Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርአዋጁ ሁሉንም አስፈጻሚ አካላት ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ስላልሆነ ዘገባው ይስተካከል

አዋጁ ሁሉንም አስፈጻሚ አካላት ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ስላልሆነ ዘገባው ይስተካከል

ቀን:

ሪፖርተር ጋዜጣ እሑድ ነሐሴ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በወጣው ዕትሙ የፊት ገጽ ዜናዎች መካከል፣ ሐምሌ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በጌትፋም ሆቴል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ረቂቅ ላይ የተደረገ ሕዝባዊ ውይይትን የተመለከተ ዘገባ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ዘገባው እውነትነትን ያልጠበቀና ሚዛናዊነት የጎደለውን ይዘት ያካተተ በመሆኑ ይህን ደብዳቤ መጻፍ አስፈልጓል፡፡  

የዘገባው ርዕስ ‹‹የመከላከያና የደኅንነት ተቋማትን የማያካትት የአስፈጻሚ አካላት መቆጣጠሪያ አዋጅ መዘጋጀቱ ቅሬታ አስነሳ›› የሚል ቢሆንም፣ ከአዋጁ ረቂቅ ርዕስና መግቢያ ለመረዳት እንደሚቻለው አዋጁ ሁሉንም የአስፈጻሚ አካላት ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ሳይሆን፣ የአስተዳደር ተቋማትን የመመርያ አወጣጥና ውሳኔ አሰጣጥ ለመቆጣጠር የሚወጣ የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ የአስተዳደር ተቋማት የአስፈጻሚው አካል አንድ ክፍል ቢሆኑም ‹አስፈጻሚ አካላት› የሚለውን ሐረግ ‹የአስተዳደር ተቋማት› የሚለውን አገላለጽ በሚተካ መልኩ መጠቀም መሠረታዊ የጽንሰ ሐሳብ መፋለስ ያስከትላል፡፡

በዘመናዊው የመንግሥት አደረጃጀት አስፈጻሚው አካል ቢያንስ ሦስት የተለያዩ ዋና ዋና ተግባራትና ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ ከእነዚህም መካከል የመጀመርያ የሚሆኑት የሰው ልጅ መንግሥት በመመሥረት ራሱን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበሩት፣ የውስጥና የውጭ ሰላምና ደኅንነትን ለመጠበቅ የሚቋቋሙት እንደ ፖሊስና መከላከያ ያሉ የታጠቁ (ወታደራዊ) ተቋማት ናቸው፡፡ በሁለተኛው ምድብ  ተጠሪነታቸው ለአስፈጻሚው አካል የሆኑ በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአስፈጻሚው አካል ሦስተኛው ክፍል የገበያ እንቅስቃሴን ጨምሮ የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩና አገልግሎት የሚሰጡ የአስተዳደር ተቋማት ተብለው የሚጠሩትን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ይይዛል፡፡

በሕግና ፍትሕ  ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ አማካይነት የተዘጋጀው የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ረቂቅ ከስሙ ለመረዳት እንደሚቻለውም ከእነዚህ የአስፈጻሚ አካላት ክፍሎች ውስጥ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችንና የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን የሚመለከት ሳይሆን፣ የአስተዳደር ተቋማትን ለመግዛት የሚወጣ የሥነ ሥርዓት አዋጅ ነው፡፡ በመሆኑም የዘገባው ርዕስ በግልጽ ተጽፎ የሚገኘውን የአዋጁ ርዕስና ዓላማ በተሳሳተ መልኩ ያቀረበ ከመሆኑም በላይ የጽንሰ ሐሳብ ግድፈትን ያንፀባርቃል፡፡

በረቂቁ ላይ በተደረገው ሕዝባዊ የምክክር መድረክ ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ይህንን የተመለከተና ‹የፖሊስ፣ የመከላከያና የደኅንነት ተቋማት ለምን የዚህ አዋጅ አካል ሆነው ቁጥጥር አይደረግባቸውም?› የሚል ነው፡፡ ዘገባው ይህን እውነታ በተገቢው መልኩ ያንፀባረቀ ቢሆንም፣ ለዚህ ጥያቄና አስተያየት ከመድረኩ አቅራቢዎች የተሰጠውን ምላሽ ሳያካተት ቀርቷል፡፡ ከመድረኩ፣ የረቂቅ አዋጁን ያዘጋጀው ቡድን አባላት የአስተዳደር ተቋማት ከሚለው ቃል ትርጉም ጀምሮ በውስጡ የትኞቹን የአስፈጻሚ አካላት እንደሚመለከትና እንደሚገዛ፣ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃም የፖሊስ፣ የመከላከያና የደኅነት ተቋማት በዚህ አዋጅ ማዕቀፍ ውስጥ ለምን ሊካተቱ እንደማይችሉ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የፖሊስ የወንጀል ምርመራ ሥነ ሥርዓትን የሚገዛው ‹የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ› የተባለው የሕግ ማዕቀፍ መሆኑን እንዲሁም የፖሊስን የወንጀል መከላከል ሥራ በተመለከተ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በኩል የኃይል አጠቃቀም አዋጅ ረቂቅ እየተሰናዳ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የመከለከያና የደኅንነት ተቋማትም የሥራቸው ባህሪይ ምስጢራዊነት የተላበሰ በመሆኑ፣ የዘመቻና የግዳጅ አፈጻጸም ደንቦች ሊኖሯቸው እንደሚችል ነገር ግን አሁን በተዘጋጀው ረቂቅ ውስጥ ማካተቱ ተገቢ እንዳልሆነ ተብራርቷል፡፡ ሆኖም ይህ ከመድረክ የተሰጠው ምላሽ በዘገባው ያልተካተተ በመሆኑ፣ ዘገባው ከተሳታፊዎቹ በኩል የቀረበውን ጥያቄና ሥጋት እንጂ ከመሠረታዊ የመንግሥት አደረጃጀትና የሕግ መርሆዎች አንፃር ተብራርቶ የተሰጠውን ምላሽ ያላገናዘበ፣ ሚዛናዊነት የጎደለው ሆኗል፡፡

ከከበረ ሰላምታ ጋር

(አብዱለጢፍ ከድር፣  የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች  አማካሪ  ጉባዔ  ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ)

******

ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሚ ላጣው አቤቱታችንን ምላሽ ይስጥ

በተደጋጋሚ አቤቱታችን ስናቀርብ የቆየነው አመልካቾች ቁጥራችን ከ500 ሺሕ በላይ እንሆናለን፡፡ በቀጣሪና አስቀጣሪ ኤጀንሲዎች በኩል ተቀጥረን ለተለያዩ የግል ድርጅቶች፣ ለመንግሥታዊ ተቋማት፣ ለዕርዳታ ድርጅቶችና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች የጥበቃና ሌሎችም አገልግሎቶችን የምንሰጥ ሠራተኞች ከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛ እየደረሰብን እንደምንገኝ በመገለጽ አቤቱታ ስናሰማ ቆይተናል፡፡

አስቀጣሪ ኤጀንሲዎች በእኛ ስም ከሚቀበሉት ሙሉ ወርኃዊ የአገልግሎት ክፍያ ውስጥን 70 በመቶውን ለራሳቸው ወስደው ቀሪዋን ብቻ ያደርሱናል፡፡ በአገሪቱ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ተገን በማድረግ 30 በመቶ ደመወዝ የሚሰጡን እነዚህ የሥራ አገናኝ ወይም አስቀጣሪ ኤጀንሲዎች፣ ከሠራተኛው ደመወዝ የሚቆርጡትን የጡረታ መዋጮም ለግል ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ገቢ እንደማያደርጉ መረጃው አለን፡፡ ሠራተኛው የሥራ ዋስትና ስለሌለውና ያገኛትን ሠርቶ ለማደር ስለፈለገ ብቻ ለሦስተኛ ወገን እንደ ዕቃ እያከራየ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሠራተኛው አቤቱታውንና ብሶቱን በተደጋጋሚ ቢያስማም፣ ሰሚ አላገኘም፡፡  ክብርት ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ እርስዎም የእኛን አቤቱታ ሳይሰሙ አይቀሩም፡፡ ሕዝብና መንግሥት በሰጠዎ ሥልጣንና ኃላፊነት በኤጀንሲዎች ጉልበታችን እየተበዘበዘ የምንገኘውን ዜጎች፣ እባክዎ ፍትሕ እንድናገኝና ተገቢ ክፍያ እንዲፈጸምልን ያደርጉ ዘንድ እንማጸንዎታለን፡፡

(ከአክባሪዎችዎ ተበዝባዥ ሠራተኞች አንዱ ነኝ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ