Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዕዳ ላጎበጠው ኢኮኖሚ የታሰቡ ለውጦች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ መንግሥትና የልማት ድርጅቶቹ ከአገር ውስጥና ከውጭ ምንጮች የተበደሩት የገንዘብ መጠን በጠቅላላው 1.5 ትሪሊዮን ብር ገደማ መድረሱ በተዘገበ ማግሥት፣ የገንዘብ ሚስቴርም ስለዚሁ ጉዳይ በሳምንቱ መጨረሻ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በተሸኘው በጀት ዓመት የገንዘብ ሚኒስቴርን የ12 ወራት አፈጻጸም በማስመልከት የተሰጠው መግለጫ አንደኛው ቅኝቱ ይኼንኑ አገሪቱን የዕዳ ክምር የተመለከተ ነበር፡፡ በመሆኑም በ2011 ዓ.ም. ብቻውን ከ368 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም 13 ቢሊዮን ዶላር ገደማ  ገንዘብ ማዕከላዊው መንግሥት ስለመበደሩ የገንዘብ ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህ የብድር መጠን በ2010 ዓ.ም. ከነበረው የ3001 ቢሊዮን ብር በ22.3 በመቶ ወይም የ67 ቢሊዮን ብር ዕዳ ጭማሪ አለው፡፡ ይህ የብድር ዕዳ መጠን ከአገር ምንጮች በተለይም ከመንግሥት ባንኮች በቀጥታ እንዲሁም ከቦንድ ሽያጭና ከመሳሰሉት የተበደረው የገንዘብ መጠን ነው፡፡

ማዕከላዊው መንግሥት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በነበረው አንድ ዓመት ውስጥ ከውጭ በአዳሪዎች 16 ቢሊዮን ዶላር ወይም 475 ቢሊዮን ቢሊዮን ብር መበደሩ ሲገለጽ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ብድሩ በጠቅላላው ከ830 ቢሊዮን ብር በላይ አሻቅቧል፡፡ 

ከማዕከላዊው መንግሥት ባሻገር የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በዓመቱ የተበደሩት ብድር መጠን ወደ 407.5 ቢሊዮን ብር ማሻቀቡ ተወስቷል፡፡ ይህም በ2010 ከነበረው የ344 ቢሊዮን ብር ዕዳ አኳያ ከ63 ቢሊዮን ያላነሰ ጭማሪ የተመዘገበበት ሆኗል፡፡ በአቶ ሐጂ አኃዞች መሠረት ከታየ የማዕከላዊው መንግሥትና የልማት ድርጅቶቹ በጠቅላላው ከ1.2 ትሪሊዮን ብር በላይ የተከማቸ ብድር አስመዝግበዋል፡፡ እንደ አቶ ሐጂ ገለፃ፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ የአገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም በማሽቆልቆል ላይ ይኛል፡፡

እያየለ በመጣው የብድር ዕዳ ጫና ሳቢያ መንግሥት የልማት ድርጅቶቹን ጨምሮ ሌሎችም መንግሥታዊ ተቋማት፣ ከፍተኛ ወለድ የሚታሰብበትና በአመዛኙ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከፈል (የንግድ ብድር ወይም ኮንሴሽናል ሎን) ውስጥ ብድር እንዳይወስዱ የብድር መመርያ በማዘጋጀት ቁጥጥር መጀመሩም ተጠቅሷል፡፡ ምንም እንኳ ይህ ይባል እንጂ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የአጭር ጊዜ ብድር ለማቆም የገባውን ቃል በማጠፍ ከአንድ ሁለት ጊዜ ይህን መሰል ብድር ውስጥ ሲገባ መታየቱን ይፋ እንዳወጣ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይህም ሆኖ አዲሱ አስተዳደር ከመምጣቱ በፊት ጀምሮ የአገሪቱ የዕዳ ጫና እያየለ በመምጣት ከዝቅተኛ የዕዳ ሥጋት ወደ ከፍተኛ ሥጋት የተሸጋገረችበት ደረጃ ላይ ስትደርስ አዲሱ አስተዳደርም ሥልጣኑን ከነዕዳው ተረክቧል፡፡ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ አገሪቱ የዕዳ ጫና ተጋላጭነት ዝቅተኛ በሚባለው ደረጃ ላይ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሐጂ፣ ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ ውስጥ መካከለኛ የሚባል የዕዳ ጫና ሥጋት ቀለበት ውስጥ ስትዋልል ቆይታ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮም ከፍተኛ የሚባለው የዕዳ ጫና ሥጋት ርከን ላይ መንሳፈፍ እንደጀመረች ካቀረቡት አኃዝ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የአገሪቱን የዕዳ ጫና ካባባሱት መሠረታዊ ምክንያቶች ውስጥም የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ከሆኑት ዋነኛው የወጪ ንግዱ ዘርፍ ሲሆን፣ አቶ ሐጂ በተቀሱት አኃዝ በ2011 ዓ.ም. ከዘርፉ የተገኘው ጠቅላላ ገቢ 2.34 ቢሊዮን ዶላር፣ ንግድ ሚኒስቴር በሚጠቅሰው አኃዝ 2.67 ቢሊዮን ዶላር (ከሁለት የአንዳቸውን አኃዝ እንዳስፈላጊነቱ መጠቀም ነው) ተመዝግቧል፡፡ የወጪ ንግዱ በየጊዜው እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ እንደ አቶ ሐጂ ገለጻ ከሆነም፣ የአገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በማሽቆልቆል ላይ ይገኛል፡፡ የወጪ ንግዱን መዳከም የሚያባብሰውም የአገሪቱ የወጪ ምርቶችና ሸቀጦች እንደሚፈለገው በጥናትና በብዛት አለመመረታቸውም ነው፡፡

በተለይ የፖለቲካው ቁርሾና የእርስ በርስ ግጭቱ ያስከተላቸው ውጥንቅጦች ምርት ወደ ገበያ እንዳይወጣ እክል በመፍጠር፣ መንገዶችን በመዝጋት፣ አምራች ፋብሪካዎችን በማቃጠልና በመሳሰሉት ጥፋቶች ሲታመስ የቆየው የወጪ ንግድ ዘርፉ፣ ይባሱን እየተስፋፋ በመጣው የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ከዋጋ በታች በመሸጥና ወጪን በማናር (አንደር ኢንቮይሲንግ፣ ኦቨር ኢንቮይሲንግ) አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ገቢ የሚያሳጡ ሕወገጥ ተግባራት እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ይህንን የሚያረጋግጠው በቅርቡ የገቢዎች ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም. ብቻ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሸቀጦች በኮንትሮባንድ መያዛቸውን ሚኒስትሯ አዳነች አቤቤ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ያልተደረሰባቸውና ያመለጡ ቢሊዮኖችን ከመገመት በቀር በአኃዝ አስደግፎ የሚያጣቅስ መረጃ ማግኘት አዳጋች ቢሆንም፣ በተለይ በቁም እንስሳት ሕገወጥ ንግድ የሚታጣው፣ በወርቅና በሌሎች ማዕድናት የሚፈልሰው የአገሪቱ ሀብት የትየለሌ መሆኑ ይነገርለታል፡፡

የመንግሥት ዕዳ የሚያከብደው ሌላው ጫና የወጪ ንግዱ ማሽቆልቆሉ ብቻም ሳይሆን፣ የተቆለለውን ዕዳ ለመክፈል የሚደረገው መፍጨርጨርም ነው፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት 16 ቢሊዮን ብር መክፈሉንና በአዲሱ በጀት ዓመትም ከ22 ቢሊዮን ብር ዕዳ ለመክፈል መታቀዱ ነው፡፡ የተከማቸውን ዕዳ በዚህ መልኩ ለመክፈል የወጪ ንግዱ የሚኖረው ድርሻ የማይናቅ ነው፡፡ የምርት አቅርቦት እንደሚፈለገው መጠን አለመጨመር፣ የሕዝብ ቁጥር መብዛትና የንግድ ዘርፉ የሚታይበት ጉድለቶች ተጨማምረው የዋጋ ግሽበት እየተባባሰ እንዲመጣ አድርገዋል፡፡

መንግሥትም የዋጋ ግሽበቱ የሚያመጣውን ጫናና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሙሉ ለሙሉ ባይቀርፍም ከውጭ ስንዴና ሌሎችም የምግብ ሸቀጦችን በማስገባት ቢያንስ ታችኛው የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሕዝብ ለመታደግ ሲሞክር ኖሯል፡፡ በዚህ ዓመትም በተለይ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ ተጓጉዞ የሚገባ 4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እየተጠበቀ እንደሚገኝ አቶ ሐጂ ገልጸዋል፡፡ ለመጪው ዓመት ከሚፈጸመው ግዥ ውስጥም እስከ ኅዳር ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ተጓጉዞ የሚገባ ተጨማሪ ሚሊዮን ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለመግዛት ከወዲሁ ጨረታ መውጣቱንም አስታውቀዋል፡፡

የመንግሥትን የዕዳ ጫና ያበራከቱት ሌሎችና አነጋጋሪዎቹ ችግሮች መንግሥት ከአቅሙ በላይ የጀመራቸው የልማት ፕሮጀክቶች ያስከተሉት ኪሳራ ነው፡፡ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ያስወጡት የስኳር ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በርካቶቹ የልማት ሥራዎች በመጓተታቸውና በሚፈለገው የጥራትና የብቃት ደረጃ ባለመግባታቸው ሕዝብም መንግሥትም ለችግር ተጋልጠዋል፡፡ በገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ መሠረትም፣ ከሁለት እስከ ሰባት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ የተጓተቱ 1,000 ፕሮጀክቶች በትንሹ የ43 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪና ኪሳራ አስከትለዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ቀውሶችን ለመከላከል የተነሳው መንግሥት፣ በሁሉም መስኮች የሪፎርም ፕሮግራሞች ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አዋጭነታቸው ችግር ያለበትን ጨምሮ ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኙለት እንደሚችሉ ያመነባቸውን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉም በከፊልም ለመሸጥ ከወሰነ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እንደ ግብርናው ባሉ መስኮች የመስኖ እርሻ በማስፋፋት፣ በተለይ በቆላማ አካባቢዎች ሰፋፊ እርሻዎችን በማልማት ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት ለማስቀረት መወሰኑን አስታውቋል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገውም እንደ አፋርና ሶማሌ ባሉት ክልሎች የሙከራ ምርት ተጀምሯል፡፡ ከ3,000 ሄክታር ያላነሰ መሬት በስንዴ ምርት መሸፈኑ ሲገለጽ እንደነበርና ይህም ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ የአገሪቱን የስንዴ ጥገኝነት ከውጭ ለማላቀቅ ተስፋ መስጠቱን ሚኒስቴሩ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በቱሪዝም መስክ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በሥነ ጥበብና ኪነ ጥበብ መስክም መንግሥት ያሰባቸው ሥራዎች ለአገሪቱ የለውጥ ጉዞ ተስፋ የተሰነቀባቸው እንደሆኑ ባለፈው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው የ‹‹አዲስ ወግ›› የወይይት መርሐ ግብር ላይ ተጠቅሷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች