ኅብረተሰቡን የሚያማርሩ ደካማ የአገልግሎት መስኮች ዛሬም ብዙ ጥያቄዎች ሲቀርብባቸው ይሰማል፡፡ ደንበኞች አገልግሎት ለማግኘት ከሚመላለሱባቸው መካከል የኤሌክትሪክና የውኃ ፍጆታ ክፍያ መፈጸሚያ ተቋማት ይጠቀሳሉ፡፡
በእነዚህ ተቋማት በኩል ክፍያ ለመፈጸም የሚያጋጥመው የተገልጋይ ወረፋ ስቃይ የተሞላበት ነበር፡፡ የውኃና የመብራት አገልግሎት ክፍያዎችን ሲያስተናግድ የቆየው የግል ኩባንያ ሥራውን እንዲያቆም ተደርጎ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እንዲፈጸም ማድረግ ከተጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁንና ከጅምሩ ‹‹ትሻልን ፈትቼ ትብስን አገባሁ›› ዓይነት ጉዳይ ተገልጋዩ ሲያጋጥመው እያታዘብን ነው፡፡
በባንኩ የሚሰበሰበው ክፍያ በተለያዩ አማራጮች በኩል መክፈል የሚቻልባቸው አሠራሮች አሉት፡፡ ሐሳቡ መልካም ነው፡፡ ክፍያዎች በቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲፈጸሙ መነሳት ቅልጥፍናን ይጨምራል፡፡ ጊዜና ገንዘብን ይቆጥባል እሰየሁ ነው፡፡ ወደፊትም እንዲህ ያለው አሠራር ሊስፋፋ ይገባዋል ያሰኛል፡፡ ለውኃ፣ ለመብራት፣ የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ለሚያስከትለው ቅጣት፣ ለኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች የሚፈጸሙትንና ሌሎችንም ክፍያዎች በባንክ በኩል እንዲከናወኑ ማድረጉ እንደሚታሰበው የተቀላጠፈና የተሻለ አገልግሎት መሆን ሲገባው የተገላቢጦሹን ሕዝብ እያሰቃየ ይገኛል፡፡
ሌላም መነሳት የሚገባው ጥያቄ አለ፡፡ እንዲህ ያሉ ከሕዝብ አገልግሎት ክፍያ የሚሰበስቡ የመንግሥት ተቋማት በሙሉ ክፍያቸው በንግድ ባንክ ብቻ እንዲሰበሰብ ማድረግ ለምን ግዴታ ይሆናል? የሚል ነው፡፡
ከተገልጋዮች የሚሰበሰበውን የአገልግሎት ክፍያ ለመሰብሰብ ንግድ ባንክ ከሌሎች ባንኮችና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በምን ብቃቱና በምን ዝግጅቱ ተመረጠ? የሚለውን ጥያቄም ማስከተል ተገቢ ይሆናል፡፡ የንግድ ባንክ የተረከባቸውን ሥራዎች በተገቢው የደንበኛ ዕርካታ ከቅልጥፍና ጋር አዛምዶ ቢያቀርብ ኖሮ ሌላውን በይደር አቆይተን ይሁን ባልን ባልከፋን ነበር፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉትን ተራ የአገልግሎት ክፍያዎች ለመሰብሰብና ለማስከፈል በየቅርንጫፎች የሚታየው ወረፋና ግርግር ግን ‹‹የጉድ ቀን ቶሎ አይመሽ›› ያሰኛል፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ መደበኛ የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ባንኩ ቅርንጫፎች የሚመጣው ደንበኛ፣ ወር በጠባ ቁጥር የመብራትና የውኃ ዕዳ ለመክፈል በሠልፍ ከሚጠብቀው ተገልጋይ ጋር ሲደመር ባንኩን ሌላ ተቋም ያደርገዋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡም ቢሆን የተበላሸና ደንበኛም ደንበኝነቱ ሳይሆን ተራ ወረፋ ጠባቂነቱ ይጎላና ባንኩን እንዲጠላ ያደርገዋል፡፡ የባንኩ ሥራ ወረፋ ማስጠበቅ እስኪመስል ድረስ ዝብርቅርና ትርምሱን እየታዘብን ነው፡፡ ተገልጋዮች አማራጭ የክፍያ ዘዴዎችን እስኪለማመዱና ወደ ባንክ ቅርንጫፍ መምጣት እስኪያቆሙ ድረስ ይህ ችግር ይስተዋላል ማለት ነው፡፡ በዚያ ላይ የአገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎት ሲሻው እየተዘጋ ሲሻው እየተከፈተ ሲሻውም ኔትወርክና ሲስተም የለም በሚበዛበት ሁኔታ ደንበኞች መፈናፈኛ በሚያሳጣ ሁኔታ በየባንኩ ደጅ ተጨናንቀው የምናይበት ጊዜ እየተበራከተ የተረበሸ ከተማ ውስጥ ያለን እስኪመስለን ድረስ አቤት ወረፋ እያሰኘን ነውና ይታሰብበት፡፡
ስለዚህ ባንኩ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ሲያስብ በዚያው ልክ ለአገልግሎቱ ቅልጥፍና በሚረዳ መልኩ የራሱን አቅም ማጎልበት አለበት፡፡ ለተሻለ አገልግሎት የታሰበው መፍትሔ ሌላ ችግር እንዳያመጣም ቶሎ እልባት ይበጅለት፡፡ በሌላ በኩል መንግሥታዊ ተቋማት የአገልግሎት ሒሳባቸውን እንዲሰበሰብላቸው ንግድ ባንክን የሚመርጡበት መመዘኛ ግልጽ ይውጣ፡፡ የመንግሥት ተቋም ስለሆነ ብቻ ‹‹እከክልኝ ልከክልህ›› ዓይነት አካሄዳቸው ይፈተሽ፡፡ ለሌሎች ባንኮችም ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ባንኮች ብቻም ሳይሆኑ ክፍያ ለመሰብሰብ አቅሙና ብቃቱ ያላቸው ተቋማት ይዘምኑ፤ ይታዩ፡፡ ሥራውም ይሰጣቸው፡፡ አብጦ ሊፈነዳ የደረሰው ባንክ በላይ በላዩ እየተጨመረለትና እየተጨመረበት ቀውስ ከማስከተሉ በፊትም አቅሙ ይፈተሽ፡፡
ስለዚህ የውድድር ሜዳው ምቹ ይደረግ፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያም ለንግድ ባንክ ብቻ ያደላውን አሠራር መቀየር መሆን አለበት፡፡ ሁሉንም በኩል ዓይን የሚያይ አሠራር ይፈጠር ካልን አገልግሎቶችን በውድድርና በብቃት ላይ እንዲመሠረቱና እንዲመዘኑ እናድርግ፡፡ ከዚህ ቀደም የኮንዶሚኒየም ቤቶች ክፍያ በንግድ ባንክ ብቻ ይስተናገድ መባሉ መንግሥትን ክፉኛ እንዳስተቸው የምናውቀው ነው፡፡ ዛሬም እንዲህ ዓይነት ነገር መደገሙ ተገቢ አይደለም፡፡ ከዚሀ በኋላ በስፋት ይተገበራል የተባለውና በባንክ በኩል ይፈጸማል የተባለው የታክስ ክፍያም ወደ ንግድ ባንክ የመምጣቱ አዝማሚያ ስላለ፣ ወደ አንድ ወገን ያዘነበለው አካሄድ ጭርሱኑ ቀውስ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ይደረግበት፡፡ ደንበኞች በፈለጉትና በሚያመቻቸው ባንክ በኩል መክፈል የሚችሉበት ዕድል ይሰጣቸው፡፡ አለዚያ ግን ለውጭ እየከፈቱ ለአገር ውስጥ በሞኖፖል መዝጋት የሚያስተዛዝብ ይሆናል፡፡
ይህም ካልሆነ፣ ሌላው አማራጭ ንግድ ባንክን ቢያንስ ሁለት ቦታ መክፈል ነው፡፡ አንደኛው መደበኛ የባንክ አገልግሎቱን የሚሰጥበት እንዲሆን ማድረግ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የአገልግሎት ክፍያዎችንና ሌሎችንም ሒሳቦች የሚሰበስብ ራሱን የቻለ የንግድ ባንክ ተቋም ይፈጠር፡፡ ንግድ ባንክ አሁን ባለው አዝማሚያ የአገልግሎት ክፍያ የሚሰበሰብ ሌላ ተቋም መፍጠር ብቻም ሳይሆን፣ በባንክ ደረጃም ቢሆን ለሁለት መከፈል የሚገባው ተቋም ይመስለኛል፡፡ ለትልልቅ ኩባንያዎች የባንክ አገልግሎት የሚሰጥና ለግለሰብ ተጠቃሚዎች አገልግሎት የሚሰጥ ተብሎ ቢከፈል ምናልባት የሚታዩበት የአገልግሎት መዘበራረቆች ይፈቱ ይሆናል፡፡ አሊያ በላይ በላዩ እያጎረሱት ባንኩን እንዲያንቀው ማድረግ እንዳይሆን ያሠጋል፡፡
ለንግድ ባንክ ከአቅሙ በላይ የማሸከም አባዜ፣ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውም ይንፀባረቃል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት የመድን ሽፋን በመንግሥት ድርጅቶች በኩል ብቻ እንዲሆን ተብሎ የሚተገበረው ያልተጻፈ አሠራር ዛሬም አልተወገደም፡፡ የነፃ ገበያን ከመፃረር ባሻገር፣ የመንግሥት ኩባንያዎች የተሻለ ዋጋና አገልግሎት ቢያገኙ እንኳ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ በማድረግ ወጪያቸው የሚያንር አካሄድ በመሆኑ ይህ ጉዳይ መታየትና መታረም አለበት፡፡
እንዲህ ያለው ችግር በግል ተቋማትም ይታያል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍና ሳይሆን፣ በዘርና በወንዝ ልጅነት ሲቧደኑና ሲጠቃቀሙ ይታያል፡፡ ቢዝነስ በቢዝነስነቱ እንጂ ዘር ሲቆጠርበት ሙያነቱ ገደል ይገባና የለውጥ ባላንጣ ይሆናል፡፡ የመንግሥትና የግል እየተባለ የታጠረው ኬላ ጥራት ባለውና ቅልጥፍና በተላበሰ ወጪ ቆጣቢ በሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ የተጉላላውን ኅብረተሰብ የሚክስ አገልግሎት በአዲሱ ዓመት ማየት እንሻለን፡፡