Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበር ተመሠረተ

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበር ተመሠረተ

ቀን:

በኅትመት፣ በብሮድካስትና የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን ውስጥ የሚሠሩ አርታኢያን፣ የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበርን በጎልደን ሮያል ሆቴል ባካሄዱት ስብሰባ መሥርተዋል፡፡

ምሥረታው ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ለዚሁ ዓላማ በተጠራው ስብሰባ ፈቃደኛ ሆነው በተገኙት የግል፣ የክልልና የፌዴራል መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ተከናውኗል፡፡

አባላቱንና ጋዜጠኞችን ከማንኛውም የሚደርስባቸው ጫናና ጥቃት ለመከላከልና ሙያዊ ብቃት እንዲሻሻል ተደራጅቶ የመሥራት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመረጃ ነፃነትና የመደራጀት መብቶች እንዲጠናከሩና በሕግ፣ በፖሊሲና በአፈጻጸም ማሻሻያዎች እንዲስፋፉ ውጤታማ ግፊት ማድረግ ማኅበሩ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ ነው፡፡

በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበር በመመሥረቱ በግል እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ መንግሥት ለማኅበሩ ስኬትና ለሌሎች የመደራጀት ጥያቄዎች ትብብር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

በምሥረታው ጉባዔ ላይ የተገኙት ባለሙያዎች በማኅበሩ የመተዳደሪያ ደንብ ይዘትና አደረጃጀት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን፣ በተጨማሪ በሚገባ ዓይተው አስተያየት እንዲሰጡና ለማስተካከል ቀጠሮ ተይዟል፡፡

መሥራች አባላት የመተዳደሪያ ደንቡን በጥልቀት ለማየት በቂ ጊዜ አለመሰጠቱን ጠቁመው፣ ማስተካከያዎች እንዲካተቱበት በዝርዝር ሐሳባቸውን ለመግለጽ ተስማምተዋል፡፡

በተጨማሪም የምሥረታ ጉባዔው ወደፊት እንዲካሄድና የዕለቱም ስብሰባ መነሻ ጉባዔ ተደርጎ ይወሰድ የሚል ሐሳብ በተሳታፊዎች ተነስቶ የነበረ ቢሆንም፣ በቅድመ ዝግጅት ወቅት በተጨባጭ ያጋጠሙ ችግሮችን ታሳቢ በማድረግ ምሥረታውን አካሂዶ መሻሻል ያለባቸውን ነጥቦች አካትቶ በማሻሻል፣ ምሥረታው እንዲካሄድ በሚለው ሐሳብ ላይ ድምፅ ተሰጥቶ ምሥረታው ተከናውኗል፡፡

በዚህም መሠረት ሰባት አባላት ያሉት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ እንዲካሄድ በጉባዔተኛው በድምፅ ተወስኖ ምርጫ ተካሂዷል፡፡

የተመረጡት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶችን በማካተት፣ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጉባዔው ተስማምቷል፡፡  

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበር ምሥረታ ላይ ጥሪ ተደርጎላቸው ፈቃደኛ የሆኑ ከ40 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ እነሱም ከ20 በላይ በክልል፣ በመንግሥትና በግል መገናኛ ብዙኃን የሚሠሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡

በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ መሠረት የማኅበሩ አባላት በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ሕግ መሠረት ተመዝግበው በየጊዜው በሚወጡ በኅትመት፣ በብሮድካስትና በበይነ መረብ የሚሠሩ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አርታኢያንን የሚያካትት ነው፡፡

በዕለቱ እንዲገኙ ለበርካታ የግል፣ የመንግሥትና የክልል መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጥሪ የተደረገ መሆኑ በአደራጅ ኮሚቴው ተገልጿል፡፡

ሆኖም የማኅበሩ ምሥረታ በዕለቱ ፈቃደኛ በመሆን በተገኙ ባለሙያዎች ተከናውኗል፡፡

ማኅበሩ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የሚሠሩ አርታኢያንና ጋዜጠኞች በሥራቸው የሚያጋጥሟቸውን የፖለቲካ፣ የንግድና የፖለቲካ ጫናዎች ለመከላከል የሚሠራ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ በዋናነት የአባላቱን ሙያዊ አቅም መገንባት፣ ሥልጠና ማመቻቸት የማኅበሩ ተግባር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የተመረጡት ሰባት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ባካሄዱት ስብሰባ የአሀዱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና አዘጋጅ ፍትሕአወቅ የወንድወሰን ሊቀመንበር፣ የዘሪፖርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ብሩህ ይሁን በላይ ምክትል ሊቀመንበር፣ እንዲሁም የፎርቹን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ፋሲካ ታደሰ ዋና ጸሐፊ ሆነው ተመርጠዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...