Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየትብብር የትምህርት ፕሮግራም እንዳይሰጡ የታገዱት ዩኒቨርሲቲዎች ኦዲት እንዲደረጉ ተጠየቀ

የትብብር የትምህርት ፕሮግራም እንዳይሰጡ የታገዱት ዩኒቨርሲቲዎች ኦዲት እንዲደረጉ ተጠየቀ

ቀን:

ከግል ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰጧቸውን የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲያቋርጡ ማሳሰቢያ የተሰጣቸው የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ኦዲት መደረግ እንዳለባቸው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ከግል ተቋማት ጋር በመተባበር ከዋና ካምፓሳቸው ውጪ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች ተማሪዎችን ተቀብለው ሲያስተምሩ የነበሩት ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲና ጅማ ዩኒቨርሲቲ የአገርን ሀብት የሚያባክን አሠራር የሚከተሉ በመሆናቸው የግድ ኦዲት መደረግ እንዳለባቸው የገለጹት፣ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሞታ ናቸው፡፡

ኤቢኤች ከተባለ አማካሪ ተቋም ጋር በትብብር በአዲስ አበባ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተምረውን የጅማ ዩኒቨርሲቲ አሠራር በምሳሌነት ያቀረቡት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በኤቢኤች ካምፓስ የሚማሩ ተማሪዎች በተርም 75 ሺሕ ብር እንደሚከፍሉና ከዚህም ውስጥ 52 በመቶ የሚሆነው ለኤቢኤች፣ ቀሪው ደግሞ ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ገቢ የሚደረግበት አሠራር መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በአዲስ አበባ ካምፓሱ ለሚሰጣቸው የትምህርት ፕሮግራሞች ጅማ በሚገኘው ዋና ካምፓሱ የሚሠሩ መምህራንን አዲስ አበባ ድረስ እንደሚያመጣ፣ መምህራኑን ከዋና ሥራቸው ለሳምንታት የሚርቁበት ሁኔታም መኖሩን፣ በአዲስ አበባ ካምፓሱ በተማሪዎች የተጋነነ ክፍያ ከመጠየቁ ባለፈ የመንግሥት ሥራ እንዲበደል ማድረጉን፣ በፕሮግራሙም ከዩኒቨርሲቲው በተለየ ኤቢኤች የተባለው የግል ተቋም ተጠቃሚ መሆኑን ኤጀንሲው በማስረጃነት አቅርቧል፡፡

ከግል ተቋማት ጋር በትብብር የሚያስተምሩ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም መሰል ችግር እንደሚስተዋልባቸው በመግለጽ ኦዲት፣ እንዲደረጉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል፡፡

ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በኤጀንሲው ቅጥር በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አራቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከግል ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰጧቸውን የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲያቋርጡ በደረሳቸው ማሳሰቢያ መሠረት ሲያቋርጡ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ግን ማሳሰቢያውን አልቀበልም ማለቱ አግባብነት እንደሌለውም ገልጸዋል፡፡

‹‹ፕሮግራማችን ኦዲት እንዲደረግ እንፈልጋለን፡፡ ምንም የምንደብቀው ነገር የለም፡፡ ኤጀንሲው ኦዲት ቢያደርገን ደስታችን ነው፤›› ያሉት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር)፣ ዩኒቨርሲቲው የመንግሥትን ውሳኔ እንደማይጋፋ፣ ነገር ግን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተወያየ መሆኑን፣ ኤጀንሲው የፋይናንስ ጉዳይን በተመለከተ የሰጠው መረጃ ግን የተሳሳተ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ኤጀንሲው እንዳቀረበው ሳይሆን ከፕሮግራም ወጪ ቀሪ የሚገኘው ገንዘብ 52 በመቶ ለዩኒቨርሲቲው፣ ቀሪው 48 በመቶ ደግሞ ለኤቢኤች የሚሰጥ ነው፡፡

የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ እዮብ ክፍሌ ከአንድ ተማሪ በተርም 75 ሺሕ ብር ክፍያ ይቀበላል ተብሎ በኤጀንሲው የተሰጠው መረጃም ስህተት እንደሆነ፣ ለሪፖርተር በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ በካምፓሱ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራም የሚማሩ ተማሪዎች ለሁለት ዓመታት የትምህርት ፕሮግራም የሚከፍሉት አጠቃላይ ገንዘብ ከ100 ሺሕ ብር በታች ነው፡፡ እስካሁንም የሕክምና ተማሪዎችን በቅድመ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራም ሁለት ጊዜ ካምፓሱ ተቀብሏል ብለዋል፡፡ የሕክምና ተማሪዎቹ በተለይም የመጀመርያ ባቾች በማስታወቂያ ዋጋ ቅናሽ ተደርጎላቸው በዓመት 120 ሺሕ ብር ወይም የአምስት ዓመት አጠቃላይ 600 ሺሕ ብር ይከፍላሉ ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ሁለተኛው ባቾች ደግሞ በዓመት 135 ሺሕ ብር ወይም የአምስት ዓመት ጠቅላላ ክፍያ ደግሞ 675 ሺሕ ብር ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ተለማማጅ ሐኪም ስለሚሆኑ ለካምፓሱ የሚከፍሉት እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡

በካምፓሱ 70 የሕክምና፣ 700 የደኅረ ምረቃ ተማሪዎች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ እዮብ፣ ለአንድ ዲፓርትመንት በሴሚስተር አምስት መምህራን እንደሚያስፈልጉ፣ ለዚህ ፕሮግራም የሚመረጡ መምህራን ቢያንስ የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያላቸው እንደሆኑ፣ ወደ አዲስ የሚመጡትም እንደተባለው ሥራቸውን በድለው ሳይሆን ዕረፍት በሚሆኑባቸው ጊዜያት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

አጠቃላይ የካምፓሱ ዓመታዊ ገቢ ከ13 እስከ 15 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ፣ ከዚህ ውስጥ ትልቁ ወጪም ለመምህራን የሚከፈለው ክፍያ መሆኑን አቶ እዮብ አስረድተዋል፡፡ አንድ ክሬዲት አወር (ከሰኞ እስከ ዓርብ ወይም ቅዳሜና እሑድ ሙሉ ቀን የሚሰጥ) ለሚያስተምር አንድ መምህር 12,800 ብር እንደሚከፈል፣ ክሬዲት አወሩ በጨመረ መጠን የሚከፈለው ገንዘብም በዚያው ልክ እንደሚጨምር ጠቁመዋል፡፡

ኤቢኤች ካምፓስ ከኤጀንሲው ዕውቅና ያላገኘ ከመሆኑ ባሻገር፣ ኤቢኤች የተባለው ተቋም በራሱ በመንግሥት ዕውቅና የሌለው ድርጅት እንደሆነ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት  ተገልጿል፡፡ እንዲሁም ካምፓስ ለማቋቋም ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ፈቃድ ማግኘት ግድ ሆኖ ሳለ፣ ዩኒቨርሲቲው ግን ይህንን ተላልፎ በራሱ ጊዜ ካምፓስ አዲስ አበባ ውስጥ እንደከፈተና ይህም ፕሮግራሙ እንዲዘጋ አንድ ምክንያት መሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ተገልጿል፡፡

ኤቢኤች ዕውቅና የሌለው ተቋም ነው ለሚለው ክስ ምላሽ የሰጡት አቶ እዮብ፣ ኤቢኤች በካምፓሱ ለሚሰጡ የትምህርት ፕሮግራሞች የሎጂስቲክስ ድጋፍና የፋይናንስ አስተዳደር ላይ ብቻ ከመሳተፍ ባለፈ፣ በአካዴሚክ ጉዳይ ተሳትፎ እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ከኤጀንሲው ፈቃድ ማግኘት እንደማያስፈልገው ሞግተዋል፡፡

ከዚህም ሲያልፍ ድርጅቱ ከተለያዩ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና እንደ ሀርቫርድ ካሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ወስዶ እንደሚሠራ፣ ከተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ክፍሎች ጋር የሚሠራቸው ፕሮጀክቶች እንዳሉት፣ እንዲሁም ትልልቅ የአገር ውስጥ ፕሮጀክቶችን ወስዶ እንደሚሠራ፣ ዓመታዊ ገቢውም 100 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደሆነ፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር በሚሠራው ፕሮግራም የሚያገኘው አጠቃላይ ሁለት ሚሊዮን ብር ያህል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኤጀንሲው ግን ራሱ ኤቢኤችም ሆነ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር የተከፈተው አዲስ አበባ የሚገኘው ካምፓሱ ዕውቅና የሌለው በመሆኑ፣ ፕሮግራሞቹ ይታገዱ በሚል ሐሳቡ መፅናቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ታምራት ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተማሪዎቹን ዕጣ ፈንታ በማያበላሽ መንገድ ጉዳዩ እንዲታይ እየተመካከርን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው የግሉና የመንግሥት ተቋማት በትምህርት ዘርፍ አብረው የሚሠሩበት የአሠራር ሥርዓት እስኪዘጋጅ፣ የፋይናንስ ጉዳዮች አስተዳደርና የኦዲት ሁኔታ የሚታይበት ወጥ ሥርዓት እስኪዘረጋ መሰል የትብብር የትምህርት ፕሮግራሞች እንዳይተገበሩም አሳስቧል፡፡

‹‹በቀላሉ ከፍተን፣ በቀላሉ የምንዘጋው ነገር ስላልሆነ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን ሰርኩላር በተመለከተ በጥልቀት እየተወያየን ነው፤›› ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጀማል (ዶ/ር)፣ ውሳኔው በተማሪዎችና በወላጆች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በጥሞና እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡

‹‹የመንግሥትና የግሉን ሴክተር ትብብር (ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ) የሚከለክል መንግሥትም የመንግሥት አካልም የለም፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ዩኒቨርሲቲው ከኤቢኤች ጋር ያለው ትብብር መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጋራ በሚሠራበት መርህ የሚመራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ትብብሩ የተመሠረተውም በገበያ ጥናት ላይ ተመርኩዞ እንደሆነ፣ ዩኒቨርሲቲዎች ገቢ የሚያመነጩበት አሠራርም በመንግሥት የሚበረታታ መሆኑን በመግለጽ፣ ከግሉ ሴክተር ጋር በትብብር የሚሠሩ መሰል ሥራዎች የመንግሥትን አቅጣጫ የተከተሉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...