Wednesday, May 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየጎዳና ተዳዳሪው የኦሮሚኛ ድምፃዊ አህመድ ያሲን

የጎዳና ተዳዳሪው የኦሮሚኛ ድምፃዊ አህመድ ያሲን

ቀን:

ድምፃዊ አህመድ ያሲን ጃፋር ባለ ትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነው፡፡ ተወልዶ ያደገውና እስከ ዘጠነኛ ክፍል የተማረው በአስበ ተፈሪ ከተማ፣ ልዩ ስሙ አርበረከቴ በተባለው አካባቢ ነው፡፡ ድምፃዊና ገጣሚ የመሆን ፍላጎት በውስጡ ያደረበት አህመድ፣ ትምህርቱን አቋርጦ ፍላጎቱን ማርካት ግድ ሆነበት፡፡ በዚህም የተነሳ በፍቅር፣ በትምህርት፣  በማኅበራዊ ጉዳይ፣ በጎዳና ኑሮ አስከፊነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ወደ 400 የሚጠጉ ልዩ ልዩ ግጥሞችን ደርሶ ከፊሉን ለሕዝብ ማቅረቡን ይናገራል፡፡

ከያኒው አህመድን ከባለቤቱና ከሦስት ልጆቹ ጋር ያገኘነው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ አጠገብ የእግረኛ መተላለፊያ መንገድ ጠርዝ ላይ ከሚገኘው መኖሪያ ቤት የግንብ አጥር ጋር አያይዞ ከዘረጋት የ‹‹ላስቲክ መጠለያ›› ውስጥ ነው፡፡ ከላስቲክ መጠለያ ፊት ለፊት በትንሽ ጠረጴዛ ለሽያጭ የተዘጋጁ ቁርጥራጭ ሶፍቶች ተጠቅልለው ተደርድረዋል፡፡

ማንነታችንን ከገለጽንለት በኋላ የሕይወት ታሪኩን እንዲያወጋን ጠየቅነው ‹‹ተዉኝ እባካችሁ! የሚነካካኝ እንጂ የሚያነሳኝ ሰው ነው ያጣሁት፤›› በሚል ምርር ያለ አነጋገር አሻፈረኝ አለን፡፡

- Advertisement -

እኛም ከብዙ ትዕግሥትና ማግባባት በኋላ ከንዴቱና ከብስጭቱ ትንሽ ጋብ ብሎ ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኝነቱን አሳየን፡፡ እንደ ከያኒው አነጋገር በላስቲክ መጠለያ ውስጥ መኖር ከጀመረ ከስድስት ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡

‹‹በመጀመርያ ቦሌ አካባቢ በሚገኝ አንድ ድልድይ ሥር ላስቲክ ወጥሬ ኑሮን ተያያዝኩት፣ ነገር ግን ‹ፖሊስ ከዚህ አካባቢ መኖር አይቻልም ተነሳ› ብሎ የወጠርኩትን ላስቲክ ከእኔና ከባለቤቴ አልባሳት ጋር አስወገደው፡፡ ከዚህ በኋላ በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ በሚባለው አካባቢ በሚገኘውና ወደ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን በሚያቀናው አደባባይ አጠገብ በቱቦ ሲሚንቶ ላይ ሸራ አስሬ መኖር ጀመርኩ፡፡ አሁንም ፖሊስ ‹ተነስ ከዚህ አካባቢ ብሎ አስነሳኝ፡፡› ለሦስተኛ ጊዜ ግን አሁን ባገኛችሁኝ ቦታ ኑሮዬን እየገፋሁ ነው፡፡ እዚህም እስካሁን ዕርምጃ ባይወስዱብኝም በየዕለቱ እየመጡ ተነስ ማለታቸውን አልተውቱም፤›› ብሏል፡፡

ከሶፍት ሽያጭ በቀን አሥርና አሥራ አምስት ብር እንደሚያገኝ፣ ሸክም ሲገኝ ደግሞ እየተሸከመ በሚከፈለው ገንዘብ ስኳርና ሻይ ቅጠል በመግዛት ቤተሰቡ አንዳንድ ዳቦ እየበሉና ሻይ ፉት እያሉ በመኖር ላይ እንደሆኑ ገልጿል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ሆድ ሲብሰውና ሲበሳጭ ከግጥሞቹ መካከል የራሱን የጎዳና ኑሮና ያጋጠመውን የሕይወት ውጣ ውረድ የሚያንፀባርቁትን ግጥሞች እየመዘዘ እንደሚያንጎራጉር፣ እንጉርጉሮውን የሰሙት አላፊ አግዳሚው ሁሉ እብድ እየመሰላቸው እንደሚመጸውቱትና እጃቸውን እንደሚዘረጉለት ከያኒው ይናገራል፡፡  

ወደ ኪነት ዓለም የተቀላቀልከው ከመቼ ጀምሮ ነው ብለን ላቀረብንለት ጥያቄ አህመድ ያሲን ሲመልስ፣ ‹‹ከዛሬ 21 ዓመት በፊት ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጎዳና ላይ እስከ ወጣሁበት ድረስ ካዘጋጀኋቸውና ከተጠቀሱት ግጥሞቼ መካከል 20 ያህሉ በእኔ፣ አብዛኛው ደግሞ በሌሎች ድምፃውያን ለሕዝብ ጆሮ ቀርበዋል፡፡ ለእኔዎቹ ዘፈኖች ግን የተለየ ቦታ ሰጥቼያቸዋለሁ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የመጀመርያ ሥራዎቼ በመሆናቸውና ከመዘፈኔም በፊት ድምፄን ከሙዚቃ ጋር የማዋሃድ ሥልጠና ለ15 ቀናት ያህል በክፍያ መከታተሌ ነው፡፡ ይህም እንዳበቃ መዝፈን ጀመርኩ፡፡ ዘፈኔን ከሙዚቃ ጋር ያቀነባበረልኝ አዲስ አበባ የሚገኝ አንድ ሙዚቃ ቤት ነው፤›› ብሏል፡፡

ከዘፈኖቹ መካከል 16ቱን በአንድ አልበም፣ የቀሩትን አራት ዘፈኖች ደግሞ ከሌሎች ዘፈኖች ጋር በኮሌክሽን ተለቅቀዋል፡፡ ዘፈኖቹን ለሕዝብ ጆሮ እንዲደርስ ያደረገው አስበ ተፈሪ ከተማ የሚገኝ የዑስማን ሙስ ሙዚቃ ቤት ሲሆን፣ በእጁ የገባለት ገንዘብ ግን ከ40,000 ብር እንደማይበልጥ የቀረውን የሙዚቃው ባለቤቶች የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር እንደነፈጉት፣ ብዙም ሳይቆይ ባለቤቶቹ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ነው የተናገረው፡፡

እንደ ከያኒው አነጋገር ድሬዳዋ አፍረንቀሎ የኪነት ቡድን በድምፃዊነትና በግጥም ደራሲነት ያገለገለ ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባም በማቅናት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የ4,000 ብር፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አጠገብ የ3,000 ብር፣ ካዛንቺስ የ2,000 ብር፣ ቃሊቲ የ1,800 ብር ቤት ከተራይቶ ኑሮውን መርቷል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ግጥሞቹን ከተጠቀሙባቸው ድምፃውያን መካከል አንዳንዶቹ አድራሻቸውን እንደሠወሩበትና ጎዳና ላይም እያዩት እንዳላዩ አድርገው እንደሚሸሹት ተናግሯል፡፡

‹‹በአንድ ወቅት ካዛንቺስ በሚገኘው ጫት መቃሚያ ቤት እግር ጥሎኝ ጎራ ስል አገኘኋቸው፡፡ ድምፃውያኑም የምንተእፍረታቸውን 100 ብር ግፋ ሲል ደግሞ 200 ብር ጣል ጣል አደረጉልኝ፡፡ ይህ ደግሞ የቤት ኪራዩን መሸፈን ቀርቶ ለአንድ ቀን ምሳ እንኳን አይውልም፡፡ ይህም ሁኔታ የባሰ አበሳጨኝ፡፡ ዋል አደር ብሎም የአስም በሽታ አደረብኝ፤›› ሲል ገልጿል፡፡

እንደ ድምፃዊ አህመድ ገለጻ፣ ላደረበት የአስም በሽታ ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት ጥቁር አንበሳ፣ ዘውዲቱና ምኒልክ ሆስፒታሎች ተመላለሶ ታክሟል፡፡ ሕክምናው ግን ለጊዜው ከማስታገስ በዘለለ ምንም ዓይነት መፍትሔ አላስገኘለትም፡፡

ወለጋ ነቀምቴ ውስጥ በባህል ሕክምና ከበሽታው መፈወሱንና ለዚህ ዓይነቱም ሕክምና 4,000 ብር ማውጣቱን አመልክቷል፡፡ ከዚህ በኋላ እጁ ባዶ ሆነ፡፡ በዚህም ሳቢያ ቤተሰቡ የሚላስና የሚቀመስ እስከማጣት የደረሰ የድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፈቀ፡፡ በዚህም የተነሳ ወለጋ ውስጥ ወደ ሠፈራ ጣቢያ ተንቀሳቅሶ ለሠፋሪዎች የእኩል አራሽነትን ተያያዘው፡፡ ይህም አልሆንት ስላለው ቤተሰቡን ይዞ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ የጎዳና ሕይወትን እንደተያያዘ ተናግሯል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ድህነትን በጋራ የማጥፋት ውጥን

ገበሬውን ተጠቃሚ ለማድረግና ድህነትን ለመቅረፍ ከተፈለገ፣ ገበሬው አምርቶና ፕሮሰስ...

ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠት እስከ ምን?

በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የሕዝቡ ስቃይ ቀጥሏል፡፡ በዌስት ባንክ...

በዋጋ ንረት የተማረሩት አሶሳዎች

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማ በፍጆታ ዕቃዎች እየታየ ባለው...