የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከግል ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰጡትን የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር እንዲያቋርጡ ያሳለፈው ውሳኔ ጥያቄ አስነሳ፡፡
ኤጀንሲው ከግል ኮሌጆች ጋር በትብብር የሚሰጡትን የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር እንዲያቋርጡ ደብዳቤ የጻፈባቸው ኤቢኤች ከተባለ አማካሪ ድርጅት ጋር ለተባበረው ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ከዮም ኮሌጅ ጋር ለሚሠራው ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ ከናሽናል ኮሌጅ ለተጣመረው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ ኮንቲኔንታል የጤና ኢንስቲትዩት ጋር ይሠራ ለነበረው ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ታውቋል፡፡
በጤና አጠባበቅ የትምህርት መስክ በድኅረ ምረቃ ፕሮግራም፣ በጤና መኮንንነት የትምህርት መስክ ደግሞ በቅድመ ምረቃ መርሐ ግብር የሚያስተምረው አዲስ ኮንቲኔንታል የጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመሥራት የጀመረውን ፕሮግራም አቋርጦ ሳለ፣ እንደ አዲስ ደብዳቤ መጻፉ ግርታ እንደፈጠረባቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኃላፊ ገልጸዋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ማንኛውም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የሚሰጠውን የትብብር የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲያቋርጥ ያሳለፈውን የመጨረሻ ማሳሰቢያ ጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደማይቀበለውም አሳውቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ኤቢኤች ከተባለ አማካሪ ድርጅት ጋር በትብብር የሚሰጣቸውን የትምህርት ፕሮግራሞቹን የመገደብ ሥልጣን ኤጀንሲው እንደሌለው አስታውቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተቋሙ ጋር በትብብር የሚሰጠው የትምህርት ፕሮግራም፣ የከፍተኛ ትምህርትና የዩኒቨርሲቲው መቋቋሚያ አዋጆች በሚፈቅዱለት አግባብ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከግል ተቋማት ጋር በትብብር እንድሠራ ይፈቀድልኛል ያለውን የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 1 (ማንኛውም ተቋም ተገቢና ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ሆኖ ሲያገኘው የድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን በሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች እንዲሰጥ ሊያደርግ ይችላል) ሥር የሰፈረውን ድንጋጌ በመጥቀስ፣ የትምህርት ፕሮግራሞቹን እየሰጠ የሚገኘው ሕጉ በሚፈቅድለት አግባብ መሆኑን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው ካምፓሱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በ2000 ዓ.ም. ከተቋቋመው ኤቢኤች አማካሪ ድርጅት ጋር ያለው አሠራርም ሕጋዊ መስመሩን የተከተለ መሆኑን በዕለቱ አሳውቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ መዘምር ሰይፉ እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው በሚሰጣቸው የትምህርት ፕሮግራሞች ኤቢኤች የማማከርና የሎጂስቲክስ ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነት ብቻ ነው ያለው፡፡ የተማሪዎች ምልመላ፣ ምዝገባና ሌሎችም የአካዴሚክ ጉዳዮችን የሚመለከተው ፕሮግራሙን በበላይነት የሚመራው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው ሚኒስቴሩ ያስተላለፈውን ማሳሰቢያ የሚቃረን፣ ዜጎችን የሚያሳስት፣ ሕጋዊ ላልሆነ ሥልጠና ገንዘባቸውና ጊዜያቸውን እንዲያጠፉ የሚያደርግ ማስታወቂያ በብሥራት ኤፍኤም 101.1 ሬዲዮ መልቀቁንና እንዲቋረጥ ማድረጉን ኤጀንሲው በፌስቡክ ገጹ ላይ አስነብቧል፡፡ ዜጎችን ለማሳሳት የሚለው አገላለጽ ግን የአንጋፋውን ዩኒቨርሲቲ ስም የሚያጠለሽ በመሆኑ፣ ኤጀንሲው ዩኒቨርሲቲውን በግልጽ ይቅርታ እንዲጠይቅ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ኤጀንሲውን በሕግ ለመጠየቅ እንደሚገደድ አቶ መዘምር ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኤጀንሲው ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮችን ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ገረሱ፣ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከግል ተቋማት ጋር የትብብር ሥልጠና መስጠት እንደማይችሉ፣ የጀመሩትንም እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ የተሰጣቸው በ2006 ዓ.ም. እንደነበር፣ ነገር ግን ተግባራዊ ሳይደረግ እንደቆየ ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎቹ ከግል ተቋማት ጋር አብረው መሥራት እንደሚችሉ በሕግ የተቀመጠ ነገር ቢኖርም፣ የተለያዩ የአሠራር ክፍተቶች በመታየታቸው የትብብር ሥራቸውን እንዲያቆሙ ተጠይቀዋል ብለዋል፡፡
ከታዩ የአሠራር ችግሮች መካከል ዩኒቨርሲቲዎች ዋነኛ ተልዕኳቸውን ወደ ጎን ብለው በትብብር የትምህርት ፕሮራሞች የሚያገኟቸውን የውስጥ ገቢዎች ማሳደድ፣ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብን እንደ ግል ተቋም ዝቅ የማድረግ ነገር መታየቱን ገልጸው፣ ‹‹በኤጀንሲው እንደ መንግሥት ተቋም ይመዘገቡና ተማሪዎችን ለመቀበል ሲሆን ግን እንደ ግል የትምህርት ተቋም የመቁረጫ ነጥብ ዝቅ አድርገው ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ማስታወቂያ ሲያስነግሩም እንደ ግል ተቋም በማስመሰል እንደሆነ፣ ይህም በአዋጅ የተቀመጠላቸውን ግዴታ የሚፃረር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ በበኩላቸው በኤቢኤች ካምፓስ የሚሰጠው የትምህርት ፕሮግራም 99 በመቶ የድኅረ ምረቃ መሆኑን፣ ለዚህም የመቁረጫ ነጥብ እንደማያስፈልግ፣ ተወዳድረው ያለፉትን የድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ተማሪዎች እንደሚቀበልና ከዚህ ዓመት ጀምሮ ግን የሕክምና ትምህርት በቅድመ መርሐ ግብር ማስተማር መጀመሩን፣ ከ460 ነጥብ ጀምሮ ያስመዘገቡ ተማሪዎች ተፈትነው መግባታቸውን በማስረዳት በትብብር የሚሰጠው የትምህርት ፕሮግራም አንድም የጥራት ችግር እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ጥራት አለበት የሚባለውም አንድም የኤጀንሲው አካል ወደ ካምፓሱ ሄዶ አስፈላጊውን የፍተሻ ተግባር ሳያከናውን እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር የሚሰጠው ፕሮግራም በአሁኑ ወቅት ከ1,000 በላይ ተማሪዎች እንዳሉት፣ ማስጠንቀቂያውንም እንደማይቀበሉና ፕሮግራሞቹም እንደማይቋረጡ የኤቢኤች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርቆስ ፈለቀ (ዶ/ር) አሳውቀዋል፡፡