Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሕፃናትና የሴቶች ንፅህና መጠበቂያዎች አምራቹ በ100 ሚሊዮን ብር ካፒታል ዳግም ሥራ ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ላይላክ›› የተባለው የሕፃናትና የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ቁሶች ማምረቻ ድርጅት፣ ከአሥር ወራት ሥራ ማቆም በኋላ በ100 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ መመለሱን ገለጸ፡፡ ከዚህ ቀደምም ለሰባት ዓመታት ሥራ አቁሞ እንደነበር ታወቋል፡፡

ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ቃሊቲ አካባቢ የሚገኘውን ማምረቻ ማዕከሉን ለጋዜጠኞች ያስጎበኘው ይህ ድርጅት በ1989 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን፣ በወቅቱ ከጣሊያን አገር በተገዛ ማሽን ‹‹ላይላክ›› በሚል መጠሪያ በኢትዮጵያ የተመረቱ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ለገበያ አስተዋውቆ ነበር፡፡ ይሁንና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሥራውን ለማቆም እንደተገደደ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ መሐመድ ዩሱፍ ገልጸዋል፡፡

ሥራ ሲጀምር ከነበረው የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች በተጨማሪ በ2006 ዓ.ም. የልጆች ንፅህና መጠበቂያ ምርትን በማካተት ሲንቀሳቀስ የቆየው ላይላክ ኩባንያ፣ በ100 ሚሊዮን ብር ካፒታል የማምረቻ ማዕከል እንደ አዲስ በማቋቋም በ2010 ዓ.ም. ዳግም ወደ ምርት ሥራው እንደተመለሰ አቶ መሐመድ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን በምንዛሪ እጥረት ምክንያት ለአሥር ወራት ሥራ አሁንም አቁመን ነበር፡፡ አሁን በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ተመልሰናል፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሥራ የጀመሩት ማሽኖች በዓመት 74 ሚሊዮን ፍሬ የሕፃናት ንፅህና መጠበቂያ፣ እንዲሁም 86 ሚሊዮን ፍሬ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያዎችን የማምረት አቅም እንዳላቸው ተገልጿል፡፡ ማሽኖቹ ከቻይና የተገዙና የአሜሪካ ስታንዳርድን  እንዳሟሉ የገለጹት አቶ መሐመድ፣ ማሽኖቹን የሚያንቀሳቅሱ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችም ለሰባት ወራት በውጭ ዜጎች ሥልጠና ተከታትለው ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ሥራ እንደገቡ አብራርተዋል፡፡  

በቀን ለስምንት ሰዓት የሚሠሩት ማሽኖቹ በደቂቃ 600 የሴቶችና 500 የሕፃናት ንፅህና መጠበቂያዎችን የማምረት አቅም ቢኖራቸውም፣ ከአቅም በታች ለማምረት እንደተገደዱ ሲገልጹ፣ ‹‹ይህን ያህል ምርት ለማምረት ከስምንት እስከ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፤›› በማለት የዶላር እጥረት በምርት ሒደቱ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ አመላክተዋል፡፡

ለ50 ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረው ይህ ድርጅት፣ በቅርቡ በመንግሥት በተካሄደ ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ በየዓመቱ የአንድ ቢሊዮን ፍሬ የሴቶችና ሁለት ቢሊዮን የልጆች ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ፍላጎት ይታያል፡፡ ይሁንና ከ85 በመቶ በላይ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ከውጭ እንደሚገቡ የገለጹት የድርጅቱ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ሞኢዝ አባስ፣ ‹‹ከውጭ የሚገቡትን በአገር በቀል ድርጅታችን ምርቶች በመተካት የምንዛሪ ችግሩን በጥቂቱ ለማገዝ እየተንቀሳቀስን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በርካታ መሰናክሎችን በማለፍ ድርጅቱ ምርቶቹን ለማስፋፋት እንደቻለ የገለጹት አቶ ሞኢዝ፣ ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የውጭ ምንዛሪ ሥርጭቱ አጥጋቢ አለመሆን፣ የብድርና ገንዘብ ተቋማት ወቅታዊ ምላሽ አለመስጠት፣ በመንግሥት አካላት በተለይም በፖሊሲ አውጪውና በአስፈጻሚው መካከል ያሉ የአሠራር ክፍተቶች፣ እንዲሁም ለውጭ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ያደላ ድጋፍ በመንግሥት በኩል መኖሩ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ፈታኝ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

በንፅህና መጠበቂያ ምርቶች መስክ ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ እንዳላቸው ያወሱት ሌላው የድርጅቱ አማካሪ አቶ ሰላሃዲን መሐመድ፣ መንግሥት የአገር ውስጥ ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታት እንዳለበት በአጽንኦት ገልጸው፣ ‹‹በእጅ ያለን ሀብት በአግባቡ መያዝ ያስፈልጋል፤›› በማለት መንግሥት ትኩረቱን ለአገር ውስጥ ባለሀብቶችም እንዲሆን አሳስበዋል፡፡

ኩባንያው ጥሬ ዕቃዎችን ከአሜሪካና ከጃፓን እንደሚያስመጣ የገለጹት አማካሪው፣ ‹‹የምንጠቀመው ጥሬ ዕቃ ከፍተኛውን የጥራት ደረጃ ያሟላ ወይም ‹A› ግሬድ የሚባለውን ደረጃ የያዘ ሲሆን፣ ለአገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ለውጭ ገበያም መቅረብ የሚችል ምርት ነው፤›› ብለዋል፡፡ አምራቹ ጥሬ ዕቃ በሚፈልገው መጠን ማግኘት ቢችል፣ ከጎረቤት አገሮች ባሻገር ወደ አሜሪካም ምርቶቹን መላክ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

ድርጅቱ የማምረቻ ቦታውን ባስጎበኘበት ዕለት፣ ለበጎ አድራጎት ተቋማት ልግስና አድርጓል፡፡ ለጌርጌሶኖን የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል የሕፃናትና የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ለሁለት ዓመታት በቋሚነት ለመለገስ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ስለእናት ለተሰኘው የሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅትም ለአንድ ዓመት የሚቆይ ችሮታ አድርጓል፡፡ ለአበበች ጎበና፣ ለአባድር ትምህርት ቤት፣ እንዲሁም በቅርቡ አራት ልጆችን በአንዴ ለተገላገለችው እናት ፍሬሕይወት አዲሱም አራቱ ልጆቿ እስኪያድጉ የሚጠቀሙበት የሕፃናት ንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የተለገሰው ቁሳቁስ በገንዘብ ሲሰላም ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን የድርጅቱ ባለቤት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች