‹‹ተጥሎ የነበረም የተነሳም ዕገዳ የለም›› ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ከዓመት በፊት በምርጫ ቦርድ አማካይነት ያላግባብ ውሳኔ መተላለፉን በመቃወም የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ነባር አመራሮች ፓርቲው መፍረሱን አሳውቆ የነበረው ቡድን፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካይነት ተጥሎበት የነበረው ‹‹ዕገዳ›› መነሳቱን አስታወቀ፡፡
አመራሮቹ ይህን ያስታወቁት ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2011 በተለያዩ የአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮችና የፓርቲው አጠቃላይ እንቅስቃሴን የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ሲዘጋጁ ነው፡፡
ምንም እንኳን በአቶ አዳነ ታደሰ ፕሬዚዳንትነት የሚመራው ብሔራዊ ምክር ቤቱ ‹‹ዕገዳው›› መነሳቱን ቢገልጽም፣ የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ወ/ሪት ሶልያና ሽመልስ፣ ‹‹ቦርዱ የጻፈው ደብዳቤ ከዚህ በፊት የተጣለ ምንም ዕገዳ አለመኖሩን እንጂ፣ አዲስ የተሰጠ ውሳኔ አያሳይም፡፡ በተደጋጋሚ ታግደናል ብለው ስለጻፉ ቦርዱ አግዷቸው እንደማያውቅ ለመግለጽ እንጂ አዲስ ውሳኔ አይደለም፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ልደቱ አያሌውን ጨምሮ ሌሎች የምክር ቤትና ሥራ አስፈጻሚ አባላትን ያካተተው ይህ ነባር አመራር በፓርቲው ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት በርካታ ውዝግቦች ውስጥ የነበረ ሲሆን፣ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በከበደ ጫኔ (ዶ/ር) የሚመራውን ቡድን ዕውቅና መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፈው የፓርቲው አመራር በሁለት ጎራ ተከፍሎ ሕጋዊ የፓርቲው አመራር እኔ ነኝ እያለ የሰነበተ ሲሆን፣ የቦርዱን ውሳኔ ተከትሎ ግን የነባር አመራሮቹ ጥያቄ ተቀባይነት ማውጣቱ የሚታወስ ነበር፡፡
ሕገወጥ የሆነ ውሳኔ ተላልፎብናል ሲል የነበረው አቶ ልደቱ አያሌውን ያካተተው የነባር አመራሮች ወገን ውሳኔውን በመቃወም ከዚህ ቀደም ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በመቀጠል ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም ከወራት በፊት ለተሾሙት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ውሳኔው እንዲታጠፍና በብሔራዊ ምክር ቤቱ ላይ ተጥሎ የነበረው ዕገዳ እንዲነሳ ሲጠይቁ መሰንበታቸውን አቶ አዳነ ታደሰ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ስለሆነም ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ላይ ተጥሎ የነበረው ዕገዳ እንደተነሳላቸው በመግለጽ፣ የረቡዕ ዕለት መግለጫ ይህን ለሕዝቡ ለማሳወቅና በቀጣይ ፓርቲው የሚያከናውናቸው ተግባራት ለማስረዳት ያለመ እንደሆነ አክለው አብራርተዋል፡፡
አቶ ልደቱ አያሌውን ያካተተው የፓርቲው ሰባተኛ ጠቅላላ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴም፣ ስለጠቅላላ ጉባዔው አካሄድና ዝግጅት ማብራሪያ እንደሚሰጥ አቶ አዳነ አስታውቀዋል፡፡
በፓርቲው አመራሮች መካከል አለመግባባት የተፈጠረው፣ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት በገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ሲካሄድ በነበረው ድርድር ምክንያት እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዚህም መሠረት የተወሰኑ የፓርቲው አመራሮች በድርድሩ መቀጠል አለብን ሲሉ፣ የተወሰኑት ደግሞ በድርድሩ መቀጠል አያስፈልግም የሚል አቋም በማራመዳቸው የተነሳ ነበር፡፡
ከዚህ ውዝግብ በኋላ አቶ ልደቱን ያካተተው ብሔራዊ ምክር ቤት ታኅሳስ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ አቶ አዳነ ታደሰን በፕሬዚዳንትነት መምረጡን አሳውቆ የነበረ ቢሆንም፣ በድጋሚ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ፕሬዚዳንትነት ለጫኔ ከበደ (ዶ/ር) በመስጠቱ ውዝግቡ ፓርቲው ፈርሷል እስከሚል መግለጫ ድረስ ደርሶ ነበር፡፡
በዛሬው ዕለት መግለጫ እንደሚሰጡ የሚጠበቁት የፓርቲው ነባር አመራሮች፣ አቶ አዳነ ታደሰን በፕሬዚዳንትነት የመረጠው ብሔራዊ ምክር ቤትና የሰባተኛው ጠቅላላ ጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት መሆናቸው ታውቋል፡፡