Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርችግራችን የተወሳሰበና የማይቻል መስሎ መታየቱ ለምን ይሆን?

ችግራችን የተወሳሰበና የማይቻል መስሎ መታየቱ ለምን ይሆን?

ቀን:

በአሰፋ ደፍርስ

ማሰብ፣ መግባባት፣ የመንግሥት በጎ ፈቃደኝነት፣ ከራስ በላይ ለአገር፣ ለወገን መስዋዕትነት መክፈልና ሌሎች የበለፀጉት አገሮች የደረሱበት ለመድረስ ወስኖና ቆርጦ በኅብረት ተባብሮ ከመነሳትና አብሮ ከመሥራት ይልቅ፣ የራስን ጥቅም የማስቀደምና በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል ወደፊት ከመራመድ ይልቅ ወደ ኋላ መጎተትና እያነስን መሄድን ማን አስተማረን? ከየትስ የመጣ ባህል ነው? ሳይታሰብ ወጥተን ለምንቀረው ሕይወት አገርንና ወገንን በድለን አንጥፋ? ካለፉት ለመማር ለምን አንሞክርም? አገራችንን በእርሻና በእርባታ ብቻ ሌሎች ከደረሱበት በልጠን የምንሄድበት ብዙ ዕድል እያለን ሁሌ ዳቦ ለማኝ ሆነን ቀረን? ምን ይሆን የጎደለን? ለም አፈር፣ ውኃ፣ የሚሠራ ጉልበት፣ በመስኩ የሠለጠኑ ምሑራን ጠፍተው ወይስ በራስ ወዳድነት የራስን ጥቅም በማሳደድ የአገርን ጉዳይ ችላ ብሎ ላሳደገውና ላስተማረው ወገን ሳይበቃ የሌሎች አገልጋይ ሆኖ ይሆን? ወይስ የሚያሠራ መሪ በማጣት ይሆን? ሰብላችንን የምንሸጥበት ገበያ ይሆን ያጣነው? ወይስ ሰብሉን በተገቢውና በአስፈላጊው ሁኔታ ሳናመርት ቀርተን ይሆን? ወይስ የሚሠሩ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ባገር ጠፍተው ይሆን? ቢጠፉም አይደንቀንም! ይኼው የምትሰሙት ነው።

በደቡብ አፍሪካ 150 ኢትዮጵያዊያን ታሰሩ፣ 140 ተፈቱ ይሉናል። ዋ ኢትዮጵያ! ኩሩ ሕዝብ፣ ለሰው ይተርፍ የነበረ፣ ተዋርዶ በሰው አገር ሲታሰር አስፈታን ይሉናል፣ የሚገርም ነው፡፡ ሃምሳ ወጣት ኢትጵያዊያን ለዘመናዊ ባርነት ውጭ ለሥራ ልንሰድ ነው ይባላል። ይልቅ የተቸገርነውን ያህል ተቸግረን ለምን ወደ ሥራ አንሰማራም? ሁሉ በእጃችን ሁሉ በደጃችን ሆኖ ሲስተሙን የሚመሩት፣ የሚያቅዱትና የሚያሠሩ ከወሬ በዘለለ እምብዛም ችሎታ የሌላቸውና ከሥራ ይልቅ መሽሞንሞን፣ መታየትንና በየታላላቅ ሆቴሎች ብርጭቆ ማጋጨትን የሚያፈቅሩና የሚያዘወትሩ፣ ከሥራ ይልቅ ለስብሰባ ቅድሚያ የሚሰጡ በመሆናቸውና ሁኔታውን በአንክሮ የመመልከት ችሎታቸው ያነሰ በመሆኑ ነው፡፡ የዘመናዊ የባሪያ ነጋዴዎች ወገኖቻችንን (Modern Slavery) ለየዓረቡ አገሮች በመመሳጠር እየላኩ ወዳሰቡትም ሳይደርሱ፣ የባህር ዓሳ ራት ሆነው መቅረታቸውን የዓለም ዜና የገለጸው የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ከሁሉ አስቀድመን የወገኖቻችንን ያላግባብ እንደወጡ መቅረትን፣ ወገን ያለ ፍርኃት ወጥቶ መግባትን፣ በየችሎታው ሥራ አግኝቶ ራሱን ችሎ እንዲኖር መፍትሔ ስናገኝለት ብቻ ነው አርፈን እንደ ልባችን መወያየት የምንችለው።  ይኼንን ስንመልስ ብቻ ነው መፍትሔ ልናገኝ የምንችለው። ወጣቱ እኮ የሚሠራውን አጥቶ በየመንገዱ፣ በየቡና ቤቱ፣ በየሻይ ቤቱ ሲንገላታ እያየን እኮ ነው።  

ይኼውም የሻዩና የቡናው ለሙ አፈራችን በያለበት ተኝቶ፣ ወጣቱ የሚሠራውን አጥቶ ከእየ ዳር አገሩ ወደ ዋና ከተማ እየፈለሰ፣ የሚያርስበት አቅም ባለመኖሩ፣ የመማር ዕድሜ ያለውም ዕድሉን በማጣቱ በየቅጣጫው ዕድሉ በመራው እየተጓዘ ከተማውን ከማጣበብም አልፎ ወደ ወንጀል ሥራ በመሰማራት ላይ ነው ቢባል ያስደንቅ ይሆን? ውኃ ጠፍቶ በመስኖ ለመሥራት፣ ለማርባትና ለማረስ ባንችል አንድ ነገር ነው። እግዚአብሔር የሰጠንን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም ወሰን ቢኖረን፣ የማስተማርና የማሰማራት ችሎታ ባይኖረን፣ አፈራችን ፈጽሞ ለአዝርዕት የማይስማማ ደረቅና አሸዋማ ቢሆንና ብዙ የቴክኖሎጂ ጥበብ ቢጠይቀን ኖሮ ምክንያት በኖረን ነበር። ሁሉ እያለን ወገኖቻችን የልመና ኮረጆ ይዘው በየጎዳናው ሲሽከረከሩ፣ ወጣት እናት ልጇን አዝላ ስትንከራተትና ስትለምን ማየቱ ምን ያህል ያሳፍረን ይሆን? ኢትዮጵያዊነት ኩራትና አለኝታነት ነው ስንል ወገናችንን ማብላት፣ ማጠጣትና የዓመት ልብሱን እንኳ ልንጥልበት ያልቻልን የት ላይ ነው የእኛ ኩራትና አለኝታነት? የአንዳንዶቻችን ቪላ ቤት ውስጥ መቀመጥ፣ ራሴን ጨምሮ፣ የመንግሥት ወኪሎቻችን ላንድ ክሩዘር መንዳት፣ ወገኖቻቸው ጥረውና ግረው ሠርተው በከፈሉት የታክስ ገንዘብ ከልማት ይልቅ ለመንግሥት ባለሥልጣናት የተሽሞነሞነ ቢሮና ተሽከርካሪ ወንበር፣ ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት ማመላለሻ መኪና ከውጭ በልመናም ይሁን በብድር በተቀላወጠ ገንዘብ በመግዛት ማንቀባረር ይሆን ታላቁ ሥራችን? ወይስ የባለሥልጣናትን ልጆች ውጭ አገር ልኮ ማስተማርና ያ ደሃው ሕዝብ እንደ ተጎሳቆለ መኖሩን መርጠን ይሆን?

በየከተማው የተሠሩት ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ይሆኑ የልማት ምልክታችን? ይህ ከሆነ ልማት ግማሽ ጎናችን ራቁት ግማሽ ወገናችን ሳይበላ እያደረ የጥቂቶቻችን ማግኘትና መዘባነን ምንም ዋጋ የሌለው ከንቱ ባዶነት ነው፡፡ መንግሥታችን ልክ እስራኤላዊያን ነፃነታቸውን ባገኙበት ዘመን በ1945 እስከ 1950 ዓ.ም. ድረስ ያደረጉትን ቆራጥነትና ውሳኔ ለእኔ ማለት ቀርቶ ለአገራችን ለኢትዮጵያ ብሎ እንዲነሳ፣ ከግለኝነት ይልቅ በጋራ እንዲያስብ እንዲተጋና ነባር ባህሉን ተከትሎ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብሎ እንዲነሳ፣ የተማረውና በሥልጣን ላይ የሚገኝ ማንኛውም ክፍል ተበረታትቶ እንዲሠራ ቢደረግ ውጤታማ እንደምንሆን እርግጠኛ ነኝ።

ከዚህ ቀጥዬ የምሰጠውን ምክር ለበስ ፕላን በጥሞና ተገንዝቦ ሁላችንንም እንደየ ችሎታችን እየጠራ፣ የመንግሥት ወኪሎች እንዲያማክሩንና ሥራ ላይ ለማዋል እንዲነሳሳ በአንክሮ ጥሪዬን አቀርባለሁ። አንብቦ እንኳ ያገባኛል የሚል ባለሥልጣን ያለ እንኳ አይመስለኝም እንዲያው ለመሞከር እንጂ። ይህ ውትወታዬ ለግል ጥቅሜ እንዳልሆነም ተገንዘቡልኝ፡፡

የዓረቡ አገሮች ከማንኛውም አገሮች ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ይቀርባሉ፡፡ በዘይት ሀብት የበለፀጉ ሲሆኑ፣ በሰው ሠራሽ ራሳቸውን ለማበልፀግ ከመሞከር ሌላ በተፈጥሮ የደረቁ አገሮች ብዙ መሆናቸው የታወቀ ሆኖ ሳለ፣ ዛሬ እኛ ከዓረብ በተለይም ካሳዑዲና ዓረቢያና ከመሳሰሉት የብርቱካን ጭማቂ፣ የጣሳ ወተት፣ የታሸጉ የወተት ተዋጽኦዎች ማስመጣታችን የሚገርም ጉዳይ ነው። አይመስላችሁም? ታይፍ የሚባለው አንዱን ደረቅ የሳዑዲ ወረዳቸውን ለምና ገነት አስመስለው ከጅግጅጋ አስበልጠው ለም አገር አለን ብለው ሲደሰቱና ሲጠቀሙበት፣ ሁሉ እያለን እኛ እንደሌለን ሆነን መገኘታችን አያሳዝንም? ሰሊጥ፣ ኑግ፣ የጉሎ ፍሬ የመሳሰሉት የዘይት ወይም የቅባት አዝዕርትና ቡናን በገፍ ለዓለም ገበያ መላክና የእነርሱን ፔትሮ ዶላርም ሆነ የሌሎቹን የቴክኖሎጂ ውጤት በቀላሉ ወደኛ ማስመጣት ስንችል፣ ሁሉንም ለማኝ ሆነን እስከ መቼ ነው የምንኖረው? የቻይናን ወር ከወር የማይዘልቁ ተልካሻ ዕቃዎች በማግበስበስ መቼ ይሆን የራሳችን ሠርተንና አልምተን ሌሎች ወደ ደረሱበት የምንደርሰው? ብለን በኅብረት የመነሻ ጊዜያችን ነውና እንንቃ! ይህንን ስል ሌሎች ሰብሎቻችንን፣ የእንስሳት ሀብታችንን እንዳላየ ማለፌ ሳይሆን፣ ለመንደርደሪያ ያህል ነው።

የመጀመርያዋ የቡና አብቃይ አገር እስከ 1620ዎቹ ድረስ ቡናችን ከጀበል ሐበሽ አፋፍ ወደ ኦክስፎርድ እግር አውጥቶ በእንግሊዝ የነገሥታቱ፣ የመሳፍንቱና የመኳንንቱ መደሰቻና መዛበቻ ሆኖ ከ80 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አሜሪካ ቦስተን ብቅ ብሎ ቲ ፓርቲ የተባለውን የፖለቲካ ስያሜ ተክቶ፣ ከዚያም ወደ ደቡብ አሜሪካ ተሸጋግሮ የደቡብ አሜሪካኖች የሀብት ምንጫቸው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን የመጀመሪያዋ የቡና ባለቤት ከመባል የዘለለ ያገኘችው ፋይዳ በጣም አነስተኛ ነው። ዛሬ ደግም ቬትናም ዋናዋ የቡና አብቃይና ተወዳዳሪ እየሆነች እኛ በተለመደው ከጭራነት አልዘለልንም፡፡ ባለቤት ያቀለለውን ባለ ዕዳ አይቀበልም እንዲሉ ወገናችን ምሁሩ ሰሙ ንጉሥ፣ አገሩ ሳትንከባከበውና እንደ ልቡ ምርምሩን እንዳይሠራ በመደረጉ የነበረውን ዕውቀት ለቬትናም ሰጥቶ፣ እነሆ ዛሬ ቬትናም በቡና ወደመታወቅ ደረጃ እየደረሰችና የዓለምን ቡና አብቃይ አገሮች ልታሽመደምድ እየሮጠች ነው። ሁሌም ካለፈ በኋላ የምንነቃ ነንና ሁሉንም በግርምት ማለፋችን ቀርቶ አሁን እንነሳ።                                                                      ብርቱካን፣ መንደሪን፣ ማንጎ፣ ግሽጣና ሙዝን የመሳሰሉት የፍራፍሬ ዓይነቶች ማብቀልና መጠቀም ስንችል፣ ከውጭ የምናስመጣበትና እጥፍ ዋጋ የምንከፍልበት የውጭ ምንዛሪ ጠፍቶ በተሸማቀቅንበት በአሁኑ ጊዜ፣ ልናፈራና ለሌሎች መትረፍ ስንችል ከውጭ በውድ ዋጋ ማስመጣት የሚያሳዝንም የሚገርምም ነው። ይህ ሁኔታ መሪዎቻችንን በተለይም የግብርና ሚኒስቴር ባለሥልጣናትን ትዝብት ላይ ሳይጥላቸው የቀረ አይመስለኝም። ይህንንም ስል ያለፈውን እያወገዝን እንኑር ማለቴ ሳይሆን አሁን እንነሳ ለማለት ነው። መሪዎች መመርያና ምክር ቤቱ የሚያወጣውን አዋጅ ሥራ ላይ ያውሉ ማለቴ እንጂ፣ ሥራውን ይሥሩ ማለቴም አይደለም። ዕድሉ ከተሰጠና ምክራችን አዎንታ ቢያገኝ ለመሥራቱም ሆነ በጀት ለማፈላለጉ በግንባር ቀደምትነት አለሁ እላለሁ።  እንድታውቁልኝ የምፈልገው የሐበሻ ምን ይሉኝ የሚለውን ባህላችንን ብዙም ያለ ቦታው የማስተናግድ ሰው አይደለሁምና  ብዙ አትገረሙ። የምችለውን እችላለሁ ባይ ነኝ እንጂ እንደ ድንገተኛ ዝንም (ዝናብ) በጎርፍ አጥለቅልቄ የምጠፋ አይደለሁም። ለምናገረው ሁሉ እቆማለሁ።                                                                     

በኢትዮጵያ ከሕፃናት መካከል ወተት ጠጥቶ ያደገ? የሚያድግስ ስንቱ ነው? ዛሬ የኢልካ ጥናት እንደሚያሳየው አዲስ አበባ ብቻ 600,000 ሊትር ወተት ስትሻ፣ ያለን የወተት ብዛት ውኃ ተቀላቅሎበትም በሊትር 60,000 ብቻ ነው። የምርት ማነስ ለጥቂቶች የገበያ ዋጋ ሰማይ ጠቀስ ሲያደርግላቸውና መግዛትና መጠጣት የሚችሉ ብቻ የታደሉ ሆነው ባሻው ዋጋ ገዝተው ሲጠጡና ሲደሰቱ፣ አቅመ ቢሶቹ ግን ከወተት ተለያይተዋል። ለዚህ ወተት እጥረት ችግሩ መሬት፣ ውኃ ወይስ የሠለጠነ የሰው ጉልበት ጠፍቶ ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ ሁሉም አለን፡፡ ነገር ግን መንግሥትና ማድረግ የሚችሉ ሰዎች የማመዛዘንና የአሠራር ብልኃትና ችሎታ የላቸውም፡፡ ወይም ከግል ጥቅም የዘለለ የሚያስቡ ባለመሆናቸው ብቻ ነው ከማለት ሌላ የምለው የለኝም።

አሁንም ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ያላቸውን ኃላፊነት ተገንዝበው ለመሥራት ይዘጋጁ ብለን በአንድነት ብንነሳ የተሻለ ይሆናል። ኢትዮጵያ እንኳን ልጆቿ ሊቸገሩ ቀርቶ ችግር ባለፈበት ሊያልፉ አይገባቸውም ባይ ነኝ። ለምን? ከላይ እንደ ጠቀስኩት ሁሉም አለንና። ከራሳችን ተርፈን ለጎረቤት አገሮች የማከፋፈል አቅሙ እያለን የበይ ተመልካች መሆናችን የሚገርም ነው፡፡ ለምንስ ሆነ? ብንል እላይ እንደ ጠቀስኩት ነው።

ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አሥረኛ መሆኗ እየታወቀ፣ በትክክል እንስሳቱ ባለመያዛቸውና የአስተዳደር (Management) ጉድለት በመኖሩ ለኢትዮጵያ ሆቴሎች ሥጋ ከደቡብ አፍሪካ ጭምር እንደሚገባ ደርሼበታለሁ። የእኛን ከብት አያያዝና አስተዳደር በተመለከተ የተጎሳቆሉትንና በሚገባ የተያዙትን ተመልክታችሁ ፍረዱ። አንድ ራሱን የቻለ ሀብታም ተናግሮ መደመጥ የሚችል ግለሰብ ‹ኒዶ ወተት ያጠነክራል› እያለ ለገበያ ሲያመቻች ሰማሁት፡፡ ከወገኑ ጋር ተገናኝቶ ምን ብናደርግ አገራችንን ከችግር ልናድናት እንችላለን ከማለትና አዋቂዎችን አሰባስቦ ከመወያየት ይልቅ፣ የሰውን ገበያ ሲያሟሙቅ ማየቱ አሳዝኖኛል። ምናልባትም ለእኛ የሚታየን ዓይታየው ይሆናል አይፈረድበትም። ሁሉን ደግሞ አዋቂ ሁን ማለት አይቻልምና። ዕውቀታቸውም ከዚያ የዘለለ ስላልሆነ።                                                                      በሠለጠነው መንገድ በጎቻችንና ፍየሎቻችንን አርብተን ለዓለም ገበያ ማዋል ስንችል፣ በዓመት የሙስሊሞች ፆም በሚገባበትና በሚወጣበት ጊዜ ብቻ እንደ ወረርሽኝ ገበያው ተጧጡፎ ያ ከያለበት የተለቃቀሙ በጎችና ፍየሎች በየዓረብ አገሮች ከተሸኙ በኋላ፣ የበግም ሆን የፍየል ዋጋ ለአገሬው ሕዝብ ሰማይ ጠቀስ በመሆን ችግር ይፈጠራል። ዋጋው መወደዱ ሳይሆን የምርቱን ማነስና የተተኪ የበግም ሆነ የፍየል መጥፋት፣ ሌላውን አርብቶ ገና እስኪተካና ያ ዓመት መጥቶ የበግ መንጋ የባቡሩንና የመርከቡን ጣቢያዎች እስኪያጣብብ ድረስ ያው በገሌ መሆኑ ነው።

ምን ይኼ ብቻ? የቀንድ ከብትም በየጊዜው ከቦረና እየተለቀሙ ለዓረብ አገሮች ገበያ ሲላኩ ተተኪው እንዴት ይሆን ተብሎ እየታሰበ አይደለም፣ ይህም ይታሰብበት። ኢትዮጵያ ስንዴ ልመና በየዓመቱ የምዕራባዊያንን በር ማንኳኳት ከጀመረች ብዙ አሥርተ ዓመታት አልፈዋል። እኛም ኢትዮጵያ ተቸገረች፣ ሕዝቡ የሚቀምሰው የሚልሰው ጠፍቶ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ በረሃብ አለንጋ ሊገረፍ ነው፣ ድረሱልን ከማለት ያለፍንበት ዘመን ላለፉት 50 ዓመታት የተለመደ እሮሮ ሆኖ ኖሯል፣ የሚቀጥልም ይመስላል። አሁን ችግሩ ምንድነው ያጣነው? የሚታረስ መሬት? ለመስኖ ውኃ? አራሽ ገበሬ? ሥልጡን የተማረ የግብርና ባለሙያ ወይስ እንዲያው የልመና ዕውቀታችን የረቀቀ መስሎ ታይቶን ይሆን?                                                                                                             ያለውን የወተት እጥረት ሰፋ አድርገን የወተት ላሞች ዕርባታ ብንጀምር አገራችን ከራሷ ተርፋ ለጂቡቲ፣ ለየመን፣ ለኤምሬትስ፣ ለኳታርና  በጠቅላላው ለዓረብ አገሮች ማቅረብና የውጭ ምንዛሪ ለአገራችን እንደሚያስገኝ በእርግጠኝነት ለመናገር እደፍራለሁ። ግን በወሬ ሳይሆን ለውጤት የተዘጋጁ መሪዎች የነገን ትውልድ በልማትና በልበ ሙሉነት ለአገራቸው አለኝታ እንዲሆኑ ማዘጋጀት፣ እንደ እንግሊዞች፣ እስራኤሎችና አሜሪካኖች በልበ ሙሉነት አድገውና ለወገናቸው አለኝታ እንዲሆኑ አሁን ካለንበት የልመና ኑሮ ወጥተን ምሳሌ መሆን ይገባናልና እንነሳ፣ እንተባበር፣ ለወሬ ጊዜ አንስጥ ነው ጥሪዬ።

ወገኖቼ በዚህ የምትስማሙ ከሆነ እንገናኝ፣ እንነጋገርና መፍትሔ እናምጣ። አገር በወሬ አይመራም፡፡ ካድሬዎች ላለፉት 50 ዓመታት ፖለቲካ አውርተዋል፣ አፋጅተዋል፡፡ ከማነስ ከፍ ያልንበት ጊዜ የለምና ያ ሁኔታ ይለወጥ፡፡ እኛ ሠርተን፣ አሠርተንና አገርን ጠቅመን ለነበርነው ጆሮዋችሁን አውሱን። ዶክተር ነኝ ብሎ መዘባነን ልምድ ከሌለ ዋጋ ሊኖረው አይችልምና ልምዱም ትምህርቱም ካለን ጋር ተገናኙ፣ ልምድም አካብቱ ነው የእኔ ጥሪ። አገርን ካላለማን ይህ ሁሉ ሽር ጉድ እንዳይፈርስ ተጠንቀቁ ነው ምክሬ። በማንኛውም ጊዜ ያገባኛል የሚል ባልሥልጣንም ይሁን ባለሙያ ሊያናገረኝ ከፈለገ፣ በኢሜይል አድራሻዬ ልንገናኝና ልንወያይ እንችላለንና ከወሬ ወደ ሥራ እንሰማራ፡፡ መንግሥትም ለቴሌቭዥን ስክሪን ብቻ ሳይሆን ከእኛው ከወገኖቹ ጋር እንዲገናኝ እየጋበዝሁ ጥሪያችሁን በጉጉት እጠባበቃለሁ፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...