Thursday, December 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በትምህርት መቀለድ ይብቃ!

‹‹የትኛውንም አገር ለማጥፋት አቶሚክ ቦምብ ወይም ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይል አያስፈልግም፡፡ የሚያስፈልገው የትምህርት ጥራትን ማውረድና ተማሪዎች ፈተናዎችን እንዲያጭበረብሩ መፍቀድ ብቻ ነው፤›› ይላል በአንድ የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ዋና መግቢያ ላይ የተጻፈ ጽሑፍ፡፡ በእንዲህ ዓይነት የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ባለፉ ሐኪሞች እጅ ታካሚዎች ይሞታሉ፣ በመሐንዲሶች ግንባታዎች ይደረመሳሉ፣ በኢኮኖሚስቶችና በአካውንታንቶች ገንዘብ ይጠፋል፣ በሃይማኖታዊ ምሁራን ሰብዓዊነት ይሞታል፣ በዳኞች ፍትሕ ይጠፋል ሲልም ጽሑፉ ያክላል፡፡ ‹‹የትምህርት ሥርዓት ውድቀት የአገርም ውድቀት ነው፤›› በማለት ያጠናክራል፡፡ የመንግሥትም ሆነ የአገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ዋና ትኩረት መሆን ያለበት፣ ትውልድ የሚያድን የትምህርት ሥርዓት ዕውን እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ የትምህርት ዋነኛ ዓላማ ከአንድ ትውልድ  ወደ ሌላው ትውልድ ባህሎችን፣ እሴቶችን፣ ማንነቶችን፣ ቋንቋዎችንና ጠቃሚ ልማዶችን ማስተላለፍ ማስቻል ነው፡፡ በተጨማሪም ዘለቄታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስተዋወቅ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ማኅበረሰቦች መፍጠር፣ በውሳኔ ሰጪነት ሒደት የዜጎችን ተሳትፎ ማበረታታት፣ ብሔራዊ አንድነትን መገንባት፣ የማኅበራዊ ፍትሕ ዓላማዎችን ማስተዋወቅና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ለዚህም ነው የትምህርት ሥርዓቱ በሁሉም ወገኖች ተሳትፎ ተቀርፆ ሥራ ላይ መዋል ያለበት፡፡ ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ እንደመሆኑ መጠን መደማመጥ ይገባል፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረው የትምህርት ሥርዓት ለጥራት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ ስለነበር፣ በዘመነ ደርግና በኢሕአዴግ ከነበሩት ሥርዓተ ትምህርቶች በጣም የተሻለ እንደነበር ይነገራል፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ሥራ ላይ የነበረው ሥርዓተ ትምህርት ለተደራሽነት እንጂ ለጥራት ሥፍራ ባለመስጠቱ፣ ብዙዎች ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ ያቀርቡበት ነበር፡፡ የመረረ ጥላቻ የነበራቸው ደግሞ ‹‹ትውልድ ገዳይ›› የሚል ስያሜም ሰጥተውታል፡፡ ሰሞኑን ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ የተነገረለት አዲሱ የትምህርት ሥርዓት መተዋወቁ አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን ገና ከጅምሩ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞዎች እየተሰሙ ነው፡፡ በተለይ የቋንቋ ጉዳይ ዋነኛውን ሥፍራ ይዟል፡፡ የኦሮሚያ  ክልላዊ መንግሥት የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት ለድርድር እንደማይቀርብ፣ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የቋንቋውን ተጨባጭ ሁኔታ አይገልጽም ብሏል፡፡ በክልሉ ውስጥ ከክልሉ ሥርዓተ ትምህርት ውጪ ማስተማር እንደማይቻል አስታውቋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ልዩነቶች ሲያጋጥሙ አገርን ማዕከል በማድረግ፣ የተሻለውን አማራጭ ማየት የውሳኔ ሰጪዎች አካላት ሚና ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ከምንም ነገር በላይ ለትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት፣ ለአገር የሚበጅ ውሳኔ ላይ መድረስ የሁሉም ወገኖች ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ በትምህርት ቀልድ የለም፡፡

 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ለትምህርት ትልቅ ሥፍራ ይሰጣል፡፡ ትምህርት የማግኘት መብት የሰብዓዊ መብቶች አካል መሆኑንም ያረጋግጣል፡፡ ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶችም በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ጭምር ይደግፉታል፡፡ ትምህርት ለሁሉም ተደራሽና ጥራት ያለው እንዲሆን ይወተውታሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን በትምህርት ተደራሽነት ከፍተኛ ለውጥ ብታሳይም፣ የጥራቱ ነገር ግን እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ምሩቃን ያሉበት ደረጃ የትምህርት ጥራቱ ውድቀት ትልቁ ማመላከቻ ነው፡፡ ይህንን የወደቀ ሥርዓተ ትምህርት በሌላ ለመተካት ሲታሰብም፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች የጥራትን ጉዳይ በፍፁም ሊደራደሩበት አይገባም፡፡ ሌሎች የልዩነት ነጥቦችን በውይይትና በድርድር እየፈቱ፣ ጥራት ላይ ግን ከፍተኛ የሆነ የጋራ አንድነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ አሁንም ልዩነት የሚታይበት ከሆነና በመቀራረብ መደራደር ካልተቻለ፣ የአገርን ውድቀት ያፋጥናል እንጂ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ ስህተቶች ወይም እንቢ ባይነቶች ያተረፉት ለአገርም ለትውልዱም ፋይዳ ቢስ የሆኑ ነገሮችን ብቻ ነው፡፡

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታዎች ማገናዘብ ይኖርበታል፡፡ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የነበሩ የትምህርት ሥርዓቶችን ድክመትና ጥንካሬ፣ በትምህርት ዘርፍ ስኬት ያላቸው አገሮች ተሞክሮዎች፣ የዘመኑ ዕውቀት የደረሰበትን ደረጃ፣ በሥራው ዓለም በተጨባጭ የሚፈለጉ ብቃቶችንና ፍላጎቶችን፣ ወዘተ. መዳሰሱ በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ እግረ መንገዱንም እየተነሳ ያለው የቋንቋ ጉዳይም ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ምንም እንኳን ትምህርት የማንኛውም ጎራ ፖለቲካ ተቀጽላ መሆን ባይገባውም፣ በተቻለ መጠን የተለያዩ ወገኖችን ፍላጎት ማማከል ይጠበቅበታል፡፡ ልምዶች ሲቀሰሙም ሆነ አዳዲስ ነገሮች ሲተዋወቁ ቅቡልነት ማግኘታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ላለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት በላይ የቆየውን ይተካል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቋንቋን መነሻ ያደረጉ ተቃውሞዎች ተሰምተዋል፡፡ አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ለማዋል አምስት ዓመታት እንደሚወስድ የተገለጸ በመሆኑ፣ የሚቀርቡ ተጨባጭ ግብዓቶችን መሠረት በማድረግ ለውይይት መዘጋጀት አገርን ከውድቀት ይታደጋል፡፡ የሚፈለገውም ይኸው ነው፡፡

ትምህርት አገርን የሚያሳድግ፣ ትውልድን በዕውቀት የሚያንፅና ዘለቄታዊ የሆነ የጋራ መግባባት የሚፈጥር መሆን የሚችለው ለጥራቱ የሚጨነቁና የሚጠበቡ ዜጎች ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የተለመደውን ጽንፍ የረገጠ ተቃርኖ ብቻ በማራገብ አንዲት ጋት መራመድ አይቻልም፡፡ ንግግሩም ሆነ ድርድሩ ሥልጡን ሆኖ የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት የሚቻለው፣ ከብሽቅሽቅ ፖለቲካ ውስጥ በመውጣት ብቻ ነው፡፡ ለመፍትሔ የሚበጅ አቅጣጫ ሳያመለክቱ ሥርዓተ ትምህርቱን የቅራኔና የግጭት መሣሪያ ማድረግ ወንጀል ነው፡፡ ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖች ከጥያቄያቸው ባሻገር፣ ምን ቢደረግ ሥርዓተ ትምህርቱ የተሻለ ሆኖ ይቀረፃል ለሚለው መልስ ጭምር ይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡ ጥያቄ የሚቀርብላቸው ወገኖችም በቀና መንፈስ ለመፍትሔ መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አገርን ለውድቀት የሚዳርግ የወረደ የትምህርት ጥራት ይዞ፣ እሱኑ መልሶ የግጭትና የውድመት መንስዔ ለማድረግ መነሳት ሕገወጥነት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የሚችለው በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እንደሆነው ሁሉ፣ የተሻለ ሥርዓተ ትምህርት ሊኖር የሚችለው ከእብሪትና ከጉልበት አስተሳሰብ መላቀቅ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በተለይ በጎን በኩል እየመጡ የሚደነፉ ወገኖች ይህንን ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም በትምህርት ጉዳይ የጋራ ስምምነት መፍጠር የሚቻለው፣ ከሕገወጥነት ይልቅ ለሕጋዊነት ቅድሚያ ሲሰጥ ነው፡፡ የትምህርት ጉዳይ የሚያሳስባቸው ወገኖች በሙሉ በትምህርት መቀለድ ይብቃ ማለት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የትምህርት ሥርዓት ውድቀት የአገርም ጭምር ውድቀት ስለሆነ፣ በትምህርት መቀለድ የለበትም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...