Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በወለድ አልባ መርህ ላይ የተመሠረተ አገልግሎት በተሟላ መንገድ የሚሰጥ ባንክ ሥራ መጀመር ለተገልጋዮች የበለጠ አማራጭ ይሰጣል›› አቶ ጀማል ሙዘይን፣ የባንክ ባለሙያ

አቶ ጀማል ሙዘይን በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ለዓመታት ያገለገሉ የባንክ ባለሙያ ናቸው፡፡ ትውልድና ዕድገታቸው በአዲስ አበባ የሆኑት አቶ ጀማል፣ በትምህርት ረገድ ከዊንጌት ትህምርት ቤት እስከ ማሌዥያ የዘለቀ ቀለም ቀስመዋል፡፡ በጄኔራል ዊንጌት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ተከታትለው፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀው አላበቁም፡፡ የማስትሬት ዲግሪያቸውን በቢዝነስ ማኔጅመንት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በኢስላሚክ ፋይናንስ መስክ በማሌዥያ ተጨማሪ የማስትሬት ዲግሪያቸውን እየሠሩ የሚገኙት አቶ ጀማል፣ ከትምህርቱ ባሻገር በኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ በወጋገን ባንክና በሕብረት ባንክ በተለያዩ የሥራ መደቦችና ኃላፊነቶች በማገልገልም በፋይናንስ መስክ ልምድ አካብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የዘምዘም ባንክ አደራጅ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ ከጥንስሱ ጀምሮ ወለድ አልባውን ባንክ ለመመሥረት ሲንቀሳቀሱ የቆዩት አቶ ጀማል፣ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎት አብራርተዋል፡፡ ወለድ አልባ ባንክ ከመደበኛ ባንክ ስለሚለይባቸው የአገልግሎት ባህሪያት፣ ወለድ አልባ ፋይናንስ እስካሁን በምን አግባብ ሲቀርብ እንደቆየና ወደፊት ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ አገልግሎት ለመስጠት የሚቋቋሙት ተቋማት በምን አግባብ ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ፣ አቶ ጀማል የሰጡትን ትንታኔ አሥራት ሥዩም እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ወለድ አልባ ወይም እስላማዊ የባንክ አገልግሎት ከመደበኛው የባንክ አግልግሎት ስለሚለይባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች በማንሳት እንጀምር፡፡ ይህን ባንክ የተለየ የሚያደርገው ምንድነው?

አቶ ጀማል፡- በጠቅላላው ማንኛውንም የባንክ አገልግሎት በሦስት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ባንኮች የሚሰጡት አገልግሎት የክፍያ ሥርዓቱን ማቀላጠፍ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ አገልግሎት በመደበኛም ይሁን በወለድ አልባ ባንኮች የሚሰጥ አገልግሎት ነው፡፡ ሁለተኛው የአገልግሎት ክፍያ የሚጠየቅበት ሥራቸው  ነው፡፡ ይህም ቦንድ ግዥ ላይ፣ ሲፒኦ ማሠራት ላይ፣ ገንዘብ ማስተላለፍ ላይ፣ የውጭ ምንዛሪ ግዥና ሽያጭ ላይ፣ የባንክ መተማመኛ ሰነድ ወይም ሌተር ኦፍ ክሬዲትን ጨምሮ ሌሎችም ክፍያ የሚጠየቅባቸው የባንክ አገልግሎቶች አሉ፡፡ በእነዚህም አገልግሎቶች አሰጣጥ ላይ በመደበኛና በወለድ አልባ ባንኮች ላይ መሠረታዊ የሆነ ልዩነት የለም፡፡ ሌላውና ሦስተኛው በቁጠባና በተንቀሳቃሽ ሒሳብ የሚሰበሰቡ ሌሎችም ተቀማጭ ገንዘቦችን የገንዘብ እጥረት ወዳለበትና ወደ ተፈለገበት ቦታ ፈሰስ እንዲደረግ ማስቻል የባንኮች ዓይነተኛ ሚና ነው፡፡ እዚህኛው ሚና ላይ ነው የመደበኛና የወለድ አልባ ባንኮች መሠረታዊ ልዩነት የሚታየው፡፡

      ወለድ አልባ ባንኮች ከአስቀማጮች ለሚስበስቡት ገንዘብ ወለድ አይከፍሉም፡፡ ብድር ሲሰጡም ወለድ አያስከፍሉም፡፡ ከወለድ ባሻገር ብድር በሚሰጡባቸው መስኮች ላይ ለምሳሌ እንደ አልኮል፣ ትምባሆና አሳማ የመሳሰሉ ለሰው ልጅ ጎጂ የሆኑና በሃይማኖት የተከለከሉ ምርቶችን ከሚያመርቱ የንግድ ዘርፎች፣ እንዲሁም ገና ለገና በወደፊት ግምት ላይ ወይም ‹‹ስፔኩሌት›› በማድረግ ከሚሠሩ ጋር አብረው መሥራት አይፈቀድላቸውም፡፡ ሌላው ከመደበኛው ባንክ የሚለያቸው ሀብት ወይም ንብረት ተኮር መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ማለት በጥሬ ገንዘብ ከማደር ይልቅ ንብረት ወይም ዕቃ ገዝቶ ለተበዳሪው ማስተላለፍ ላይ የተመሠረተ የገንዘብ አገልግሎት ሲሆን፣ በሌላ ወገን ሥጋትን የመጋራት አገልግሎትም ከመደበኛው ባንክ የሚለይበት ነው፡፡ ሥጋትን በመጋራት ሒደት ትርፍንም ኪሳራንም ሊጋሩ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ባንኩ ብቻም ሳይሆን አስቀማጮችም ሥጋትን የሚጋሩበት አሠራር አለው፡፡ በመሆኑም በማክሮ ደረጃ ካየኸው፣ ተበዳሪው ላይ ብቻ የሚጫነውን ሥጋት ወደ ሌሎችም ማከፋፈል ጠቀሜታው እንደሚጎላ ይታመናል፡፡ በጥቅሉ ወለድ አልባ የባንክ አሠራር እንደ መደበኛው ባንክ ቢያገለግልም ወለድ አይከፍልም፣ እንዲሁም አያስከፍልም፡፡ በመሆኑም የወለድ አልባ ባንኮች አሠራር በሦስት መንገድ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ይኸውም እንደ ማንኛውም መደበኛ ባንክ የክፍያ ሥርዓቱን ማቀላጠፍና ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት፣ አንድ መደበኛ ነጋዴ የሚሸጡ ዕቃዎችን ገዝቶ ለተበዳሪዎች ማስተላለፍ ለምሳሌ የመኪና ብድር ለሚፈልግ መኪና ገዝቶ ለተበዳሪው ሊሸጥ ይችላል፡፡ እንዲሁም እንደ የንግድና የኢንቨስትመንት አጋር በመሆን በሽርክና ወይም በሽርካ ንግድና ኢንቨስትመንት ውስጥ ይሳተፋል፡፡ በእነዚህ አገልግሎቶቹ ወለድ አልባ ባንክ ከመደበኛው የባንክ ዘርፍ ይለያል ማለት ነው፡፡

      ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ እየተሰጠ ቢሆንም፣ ከላይ የጠቅስናቸውን አገልግሎቶች በተሟላ መንገድ ሳይሆን በተወሰኑት ላይ በተለይም ‹‹ሙረባሃ›› የሚባለው፣ ባንኩ እንደ ሻጭ ዕቃ ገዝቶ ለተበዳሪው የሚያስተላልፍበት ዘርፍ ላይ በስፋት እየሠሩበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለአስቀማጮች ጥቅም ማጋራትም በተወሰነ ደረጃ እየተተገበረ ነው፡፡ በወለድ አልባ መስኮቶች አሁን እየሠሩ ያሉ ባንኮች ትንሽ የማይባል ተቀማጭ ገንዘብ ማንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን በተቀማጭነት የተሰበሰበውን ገንዘብ በበቂ ሁኔታ በብድር መልክ ሥራ ላይ እንዲውል ለማድረግ የቻሉ አይመስለኝም፡፡ ለዘምዘም ባንክ ባደረግነው ጥናት እንደለየነውም ወደ ሥራ ሲገባ ትልቅ ፈተና ይሆናሉ ብለን የምንጠብቀው፣ ይህንን የመሰሉ የተሟላ የወለድ አልባ የብድር አገልግሎት ለመስጠት የሚገጥሙንን ችግሮች ነው፡፡ እነዚህም ውስጣዊና ውጫዊ ብለን የለየናቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ውስጣዊ ያልናቸው አንዱ የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ በፕሮጀክት ጥናት ላይ ከፍተኛ ልምድና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የምርምርና ልማት ሥራዎች፣ እንዲሁም የፕሮጀክት ሥራዎችን የሚመራው ክፍል በጣም ጠንካራ መሆን መቻል አለበት፡፡ ወለድ አልባ ባንክ ለተበዳሪዎች ገንዘብ ከማቅረቡ በፊት ብድር የሚሰጥባቸውን ዘርፎች በሚገባ ማጥናት ይገባል፡፡ ምክንያቱም በጋራ ኢንቨስት የምታደርግበት ገንዘብ ምን ላይ እንደሚውል በሚገባ ማወቅና ማጥናት ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ የተቋማዊና የሰው ኃይል አቅም፣ እንዲሁም የሲስተም አቅም ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

      ውጫዊ ፈታኝ ሁኔታዎች ከሚባሉት ውስጥ የሕግ ማዕቀፉ አንዱ ነው፡፡ እስካሁን ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁንም ፈታኝ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ገደቦች አሉ፡፡ ባንኮች በሌሎች የንግድና የሥራ መስኮች ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉት የገንዘብ መጠን ገደብ ተቀምጦለታል፡፡ ለወለድ አልባ ባንኮች ደግሞ በሌሎች የሥራ መስኮች ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደ መደበኛ ሥራቸው/ብድር የሚቆጠር ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ገደቦችና ከታክስ ጋር የተያያዙ ገደቦችም ይኖሩታል፡፡ ተደራራቢ ታክስም ሥጋት ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ሻጭና እንደ ባለድርሻ ባንኩ በሚሠራበት ጊዜም የገቢ ግብር፣ የትርፍ ግብር፣ የኤክሳይስ ታክስና ሌሎችም  ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን በሌሎች አገሮች ውስጥም እንደሚደረገው ወለድ አልባ ባንክ እንደ ባንክ ታይቶ እነዚህ ገደቦች ይስተካከላሉ ብለን እንገምታለን፡፡

      በውጫዊ ሥጋትነት የለየናቸው በዋናነት በአብዛኛው የማኅበረሰባችን ክፍል ዘንድ የሚስተዋሉት የሥነ ምግባርና የአመለካከት ችግሮች ናቸው፡፡ ታክስ ማጭበርበርና መሰወር፣ ተገቢውን የሒሳብ ሪፖርት ለመንግሥት አለማቅረብ የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ ምን ያህሉ የአገራችን ድርጅቶች ናቸው ግልጽ የሒሳብ መዝገብ የሚይዙት? ምን ያህሉስ በአግባቡ ኦዲት ደደረጋሉ? ምን ያህሉስ በተገቢው መንገድ ታክስ ይከፍላሉ? ትክክለኛ የዕቃዎችን ዋጋ ይተገብራሉ ወይ? የሚለው ሲታይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ይታሰባል፡፡ እንደ ባለድርሻ አብረን እንሠራለን ብለን ስንገባ፣ ከስሬያለሁ የሚለንን ነጋዴ በትክክል መክሰሩን የምናረጋግጠው በምን አግባብ ነው? የሚለው ትልቅ ፈተና ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት መሠረት አንድ አዋጭ መሆኑ የታመነበት ፕሮጀክት ገንዘብ ማግኘት የሚችለው በዕቃና አገልግሎት አቅርቦት እንጂ፣ ፕሮጀክቱን ለማስተግበር የሚያስችል ገንዘብ አይለቀቅለትም ማለት ነው?

አቶ ጀማል፡- በወለድ አልባ ባንክ አሠራር ብድር በጥሬ ገንዘብ ወደ ሒሳብ ገቢ የሚደረግበት አካሄድ አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ ለምሳሌ አንድ ፕሮጀክት ቢኖርህ ወለድ አልባ ባንክ የፕሮጀክት አጋርህ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ትርፍና ኪሳራህን የመጋራት አልያም ትርፍን ብቻ የመጋራት ስምምነት በማድረግ፣ ከሁለቱ በአንዱ መንገድ ባንኩ የፕሮጀክቱ የጋራ ባለቤትና ሸሪክ ይሆናል፡፡ እንደ ሁኔታው የፕሮጀክቱን ወጪ ሙሉ በሙሉ አልያም በመቶኛ የሚሰላ ለምሳሌ 70 በመቶ ገንዘብ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ የፕሮጀክቱ አዋጭነትና ሌሎችም ጥናቶች ተሟልተው ባንኩ የተወሰነውን የፕሮጀክት ወጪ የሚሸፍን ከሆነ፣ አንተ ቀሪውን ለምሳሌ 30 በመቶ ገንዘብ ታዋጣና ወደ ትግብራው ትገባላችሁ፡፡ ይሁንና ስምምነቱ ቀድሞ ሲደረግ ምናልባት ትርፍ የመጋራት ሁኔታው 50 በመቶ እኩል መካፈል ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የፕሮጀክቱ ባለቤት የፕሮጀክቱና የሥራው ፈጣሪ ስለሚሆን፣ ባንኩም ፕሮጀክቱን ቀን ተቀን ስለማይመራው የፕሮጀክቱን ተጋሪ ትርፍ በስምምነቱ በሚወሰነው መሠረት ከፍ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ኪሳራ ሲኖር ግን ለፕሮጀክቱ በተዋጣው ገንዘብ መቶኛ ላይ ብቻ መሠረት በማድረግ ይጋሩታል፡፡ 30 በመቶ ያዋጣው ወይም 70 በመቶ ያዋጣው እንዳዋጣው ልክ የኪሳራውንም መጠን ይጋራል፡፡ ካዋጣው በላይ በኪሳራ መጠየቅ አይፈቀድም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ግን በምን አግባብ የተቀመጠ ሥሌት ነው?

አቶ ጀማል፡- ትልቁ ነገር የንግድ ፍትሐዊነት፣ እንዲሁም መጀመሪያ ያደረግኸው ስምምነት ነው፡፡ የገነባኸውን ስም፣ ያዋጣኸውን ካፒታል፣ ጊዜህንና ጥረትህን በኪሳራ አጥተሃል፣ ከዚያ በላይ ልታጣ አይገባህም የሚል መርህ ነው፡፡ በዚህ ላይ የሸሪዓ ባለሙያዎች የበለጠ ሊያብራሩት ይችላሉ፡፡ ትርፍ ሲሆን ግን በስምምነታቸው ላይ የተመሠረተ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ባንኩ ለምሳሌ ለአንድ ኮንቴይነር ጭነት ሌተር ኦፍ ክሬዲት ቢሰጥ፣ ለዕቃው የሚያስፈልገው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ጥናት ይደረጋል፡፡ ከውጭ የሚገባው ዕቃ ዋጋው ከተጠና በኋላ ዕቃው ገብቶ ሲሸጥ፣ ከሚሸጥበት ዋጋ የምናገኘው ይህን ያህል ስለሚሆን እንካፈለዋለን የሚል ስምምነት በቅድሚያ ታስቀምጣላችሁ፡፡ ይህ አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ዕቃው በባንኩ ስም ይመጣና በዕቃው ዋጋ ላይ የተወሰነ ጭማሪ በማከል ይህን ያህል ግዛኝ ብዬ እንደ ባንክ ልጠይቅ እችላለሁ፡፡ በዚህ መሰሉ ስምምነት መሠረት ባንኩ ሙሉ በሙሉ አልያም በተወሰነ ድርሻ ዕቃውን አስመጥቶ ላንተ ሊሸጥልህ ይችላል፡፡ ሲሸጥልህም ሙሉ በሙሉ ወዲያውኑ ገንዘቡን ክፈል አይልህም፡፡ ዕቃውን የምትሸጥበት ዋጋ ሊወጣና የምትሸጥበት ጊዜም ሊወሰን ይችላል፡፡ ዕቃው ዋጋው ጨምሯል ቀንሷል የሚሉ ውጣ ውረዶች አይኖሩም፡፡ ቀድሞ ስምምነት በተደረገበት ዋጋ መሠረት ክፍያው ይፈጸማል፡፡ ለምሳሌ በአሥር ሚሊዮን ብር ያመጣኸውን ዕቃ ባንኩ 11.5 ሚሊዮን ብር እንድትከፍለው በመስማማት ወጪውን ቢሸፍንልህ፣ ይህንኑ ትመልሳለህ እንጂ የዕቃው ዋጋ ገበያው ላይ 13 ሚሊዮን ብር ወይም ከዚያ በላይ ቢያወጣ ያንን አስቦ አያስከፍልህም፡፡ ክፍያውም እንደ ስምምነታችሁ በየጊዜው አልያም ዕቃው ተሸጦ እንዳለቀ ሊፈጸም ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ መካከል ግን ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ቢከሰቱ ማለትም የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ቢኖር፣ ባንኩ በለውጡ ምክንያት የመጣውን የዋጋ ልዩነት የሚጠይቅበት አግባብ አለ?

አቶ ጀማል፡- ይህ እንደተደረገው ስምምነት ይወሰናል፡፡ የአጋርነት ወይም በሽርክና ስምምነት ከሆነ ባንኩ ኪሳራውን ይጋራል፡፡ ነገር ግን እንደ ሻጭ ወይም ‹‹ሙረባሃ›› በሚባለው ስምምነት መሠረት ከሆነ ደግሞ፣ ዕቃው ተገዝቶ የተሰጠው ደንበኛ ነው ኪሳራውን የሚሸፍነው፡፡ ኃላፊነቱ የባንኩ አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- በሦስት ተከፍለው የቀረቡት የወለድ አልባ ባንክ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዳሉ ሆነው፣ አንድ ገንዘብ አስቀማጭ የባንኩ ደንበኞች ከባንኩ ጋር የሚገቡት ስምምነት ይኖራል? ወለድ ስለማይከፈላቸው በምን አግባብ ይስተናገዳሉ? 

አቶ ጀማል፡- በሁለት መንገድ ይታያል፡፡ ገንዘብ አስቀማጮች በመሠረቱ በወለድ አልባ ባንክ ውስጥ እንደ ባለቤት ነው የሚታዩት፡፡ ልዩነታቸው ድምፅ አለመስጠታቸው ነው፡፡ ድምፅ የማይሰጡ ነገር ግን የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ሲደረግ የመጀመሪያዎቹ ተከፋይ ናቸው፣ ልክ እንደ ድምፅ የማይሰጡ ወይም ‹‹ፕሪፈረንሺያል ሼር›› ያላቸው ባለድርሻዎች ናቸው፡፡ ወልድ አልባ ባንክም ሁለት ዓይነት አሠራሮች አሉት፡፡ አንደኛው ‹‹ቀርድ›› ይባላል፡፡ በእኛ አገር እንደተለመደው ምንም ዓይነት ጥቅም የማይፈልጉ ሰዎች፣ በባንክ ገንዘባቸውን ያለ ወለድ የሚያስቀምጡበት ሥርዓት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አስቀማጭ ገንዘቡን በባንክ በሚያስቀምጥበት ወቅት ጥቅም የሚፈልግ ደንበኛ ነው፡፡ ገንዘባቸውን ባንክ በማስቀመጣቸው ጥቅም ማግኘት የሚፈልጉ አስቀማጮች፣ በጥቅልና በተናጠል የሚመደቡበት አሠራር አለ፡፡ በተናጠል የተወሰነ መስክ ላይ በሚውል ገንዘብ ከሚገኝ ጥቅም ተጋሪ መሆን የሚፈልጉ አሉ፡፡ በጥቅል የሚመደቡት ደግሞ ባንኩ ከሚሰጣቸው አጠቃላይ አገልግሎቶች ከሚያገኛቸው ጥቅሞች ለአስቀማጮቹ የሚደርሳቸውን እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ይህም ቢሆን አስቀማጮች ገንዘብ ለማስቀመጥ ሲመጡ በሚገቡት ስምምነት መሠረት የሚከናወን ነው፡፡ ገንዘቡን ለምን ያህል ጊዜ አስቀማጩ በባንኩ ማስቀመጥ እንደሚፈልግ በስምምነቱ ወቅት ስለሚያሳውቅ፣ ባንኩ በዚያ ጊዜ ውስጥ የሚያገኘው ጥቅም አስቀማጩ ባስመቀጠው ገንዘብ ልክ መጠን ተሠልቶ ከባንኩ ትርፍ ተካፋይ ይሆናል፡፡ ስምምነቱ ግን ባንኩ ያትርፍ አያትርፍ ሳይታወቅ የሚደረግ ነው፡፡ ባንኩ በአስቀማጩ ገንዘብ ሠርቶ ከሚያገኘው ትርፍ አስቀማጩን እንደ ስምምነቱ ተጋሪ ያደርጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተቀማጭ ገንዘቡ ለረዥም ጊዜ የሚቀመጥ ከሆነ የትርፍ ህዳጉ ሊጨምር ይችላል፡፡ ተቀማጭ ገንዘቡ ላይ የሚታሰበው ትርፍ በመቶኛ ቁርጥ ሆኖ በስምምነቱ ይቀመጣል፡፡ አንዳንዱ ኪሳራውን መጋራት አልፈልግም፡፡ ንፁህ ትርፉን ብቻ ነው መጋራት የምፈልገው የሚል አስቀማጭ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ወቅት የትርፍ ህዳጉ ሊያንስ ይችላል፡፡ ባንኩ ኪሳራ ሲያጋጥመው አስቀማጮችም ኪሳራውን የሚጋሩበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ባንኩ ይህንን ዓይነት አሠራር ካላመቻቸ አደጋ ውስጥ ሊጥለው የሚችል ሥጋት ውስጥ ስለሚወድቅ፣ አመጣጥኖ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የባንኩን ኪሳራ ለመጋራት የሚስማማ አስቀማጭ የሚያገኘው ትርፍም ከፍ ያለ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዓይነት አሠራር የአክሲዮን ባለድርሻዎች ሚና ምን ይሆናል?

አቶ ጀማል፡- የአክሲዮን ባለድርሻዎች የባንኩ ባለቤት እንደ መሆናቸው ድምፅ የመስጠት መብት አላቸው፡፡ ከአስቀማጮች የሚለያቸውም ይህ መብታቸው ነው፡፡ ድምፅ በመስጠት መብታቸው ተጠቅመው የባንኩን አካሄድ ይወስናሉ፡፡ ባንኩ ከሚያገኘው ትርፍ ባዋጡት ድርሻ ልክ ደግሞ ይካፈላሉ፡፡ ባንኩ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ ስለመሆኑ በቦርድ አማካይነት ይቆጣጠራሉ፡፡ በተቀመጠለት የአሠራር ሥርዓት መሠረት መሥራት አለመሥራቱን ተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይከታተላል፡፡ ወለድ አልባ እንደ መሆኑ መጠን የሸሪዓ ቦርድ ይቋቋምለትና በዚህ ቦርድ አማካይነት ክትትል ይደረግበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሸሪዓ ባለሙያዎች ክፍል ይኖረዋል፡፡ ኦዲትም ያደርገዋል፡፡ የአክሲዮን ባለድርሻዎች እንደ ማንኛውም ባንክ የባንኩ የጥቅም ተጋሪ ናቸው፡፡ አስቀማጮች ናቸው በተለየ መንገድ የሚስተናገዱት፡፡ እነሱም ቢሆኑ ድምፅ አይስጡ እንጂ፣ የትርፍ ተጋሪዎችና ባለድርሻዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አስቀማጮች ከባንኩ ትርፍ ከተካፈሉ በኋላ ነው ዋናዎቹ ባለአክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ ክፍፍል የሚደረግላቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- የወለድ አልባ የባንክ አግልግሎት እየሰጡ የሚገኙት መደበኛ ባንኮች ተሞክሮ እንደሚያሳያው ከሆነ፣ በንግድ መስክ ዕቃዎችን ከተወሰኑ አቅራቢዎች ለሚረከቡ ወለድ አልባ ተጠቃሚዎች አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

አቶ ጀማል፡- ባንኩ የተወሰኑ አቅራቢዎች ይኖሩታል፡፡ ባንኩ ከእነዚህ አቅራቢዎች ይገዛና በውክልና ላንተ ሊሰጥህ ይችላል፡፡ ዕቃውን ተቀብለህ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሁለት ኮንትራቶች ይተገበራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በመደበኛ ባንኮች በመስኮት እየቀረበ የሚገኘው ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት እንዲህ ያለው ውስን አገልግሎት ላይ ብቻ ማተኮሩ ይነገራልና የንግድ ሞዴሉ እንዴት ያለ ነው? አስቀማጭም ገንዘብ ተቀባይም ሥጋት ይጋራሉ የሚል መነሻ ካለ፣ አሁን ያሉት ባንኮች ይህንን በምን አግባብ እያተስተናገዱ ነው?

አቶ ጀማል፡- ይህ የእኔም ጥያቄ ነው፡፡ ባንኮቹ ከ37 ቢሊዮን እስከ 40 ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ በወለድ አልባ አገልግሎት አንቀሳቅሰዋል የሚል መረጃ አለ፡፡ የገንዘብ አገልግሎቱ ወይም ብድር አሰጣጡ ሲታይ የተንቀሳቀሰውን ገንዘብ አሥር በመቶ እንኳ የሚሞላ አይመስለኝም፡፡ በእንዴት ያለ የንግድ ሞዴል እንደተገበሩትና እንዴት ዘለቄታ እንደሚኖረው መታየት እንዳለበት አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ቅድም እንደገለጹት በጥቅሉና በተወሰነ የባንኩ የሥራ መስኮች ከሚገኝ ትርፍ መጋራት የሚፈልጉ አስቀማጮች አሉ፡፡ ይሁንና በመደበኛ ባንኮች በመስኮት የሚስተናገደው የወለድ አልባ አስቀማጭ ግን ከተወሰነ ዘርፍ ከሚገኝ ጥቅም ተጋሪ የሚሆንበት ዕድል ያለ አይመስልም፡፡ በጥቅል ከተባለ ወለድ ወደሚጠየቅባቸው መስኮችም ሊያስገባው ስለሚችል ማለት ነው፡፡ 

አቶ ጀማል፡- ከመደበኛ ባንኮች ጋር ሲነፃፀር የወለድ አልባ ተጠቃሚና ገንዘብ አስቀማጭ፣ ከጠቅላላው የባንክ አገልግሎት ከሚገኝ ጥቅም ተጋሪ ሊሆን አይችልም፡፡ በብዛት ‹‹ቀርድ›› የሚባለውና ምንም ዓይነት ጥቅም የማይታሰብበትን የወለድ አልባ አስቀማጮች አገልግሎት ነው የሚጠቀሙት፡፡ ባንኮቹም ይህንን ዓይነት አገልግሎት ነው የሚሰጡት፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ቀርድ›› ማለት በጊዜ ገደብ ከሚቀመጥ ተቀማጭ ገንዘብ ጋር ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ጀማል፡- ቀርድ በተንቀሳቃሽ ሒሳብ ውስጥ እንደሚቀመጥ ገንዘብ የሚታይ ነው፡፡ ተቀማጭ ገንዘብ እንደ መሆኑ የወለድ አልባ ተጠቃሚዎች ገንዘባቸውን የማስወጣትና የማስገባት አገልግሎት ከመደበኛ ባንኮች ያገኛሉ፡፡ ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ከተሰበሰበው ገንዘብ አብዛኛው በዚህ መንገድ የተሰበሰበ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኮች እስከ 40 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻሉበት መንገድ ያለ ወለድና ሌሎች የትርፍ ክፍያዎች በመሆኑ፣ አስቀማጭም ምንም የተንቀሳቃሽ ሒሳብ አገልግሎት ካልሆነ በቀር ሌላ ጥቅም ሳያገኝ ይህን ያህል ገንዘብ ማስቀመጡ አስገራሚ ሳይሆን አይቀርም፡፡

አቶ ጀማል፡- አስቀማጩ አማራጭ ማግኘት አልቻለም፡፡ በመደበኛው ባንክ ጥቅም የሚያስገኝ ሊገለገል የሚችልበት አማራጭ ወለድ አልባ አገልግሎት ማግኘት አልቻለም፡፡ የንግዱ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ አዋጭ በሆነበትና በወለድ ምጣኔና በዋጋ ግሽበት መካከል ባለው ከፍተኛ ልዩነት ወይም ወለድ ከዋጋ ግሽበት በእጅጉ ባነሰበት አግባብ፣ ገንዘብን ባንክ ማስቀመጥ ብዙም ፋይዳ በሌለበት ወቅት ለማንም ሰው ግልጽ እንደሚሆነው አዋጭ አይደለም፡፡ እንዲያውም በተቻለ መጠን በዚህ ወቅት ሥራህን በሙሉ ብድር ላይ በተመሠረተ ገንዘብ ብታንቀሳቅስ ተጠቃሚ ትሆናለህ፡፡ ክፍያንም ለማቀላጠፍ ይጠቅማል፡፡ ነገር ግን ምርጫ ከማጣትና ገንዘብን ቤት ውስጥ ከማስቀመጥ፣ ለዋስትናውም ሲባል ገንዘብ ወደ ባንክ መውሰድ ስለሚመርጡ፣ እንዲሁም የግንዛቤ ችግር ስላለ እንጂ በዚህ ወቅት በባንክ ከማስቀመጥ መበደር ለብዙዎች አዋጭ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደፊት ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ሲመጡ፣ በአሁኑ ወቅት በመስኮት ከሚቀርው አገልግሎት የተለየ ምን ተጨማሪ ነገር ይዘው ይመጣሉ? ደንበኛው የሚያገኘው ጥቅም ምንድነው? 

አቶ ጀማል፡- ሙሉ በሙሉ የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት መጀመር ለማኅበረሰቡ አንድ አማራጭ ነው፡፡ ዘምዘም ባንክ ሲመጣ ሰው ሁሉ በጉጉት ጠብቆ ነበር፡፡ ነገር ግን የተሟላ የወለድ አልባ አገልግሎት ቀረና በመስኮት ተገደበ፡፡ ነገር ግን አሁን እንደገና የተሟላ ወለድ አልባ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ሲመጣ እንደ ባለአክሲዮን የባለቤትነት ስሜት ማሳደሩ አንዱ ነው፡፡ በመስኮት የሚሰጠው አገልግሎት ምንም እንኳ የሸሪዓውን ሥርዓት ያሟላ ቢሆንም፣ በተወሰ ደረጃ አሁንም ጥርጣሬ ያላቸው አንዳሉ ይታወቃል፡፡ በወለድ አልባ መርህ ላይ የተመሠረተ አገልግሎት በተሟላ መንገድ የሚሰጥ ባንክ ሥራ መጀመር በዚህ መንገድ መጠቀም ለሚፈልጉ ተገልጋዮች የበለጠ አማራጭ ይሰጣል፡፡ ዋናው ግን የወለድ አልባ አገልግሎቶች በርካታ ራሳቸውን የቻሉ ሌሎች ዘርፎች አሉዋቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወለድ አልባ ባንኮችም ሆኑ ተጠቃሚዎቹ በሸሪዓው መሠረት ‹‹ዘካ›› ወይም በዓመቱ ከተገኘው ትርፍ 2.5 በመቶ ለማኅበራዊና ለሰብዓዊ ሥራዎች ለማዋል ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወለድ አልባ ባንክ ይህንን ማድረግ ግዴታው ነው፡፡ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ይህንን ድጋፍ የመስጠት ሥራ ማከናወን አለባቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር የኢንቨስትመንት ባንክ አካሄድም ሊኖረው ይችላል፡፡ ወለድ አልባ ባንኮች ትልልቅ በሆኑ ኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ለምሳሌ መንግሥት ወደ ግል በሚያዛውራቸው ኩባንያዎች ላይ ጥናት በማድረግና ድጋፍ በመስጠት፣ እንዲሁም የአክሲዮን ኩባንያዎች እንዲመሠረቱ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችሉ አካሄዶች ሊመጡ ይችላሉ፡፡ የድርጅት ወይም የባንክ አክሲዮን መግዛት ፈልገው በሃይማኖታቸው ምክንያት መግዛት ላልቻሉትም አካታች የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ታግዛቸዋለህ፣ አማራጭ ትሆንላቸዋለህ ማለት ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...