Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊወደ ሦስተኛ ደረጃ መድኃኒት የተሻገረው ኤችአይቪ ኤድስ

ወደ ሦስተኛ ደረጃ መድኃኒት የተሻገረው ኤችአይቪ ኤድስ

ቀን:

በዓለም ከሚገኙ ጥቂት ወግ አጥባቂ አገሮች ተርታ ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች፡፡ የሕዝቦቿ ወግ አጥባቂነት አንዳንዴ ዘመናዊነትን የመጥላት፣ የመገዳደር ያህል የተጋነነ ሊመስል ሁሉ ይችላል፡፡ ብዙ አዳዲስ አስተሳሰቦችና ፈጠራዎች በአገሪቱ ተግባራዊ ከመደረጋቸው አስቀድሞ በባህልና ሃይማኖት መነጽር ማኅበረሰቡ እንዴት ሊመለከተው እንደሚችል በቅድሚያ በጥልቀት ይጤናል፡፡

ቁሳዊና ትውፊታዊ ባህሎቿ፣ ወጓ ሃይማኖታዊ መሠረት ያላቸው፣ በትውልድ ቅብብሎሽ ዘመናትን የተሻገሩና በጊዜ መተካካት የበሰሉ ናቸው፡፡ ሐሳቡን በቀላሉ ለማስረዳት የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ፣ የቅዱስ ቁርዓን ሱራ ማጣቀስ የሚቀናው ሕዝቧ፣ አገሪቱ የጠኔ ምድር ብቻ ሳትሆን ለፈጣሪ የተገዙ ፃድቃን መኖሪያም ሆና በዓለም ትታወቅ ዘንድ ረድቷታል፡፡ በሃይማኖት ላይ የፀናው የኢትዮጵያ የኋላ ታሪክ፣ የአሁን ህልውና ቅድስት አገር የሚል ቅጽል ታገኝ ዘንድም ምክንያት ሆኗል፡፡

በቀሪው ዓለም ብዙ ባህልና ልማድ ከጊዜው ጋር እንዲሄድ ተደርጎ እየታደሰ፣ እየተከለሰና እየተቀነሰ የዘመናዊነት ቁንጮ የሆኑ አሁናዊ ባህሎች ተቀርዋል፡፡ በቅድስቲቱ ምድር ግን ብዙዎቹ ልማዶችና ባህሎች ቀድሞ ከነበራቸው ቅርፅ ብዙም ሳይለወጡ እዚህ ደርሰዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ለአገሩ ያለው ፍቅር፣ ለወላጆቹ ያለው ክብር፣ ለትዳሩ የሚከፍለው መስዋዕትነት አሁንም እንደ ጥንቱ፣ እንደ ወጉ ነው፡፡

አዎ ይኼ እኩሉ እውነት እኩሉ ደግሞ ማጋነን ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም የፖለቲካ ዕጩዎችምርጫ መቀስቀሻነትና መደለያነት የተጠቀሙበት ዲስኩር ሊመስልም ይችላል፡፡ የተባለው ሁሉ እውነት ነው የሚል ወግ አጥባቂም ከእናንተ አንባቢዎች መካከል አይጠፋም፡፡ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ተደርገው የሚታሰቡ ማኅበራዊ እሴቶች ምን ያህል መዘንጋታቸውን፣ በሥውርም ይሁን በይፋ መጣሳቸውን፣ መገደፋቸውን ለማስረዳት ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ በትዳር ረገድ ያለውን ሁኔታ ማንሳት በቂ ነው፡፡

አመንዝራን በሚጠየፍ ወግ አጥባቂ ማኅበረሰብ መካከል ስንቶች ከትዳር አጋራቸው ተሸሽገው በድብቅ ከጎረቤት ተዋልደዋል? ስንቶች ተገደው ተደፍረዋል? ስንት አባታቸው የካዳቸው ሕፃናትስ በአያትና በአጎት ስም እየተጠሩ አድገዋል? ይህንን የአደባባይ ሚስጥር እየሆነ የመጣውን መራር እውነታ ቤት ይቁጠረው ተብሎ ግን አልታለፈም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ሰኔ 28 ቀን 2011 .ም. ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት፣ ከመቶ ባለትዳር ወንዶች መካከል ቢያንስ 26 በትዳር አጋራቸው፣ በልጆቻቸው እናት ላይ ይማግጣሉ፡፡ ከመቶ ባለትዳር ሴቶች መካከልም ዘጠኝ የሚሆኑት በውዳቸው ላይ ሌላ ይደርባሉ፡፡ ይህ ጠበብ ተደርጎ ሲታሰብ የግለሰቦች ጉዳይ፣ ሰፋ ተደርጎ ሲታይ ደግሞ አገራዊ ችግር ይሆናል፡፡

የችግሩ አሳሳቢነት ትዳር በመፍረሱ በግለሰቦች ደረጃ ከሚፈጠር የሥነ ልቦና፣ የኢኮኖሚና ሌሎች ማኅበራዊ ቀውሶች ጀምሮ የአባላዘር በሽታዎችን ሥርጭት ከፍ እስከማድረግ ደርሷል፡፡ ምክንያቱም በትዳራቸው ላይ የሚማግጡ ብዙዎች መከላከያ አይጠቀሙም፡፡ ችግሩ በተለይም በሴቶች እንደሚብስ የሚያሳየው ጥናቱ፣ ከትዳር ውጪ ከሚሄዱ 100 ሴቶች መካከል 42 የሚሆኑት ተያይዞ ስለሚመጣው መዘዝ አያስቡም፣ መከላከያ ኮንዶም አይጠቀሙም ይላል፡፡ ይህም በከተማው ያለውን የኤችአይቪ ሥርጭት እንዳይቀንስ እያደረጉ ካሉ ግንባር ቀደም ምክንያቶች አንዱ ነውም ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ 610,335 የኤችአይቪ ሕሙማን መካከል 104,851 የሚኖሩት በአዲስ አበባ ነው፡፡ ይህም በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ከሚሠሩ 100 ሰዎች መካከል ሦስቱ ወይም አራቱ ከኤችአይቪ ጋር አብረው ይኖራሉ እንደማለት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ያለው የበሽታው ሥርጭት ከጋምቤላ ክልል በመቀጠል ከፍተኛው ነው፡፡

በእርግጥ በከተማዋ ያለው የሥርጭት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደመጣ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2005 በአዲስ አበባ የነበረው የኤችአይቪ ሥርጭት 6.28 በመቶ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2010 ወደ 4.26 ወርዷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 ደግሞ ወደ 3.83 ቀንሶ ነበር፡፡ ነገር ግን እ.ኤ.አ. ከ2016 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ውስጥ የሥርጭት መጠኑ በ3.79 እና 3.45 መካከል ተገድቦ ቀርቷል፡፡ ከዓመት ወደ ዓመት ያለው የሥርጭት መጠን እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም፣ የሚቀንስበት መጠን እንደ ከዚህ ቀደሙ ፈጣን አለመሆኑ ግን ሥጋት ነው፡፡

እንደ አገር ያለው የሥርጭት መጠን 0.9 በመቶ ሆኖ ዝቅተኛ ቢመስልም፣ በአዲስ አበባ ያለው ሁኔታ ግን ከተማዋ አሁንም በኤችአይቪ ወረርሽኝ ውስጥ መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡ ሁኔታው ወረርሽኙ ያገረሽ ይሆን የሚል ሥጋት ሁሉ ፈጥሮ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ቀደም ሪፖርተር በሠራቸው ዘገባዎችም አንዳንድ ባለሙያዎች የማገርሸት አዝማሚያ መኖሩን በቁጥር አስደግፈው ይገልጹ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡

የኤችአይቪ ሥርጭት መጠን ጣራ በነካበት የጨለማ ወቅት ከ100 ሰዎች 23 የሚሆኑት የወረርሽኙ ሰለባ እንደነበሩ አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በአንድ ወቅት መላዕከ ሞት የነበረው ቫይረሱ በርካቶችን ረፍርፏል፡፡ በኤችአይቪ ሕፃናት ያለ ወላጅ ቀርተዋል፣ ትዳር ተበትኗል፣ ወላጆች ጧሪ ቀባሪ አጥተዋል፣ ሕፃናት ረግፈዋል፣ አገር ተናግቷል፡፡ ጥርጣሬና መፈራራት በነገሠበት በዚያ ቀውጢ ወቅት ሕሙማን ሜዳ ተጥለዋል፣ ይደርስባቸው የነበረው መድልዎና መገለልም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ፋታ የማይሰጠውን የወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታት በቂ ፍተሻ ሳይደረግባቸው በመገናኛ ብዙኃን የተሠሩ የዘመቻ ሥራዎች ሳይቀሩ ሳይታሰብ ችግሩ እንዲባባስ ምክንያት ሆነውም ነበር፡፡

ታዲያ እናትን ከልጅ ያቃቃረው፣ የሐኪሞችን ትዕግሥት የፈተነው፣ የአገርን ኢኮኖሚ ያንገዳገደው፣ የምርምር ተቋማትን ትዕግሥት የፈተነው ይህ ክስተት በየቤቱ ገብቶ ሁሉን አስለቅሷል፡፡ በኤችአይቪ ቢያንስ አንድ ዘመዱን ያልቀበረ የለም ለማለት አያስደፍርም፡፡ በርካቶች እንደ ቅጠል ከረገፉ በኋላ መከላከያ ዘዴዎቹ እንደ ልብ ሲሆኑ ነገሮች አብረው ቀሩ፡፡ በጥንቃቄ በተሠሩ የማንቂያ ሥራዎች በፊት የነበረው ሕሙማንን እንደ ጭራቅ የማየት ሁኔታም ታረመ፡፡ መገለልና መድልዎ በአስገራሚ ፍጥነት ቀነሰ፡፡ ፈጣን የነበረውን ሥርጭቱን መቆጣጠርና መቀነስ ተቻለ፡፡ አገሪቱን በታሪክ የማይዘነጋ ጽልማሞት አልብሶ ከነበረው የኤችአይቪ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ነፃ መሆኗም ታወጀ፡፡ ይህ የአገሪቱን ስም ክፍ ያደረገ ግዙፍ ድል ነበረና አገሮች በአንድ ድምፅ ኢትዮጵያን አወደሱ፡፡ የዓለም አቀፍ ቋማት ትኩረትም ወደ ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዞረ፡፡

ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ግን የመዘናጋት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ሥርጭቱ ከዓመት ወደ ዓመት የሚቀንስበት ፍጥነት ከበፊቱ ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑ በጥናት ተረጋገጠ፡፡ ይህንን ተከትሎ በተሠሩ ጥናቶች ማኅበረሰቡ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ በእጅጉ ማሽቆልቆሉ ተለየ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ከቀናት በፊት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ስለ ኤችአይቪ ዕውቀት ያላቸው ከ100 ሰዎች መካከል 48 ገደማ ናቸው፡፡ ይህ ብዙዎችን ያስደነገጠና ምናልባትም ወረርሽኙ እንደገና ሊያገረሽ ይችላል የሚል ሥጋት የፈጠረ ክስተት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ሰፊው ሕዝብ ተመርምሮ ራሱን ያውቅ ዘንድ ይበረታታ፣ የዘመቻ ሥራም ይሠራ ነበር፡፡ ለጋሽ ድርጅቶች ፊታቸውን ወደ ሌሎች ፕሮጀክቶች ማዞር እጅ እንዲያጥር በማድረጉ እንዲመረመሩ የሚበረታቱት ተጋላጭነት ያላቸው የኅብረተሰቡ ክፍሎች ብቻ ሆኑ፡፡ እንደ ልብ የነበረው የምክር አገልግሎትም እንደዚሁ ለውስን የማኅበረሰቡ አካላት ሆነ፡፡ በዚህ ዓመት የኤችአይቪ ምክርና ምርመራ አገልግሎት ያገኙ አዲስ አበቤዎች ብዛት 374,767 ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከል 8,901ዱ በደማቸው ውስጥ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ 5,271 ሰዎችም በበጀት ዓመቱ ወደ ፀረ ኤችአይቪ አገልግሎት ገብተዋል፡፡ በከተማዋ ከሚገኙ 104,851 የኤችአይቪ ሕሙማን መካከል የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና አገልግሎት ያገኙት 950,77 ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 233 ሞተዋል፣ 1,408 የት እንዳሉ አይታወቅም፣ 355 ሕክምናውን አቋርጠዋል፡፡ በአጠቃላይ 1,756
ሕሙማን የፀረ ኤችአይቪ ሕክምናቸውን እየተከታተሉ አይደሉም፡፡

ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን የሚናገሩት በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በሽታ መከላከል ውስጥ የኬር ኤንድ ሰፖርት አማካሪዋ ሲስተር ሃና ኩምሳ፣ አሁንም ድረስ መገለልና መድልዎ በመኖሩ ሕሙማን መድኃኒቱን ሲወስዱ ላለመታየት ሲሉ ብቻ ክትትል እንደሚያቋርጡ ገልጸዋል፡፡ መገለልና መድልዎ በጎረቤትና ጓደኛሞች መካከል ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ መካከልም እንዳልቀረ ‹‹እህትማማቾች የፀጉር ማበጠሪያሽን እዚያው ያዥ፣ አትጠጊኝ፣ አትንኪኝ ይባባላሉ፤›› ብለዋል፡፡

ማኅበረሰቡን ለማስተማር ‹‹እኔ ከቫይረሱ ጋር ነው የምኖረው›› ብለው ይፋ የወጡ ሳይቀሩ በውሳኔቸው እንዲፀፀቱ እየሆነ ነው፡፡ መገለልና መድልዎ መልኩን ቀይሯል የሚሉት የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አለኸኝ ንጋቱ ‹‹መገለልና መድልዎ በዘመናዊ መንገድ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ ጎረቤት ድግስ ኖሮ ላግዝ ብትል ‹አይ አንቺ ደክሞሻል እረፊ› ትባላለች፤›› በማለት በመላ በሰበብ ከማኅበራዊ ኩነቶች የሚገለሉበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ሕሙማን መድኃኒቱን ሲወስዱ ላለመታየት የሚያደርጉት ጥረት የመድኃኒት መውሰጃ ሰዓታቸውን ከማዛባት ባለፈም በሌሎች ውጣ ውረዶች የተሞላ ነው፡፡ መገናኛ አካባቢ የሚኖር አንድ ሕመምተኛ በአቅራቢያ ከሚገኝ የጤና ተቋም መድኃኒቱን ከመውሰድ ይልቅ ራቅ ወዳለና ወደ ማይታወቅበት ቦታ ሄዶ መውሰድን ይመርጣል፡፡ ሕሙማን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሕክምናውን መከታተል የሚከብዳቸው ሁኔታ ውስጥ ቢገቡ እንኳ ቤት ለቤት ለሚደረግ ክትትል አድራሻቸውን የግድ መገኘት አለበት፡፡ ይሁንና ብዙዎቹ ሐሰተኛ አድራሻ ስለሚሰጡ ባለሙያዎች ተከታትለዋቸው ሕክምናውን እንዲቀጥሉ የሚያደርጉት ጥረት ከጅምሩ ይደናቀፋል፡፡ ቀድሞውኑ ሐሰተኛ አድራሻ የሚሰጧቸው ላለመገኘትስ አይደል?

ከዚህ ባሻገርም ኤችአይቪን በፀሎትና በፀበል እንዲሁም በባህላዊ መድኃኒት ለማዳን የሚያስቡ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቱን እያቋርጠው እንደሚጠፉ ሲስተሯ ገልጸዋል፡፡ በደማቸው ውስጥ ያለው የቫይረሱ ሥርጭት መቀነሱን በምርመራ ያረጋገጡም ‹‹በፀሎት ዳንኩኝ›› የሚል እምነት እንደሚያድርባቸውና ሌሎችም መድኃኒቱን አቋርጠው የእነሱን ፈለግ እንዲከተሉ እንደሚያደፋፍሯቸው፣ ነገር ግን ውሎ ሲያድር ሕመሙ እንደገና እንደሚያገረሽና እንደሚሰቃዩ አስረድተዋል፡፡ ጥናቱ እንደሚያሳየውም፣ በከተማው ውስጥ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ከሚወስዱት መካከል በደማቸው ውስጥ ያለው የቫይረሱ ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰላቸው 58 በመቶ ያህሉ ናቸው፡፡

መድኃኒቱን ማቋረጥ በሽታው እንዲያገረሽ ከማድረግ ባለፈ ሌላም ጣጣ ማስከተሉ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ መድኃኒቱን ጀምሮ ማቋረጥ ቫይረሱ መድኃኒቱን እንዲላመድ መንገድ ይከፍትለታል፡፡ በግሎባል ፈንድ ድጋፍ እየታገዛ ለኤችአይቪ ሕሙማን የሚቀርበው ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ተላመደ ማለት ታማሚው ሁለተኛ ደረጃ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት መውሰድ ይኖርበታል ማለት ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች የሚያስተላልፈውም መድኃኒቱን የተላመደ ቫይረስ ነው፡፡ መድኃኒቱን ለተላመደ ቫይረስ የሚታዘዘው መድኃኒት ደግሞ ከመጀመርያው ደረጃ መድኃኒት ዋጋ ወደድ ይላል፡፡

እንደ ሲስተር ሃና ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ውስጥ 4,269 ሕሙማን ሁለተኛ ደረጃ የኤችአይቪ መድኃኒት በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይብስ ብሎም ወደ ሦስተኛው ደረጃ መድኃኒት የተሸጋገሩ የከተማው ነዋሪዎችም አሉ፡፡ አስደንጋጩ ጉዳይ ግን ይህም አይደለም፡፡ ሥጋቱ ፀረ ኤችአይቪ ከተወሰነ ደረጃ በላይ ያልተሠራ በመሆኑ በቀጣይ ለሚከሰቱ የተላመዱ ቫይረስ ዝርያዎች የሚሆን መድኃኒት እንዳይጠፋና የቀድሞው አስከፊ ገጽታ ዳግም እንዳይከሰት ነው፡፡

ይህ ካልሆነ ግን በኤችአይቪ ወረርሽኝ ውስጥ ያለችውን አዲስ አበባን መታደግ ከባድ ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ባለድርሻ አካላትም በጉዳዩ ጠለቅ ያለ ጥናትና ክትትል እያደረጉ በየጊዜው ለማኅበረሰቡ ይፋ ማድረግን ተያይዘውታል፡፡ ከቀናት በፊት ይፋ የተደረገው ጥናትም የተለያዩ አኃዛዊ መረጃዎችን አስደግፎ ሥርጭቱን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ዕድል የሚሰጥ ዓይነት ነው፡፡

በጥናቱ በየትኞቹ የከተማዋ አካባቢዎች ሥርጭቱ እንደሚበዛ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ በአሥሩም ክፍለ ከተሞች ለኤችአይቪ ሥርጭት ምቹ የሆኑ አካባቢዎች ተለይተዋል፡፡ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣ ወረዳ 2፣ ወረዳ 5፣ ወረዳ 9 እና ወረዳ አሥር በተለይም ጣይቱ ሆቴል አካባቢ፣ ሠራተኛ ሠፈር፣ ዳትሰን ሠፈር፣ ከጊዮርጊስ እስከ ሰሜን ሆቴል ያለው መስመር፣ ዶሮ ማነቂያ፣ እሪ በከንቱ፣ አራት ኪሎና ስድስት ኪሎ አካባቢዎች ከፍተኛ ሥርጭት እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች የሚገኙ ሆቴሎች፣ ማሳጅ ቤቶች፣ ሽሻ ቤቶች፣ የምሽት ክለቦችና በቱሪስት የሚዘወተሩ የመዝናኛ ሥፍራዎች ለሥርጭቱ ከፍተኛ መሆን ዋነኛ ምክንያት እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2፣ ወረዳ 6፣ ወረዳ 7፣ ወረዳ 8፣ ወረዳ 9፣ ወረዳ 10፣ ወረዳ 11፣ ወረዳ 12 እና ወረዳ 14 በተለይም ቁጭራ ሠፈር በመባል የሚታወቀው ሾላ አካባቢ፣ እንደ ራሴ ሆቴል ዙሪያ፣ መሳለሚያ (ሁካታ ሠፈር፣ ዜሮ ሁለት፣ ወሰን ካራ መስመር፣ የጎዳና ሴተኛ አዳሪዎች የሚበዙበት ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ አካባቢና ላምበረት መናኸሪያ) በክፍለ ከተማው ከፍተኛ ሥርጭት የሚታይባቸው አካባቢዎች እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በኮልፌ ቀራኒዬ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17፣ ወረዳ 2፣ ወረዳ 7 እና ወረዳ 15 ከፍተኛ የኤችአይቪ ሥርጭት አለባቸው ተብለው ተለይተዋል፡፡ በቂርቆስ ክፍለ ከተማም አምባሳደር፣ ፍል ውኃ፣ መሹዋለኪያ፣ ጨርቆስ፣ ማርገጃ ሠፈር፣ ካዛንቺስ፣ ሒልተን ሆቴል ጀርባ፣ ጎተራ ኮንዶሚኒየምና መስቀል ፍላወር አካባቢዎችም እንዲሁ ተለይተዋል፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣ ወረዳ 3፣ ወረዳ 6፣ ወረዳ 7 እንዲሁም ወረዳ 8 በንፋስ ስልክ ላፍቶ 4 ወረዳዎች፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ 5 ወረዳዎች፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 6 ወረዳዎች፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማ 6 ወረዳዎች፣ በልደታ 5 ወረዳዎች ከፍተኛ የኤችአይቪ ሥርጭት እንዳለባቸው በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡

በእነዚህ የከተማይቱ አካባቢዎች የቫይረሱን ሥርጭት እያባባሱ ከሚገኙ አጋጣሚዎች መካከል አደንዛዥና አደገኛ መድኃኒቶችን መጠቀም፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ ድንግልናን መሸጥ እንዲሁም ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኛ መያዝና ቀጣይነት የሌለው የኮንዶም አጠቃቀም ልማድ በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር ተጋላጮችንና ቅድሚያ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን የኅብረተሰቡን ክፍሎች ማዕከል ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ የማንቂያ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ተጋላጭ ተኮር የኮንዶም አቅርቦትና ሥርጭቶች፣ የምክክርና የምርመራ አገልግሎትና የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና እንዲያገኙም ያደርጋል፡፡ ይሁንና በበጀት እጥረት ሳቢያ የሚጠበቅበትን ያህል መሥራት እንዳልቻለ ተመልክቷል፡፡ ቀጣይነት ያለውና የማይቆራረጥ የግብዓቶች አቅርቦት በተለይም የመመርመርያ ኪት አለመኖር፣ ለተጋላጭና ቅድሚያ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሠራጨው ኮንዶም መጠን አነስተኛ መሆን ሥርጭቱን በሚጠበቀው መጠን ለመቀነስ ፈተና እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...