እነሆ ከፒያሳ ወደ አዲሱ ገበያ ልንጓዝ ነው፡፡ ታሪክን በተንተራሰ የህልውና መስመር፣ ትናንትና ነገ በትውስታ በሚደጋገፉበት ጎዳና ላይ ልንጓዝ ነው። ሥጋ ለባሽ ፍጡር ይይዝ ይጨብጠውን አጥቶ ይራወጣል። የእንጀራ ነገር! ደመናው የቋጠረውን ሊለቀው ለቀብር እንደ ተጠራራ ዕድርተኛ በአንድ ሥፍራ ተሰብስቧል። በእኩለ ቀን መጣሁ ሄድኩ በሚለው የነሐሴ አጋማሽ ማለቂያ ዶፍ ውሎው እንዳይበላሽና ሐሳቡ እንዳይስተጓጎል የሰጋው መንገደኛ ቁጥር ይህ ነው አይባልም። በተፈጥሮ ቁጥጥር ሥር እስካለን ድረስ ያደረገንን ሆነን ባስቀመጠን ተገኝተን ከመኖር ሌላ ምን ምርጫ አለን? በአንፃሩ ጊዜን የሚቀድም የሚመስለው ከደመናው በላይ የማትጠፋውን የማትበራ ፀሐይ ባለችበት ሊያቆይ የሚሻው፣ በትከሻው ሌላውን መንገደኛ እየገጨ ያዝግማል። ‹‹ቀስ አትልም እንዴ?›› አንዱ ትከሻዋን አውልቋት ሲሄድ አንዲት ሞንዳላ ጮኸች። አላስተረፋትም መሰል፡፡
‹‹ዘመናይ መንገዱን በሊዝ ገዛሁት እንዳትይ ብቻ፡፡ ዘንድሮ በሊዝ የሚሸጠውን የሚሻማውን አልቻልነውም፤›› ብሏት መንገዱን ይቀጥላል። ትከሻዋን እያሸች ቦርሳዋን አጥብቃ ይዛ ንጭንጯን ሳታባርድ ታክሲ ፍለጋ ትቃብዝ ጀመር። እንዲህ ነን . . . ከእነ ሕመማችን፣ ከእነ ቁስላችንና ከእነ ትዝታችን ነዋ ስንጓዝ የኖርነው። እስኪሻለን አረፍ ያልንበት ዋርካ መቼ አለን? ትካዜያችን ደም ሥር ውስጥ እንደገባ አልኮል ለቆ ትቶን እስኪሄድ በዕፎይታ ተደጋግፈን የተኛንበት ሜዳስ አለን? ዘለዓለም ሩጫ! ዘለዓለም ጥድፊያ! ስክነት እንደ ራቀን በጥፋት ላይ ጥፋት፣ በጥያቄ ላይ ሌላ ጥያቄ ስናዋልድ እዚህ አልደረስንም? ዛሬም በቃላት ጋጋታ፣ በፕሮፓጋንዳ ሐተታ ልናሽረው ያልቻልነው እልፍ የኑሮ ጣጣ ላይ እንደነገሥን አለን። ማለቂያ የሌለው ትውልድ የሚቀባበለው የኑሮ ሸክም የሕይወት እሰጥ አገባ፣ ከዚህ አስጉዞ እዚያ እንዳደረሰን ደግሞ ከዚያ አሳፍሮ ወዲህ ይልከናል። ጎዳናው ላይ ያልተንከላወስንበት አካል የለንም። ውጣ ውረድ ይባላልና መስመሩ፡፡
ተሳፍረናል። ጎዳናው በካፊያ መርጠብ ጀምሯል። የበቆሎ እሸት ጥብስ ይዞ የተሳፈረ፣ ብቻውን መኖርና መብላት ያለመደበት እንብላ እያለ ያስፈለፍለናል። ለብቻ ተሠርቶ ለብቻ መክበር የኑሮ ዘዬ በሆነበት በዚህ ጊዜ እንዲህ ያለው ደግ ‘ክንፍ ቀረሽ’ ተብሎ ይንጓጠጣል። ‹‹ደግ መቼ ይበረክታል?›› እያለ አንድ ክልስ ፊት ያለው ጎልማሳ ከጎኑ አብሮት ከተቀመጠ ሰው ጋር ወሬ ይጠርቃል። ‹‹ተወኝ እስኪ!›› ይላል የወዲያኛው። ወያላው ክርኗ ተቀዳ የተጣፈች ሹራቡን እየደረበ፣ ‹‹የሚለብሰው የሌለው የሚከናነበውን እየሸመተ ባለባት አገር፣ እኔ ሳልቫጅ መቀየር ያቅተኝ? ወይኔ የሰውዬው ልጅ!›› እያለ ብሶቱን ለሾፌሩ ያካፍላል። ‹‹ሰው አይንሳህ አቦ! ልብስ ቢደረብ ያለ ሰው መቼ ይሞቃል?›› ይለዋል ሾፌራችን።
ጋቢና የተሰየመ ወጣት ደግሞ፣ ‹‹አይደል? የዘመኑን ሰው እኮ ገንዘብ ይዞት ጠፋ፤›› እያለ የገዛ ሕይወቱን ውጣ ውረድ ሳይጠይቀው ለሾፌሩ ይነግረዋል። ሾፌሩ ራሱን እየነቀነቀ አንዴ መንገዱን አንዴ የተራኪውን ዓይኖች እያየ ይዘውራል። ‘ደግ አይበረክትም’ ባዩ ጎልማሳ ወዳጁን ዘወር ብሎ፣ ‹‹ኧረ ለመሆኑ ያ ማነው ስሙ ደህና ነው?›› ሲል የተረሳ ወዳጁ ያነሳል። ‹‹ምን ይሆናል እሱ? ያችን ልጅ እንዳትሆን አድርጎ ተጫውቶባት ካበቃ በኋላ በዓመቱ መቼ ነው? . . . ባለፈው ወር መሰለኝ ሠርግ ደገሰ. . .›› የሚል መልስ ያደርሰዋል። ‹‹ወይ ድፍረት? እንኳንም ኢየሱስ ክርስቶስ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አልመጣ፤›› ይላል። “እንዴት?” ይጠይቀዋል ግርምት በተቀላቀለበት የድምፅ ቃና። ‹‹እህ ያኔ አንድ ሰው ነው አሳልፎ የሰጠው። አሁን ቢሆን ኖሮ አሥራ ሁለቱም አሳልፈው አይሰጡትም ብለህ ነው?›› ይላል ያኛው። ገጻችን በፈገግታ ተሳስቦ ቢወጠርም ውስጣችን በሽብር ተንጧል። ስለራስ ዋጋ የለሽነትና ፅናተ ቢስ የኑሮ ልማድ እንዲህ በአደባባይ ዕውቅና እየሰጡ እንደ መጨዋወት ታዲያ ሌላ ምን የሚያም ነገር ይኖራል?
‹‹ማን ስለሆነ? ምኑ ይሰረቃል ደግሞ እሱ? ቢል ጌትስ ወይስ ዋረን ቡፌት ነው?›› ድንገት ያንዲት ወጣት ድምፅ በጥያቄ አስገመገመ። ‹‹ኧረ ዝም በይውማ እሠራለታለሁ፤›› ትላለች አጠገቧ የተቀመጠች ወዳጇ። ‹‹እንዴ ሌላው ሰው በቃ ምንም የለውም? እንዲህ የዓለማችንን ታላላቅ ቱጃሮች እየጠራችሁ በሞራላችን የምትረማመዱት?›› አላት አጠገቤ የተመቀጠ ወጣት ተንጠራርቶ። ሴቶቹ እርስ በርሳቸው ተያይተው ሲያበቁ፣ ‹‹ሌላው የእኛውማ ወይ ጤና ወይ ድምፅ ነው ያለው፤›› አለችው አንደኛዋ። ታክሲያችን በሆታ ሳቅ ተናጋች። ‹‹አንቺ? ያውም በዚህ ወጣት ባለሀብቶች በበዙበት ዘመን እንዲህ ይባላል?›› አላት ልጁ መልሶ። ‹‹ሀብታቸው በዓለም እንዳያሳውቃቸው አመጣጡ አይታወቅም እባክህ። ‘ፓስወርዱ’ የማይታወቅ ሀብት አይሠራም፤›› አለች ደግሞ ሌላኛዋ። ‹‹ወይ ታክሲ ስንቱን ያሰማናል?›› ትላለች ጠና ያለች ወይዘሮ ከመጨረሻ ወንበር። ‹‹ሲያዩሽ የኑሮ ‘ፓስወርድ’ የገባሽ ይመስላል። ለመሆኑ ይህ ያንቺው የሚስጥር ቁጥር በሙስናና በሽብር የሚያስጠረጥር ነው ወይስ ሰላማዊ ነው?›› አንድ አንድ መባባሉ ሩቅ የሚያስኬደው የመሰለው ልጅ ጥያቄውን አላቆመም።
ልጆቹ ቆንጅዬዎች ናቸው። መቼም ዘንድሮ መንገዱ በቆንጆዎች የተወረሰ ነው የሚመስለው እኮ! ‹‹አንተ! ፋራ ነህ መሰል? በኮምፒዩተር ዘመን ተወልደህ ያደግክ መስሎኝ? የግለሰብ ‘ፓስወርድ’ ይጠየቃል እንዴ?›› አሉት ለሁለት። ‹‹ምን ችግር አለው? ኃያላን መንግሥታትና የመረጃ ቀበኞች ሳያንኳኩ ሰብረው ይገቡ የለ። እንዲያውም እኔ በፀባይ ጠየቅኩሽ፤›› አላት። ወጣቶቹ መድረኩን እንደ ተቆጣጠሩት ዘለቁ። ልጁ ያሻውን የኑሮ ሚስጥር ቁጥር ግን እንዳሰበው አላገኘውም። ‹‹ለአንዱ የቀናው መንገድ ለሌላው ይቀና መሰለው እንዴ ይኼ? አቦ ተፋታቸው. . .›› መጨረሻ ወንበር ከወይዘሮዋ ጋር የተቀመጡ ጎረምሶች። አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት አልሰማቸውም። ባልተሄደበት መንገድ መሄድ ባልተመነጠረ ጥሻ ውስጥ የራስን መንገድ ማቅናት፣ ለእኛ ለሐበሾች የሚሞከር ነገር እንዳልሆነ አመጣጣችን ብዙ ይናገራል። ለዚህም ይሆናል በሰው ቁስል እንጨት ስንሰድ፣ በሰው ገበታ ጣታችንን ስናስገባ፣ የሰው ድስት ስናማስል የእኛ የምንለው የሌለን ሆነን ያረፍነው። ዝንት ዓለም ከሰረቀው ጋር ስንሰርቅ ከሸፈተው ጋር ስንሸፍት የማይሰለቸን። መጥኔ!
ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። መጨረሻ ወንበር የተቀመጡት ጎረምሶች ተማሪዎች ናቸው። ወቅታዊና መሳጭ ጭውውት ይዘዋል። ‹‹በመጪው ዓመት ልትመረቅ ነዋ?›› ይሉታል አንደኛውን ጓደኛቸውን። ‹‹ዕድሜ ለበለጬ ይኼው እዚህ ደረስን፤›› አላቸው እየሳቀ። ‹‹እንዲህ ብለህ ባልሆነ ፎቶ ተነስተህ የምረቃ መጽሔታችሁ ላይ የወጣኸው?›› አለው አንዱ። ‹‹እዚያ ላይማ ‘ሥራ አጥነት መጣንልሽ’ ብያለሁ አይደለም እንዴ?›› በማለት ይመልሳል። ‹‹ብራቮ! ብራቮ!›› ትከሻውን እየቸመቸሙ ያደንቁታል። ‹‹ቆይ ልውረድና እፈርምላችኋለሁ!›› ቢላቸው፣ ‹‹ግድ የለም! የፊርማውን ነገር ከመጪው ዓመት ምርጫ በኋላ። ለጊዜው እንፈልግሃለን። ከእነ ‘ጋውንህ’ ደግሞ ወህኒ ወርደህ፤›› እያሉ ያሾፋሉ። እርስ በርስ በክፉም በደጉ የሚተዋወቁ የሚመስሉት እነዚህ ወጣቶች ወጋቸው አይጨበጥም። በመጪው ዓመት ተመራቂ የሆነው ተማሪ ደግሞ በተራው ከተጠያቂነት ወደ አቀንቃኝ ተጫዋችነት ተገልብጧል።
‹‹እከሌን’ ታስታውሱታላችሁ?›› አላቸው። ሊያስታውሱት ብዙም ሳይደክሙ ‹‹ምን ሆነ ደግሞ?›› አሉት። ‹‹ምን ይሆናል አሁንማ የሆነውን አንዴ ሆኗል። ያን የመሰለ ብሩህ ቀለሜ በምግብ መመረዝ ባይታመም ኖሮ አብሮን ይመረቅ ነበር፤›› እያለ ከንፈሩን ይመጣል። ‹‹በኑሮ መመጣጠን አቅቶን በተመጣጠነ አመጋገብ አለመኖራችን ሳያንስ ጭራሽ ዘንድሮማ አየሩም ተበክሏል ይሉናል፤›› የሚለኝ አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት ነው። ‹‹ታዲያ ላይታመም ኖሯል! በፊውዳሉ ጊዜ ንጉሡ ራሳቸው ሙዝና ብርቱካን ይዘው የሚጠይቁት፣ በጥራት ተመግቦ በጥራት ተማረ የነበረው ዛሬም በስተርጅና አገር የሚያተራምሰው ትውልድ፣ ‘የለም ከጥራት በብዛት አምናለሁ’ እያለ መስሎን ጉድ የሚሠራን፤›› ሲል አንደኛው ይመልሳል። ወዲያው ደግሞ በሩቅ ያለ ጓደኛቸውን አንስተው (የሚታማው ልጅ በትምህርቱ ቸልተኛና ግድየለሽ እንደሆ ካነጋገራቸው ያሳብቃል) ‹‹የምረቃ መጽሔቱ ላይ ምን ሊል ተዘጋጅቷል?›› ሲሉት ተመራቂው ወጣት ሳቅ እየቀደመው፣ ‹‹ከትልቁ ሾላ ከዛፉ ደርሼ፣ ያለ ዕድል አይበሉ መጣሁ ተመልሼ’ ካላልኩ እያለ ነው፤›› ብሏቸው ከት ብለው ሳቁ። የሳቁ ኃያልነት ብዙም አልገባን። ትውልዱ ከአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ እስከ ገዛ ስንፍው በመሳለቅ ወደር የለሽነቱ እንደተጠበቀ እንዳለ ግን አረጋገጥን። ከቴም ሪኮርድ አያ!
ወደ መዳረሻችን ነን። ‹‹እናንተ ይኼ የአውሮፓ እግር ኳስ እንዴት አድርጎ ይዞን ሰንብቶ ኖሯል?›› ሲል በግርምት ጎልማሳው እያወራ ነው። “እንዴት?” አብራራው ይባላል። ‹‹ይኼው አሁን ጀመረልን እንጂ በክረምቱ ጭር ቢልብን የምንሰማው ዜና ሁሉ የሽብርና የጦር ነበር። ሐማስና እስራኤል ተፋጠጡ። ሶሪያና የመን አሳራቸውን በሉ። ዓለም የሚሰነዘርባትን የሽብር ጥቃት ለመከላከል አቃታት፣. . . የመሳሰሉት ወሬዎች አልታከቷችሁም?›› ከማለቱ ወያላው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹መርጠን እያየንና እየሰማን እንጂ ኳሱስ ቢሆን በንክሻ የደመቀ፣ በቴስታ የታጀበ፣ በብሔርተኝነት ዱላ የጨቀየ አልነበረም እንዴ? በአገር ደረጃ ሲሆን ግለሰብ እየተደፈጠጠ እንጂ. . .›› ብሎ ተናገረ። ‹‹እግዚኦ! እንዴት ያለ ዘመን ላይ ደርሰናል ግን?›› አለች ወይዘሮዋ። ‹‹እናንተ በሩቁ ትገረማላችሁ? በዕለተ ሰንበት ሲያቀብጠኝ ሬዲዮ ብከፍት ከኢትዮጵያዊ ወግና ጨዋነት በማይጠበቅ ጭካኔ፣ ማጭበርበር፣ ማታለልና ስርቆት፣ ፈተና በአግባቡ ባለመታረሙ የደረሰው ውንዥንብርና የወንጀል ድርጊት ያልሰማሁት ምን አለ? እንዲያው ሰምቶ እንዳልሰማ ዓይቶ እንዳላየ መሆን እንዴት ደግ ነው በፈጣሪ. . . በዚያ ላይ በፈተናው ውጤት ምክንያት የሚሰማው ፉከራና ቀረርቶ ከፈተና አውጣኝ አያሰኝም ወይ. . .›› አለች አክላ። ታክሲያችን መቆሚያ ሥፍራ ፈልጋ ስታቀዘቅዝ ወያላው በሩን ከፍቶ “መጨረሻ” አለ። ወይዘሮዋ ለራሷ እያጉረመረመች ወርዳ መንገዷን ስትጓዝ፣ መንገዴ መንገዷ ሆኖ የምትለውን እሰማ ነበር። ጭብጧ ከጀመረችው ጉዳይ አይዘልም። ‘ምርጫ ያጡ ለታ ወዴት ይደረሳል?’ ልላት ሳስብ የፈተናው እሰጥ አገባ እኔንም ግራ አጋባኝ። መልካም ጉዞ!