ ጋር ተያይዞ ማውረስ የሚቻለው ለቤተሰብ አባልና ከባለይዞታው ጋር ተጠግቶ የሚኖርንም ስለሚያካትት፣ ተጠግቶ መኖር አንድ ወር ይሁን ወይም ሌላ ግልጽ ሆኖ የተቀመጠ ነገር ስለሌለ በዝርዝር መቀመጥ እንዳለበት አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡ ሴቶች መሬት የማግኘት መብት እንዳላቸው በፌዴራሉም ሆነ በክልሎች ሕግ ውስጥ የተካተተ ቢሆንም፣ ቅድሚያ ማግኘት እንዳለባቸው በዝርዝር ሕግ መካተት እንዳለበትም አክለዋል፡፡ ክልሎች መሬትን የሚያስተዳድሩበት ሕግ ያወጣሉ ነው እንጂ፣ የንብረትነት መብት የሚወስኑበት ሕግ እንዳልሆነ መገንዘብ እንዳለባቸው ለክልሎች ጠቁመዋል፡፡ አዋጁ ስለውርስ፣ ማስተዳደርና ስጦታ ያለው ነገር ባይኖርም የፍትሐ ብሔር ሕጉና ሥነ ሥርዓት ሕጉ በዝርዝር ስላስቀመጡ፣ ከእነሱ ጋር ማጣጣም ግድ እንደሚልም አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡ ከላይ የዘረዘሯቸውን ችግሮች ይቀርፋል የሚባል ረቂቅ የመሬት አስተዳደር አዋጅ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ ከውርስ ስጦታና ማከራየት ጋር በተያያዘ ሰፋ ባለ ሁኔታ በረቂቅ አዋጁ መካተቱን አመለክተዋል፡፡

  የመሬት ይዞታን በሚመለከቱ የፌዴራል መንግሥት ተደጋጋሚ አዋጆችን ማውጣቱንና የማስተዳደር ሥልጣኑን ለክልሎች መስጠቱን በማስታወስ፣ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ተፈሪ ገብሩ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ክልሎች ያወጧቸው ሕጎች ሙሉ በሙሉ አዋጁን የተከተሉ እንዳልሆኑ ጠቁመዋል፡፡ በፍርድ ቤቶች የተመረጠው የክርክር ሒደትና አፈታት ሒደት ከሕጎቹ አወጣጥ ጋር ብዙ የማይለያይ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ክርክሮች በስምምነትና በሽምግልና እንደሚፈቱ ክልሎች ባወጧቸው ሕጎች የደነገጉ ቢሆንም፣ ይኼም ከፌዴራሉ ሕግ ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የክልል አስተዳደር ሕጎች ክርክሮች በፍርድ ቤት የሚፈቱበትን ሁኔታ ለማስቀመጣቸው በዓመት ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ክርክሮች እንደሚቀርቡ፣ የአማራ ክልል በአንድ ዓመት ውስጥ ከ350,000 እስከ 400,000 ክርክሮችን ማስተናገዱን በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በዋናው ሕግ መሠረት ክርክሮች የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብትን በጠበቀ መንገድ በፍርድ ቤት ቢካሄዱ ተመራጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  በየክልሎቹ ያሉትን የክርክር መፍቻ ሒደቶች በጥልቀት የዳሰሱት ተፈሪ (ዶ/ር)፣ የመሬት አዋጅ ልዩ ሕግ መሆኑን በመጥቀስ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 133604 አስገዳጅ ትርጉም እንደሰጠበት ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ጉዳዮች ከታች ከስምምነት፣ ከሽምግልናና ከዞን ፍርድ ቤቶች ጀምሮ እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት መድረስ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 ድንጋጌ መሠረት ‹‹ፍትሕ የማግኘት መብት› አንፃር ሥልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች እንዲታዩ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

  ክርክሮች ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ እስከ ዝርዝር ሕግጋት በማካተት ዕውቀትና ችሎታ ባለው ዳኛ ውሳኔ (ዳኝነት) ማግኘት እንዳለባቸውም ተፈሪ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

  ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥት ትርጉም አሰጣጥ ዙሪያ የራሳቸው ሚና እንዳላቸው ከዝርዝር ሕጎች መረዳት እንደሚቻል ጠቁመው፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሥራ ሲባል ሕገ መንግሥቱ ሕይወት እንዲኖረው የማድረግ ሥራም መሆኑንም አክለዋል፡፡ ይኼም ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና የሚሰጡ ውሳኔዎች ሕገ መንግሥቱን መሠረት ካደረጉ በአንቀጽ 9 ስለተገለጸው ሕገ መንግሥቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ስለመሆኑ ማሳወቅ እንደሚረዳ አውስተዋል፡፡

  ሕጎች ሁሉ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ማድረግና ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መውጣት ስለሌለባቸው፣ ከዚያ ውጪ ከሆኑ ውድቅ ማድረግ መለመድ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ አዋጅ ቁጥር 250፣ 798 እና የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 62፣ 82፣ 13 እና 37 ተደምረው ሲታይ፣ ሕገ መንግሥቱን የሚገዳደር ነገር ካልሆነ በስተቀር ትርጉም የሚጠየቅበት ነገር እንደሌለ በቀላሉ መገንዘብ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚሰጥባቸው ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ የወጡ ሕጎች ሁሉ እንደሚያሳዩ ጠቁመው፣ ፍርድ ቤቶች እነዚህን ድንጋጌዎች ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በውሳኔዎች ውስጥ መጥቀስ ኅብረተሰቡ በቀላሉ የሕገ መንግሥትና የሕግ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ክርክሮችን  ወደ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት መቼ መሄድ እንዳለባቸው በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 3(1) መደንገጉንና ለፍርድ ቤቶችም ሥልጣን እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡

  ላለፉት በርካታ ዓመታት ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎቻቸው ሕገ መንግሥታዊ መሠረት እንዲኖራቸው አለማድረጋቸው ስህተት በመሆኑ፣ በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ በውሳኔዎች ውስጥ እያጣቀሱ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የክልል የመሬት አስተዳደር ኃላፊዎች፣ ዳኞችና የተለያዩ ሙያ ያላቸው ኤክስፐርቶች የተገኙበትን ስብሰባ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ በ‹እንኳን ደህና መጣችሁ› መልዕክት ዓውደ ጥናቱን ከፍተዋል፡፡ ውይይቱን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሰለሞን አረዳ የመሩ ሲሆን፣ የውይይቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ ሕግ ነክ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ተሳታፊዎቹም በረቂቅ አዋጁ እንዲካተቱ የፈለጉዋቸውን ሐሳቦችም አንስተዋል፡፡  

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...