Friday, December 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከመፍትሔ ይልቅ ችግር መቆለል የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይከታል!

ነገሮችን በማወሳሰብ ችግር ለመፍጠር ግንባር ቀደም የሆኑ፣ ከሰላም ይልቅ ግጭት የሚቀናቸው፣ ስህተት ለማረም ሳይሆን ስህተት ፍለጋ ላይ የተጠመዱና በአጠቃላይ አገርን ቀውስጥ ውስጥ ለመክተት የሚባዝኑ በዓይነትም በቁጥርም እየጨመሩ ነው፡፡ ከአቅሟ በላይ ችግሮች የተቆለሉባት ኢትዮጵያን ከድጡ ወደ ማጡ እየገፉ ያሉ ኃይሎች አንድም ቀን ተሳስተው ለሰላም፣ ለጋራ ዕድገትና ለአብሮነት ሲማስኑ አይታዩም፡፡ በየዕለቱ የፀጥታ ሥጋትና የሕዝብ መከራ ሆነው ያሳቅቃሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለአገር ሰላም፣ ለሕዝብ ደኅንነትና ህልውና በአንድነት መቆም የሚገባቸው፣ ለአገር የማይጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ተጥደዋል ወይም ተሳትፎአቸውን ገድበዋል፡፡ ነገር ግን አገር ከመቼውም ጊዜ በላይ የህልውናዋ ጉዳይ አሳሳቢ ሲሆን፣ ቸልታ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰሞኑን ይፋ በተደረገው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ምክንያት የሚሰሙ አደናጋሪ አስተያየቶች፣ የአገሪቱ ችግር ምን ያህል እየተወሳሰቡ መሄዳቸውን ያመላክታሉ፡፡ በጋራ ጉዳይ ላይ መግባባት ስላቃተ ሰከን ብሎ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ በጥፋት ላይ ጥፋት መደራረብ የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡

ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ለማውጣት በፖለቲካ፣ በፍትሕና በዴሞክራሲ መስኮች የተቋማት ግንባታ ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በደካማ መንግሥታዊ መዋቅርና ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ በማይመች የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ መውረግረግ የትም አያደርስም፡፡ አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ስብስቦች የሚገዙበት የጋራ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት መፈጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ፓርቲዎቹ በምርጫም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠራቸው የግድ ይሆናል፡፡ የአባላትና የደጋፊዎቻቸውን ንቃተ ህሊና ለማጎልበት ደግሞ የሲቪክ ማኅበረሰቦች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህን ነገሮች ማሟላት ካልተቻለ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አቅም ደካማ ከመሆኑም በላይ፣ የአገርን ጉዳይ ኃላፊነት ለማይሰማቸው ኃይሎች አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ በተለይ በመብት ተሟጋችነት ስም ሥርዓተ አልበኝነት እያሰፈኑ ኃይሎች ይህንን አጋጣሚ እየተጠቀሙበት፣ አገርን መቀመቅ ውስጥ እየከተቱ ነው፡፡

የወቅቱ አገራዊ ጉዳዮች መዘወር ያለባቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለባቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዳዮች ልሂቃንና ባለሙያዎች መሆን ሲገባቸው፣ መፍትሔ ከማመንጨት ይልቅ ችግር በመቀፍቀፍ አገር የሚያምሱ ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ወዲህ የገባችበት የሽግግር ምዕራፍ በስኬት ተጠናቆ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት መጣል ሲገባ፣ በእያንዳንዱ ዕርምጃ መሰናክል የሚያስቀምጡ አላራምድ እያሉ ነው፡፡ ሽግግሩ አልጋ በአልጋ ሆኖ ያለ ምንም መሰናክል እንደማይራመድ ቢታወቅም፣ እግር በእግር እየተከታተሉ የሚያደናቅፉት ሲበዙ ግን ዝም ማለት ትክክል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በታሪክ ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጠው ወሳኝ ምዕራፍ ውስጥ ከገባች በኋላ፣ መልካም አጋጣሚዎችን የሚያበላሹ ድርጊቶችን በይሉኝታ ወይም በቸልታ ማለፍ አደጋ አለው፡፡ ይልቁንም የተሳሳቱትን በማረም፣ በመገሰፅና አለፍ ሲልም በመቅጣት የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይመረጣል፡፡ አገር የምትፈልገው ከእግር እስከ ራሷ የወረራት ችግር እንዲበራከት ሳይሆን፣ ከችግሩ የሚገላግላትን መፍትሔ መሆኑን መረዳት የግድ ይላል፡፡ የማደግና ታላቅ የመሆን ዕምቅ ኃይል ያላትን ኢትዮጵያ፣ የችግር ቤተ ሙከራ ማድረግ በታሪክ እንደማያስጠይቅ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ መጪው ጊዜ ያሳስባል፡፡

ለአገር የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ነገር ሲያጋጥም በመንጋ የድጋፍና የተቃውሞ አሠላለፍ ከማራገብና ግጭት ለመቀስቀስ መከራ ከማየት፣ የተፈጠሩ ስህተቶችን በጋራ በማረም የተሻለ ለመሥራት መንቀሳቀስ ያስከብራል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ለዓላማቸው ስኬት ሲሉ የሚፈጥሩት አዘናጊ አጀንዳ ላይ በመንጋ በመረባረብ ጊዜ ከማጥፋት፣ እንዲሁም በሌሎች ደራሽና እንግዳ  አጀንዳዎች እንደገና ከመዋጥ ለአገር የሚጠቅም ጉዳይ ላይ ማተኮር ተመራጭ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የሚነሳው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በተለይ ወጣቶችና ተምረናል የሚሉ ወገኖች ንፋስ እንደሚንጠው ጀልባ የሚዋልሉት፣ መሰሪዎች ሆን ብለው ወቅት እየጠበቁ በሚለቋቸው በሐሰተኛ ወሬ በታጀቡ አጀንዳዎች ምክንያት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሲያጋጥሙ መቼ? የት? ለምን? እንዴት? ምን? ከማለት ይልቅ፣ እንደ ድንገተኛ ጎርፍ በሚለቀቁ ሐሰተኛ ወሬዎች ተሸብሮ አገር ማሸበር የተለመደ ሆኗል፡፡ ለአገር ምንም ፋይዳ የሌላቸው ነገሮች ላይ ውሎ ማደር ከመብዛቱ የተነሳ ችግሮችን ከመቅረፍ ይልቅ፣ ችግሮችን ማባባስ ልማድ ሆኗል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አሰልቺና አስከፊ ሁኔታ ውስጥ በቶሎ መውጣት ካልተቻለ፣ የአገር ዕጣ ፈንታ ከሥጋት ሊላቀቅ አይችልም፡፡

‹ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ነበረች ትሆናለችም› ሲባል በከንቱ አይደለም፡፡ በአርምሞ ውስጥ ያሉ ልጆቿ ዝምታቸውን ሰብረው ከወጡ፣ ኢትዮጵያ ታላቅ የማትሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ እኩል የጋራ ቤት እንድትሆን ጠንክሮ በጋራ መሥራት ከተቻለ ተዓምር መሥራት አይቸግርም፡፡ ሌላው ቀርቶ በየምክንያቱ ኩርፊያና ቅያሜ የበዛበት ለውጥ ላይ በጋራ መክሮ በአንድነት መነሳት ከተቻለ፣ ከዚህ ቀደም የተሠሩ ስህተቶች ሳይደገሙ አስደማሚ ውጤት ማግኘት ይቻላል፡፡ ለተቋማት ግንባታ ልዩ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀስ ከተቻለ፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት መሠረቱ ይጣላል፡፡ ልዩነቶችን ይዞ አብሮ መሥራት፣ መወያየት፣ መከራከር፣ መደራደር፣ ወዘተ. ከተለመደ የዘመናት ችግሮች እንደ ገለባ ይቀላሉ፡፡ ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም በላይ አገርን የሚያስቀድሙ አጀንዳዎች ወደ ውይይት መድረኮች ብቅ ሲሉ፣ ለማመን የሚያዳግቱ ጥራት ያላቸው አገር ገንቢ ሐሳቦች በስፋት ይቀርባሉ፡፡ ለሕግ የበላይነት ከፍተኛ ክብርና ሥፍራ ሲሰጥ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት አደብ ይገዛሉ፡፡ ወጣቶች ንቃተ ህሊናቸው ሲዳብርና ከታላላቆቻቸው አርዓያነት ያላቸው ተግባሮችን ሲማሩ፣ በመንጋ መነዳትና ውድመት ውስጥ መሰማራት ታሪክ ይሆናሉ፡፡ መጠየቅ፣ መሞገትና የተሻለ ሐሳብ ማመንጨት ይለመዳል፡፡ ኢትዮጵያ የምትፈልገው ይህንን ነው፡፡ ችግር የሚቆልሉት ላይ ሳይሆን መፍትሔ የሚያመነጩት ላይ ትኩረት ይደረግ፡፡ አለበለዚያ ከመፍትሔ ይልቅ ችግር መቆለል የማይወጡት አዘቅት ውስጥ እንደሚከት የታወቀ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...