Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበጎርፍ አደጋ ከ23 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቀሉ

በጎርፍ አደጋ ከ23 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቀሉ

ቀን:

የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ በተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውን፣ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ በሐምሌና በነሐሴ ወር ብቻ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ወንዞችና ግድቦች በመሙላታቸው አደጋዎቹ መድረሳቸውን፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ባለፉት ሁለት ወራት በደረሱ የጎርፍ አደጋዎች በአጠቃላይ 23,990 ዜጎች መፈናቀላቸውን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ደመና ዳሮታ፣ ነሐሴ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል፡፡

የአደጋው ሰለባ የሆኑ አብዛኞቹ ዜጎች የአፋር ክልል ነዋሪዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡ በክልሉ በፋንቲ ራሱ፣ ጋቢ ራሱና አውሲ ራሱ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ቴሩ ዱብቲ ገልአሎና ዱለቻ ወረዳዎች የሚኖሩ 15,310 ሰዎች ለጉዳት እንደተዳረጉ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ወረዳ በአዋሽ ወንዝ ሙላት በተፈጠረ የጎርፍ አደጋም 6,615 ሰዎች መፈናቀላቸውን፣ በአማራ ክልልም እንዲሁ ደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከመከም ወረዳ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ 700 ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን፣ በደቡብ ክልልም በስልጤና በካፋ ዞኖች፣ በኮንታ ልዩ ወረዳ፣ በወላይታ አካባቢዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ 1,284 ዜጎች መፈናቀላቸውን አቶ ዳሮታ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አደጋው የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስና ለመከላከል በፌዴራል ደረጃ የጎርፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን፣ በክልሎችም በየደረጃው የጎርፍ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ማሳሰቢያ መተላለፉ በዕለቱ ተገልጿል፡፡

በቅድመ ጎርፍ መከላከልና በጎርፍ ወቅት ምላሽ ለመስጠት፣ እንዲሁም በጎርፍ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያገለግል የመጠባበቂያ ዕቅድ እንደተዘጋጀ የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ 1,336,355 ወገኖች ከዚህ በኋላ በጎርፍ ሊጠቁ እንደሚችሉ፣ ከእነዚህም ውስጥ 335,814 ዜጎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ እንደሚሉት በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች  በጎርፍ ምክንያት ለተፈናቀሉ 23,999 ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡ በደቡብ ክልል ለሚገኙ 1,284 በጎርፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች 238 ኩንታል ምግብና 1,799 ልዩ ልዩ የመመገቢያ ቁሳቁሶች፣ መጠለያና አልባሳት በመሠራጨት ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በአማራ ክልል ለሚገኙ 700 ተፈናቃዮችም 130 ኩንታል ምግብና ሌሎች የመሠረታዊ ፍላጎቶች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን፣ ለ6,615 የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮችም 1,225 ኩንታል ምግብ ሥርጭት እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ሌሎችም ልዩ ልዩ ቁሳቁስ፣ አልባሳትና መጠለያ ድጋፍ በመከናወን ላይ መሆናቸውን፣ ለ15,310 የአፋር ክልል ተፈናቃይ ዜጎችም 2,716 ኩንታል ምግብ ድጋፍ እየተሠራጨ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ለደረሱትና ሊደርሱ እንደሚችሉ ለሚጠበቁት የጎርፍ አደጋዎች የግድቦችና የተፋሰሶች ሙላት ዋነኛ መንስዔ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ከተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን የተሰጠ መግለጫ እንደሚያሳየው፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በሁሉም ግድቦች ከፍ ያለ የውኃ መጠን ገብቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በላይኛው የአዋሽ ተፋሰስ ከበልግ ወቅት ጀምሮ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ የቆቃና የከሰም ግድቦች በከፍተኛ ሁኔታ ሞልተዋል፡፡ ትንበያዎችንና የኃይድሮሎጂ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ በቆቃ ግድብ ከነሐሴ ወር መጀመርያ ጀምሮ ከፍተኛ ውኃ የመልቀቅና የማስተንፈስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን፣ ይሁንና እየጣለ ባለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የግድቡ የውኃ መጠን በአግባቡ ሊቀንስ አለመቻሉ ተገልጿል፡፡

የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ግዛው እንደሚሉት፣ በወሩ መጀመርያ አካባቢ በአማራ ክልል በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ሁመራ አካባቢ የጣለው ከባድ ዝናብ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ አደጋ አድርሷል፡፡ ከቀናት በፊትም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የገባር ወንዞች ቅጽበታዊ ጎርፍና የአዋሽ ወንዝ ሙላት በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ እነዚህ አካባቢዎች በተለይ የላይኛው አዋሽ ከምዕራብ ሸዋ ጀምሮ ምሥራቅ ሸዋ ቆቃ ግድብ ድረስ የውኃ ማቆሪያ መሠረተ ልማት (ግድብ) ስለሌላቸው፣ በተደጋጋሚ ከፍተኛ ጎርፍ የሚጠቁ ናቸው፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮችም ውኃውን ተጠቅመው ማምረት የሚችሉበት የተመቸ መሬት እያለ በየዓመቱ ለዕርዳታ እየተዳረጉ መሆናቸው ይነገራል፡፡

‹‹አሁን የቆቃ ግድብ ከፍተኛ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ በዚህ ሳምንት ብቻ ከታች ካሉ ገባር ወንዞች ጋር ተዳምሮ አደጋ እንዳያስከትል ጥንቃቄ በተሞላበት አግባብ በተደጋጋሚ የማስተንፈስ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ከፍተኛ ውኃ እየተለቀቀ ይገኛል፡፡ ያም ሆኖ እየገባ ካለው ውኃ ጋር መመጣጠን ስላልተቻለ የግድቡ የውኃ መጠን እየጨመረ ይገኛል፤›› ሲሉ አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡

ስለዚህ ከግድቡ ግርጌ የአዋሽን ወንዝ ተከትሎ የሚገኙ በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ የአርሲ ዞን፣ እንዲሁም በአፋር ክልል የገቢረሱ ዞን ነዋሪዎች ላይ የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ ከቆቃና ከከሰም ግድብ በታች ወደ ወንዙ ተጠግተው፣ እንዲሁም ከግድቦቹ ኋላ ወደ ግድብ ውኃ መተኛ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ቀድመው አካባቢውን በመልቀቅ ወንዙና ግድቦቹ እስኪቀንሱ ድረስ፣ ከሥጋት ነፃ ወደ ሆኑ አካባቢዎች እንዲቆዩ ባለሥልጣኑ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...