Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየከተማው ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ኃላፊዎች ራሳችሁን ፈትሹ

የከተማው ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ኃላፊዎች ራሳችሁን ፈትሹ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የኅብረት ሥራ ማኅበራትን እንቅስቃሴ በበላይነት የሚመራው የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደተቋም ላይ ላዩን እየተንቀሳቀሰ የቢሆንም፣ በውስጡ ለሚሠሩና የቅርብ ግንኙነት ላላቸው ባለድርሻ አካላት ግን ፍፁም ተቃራኒ ሁኔታዎች እንዳሉበት ግልጽ ነው፡፡

ከመጀመርያው ሲታይ የኤጀንሲው ኃላፊዎች በተቋሙ ውስጥ ወጣ ገባ እያሉ ለስድስት ዓመታት ቆይታ ያደረጉና ተቋሙ ከሥራ ሒደት ወደ ኤጀንሲነት ደረጃ እንዲያድግ ባደረጉት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ምሥጋና የሚገባቸው ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ የኤጀንሲው የበላይ ኃላፊዎች በመድረክ ተናጋሪ ከመሆናቸው በቀር፣  የጠለቀ የአመራርነትና የማስተባበር ችሎታ የሚጎድላቸው ናቸው፡፡

ሌላውን ሁሉ ትተን፣ ቅሬታዎች ሲቀርብላቸው ኃላፊነቱን በሚያምኑባቸው ግለሰቦች ላይ ብቻ ጥለው ጉዳዩ የደረሰበትን ደረጃ ለማወቅና ክትትል ለማድረግ የሚሳናቸው ግለሰቦች የሚመሩት ተቋም ነው፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ከአንድ ዓመት በፊት ከክፍለ ከተሞች ተመርጠው የመጡና አሁን እንዳሉት ሌሎች ኃላፊዎች  ሁሉ ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ሥራዎች ጋር ግንኙነት የሌላቸው፣ በሌላ ዘርፍ ላይ የነበሩ በመሆናቸው ተቋሙን ጎድተውታል፡፡ ኤጀንሲው አሁን ለሚገኝበት ደረጃ ያበቃውንና ነባሩን የኅብረት ሥራ ባለሙያ ሁለት ጊዜ የሠራተኛ ምደባ በሚል ጊዜን እየጠበቁ ያለ አጥጋቢ ምክንያት ከሥራ መደቡ በማንሳት በምትካቸው፣ ከጥቂት ወራት በፊት ከክፍለ ከተሞች የሚያመጧቸውን ጀማሪ እንዲሁም በዘርፉ ጥቂት ዓመታት ብቻ ያገለገሉት ፈጻሚዎች በዳይሬክተርነትና በቡድን መሪነት መድበዋል፡፡ ኃላፊዎቹ ግፍንም ፈጣሪንም መፍራት ትተዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር የሠራተኛውን ችግርና አቤቱታ በግልጽም ሆነ በስውር ለመፈተሽ ያደረገው ምንም ዓይት ጥረት የለም ማለት ይቻላል፡፡ አለያም አውቆ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል ለማለት እደፍራለሁ፡፡ በአገራችን ከዳር እስከ ዳር በሚባል ሁኔታ የለውጥና የመደመር ሐሳብ እየተቀነቀነ ኤጀንሲውን ለምን እንዳልጎበኘው ግን አልገባኝም፡፡ በከተማ አስተዳደሩ የበላይ ኃላፊዎች ዘንድ ኤጀንሲው ትኩረት ተሰጥቶት በሙያው ባለቤቶች ሊመራ ይገባዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አሁን በኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ በስፋትና በተጨባጭ የሚታየው ምዝበራ፣ ብልሹ አሠራር፣ የክህሎት ማነስ ወዘተ. ችግር በቅድሚያ ኅብረት ሥራ ማኅበራቱን በመቀጠል ተቋሙን በነበር ሊያስቀረው ይችላል፡፡

በአገሪቱ የሚስተዋለውን ጊዜያዊ ችግር ተገን አድርገው ልክ የፖለቲካ ድርጅት የሆነ እስኪመስል ድረስ ለተቋሙ ሳይሆን፣ ለራሳቸው ህልውና በመሮጥ ቁልፍ ቦታዎችን ያስያዟቸው የፖለቲካ ድርጅት አባላት በእቅፋቸው ይዘው፣ በአንጻሩ ግን የሠራተኛውን ሞራል በመግደል ዕርካታ የተላበሱ የሚመስሉት የአመራር አካላት፣ ‹‹የግርግር ገበያ፣ ለሌባ ያመቻል›› እንዲሉ፣ ለተበዳይ ቀን የማይወጣለት መስሏቸው ከሆነ፣ ተሳስተዋልና የዕርምጃው ቀንደኛ ተጠያቂ ከመሆናቸው በፊት ራሳቸውን ቢያስተካክሉ አላለሁ፡፡

(ደራ ዱላ ዲማ፣ ከአዲስ አበባ)

***

መንግሥት እስከ መቼ የጎዳና ነጋዴዎችን ሲያባብል ይኖራል?

ዕውቀት፣ ሕጋዊነት፣ አማራጭ የሥራ ዘርፍና ተደራሽነት ሌላም ጉዳይ የማይጠይቅ ክፍት የሥራ መስክ ቢኖር፣ የጎዳና ንግድ ይመስለኛል፡፡ በመንግሥትና በግል ሥራ መስኮች በቆየሁባቸው 36 ዓመታት ውስጥ በርካታ ሕገወጥ ሥራዎችና እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ የመጣት በቅርቡ ነው፡፡

ለእርሻ፣ ለአነስተኛና ጥቃቅን ሥራ፣ ለጋብቻ፣ ለውትድርና፣ ለቤት ሠራተኛነት፣ ለትምህርትና ለግንባታ ሥራ ብቃትና ዕምቅ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች ከየገጠሩ ፈልሰው በመምጣት በየመንገዱ ቁሳቁሶችን ለመሸጥ ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ ፖሊስና ደንብ አስከባሪዎችም እነዚህ የመንገድ ላይ ነጋዴዎች ለመቆጣጠር መደበኛ ሥራቸው ሆኗል፡፡ በዚህ ውጤት አልባ ቁጥጥር መንግሥት ምን ያህል ጊዜና ገንዘብ እንደሚያባክን መገመት ይቻላል፡፡ ሥራው ለነጋዴዎቹም ቢሆን፣ ለዕለት ጉርስ መሸፈኛ ካልሆነ በቀር ዘላቂ ትርፍ የሚያስገኝላቸው አይመስልም፡፡ ወጣቶቹም ከተማ ከለመዱ በኋላ ምንም ቢደረግላቸው ዳግመኛ ወደመጡበት ይመለሳሉ ማለት ከንቱ ግምት ነው፡፡

ጎዳና ላይ መነገድ፣ መንገድ መዝጋት፣ እግረኛን ማወክ ለነጋዴዎቹ መብታቸው ይመስላቸው ይሆናል፡፡ ይህን አታድረጉ ከሚሏቸው ሥርዓት አስከባሪዎች ጋር ይጋጫሉ፡፡ ሁከት ይፈጥራሉ፡፡ የሁከት ድምፅ በማሰማት፣ ከትራፊክ መብራቶችና በፍጥነት ከሚከንፉ ተሽከርካሪዎች ሥር በመሹለክም ራሳቸውና መንገደኛውን ለአደጋ ያጋልጣሉ፡፡

እውነት ለመናገር መንግሥት ካለበት የፀጥታ ሥጋት አኳያ ሲመዘን፣ በየአካባቢው የሚሰማሩት ተቆጣጣሪዎችና ኃላፊዎች ቁርጠኛና የተቀናጀ እንቅስቃሴ ቢኖራቸው፣ የመንገድ ላይ ነጋዴዎችን ደረጃ በደረጃ ወደ ሕጋዊ መስመር ማስገባት ይቻላል፡፡ በዝምድናና በገንዘብ በመሞዳሞድ፣ ተቆጣጣሪዎቹ ወይም ደንብ አስከባሪዎቹ ለቁጥጥር ሲሰማሩ ቀድመው ለሚያውቋቸው ነጋዴዎች በስልክ በማሳወቅ ከደንብ ጠባቂዎች ዕይታ ገለል እንዲሉ የማድረግ እኩይ ተግባር እንዳለ ነጋዴዎቹ ራሳቸው ሲያወሩ እንሰማለን፡፡

ይህ ሥርዓት ያጣ አካሄድ መፍትሔ ካልተበጀለት በቀር በከተማውና በነዋሪዎች ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል አደጋ ያመጣል፡፡ ስለዚህም በሕግና በሕጋዊነት   ላይ በመመሥረት ነጋዴዎቹን በማደራጀትና በሕጋዊነት በመመዝገብ በተፈቀዱ መነገጃ ቦታዎችና በመጠለያዎች የሚስተናገዱበት ዘዴ ቢፈጠር የሚል ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡ በተለይ በመገናኛ አደባባይና ዙሪያውን ሕዝብ እንደ አሸን የሚተላለፍበት መንገድ በነጋዴዎቹ እየተዘጋ እግረኛው ከተሽከርካሪ እየተጋፋ ለአደጋ በሚያጋልጠው አኳኋን ለመጓዝ ሲገደድ እየታየ ነውና የሚመለከታችሁ አካላት መጥታችሁ ጎብኙት፡፡

(ከመልካሙ በኃይሉ፣ ከአዲስ አበባ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...