Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ብዙ ጊዜ ወሬያችን ስለመሬት አይደል? መሬት ራሱን የቻለ የቅራኔ ምንጭ ሲሆን ዝም ማለት ይቻላል እንዴ? እኔም ይህንን መሠረታዊ ጉዳይ በተመለከተ ያጋጠሙኝን በቅደም ተከተል ልንገራችሁ፡፡ በአንድ ወቅት የሊዝ አዋጅን አስመልክቶ የተፈጠረውን ግራ መጋባትና የሚሰጡትን ማብራሪያዎች በየፈርጁ እየሰማኋቸው ነበር፡፡ የሊዝ አዋጁ የይዞታ ባለቤትነት መብትን ከመጋፋቱም በላይ፣ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን ሀብት የማፍራት እንቅስቃሴ ይገታል የሚሉ ክርክሮች አሉ፡፡ መሬትን በሊዝ ሥርዓት በማስተዳደር የሌብነት ድርጊትን በመገደብ ዜጎች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምኅዳር ይፈጠራል የሚሉ አመለካከቶችም ይደመጡ ነበር፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ አዋጁን የሚያስፈጽሙ ደንቦችና መመርያዎች ምን ይዘው እንደሚመጡ ገና ግልጽ አይደለም፡፡ የነባር ይዞታ ባለመብቶች ጥቅማቸውን በሚያሰሉበት መንገድ፣ መንግሥትም የራሱን ድርሻ እያሳበ በመምጣቱ የከተማ መሬት ገና ብዙ ጣጣ ያለበት ይመስለኛል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከቢጤዎቼ ጋር ስንወያይ አንደኛው ጓደኛችን አንድ ሐሳብ አቀረበ፡፡ የመሬት ጉዳይን በተመለከተ መንግሥት የሚከተለው ፖሊሲ የሶሻሊስት ፍልስፍናን መሠረት ያደረገ በመሆኑና በሕገ መንግሥቱም መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ተብሎ ስለተደመደመ፣ የሊዝ አዋጅ ቢኖርም ባይኖርም በነፃ ገበያ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ለመሞገት መነሳት ፋይዳ የለውም አለን፡፡ ‹‹መሬት የመንግሥት ነው በተባለበት አገር ውስጥ ስለግል ይዞታ በማሰብ ጊዜን ማጥፋት ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ነባርም በሉት አዲስ ዞሮ ዞሮ መንግሥት በፈለገው ጊዜ መውሰድ እስከቻለ ድረስ፣ በማንኛውም ጊዜ የሆነ ሕግ ወይም መመርያ ቢወጣ ሊገርመን አይገባም፤›› አለ፡፡ ሰው የመሰለውን የመናገር መብት ስላለው በአንክሮ ሰማነው፡፡

ሌላው ጓደኛችን ግን የቀረበውን ሐሳብ በፅኑ ተቃወመው፡፡ በነፃ ገበያ ሕግ ኢኮኖሚውን እመራለሁ የሚል መንግሥት፣ ከቶውንም የዜጎችን ነፃነት የሚጋፋ ተግባር ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ ነባር ይዞታ ያለው ሰው በሊዝ ሥሪት ውስጥ ሲገባ ንብረቱን መሸጥ ሲፈልግ እንኳ፣ በወቅቱ የገበያ ዋጋ ጠቀም ያለ ጥቅም አያገኝም፡፡ ገዥው ለመሬቱ ተጨማሪ የሊዝ ክፍያ ስለሚጠየቅ ዋጋውን ያራክስበታል፡፡ መንግሥት በፈለገው ጊዜ ቦታውን እፈልገዋለሁ ካለ ወይም በወጣው የሊዝ ዘመን መሠረት ውሉ ከተጠናቀቀ፣ ንብረቱን አፍርሶ እንዲነሳ ይገደዳል፡፡ ደረጃቸውን ያልጠበቁ በሚል በነባር ይዞታ ላይ የሚገኙ ቤቶች ሲፈርሱ በወቅቱ ዋጋ ካሳ አይከፈላቸውም፡፡ በእነዚህና በሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች ጉዳቶች ያጋጥማሉ አለን፡፡ የእዚህኛው ሐሳብም በሚገባ ተደመጠ፡፡ የማያባራው ክርክር ግን ቀጥሏል፡፡

የእኔና የሌሎቹ ጓደኞቼ ወግ ድንገት ሳናስበው ከከተማ መሬት ወጥቶ ወደ ገጠር መሬት ጉዳይ ገባ፡፡ አንዱ ጓደኛችን ኢትዮጵያ በዓለም የመገናኛ ብዙኃን በመሬት ወረራና ሽሚያ ስሟ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ ይህ ደግሞ አፍሪካን በልማት ስም ሊቀራመቱ ለመጡ ወራሪዎች እጅ እንደ መስጠት ነው አለ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጥብቅ ደኖች፣ ፓርኮችና የአርሶ አደር መሬቶች ሳይቀሩ የእነዚህ አዲስ ወራሪዎች ሰለባ ከመሆናቸውም በላይ የተገኘ የረባ ነገር የለም አለን፡፡ መሬት በገፍ የሚወስዱት ባዕዳን መሬቱን የሚያገኙት በሳንቲም ቤት እንደሆነ በኩራት መናገራቸው ያናድድ ነበር ብሎን፣ ‹‹እነሱ ከማያመርቱት ምርት እሸቱን እንኳን የመቅመስ ነፃነት ስለሌለን ስለምግብ ዋስትና አፋችንን ሞልተን መናገር አንችልም፡፡ የሚገርመው ግን በቅርቡ አንዲት ምሁር ይፋ ባደረጉት ጥናት መሠረት የተገኘ ምርት አልነበረም፤›› ብሎ አሳረገ፡፡ በሚገባ አዳመጥነው፡፡ ሌሎች ሐሳቦችም ተዘረዘሩ፡፡

ሌላው ጓደኛችን ሌላ ሐሳብ አመጣ፡፡ አገሪቱ እጅግ በጣም ሰፊ ያልታረሰ መሬት እንዳላት፣ በመላ አገሪቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች ብንጓዝ እንኳን ለውጭ አልሚዎች አይደለም፣ ከእኛ ተርፎ ፆሙን የሚያድር በርካታ መሬት በመኖሩ መጨነቅ አይገባንም አለን፡፡ ‹‹እኛ አቅም ከሌለን ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና ልምድ ያላቸው የተመሰከረላቸው የውጭ ባለሀብቶች ቢመጡ በጣም ሰፊ መሬት ከመልማቱም በላይ የዕውቀት ሽግግር ይገኛል፡፡ ለአርሶ አደሩም ሆነ ለሌላው ሕዝብ የሥራ ዕድል ይፈጠራል፡፡ ከኤክስፖርት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይገኛል፤›› አለ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰፊና በተግባር የሚታይ ኢንቨስትመንት ሲፈጠር የአገር ውስጥ አልሚው ስለሚነቃቃ፣ የምግብ ችግርን ለማስወገድ ይረዳል አለን፡፡ በተጨማሪም በስንፍናችን ምክንያት ስንዴና ሌሎች ምግቦችና ማጣፈጫዎች ከውጭ ማስገባታችን ሊቆጨን ይገባል ብሎ ንግግሩን ጨረሰ፡፡ እኛም በሚገባ ሰማነው፡፡ ሌሎች ነገሮችም ተባሉ፡፡ ክርክሩ መቋጫ ስለሌለው ሌላ ቀጠሮ ያዝን፡፡ ዕድሜ ለመከባበርና ለዴሞክራሲ በሰላም ተለያየን፡፡ በመሬት የተነሳ ስንት ድርጊት በሚፈጸምበት አገር በሰላም መለያየት በራሱ ጥሩ ነው፡፡

ምሽት ላይ ቤቴ ገብቼ ለቤተሰቦቼ ስለውሎዬ ስነግራቸው ትልቋ ልጄ በጣም ሳቀች፡፡ ሳቋ ገርሞኝ ስለነበር፣ ‹‹ምን ያስቃል?›› አልኳት፡፡ አሁንም እየሳቀች፣ ‹‹በቃ እዚህ አገር ከጥንት ጀምሮ የያዘን የመሬት አባዜ አይለቀንም እንዴ?›› በማለት ጠየቀችኝ፡፡ ‹‹መሬት እኮ የምንኖርበትና ለኑሮአችን የምንጠቀምበት ስለሆነ ብንነጋገርበት ምን ይደንቃል?›› በማለት ቆጣ አልኩ፡፡ ‹‹አይ ዳዲ ለምን ትቆጣለህ? ኖረን ኖረን ተመልሰን የምንገባውም መሬት ውስጥ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ከመሬት በላይ ስለሌሎች ነገሮች ማሰብ ብንጀምር እኮ ባህሪያችንም ይቀየር ነበር፡፡ በመሬት የተነሳ ስንገዳደል መኖራችንን አትርሳ፡፡ አሁንም በመሬት የተነሳ ስንቶቻችን ሰላም አለን? መሬትን ብሔር አድርገን የጀመርነው ትንቅንቅ ራሱ ስንትና ስንት መከራ አለበት መሰለህ? መሬትን ትተን እስቲ ስለሌሎች መሠረታዊ ችግሮቻችን ተነጋግረን መፍትሔዎችን እንፈልግ. . .›› አለችኝ፡፡ አሁንም እየገረመኝ፣ ‹‹ለምሳሌ ስለምን?›› ማለት፡፡ ቆጣ እያለች፣ ‹‹ስለሰብዓዊነት፣ ስለመከባበር፣ ስለመፈቃቀር፣ ስለዴሞክራሲ፣ . . . ›› ስታፈጥብኝ ደነገጥኩ፡፡ ይኼም አለ ለካ?

(አቤል ሰፎንያስ፣ ከሲኤምሲ)   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...