Thursday, May 30, 2024

መንግሥት አገሪቱን ከዕዳ አጣብቂኝ አውጥቶ የኢኮኖሚውን ጤንነት የማረጋገጥ ፈተናን እንዴት ሊወጣው ይችላል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2019 ድረስ ያለባትን አጠቃላይ የአገር ውስጥና የውጭ ብድሮች የዕዳ መጠን 1.5 ትሪሊዮን ብር ወይም 52.57 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘውን መረጃ በመጥቀስ በእሑድ ዕትም መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ከተጠቀሰው አጠቃላይ የአገሪቱ ዕዳ ውስጥ 26.93 ቢሊዮን ዶላር ወይም 769.08 ቢሊዮን ብር ከተለያዩ የውጭ አበዳሪዎች ተገኝቶ ያልተከፈለ ዕዳ ሲሆን፣ የተቀረው 730.5 ቢሊዮን ብር ወይም 25.6 ቢሊዮን ዶላሩ ደግሞ ከአገር ውስጥ የመንግሥት ባንኮች ማለትም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር፣ እንዲሁም ከመንግሥት ሠራተኞችና ከግል ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና (ጡረታ) ፈንዶች ተወስዶ ያልተከፈለ ዕዳ ነው፡፡

አገሪቱ ካለባት የውጭ ዕዳ ውስጥ የማዕከላዊ መንግሥት (Centeral Government) ዕዳ 449.7 ቢሊዮን ብር (15.73 ቢሊዮን ዶላር) ሲሆን፣ ቀሪው 319.3 ቢሊዮን ብር (11.17 ቢሊዮን ዶላር) ደግሞ የተለያዩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መንግሥት በገባላቸው የብድር መክፈያ መተማመኛ (Loan Guarantee)፣ ሌሎች ሁለት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ደግሞ ያለ መንግሥት የብድር መክፈያ መተማመኛ በራሳቸው ከውጭ አበዳሪዎች በቀጥታ ተበድረው ያልከፈሉት ዕዳ ነው፡፡ ያለ መንግሥት የብድር መክፈያ መተማመኛ ከውጭ የተበደሩት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም መሆናቸውን መረጃው የሚያመለክት ሲሆን፣ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ከውጭ አበዳሪዎቻቸው ያለ መንግሥት ዋስትና በቀጥታ ተበድረው እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2019 ድረስ ያልከፈሉት ዕዳ 3.9 ቢሊዮን ዶላር ወይም 111.96 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ሎሎቹ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገቡላቸው የብድር መክፈያ መተማመኛ በመጠቀም ከወሰዱት የውጭ ብድር ውስጥ፣ እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2019 ድረስ ያልከፈሉት የዕዳ መጠን 207.38 ቢሊዮን ብር (7.27 ቢሊዮን ዶላር) እንደሆነ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2019 ድረስ አገሪቱ የተመዘገበው 730.5 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ዕዳ አሉታዊ ተፅዕኖን ለጊዜው መቋቋም እንደሚቻል ባለሙያዎች የሚያምኑ ቢሆንም፣ ማዕከላዊ መንግሥትና የልማት ድርጅቶች ከውጭ አበዳሪዎች ወስደው መመለስ ያልቻሉት 769 ቢሊዮን ብር (26.9 ቢሊዮን ዶላር) ዕዳ ግን አገሪቱ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ካፒታል ማግኘት እንዳትችል እያደረጋት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህም ኢኮኖሚውን ከማቀዛቀዝ አልፎ ግብፅ እንደገባችበት ዓይነት የኢኮኖሚ ዕድገት መገታት (Economic Stagnation)፣ ወይም ባለሙያዎች በተለየ አዎንታዊ አገላለጽ የኢኮኖሚ ልማት ዕድገት አጣብቂኝ (Development Trap) ውስጥ የመግባት አደጋ አፍጦ ስለመምጣቱ በመግለጽ ስለፈጣን መፍትሔ አስፈላጊነት ያሳስባሉ፡፡

በአገር ውስጥ በሚገኝ አንድ የውጭ ተቋም ውስጥ በአማካሪነት በመሥራታቸው ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ በተሸከመችው የውጭ ዕዳ ምክንያት በዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ጫና (High External Debt Distress) በሚባለው የመለኪያ መደብ ውስጥ መካተቷን፣ ከዚህ በኋላ ዕዳዋን ሳታቃልል በገበያ የወለድ ተመን ሌላ ተጨማሪ የውጭ ብድር ብትወስድ አሁን ካለችበት ምድብ በመውጣት ዕዳዋን መክፈል ያልቻለች አገር (Highly Indebted Country) ዝርዝር ውስጥ እንደምትካተት ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ምድብ ውስጥ መካተት ማለት ማንኛውም የውጭ አበዳሪ ለኢትዮጵያ የፕሮጀክት ልማት ብድር እንዳያቀርብ እንደሚያስገድደው፣ ይህም ያለ መንግሥት ዋስትና የውጭ ብድር እያገኙ የሚገኙትን ብድራቸውን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ድርጅቶችን ጭምር አዲስ ብድር እንዳያገኙ እክል የመፍጠር አቅም እንደሚኖረው፣ መንግሥት የዕዳ መጠኑን ቢያቃልል ኢንኳን ከዚህ ምድብ ለመውጣትም ረዥም ዓመታት እንደሚወስድ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው አንድ ዓመት በገበያ የወለድ ምጣኔ አዲስ የውጭ ብድር ላለመውሰድ ያሳለፈው ውሳኔና ቁርጠኝነትም ይህንኑ ሥጋት ከመረዳት የመነጨ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፣ ውሳኔው ተገቢ ቢሆንም ለካፒታል ፕሮጀክት ወይም ለኢኮኖሚ ልማት የሚውል ተጨማሪ ሀብት መፍጠር ባለመቻሉ የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ፣ የሥራ አጥነት መስፋፋት ምልክቶችን በማሳየት ላይ እንደሚገኝ፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከዚህና ከሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ጋር ተዋህዶ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በመቀስቀስ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመውጫ መንገዱ ምንድነው? የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር የጀመረውን የኢኮኖሚ ሪፎርም አስመልክቶ ሰሞኑን በተካሄደው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው የሪፎርሙ መሠረታዊያንን በተመለከተ ማባራሪያ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከፍተኛ አማካሪ ማሞ እስመለዓለም ምሕረቱ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ለመቅረፍና የንግድ ሥራ እክሎችን በማቅለል የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ፍሰታቸው እንዲጨምር በሚያስችል ደረጃ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ለማስተካከል ከተቀየሱ የፖሊሲ ግቦች መካከልም በመስኖ ልማት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማካሄድ በግብርናውና በኢንዱስትሪው መካከል ያለውን የመመጋገብ ክፍተት መቅረፍ፣ የተሻለ የግብርና ኤክስፖርት ገቢ ማመንጨትና በሒደቱም ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለግብርና ዘርፉ ከተሰጠው ልዩ ትኩረት በተጨማሪ በቱሪዝምና በማዕድን ዘርፎች ተመሳሳይ ትኩረት በመስጠት፣ ተጨማሪ ገቢና የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታሰቡን ገልጸዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑትና ሌላው ሐሳብ አቅራቢ የነበሩት ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በፕሮጀክት አስተዳደር ችግር ውጤታማ መሆን ያልቻሉትን፣ በዚህ ምክንያትም ፕሮጀክቶቹ ታስቦ የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ውጤት ማስገኘት ሳይችሉ በውጭ ዕዳዎች ታንቀውና የአገሪቱን የውጭ ዕዳ አንረው የሚገኙትን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በፕራይቬታይዜሽን ለግል ባለሀብቶች በመሸጥ፣ የአገሪቱን ዕዳ ማቃለል በኢኮኖም ሪፎርሙ ትኩረት የተሰጠው ሌላው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አንዳንዶቹ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች እስከ አንገታቸው ድረስ በዕዳ የተዘፈቁና ተጨማሪ ካፒታል እንዲያገኙ ቢደረግ እንኳን መዳን የሚችሉ ባለመሆናቸው፣ በሽያጭ ወደ ግል ተዘዋውረው እንዲተርፉ ማድረግ ለመንግሥት የቀረው ብቸኛው አማራጭ መሆኑን አማካሪው ብሩክ (ዶ/ር) ተናረዋል፡፡ ሙሉ በሙሉና በከፊል የሚሸጡትም ድርጅቶች እ.ኤ.አ. እስከ ማርች 2019 ድረስ ብቻ 319.3 ቢሊዮን ብር (11.17 ቢሊዮን ዶላር) የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ ውስጥ የተዘፈቁት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ማለትም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም መሆናቸው ታውቋል፡፡

 ከእነዚህ በተጨማሪም አገሪቱ ለአውሮፓ ገበያ በሸጠችው ዓለም አቀፍ የዕዳ ሰነድ (ቦንድ) ባገኘችው አንድ ቢሊዮን ዶላር የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በሽያጭ ለግል አልሚዎች እንዲተላለፉ ተወስኗል፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያ እንደሚሉት ከሆነ፣ መንግሥት የገባበት አጣብቂኝ ሁለት እርስ በርስ የተጠላለፉ ቋጠሮዎችን መፍታት ነው፡፡ ከእነዚህ አንዱ የኢኮኖሚ ቅርቃር ውስጥ ላለመግባት የሚያስፈልገውን የኢንቨስትመንት ካፒታል በማመንጨት የኢኮኖሚ ልማቱን ማስቀጠል ሲሆን፣ ይህንን ለማድረግ የሚያስፈልገው ፋይናንስ ቀደም ሲልም ሆነ አሁን ከአገር ውስጥ ገቢዎች የሚመነጭ አይደለም፡፡ በመሆኑም የውጭ ሀብትን አፈላልጎ ማምጣትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ኢኮኖሚውን ለማስቀጠል የሚፈለገውን ተጨማሪ የውጭ ፋይናንስ ለማግኘት፣ አገሪቱ የተሸከመችውን የውጭ ዕዳ ከፍሎ ማቃለል የግድ የሚጠይቅና ሁለቱ ጉዳዮች እርስ በርስ የተጠላለፉ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ አንፃር ሲመዘን መንግሥት ያለው አማራጭ ዕዳ የተሸከሙትን ድርጅቶች በመሸጥ ዕዳውን ማቅለል፣ የዕዳ መክፈያ ጊዜያቸው ገና ከሆነ የልማት ድርጅቶች ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ኢኮኖሚውን ለማስቀጠል ለታቀዱ ልማቶች ለማዋል የተቀመጠው የፖሊሲ አቅጣጫ በጥንቃቄ ከተተገበረ፣ የሚፈለገውን ውጤት እንደሚያስገኝ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለግብርናና ለመስኖ ልማት ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን መልካም ነው ባለሙያው፣ አገሪቱ የተለመችውን የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመገንባት ረዥም ርቀት የወሰደባት በሁለቱ ዘርፎች መመጋገብ ባለመኖሩ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ጥሬ ቆዳና ጥጥ ከውጭ እያስገቡ የሚገነባ የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ መሠረት እንደማይኖረውና በዓለም ገበያ ላይም ለመወዳደር እንደማይቻል ያስረዱት ባለሙያው፣ እስካሁን ባለው ሒደት ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን ትልልቅ የውጭ አምራቾች የሳበው ጉዳይ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ለታዳጊ አገሮች የሰጡት የቀረጥና ኮታ ነፃ ገበያ ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋቸው ገምተው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለግብርና ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ከቀድሞው በተሻለ መንገድ ሆኖ ስኬት የሚያመጣ መሆን እንደሚገባው ያሳስባሉ፡፡

ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ፕራይዜታይዜሽንና ሪፎርም በማስመልከት መግለጫ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሐጂ ኢብሳ፣ መንግሥት በይዞታው ሥር የሚገኙ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በፕራይቬታይዜሽን ወደ ግል ይዞታነት ለማዛወር ያስቀመጠውን አቅጣጫ ለመፈጸም በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮ ቴሌኮም፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችና የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንግሥት ትልቁን ድርሻ ይዞ ቀሪው አክሲዮናቸው ወደ ግል እንዲተላለፍ አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል፡፡ የስኳር፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የባቡርና ሌሎች በማምረት ወይም በአገልግሎት ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎችም ሆኑ አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች፣ እንዲሁም በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል እንዲዛወሩ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ከጠቅላላ ከድርጅቱ የአክሲዮን ድርሻ እስከ 49 በመቶ ለሽያጭ በማቅረብ አብላጫ ድርሻውንና የቦርዱን አስተዳደር ይዞ እንዲቀጥል እንደሚደረግ፣ ይህንንም ለመተግበር መንግሥት የቅድመ ፕራይቬታይዜሽን ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በቀጣይ ኢትዮ ቴሌኮም በሁለት ምድብ ማለትም በመሠረተ ልማት (መስመር) ዝርጋታና በአገልግሎት አቅርቦት ዘርፍ ይደራጃል፡፡ የመስመር ዝርጋታው ዘርፍ ዓለም አቀፍ መገናኛዎችን፣ አገር አቀፍ የፋይበር ኦፕቲክ፣ ለኔትወርኩ ጠቃሚ የሆኑ እንደ የሞባይል ኔትወርክ ማማ (Cellular Towers) ያሉትን ሥራዎች የመገንባት ድርሻ ሲኖረው፣ የአገልግሎት ዘርፉም የሁሉንም የሞባይል፣ የኢንተርኔትና የመደበኛ ስልክ የችርቻሮ ሽያጭ ኃላፊነትን ተረክቦ የሚሠራ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡

መንግሥት የተለያዩ ቅድመ ፕራይቬታይዜሽን ዕርምጃዎች በመውሰዱም በዓለም ላይ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ የቴሌኮም ድርጅቶችን ፍላጎት እየሳበ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በማዘዋወር ሒደቱ ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ በቴሌኮም ዘርፍ የገበያ ውድድር እንዲጨምር መሠረት የሚጥል በመሆኑ የተሻለ የቴሌኮም አገልግሎት እንደሚኖርና ይህም የአገልግሎት ክፍያዎችን በመቀነስ፣ የአገልግሎት ተደራሽነቱን በማስፋት በመንግሥት የታቀደውን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቂ ሽፋን የመስጠት ግብን የሚያሳካ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፉን ለውድድር መክፈቱና ገበያን ወደ ግል ማዞሩም የውጭ የቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ማሻሻያው አካል ለሆነው ኢንቨስትመንትን የማስፋፋትና ሥራን የማቀላጠፍ ውጥን አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያውን ለመደገፍ እንደሚውል፣ ይህም ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ ለአገራዊ ብድር ጫናውም ሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በመቅረፍ ረገድ ሚናው የጎላ እንደሚሆንና ኢኮኖሚውን በሚደጉም ሥልት የሚፈጸም መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ የስኳር ፋብሪካዎችን ባለቤትነት ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ማዛወርን፣ የማኔጅመንት የኮንትራት ውልን፣ እንዲሁም የመንግሥትና የግል አጋርነትን አስመልክቶ መንግሥት ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ የስኳር ፋብሪካዎችን የፕራይቬታይዜሽን ሒደት ማመቻቸት በተመለከተም ገንዘብ ሚኒስቴር የንብረቶቹን ዋጋ፣ የፋብሪካዎችን አቅም፣ እንዲሁም እያንዳንዱ ፋብሪካ በተቋቋመበት አካባቢ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳዮችን አስመልክቶ ጥናት እያካሄደ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሐጂ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘም የገንዘብ ሚኒስቴር የስኳር ፋብሪካዎችን አዋጅ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዚህ አዋጅ ዋነኛ ዓላማ ስኳር የማምረት፣ የመሸጥ፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡና ወደ ውጭ የሚላኩ የስኳር ምርትን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የስኳር ፋብሪካዎቹ ሽያጭ ሒደት ግልጽና ለውድድር የሚጋብዝ እንዲሆንም ሚኒስቴሩ እየሠራ መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅትም የተመረጡ የስኳር ፋብሪካዎች ጠቅላላ ይዞታ ጥናት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከስኳር ፋብሪካዎቹ ሽያጭ በተጨማሪ ከስኳር ምርት ዘርፍ የእንስሳት መኖ፣ የእንስሳት ማድለብ፣ የወረቀት ሥራ፣ የአልኮል ምርትና ሌሎች ተያያዥ ፕጀክቶች በጣም ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ታሳቢ መደረጉን ገልዋል፡፡ ከስኳር ፋብሪካዎቹ መካከል አምስት ወይም ስድስት ያህሉን ወደ ግል የማዛወር ሥራ በቀጣይ ከስድስት እስከ 12 ወራት ባሉት ጊዜያት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -