Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየሕገወጥ ቤቶች ግንባታና መፍትሔው

የሕገወጥ ቤቶች ግንባታና መፍትሔው

ቀን:

በደረሰ መርሻ

በቅርቡ በፓርላማ ተሻሽሎ የፀደቀው የካሳ አዋጅ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታቸውን ለሚለቁ ዜጎች በልማት እንዲሳተፉ የሚረዳቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ችግሮችም አብረው ሊታዩና መፍትሔ ሊበጅላቸው ይገባል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ ለአንዱ ያለኝን  ሐሳብ መግለጽ ነው፡፡

ሰሞኑን በተለያዩ የአገሪቱ ቦታዎች ሕገወጥ ግንባታን በተመለከተ ያሉትን ጉዳዮች ስንከታተል ነበር፡፡ እንደምንሰማው ከሆነ የችግሩ መነሻ ዜጎች የራሳቸው የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው በመፈለግ፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ መሬት በቀጥታ ከገበሬ ወይም በደላላ በኩል ገዝተው ቤት መሥራታቸው መሆኑን ሰምተናል፡፡ ችግሩ እንዲባባስ ያደረገው ደግሞ በዚህ መንገድ መሬት መግዛትና ቤት መሥራት ለረዥም ጊዜ ያለ ከልካይ ሲካሄድ የቆየ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሕገወጥ አካሄድ መስመር ለማስያዝ ሲሞከር ደግሞ ጉዳዩ የተለያየ የፖለቲካ ትርጉም እየተሰጠው የሕግ ማስከበር ሥራው ሲሰተጓጎል ይስተዋላል፡፡

በዚህ መንገድ መሬት የማግኘት አካሄድ እስከ ትንንሽ የወረዳ ከተሞች ድረስ ሥር የሰደደና እየተከማቸ የመጣ ችግር ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከለውጡ ጋር ተያይዞ በነበረው አለመረጋጋት በሰፊው የመሬት ወረራ ሲካሄድ የነበረ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ እንኳን ከገበሬ መሬት መግዛት ይቅርና በሕጋዊ መንገድ ከከተማ አስተዳደር መሬት አግኝቶ፣ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ቤት ሳይሠሩበት የቀሩ ሰዎች ቦታቸው ሰበብ አስባብ እየተፈለገ የተወሰደባቸውን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ መሬታቸው ተወስዶባቸው ለማስመለስ በየማዘጋጃ ቤቱና በየፍርድ ቤቱ የሚንከራተቱት ብዙ ናቸው፡፡

ለዚህ ዓይነት አካሄድ ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው፡፡ የመጀመርያውና ዋነኛው ምክንያት  የሕዝብ ብዛት እየጨመረ መሄድና መሬት እያነሰ መሄድ ነው፡፡ በቂ የሆነ የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርት ባለመኖሩና ‹ልጅ ይወለድ እንጂ በዕድሉ ያድጋል› የሚል ልማድ ሥር የሰደደ በመሆኑ፣ በቂ የሆነ ገቢ ሳይኖራቸው ልጆች በማብዛታቸውና እነዚህም ሲያድጉ የራሳቸው ኑሮ መመሥረት ስለሚፈልጉ የመሬት ጥበቱ ይከሰታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የዜጎች ቤት የማግኘት ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ለአቅመ አዳም/ሔዋን ሲደርሰ የራሱ ቤት ኖሮት እንደ ወላጆቹ ቤተሰብ መመሥረት ይፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ አዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች የመኖሪያ ቤት መሥሪያ መሬት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ማግኘት፣ ካለው የመሬት ጥበት የተነሳ በጣም ከባድ ነው፡፡ ቢኖርም እንኳን የሊዝ ጨረታ ዋጋው የሚቀመስ አይደለም፡፡ ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ወጥ የሆነ የመሬት አስተዳደር ባለመኖሩና መሬት በከፍተኛ ደረጃ ለሙስና የተጋለጠ በመሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ በየማዘጋጃ ቤቱ ያሉ የመሬት ባለሙያዎች ወደዚህ ሥራ የሚገቡት፣ መሬት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመሸጥና ከደላላ ጋር ለሚገኘው ጥቅም ሲሉ ነው፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው ከየማዘጋጃ ቤቱ በየጊዜው በግምገማ የሚባረሩት ባለሙያዎች ናቸው፡፡ የሐሰት ካርታ ከማዘጋጀት ጀምሮ መሬት ሲለኩ እያሳለፉ በመሥፈርና ለሚመለከታቸው በመስጠት የቀረችዋን እላፊዋን ደግሞ በመሸጥ የሚያገኙት ገቢ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእያንዳንዱ አካባቢ የመሬት ልኬት በትክክል ተመዝግቦ ስለማይታወቅና ሆን ተብሎ እንዲዝረከረክ በመሆኑ ነው፡፡

ይህ ዓይነት የመሬት ወረራ በጊዜ መፍትሔ ካልተሰጠው ብዙ ችግሮችን ይዞ እንደሚመጣ ዕሙን ነው፡፡ የመጀመርያው በዚህ መንገድ የገበሬ መሬት ሕገወጥ በሆነ መልኩ ለቤት መሥሪያነት ማዋል ገበሬው የሚያርሰው እንዲያጣና በረዥም ጊዜ ደግሞ ለምግብ እጥረት መጋለጥን ያመጣል፡፡ እንኳንስ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ይቅርና በሕጋዊ መንገድ ማዘጋጃ ቤቶች በየወረዳው የገጠር ቀበሌዎችን ወደ ከተማ አስተዳደር እያስገቡ፣ ይህንኑ በሊዝ መሸጥ ሄዶ ሄዶ ችግር ማምጣቱ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ በአንዳንድ የወረዳ ከተሞች አዋሳኝ የነበሩ የገጠር ቀበሌዎች ቡናና  ባህር ዛፍ በማልማት ይተዳደሩ የነበሩ ገበሬዎች፣ ዛሬ መሬታቸው ወደ ከተማ ተከልሎ በአትክልታቸው ላይ መስቀለኛ መንገድ ወጥቶባቸው ቡናውና ባህር ዛፉ ተነቅሎ፣ መሬቱ በአብዛኛው ለነዋሪዎች ቤት መሥሪያነት ተሰጥቷል፡፡

በዚህ መሬት ላይ የነበረው አትክልት ቢቆይና ምርት ቢሰጥ ጥቅሙ ለባለቤቱ ብቻ ሳይሆን፣ ለመንግሥትና ለአካባቢው ነዋሪም ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ መሬት ይጠቀሙ የነበሩ ገበሬዎች በዚህ መንገድ መሬት ሲወሰድባቸው ዕጣ ፈንታቸው ሥራ ፈት መሆንና ወደ ሌላ አላስፈላጊ ሁኔታ መግባት ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸውንም መመገብ ስለሚያቅታቸው ችግር ላይ ይወድቃሉ፡፡ እዚህ ላይ ማንኛውም ዜጋ የቤት መሥሪያ ቦታ ማግኝት እንዳለበት ብስማማም፣ በዚህ ባልኳችሁ አካባቢ አትክልቶቹ ተነቅለው የተሠሩት ቤቶች ለመኖሪያነት እየዋሉ አይደለም፡፡ ሰዎች በወሰዱት መሬት ላይ ትንሽ ዛኒጋባ ቤት ለመሬት መያዣነት ብቻ ቀልሰው ሳይገቡበት ለረዥም ጊዜ በመቆየቱ፣ በዚያ አካባቢ እነዚህን ቤቶች ተገን አድርገው ሌቦችና ሕገወጦች  ኢሞራላዊ የሆነ ነገር ይፈጽሙበታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ለኢንቨስትመንትና ለንግድ ሥራ የሚውል መሬት እየቀነሰ ስለሚሄድ፣ ሥራ አጥነት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የአገር ችግር መሆኑ ይባባሳል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በአገራችን ከፍተኛ ችግር ከትምህርት ተቋማት ለሚጨርሱ ምሩቃን የሥራ ዕድል ማግኘት አለመቻላቸው ነው፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ሥራ ለመሥራት ሲነሱ ደግሞ የመሥሪያ ቦታ አቅርቦት ዋናው ማነቆ ነው፡፡ አብዛኛው የከተማ መሬት ማስተር ፕላኑን በጠበቀ መንገድ የተገነባ ባለመሆኑ፣ ለዚህ ዓይነት የንግድ ሥራ የሚውል መሬት ማግኘት ከባድ እየሆነ ነው፡፡ በተጨማሪም ለኢንቨስትመንት አመቺ የሆነ መሬት ለቤት መሥሪያ በመዋሉ ምክንያት፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች መፍጠር ያስቸግራል፡፡

ይህ ዓይነት አካሄድ የመንግሥትን የመሠረተ ልማት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር፣ መንግሥትን ለአላስፈላጊ ወጪ ይዳርጋል፡፡ መንግሥት በዚህ ሁኔታ ለተሠሩ ቤቶች የመብራት፣ የመንገድና የውኃ መስመር መዘርጋት ጥያቄ ስለሚመጣበት ለዚህ ከፍተኛ በጀት ለመመደብ ይዳረጋል፡፡ ይህም የአገር ኢኮኖሚ ያዳክማል፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሔው የከተማ ሰው የጋራ መኖሪያ ቤት (የኮንደሚኒየም) እና በአፓርታማ መኖር ሲጀምር ነው፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤት እየተሠራ ለእውነተኛ ቤት ፈላጊ ዜጋ እየተላለፈ በዚህ መንገድ ሰው መኖር ካልጀመረ ችግሩ መፍትሔ አያገኝም፡፡ ሕጋዊና ሕገወጥ በሆነ መንገድ ሰው 200 ካሬ ሜትር መሬት እየያዘ በዚህ ላይ ትንሽ ዛኒጋባ ቤት ሠርቶ ሌላውን ደግሞ አጥሮ መኖር ወደፊት አስቸጋሪ ሁኔታ ያመጣል፡፡ ይልቁንም መንግሥት እስካሁን ያለውን የከተማ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ችግር አጥንቶ የግል አልሚዎችን በማሳተፍ፣ ለከተማ ነዋሪዎች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በሰፊው ማቅረብ አለበት፡፡ እውነተኛ ቤት ፈላጊዎችም አስፈላጊውን ቁጠባ እየፈጸሙ በዚህ መልኩ ለመኖሪያ ቤት የሚሠሩ የጋራ ሕንፃዎችን የመጠቀም ባህል ሊያዳብሩ ይገባል፡፡

ከትንንሹ የወረዳ ከተማ አንስቶ እስከ ትልቁ የፌዴራል ዋና ከተማ አዲስ አበባ ድረስ ለሁሉም የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶ፣ ለእያንዳንዱ ከተማ መሠራት ያለበት የጋራ መኖሪያ ቤት ዲዛይን በባለሙያ ደረጃ ወጥቶላቸው ሕዝብ ሰብሰብ ብሎ አንድ አካባቢ መኖር መልመድ አለበት፡፡ ለዚህም ማዘጋጃ ቤቶች ለግለሰብ ቤት ሠሪዎች መሬት እየሸነሸኑ የሚሰጡትን ማቆም አለባቸው፡፡ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ማለትም 10/90፣ 20/80 እና 40/60 በመቅረፅ ዜጎች በዚህ መሠረት ገንዘብ እንዲቆጥቡ በማድረግ፣ በረዥም ጊዜ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን መንገድ  እያንዳንዱ ትንንሽ የከተማ አስተዳደር ሳይቀር ማሰብ ይኖርበታል፡፡

ይህ ዓይነት የጋራ መኖሪያ ቤት አሠራር ከአዲስ አበባ ውጪ ተሞክሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ግን በቂ ጥናት ሳይደረግበትና አስፈላጊው የአመለካከት ሥራ ሳይከናወን ተጀምሮ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቆሟል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው የራሳችንን ቤት ከሠራን በኋላ አጥር አጥረን የግለኝነት ኑሮ መኖር የለመድን ስለሆነ፣ ይህንን ጎጂ ባህል መለወጥ በአንዴ ሊከብድ ቢችልም ሳንሰለች የግንዛቤ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ያህልም በህንድ የመሬት ችግር ስላለ ቤተሰብ ሲመሠረት እንደ ምንም ብሎ ትንሽ መሬት ካገኘ በዚያች ላይ በረዥም ጊዜ ዕቅድና በጥንቃቄ ሕንፃ ዲዛይን ይጀመርና አቅሙ የቻለውን ያህል ሠርቶ፣ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ለአቅመ አዳም ሲደርሱ ደግሞ ወደ ላይ እንዲቀጥሉበት መሠረት ይጥላል፡፡ እኛም ይህንን ዓይነት ልምድ ልንወስድ ይገባል፡፡ በብጥስጣሸ መሬት ላይ መደዳ ቤት እየሠሩ ለግብርናና ለኢንቨስትመንት የሚሆን መሬትን መቀራመት ለሚቀጥለው ትውልድ ጭምር አለማሰብ ነው፡፡

ይህ ዓይነት አሠራር የመንግሥትን ቁርጠኛ አቋም ይጠይቃል፡፡ በአብዛኛው የከተማ አስተዳደሮች መሬት እየሸነሸኑ በሕጋዊ መንገድ የሚሰጡት፣ ከዚያ የሚገኘውን የሊዝ ገቢ በማሰብ ነው፡፡ ገበሬዎች የእርሻ መሬታቸውን ለቤት መሥሪያ ሕገወጥ ባልሆነ መንገድ የሚሸጡት፣ እንደዚሁ በመንግሥት ላይ እምነት ስለሌላቸው ነው፡፡ ከዛሬ ነገ መንግሥት ከሚወስደው እኔ ሸጨ ልጠቀም ከሚል እምነት ማጣት ነው፡፡ ይህም መንግሥት ከሚከተለው የመሬት ፖሊሲ፣ ማለትም መሬት የመንግሥት መሆኑና ዜጎች በማንኛውም ጊዜ መሬቱ ለተለያዩ አልሚዎች ሊሰጥ ሲፈለግ ሊያነሳቸው እንደሚችል ስለሚያውቁ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን አሠራር ማስተካከያ በማድረግ መንግሥት ለጊዜው ከመሬት ሊዝና ኪራይ ከዜጎች የሚሰበስበው ገንዘብ ቢቀንስም፣ በረዥም ጊዜ በኢንቨስትመንት  ከሚገኝ የገቢ ግብር  ሊሰበስብ ይችላል፡፡

ይህ ዓይነት አሠራር ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ የመጀመርያው ሽንሽኖ ለቤት መሥሪያ የሚውል መሬት ለግብርናና ለኢንቨስትመንት እየዋለ ምርታማነቱን በመጨመር፣ በረዥም ጊዜ የአገሪቱን ዕድገት ያፋጥናል፡፡ ሁለተኛ የመንግሥት መሠረተ ልማት አቅርቦት ችግር ያቃልላል፡፡ ሰዎች በጋራ መኖሪያ ቤቶች ሰብሰብ ብለው ሲኖሩ ለእነሱ የሚያስፈልገው የመንገድ፣ የመብራትና የውኃ መስመር ዝርጋታ ብዙ ወጪ አያስወጣም፡፡ ሰዎች ከዚህ በፊት በተለመደው መንገድ ተበታትነው ሲኖሩ ግን፣ እነዚህን መሠረተ ልማት ማዳረስ ያስቸግራል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ መሬትን ተጠቅመው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመክበር የሚፈልጉ ደላሎች፣ ባለሀብቶችና የአስተዳደር ሰዎች ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ በስተመጨረሻም በዚህ መንገድ መሬት ተወስዶባቸው ባዶ እጃቸውን የሚቀሩ ገበሬዎች እንዳይኖሩ በማድረግ፣ በአገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት ይፈጥራል፡፡ እንደ እኔ አስተሳሰብ ይህ ችግር ሊቀረፍ የሚችለው ከላይ የተዘረዘሩትን የመፍትሔ ሐሳቦች በመተግበር ነው እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...