የኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽን የተጨዋቾችንና የአሠልጣኞችን ወርኃዊ ክፍያ አስመልክቶ የደረሰበትን ውሳኔ የተጨዋቾችና የአሠልጣኞች ማኅበር ተቃወመው፡፡ ማኅበሩ ውሳኔው ከፌዴሬሽኑ ደንብና መመርያ አኳያ ታይቶ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ያላሳተፈ መሆኑን ጭምር በመግለጽ ቅሬታውን ለፌዴሬሽኑ አስገብቷል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለር አሶሴሽን›› በሚል በቅርቡ ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘው የተጨዋቾችና አሠልጣኞች ማኅበር 08/12/2011 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ቅሬታውን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስገብቷል፡፡ ማኅበሩ ተቃውሞውን ያቀረበው መስከረም 27 ቀን 2004 ዓ.ም. በወጣው የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ በአንቀጽ 5 የአባላት የጋራ ጥቅም እንዲሁም በአንቀጽ 11፣ 46 እና 47 የአባላት መብቶችና የዓለም አቀፍ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት ከሚከተሉት ሕጋዊ አሠራር ባፈነገጠ መልኩ የተላለፈ ውሳኔ እንደሆነ ጠቅሶ ውሳኔውን እንደማይቀበለው አብራርቷል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በ08/12/2011 ዓ.ም. ለሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በጻፈው የእንድታውቁት ደብዳቤ፣ ጉዳዩ በራሳቸው በክለቦቹ ጥያቄ መሠረት በ03/12/2011 በቢሾፍቱ በተዘጋጀው መድረክ ነባሮቹ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችና በ2012 የውድድር ዓመት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉትን ጨምሮ በድምሩ 15 ክለቦች በተጨዋቾችና አሠልጣኞች ወርኃዊ ክፍያ ላይ ውይይት አድርገው ታክስን ጨምሮ የደመወዙ ጣሪያ 50,000 እንዲሆን የደረሱበትን ውሳኔ ለክለቦች ማሳወቁን ተከትሎ የቀረበ ተቃውሞ ስለመሆኑ ማኅበሩ በመግለጫው አካቷል፡፡
ፌዴሬሽኑ ነሐሴ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በዓለም ገና ከተማ በዚሁ ጉዳይ የብሔራዊና የከፍተኛው (ሱፐር) ሊግ ክለቦች ተወያይተው ውሳኔ እንዲያሳልፉ መድረክ አዘጋጅቶ እንዲመክሩ ካደረገ በኋላ ውሳኔያቸውን እንደያሳውቁ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከነባር ተጨዋቾች አንዳንዶቹ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ከሠራተኛና አሠሪ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ማኅበራት ደንብና መመርያ ጋር ፍፁም የሚቃረን ስለመሆኑ የተናገሩ አሉ፡፡ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ከሰጡት ተጨዋቾች መካከል ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2012/13 ለአፍሪካ ዋንጫና ለቻን የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ ተሳትፎ ያበቋት ሥዩም ተስፋዬና ዳዊት እስጢፋኖስ ይጠቀሳሉ፡፡
ቀድሞ በደደቢት አሁን ደግሞ ለመቐለ 70 እንደርታ በመጫወት ላይ የሚገኘው ሥዩም ተስፋዬ በበኩሉ፣ ውሳኔው የጉዳዩ ባለቤቶችን ያላሳተፈ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን የደመወዝ ጣሪያ እንዲቀመጥ የተሰጠው ምክንያት ከመርህ ውጪ፣ የተጨዋቾችን የዜግነት መብት ግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
ክፍያው ከአገሪቱ እግር ኳስ ውጤት ጋር የሚጣጣም እንዳልሆነ ቢያምንም ነገር ግን ለዚህ ተጠያቂው ተጨዋቾች ሊሆኑ እንደማይገባም ያምናል፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶ ተጨዋቹ፣ ሁሉም ውጤት ስለሚል ብቻ ውጤት እንደማይመጣ፣ ለውጤት ወጣቶችን ያማከሉ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ለችግሩ መፍትሔ መሆኑን ጭምር ተናግሯል፡፡
ሌላው በፌዴሬሽኑ ውሳኔ ላይ ተቃውሞ እንዳለው የተናገረው ዳዊት እስጢፋኖስ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑ በግለሰብ ላይ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ የማሳለፍ መብት እንደሌለው ነው የሚያምነው፡፡ (ለመጣጥፉ ዳዊት ቶሎሳ አስተዋጽኦ አድርጓል)