Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየፌዴራል ሕገ መንግሥቱ ውሳኔ ሕዝብ ያስፈልገዋል

የፌዴራል ሕገ መንግሥቱ ውሳኔ ሕዝብ ያስፈልገዋል

ቀን:

በሰለሞን መለሰ ታምራት

ሕወሓት ደርግን አስወግዶ ሥልጣን ላይ ሲወጣ የነበረውን የፖለቲካና የዜግነት መዋቅር ብትንትኑን በማውጣት በተግባር ላይ ካዋላቸው ጉዳዮች መካከል፣ ኢትዮጵያን በ14 ክልላዊ አስተዳደሮች መከፋፈል ነበር፡፡ ዘግየት ብሎም የመጣው ሕገ መንግሥት ከክልል 7 እስከ ክልል 11 ያሉትን አንድ ላይ በመጨፍለቅ፣ በደቡብ ክልልነት ወስኖና 14ኛውን ክልል የከተማ ‘መስተዳድር’ ብሎ ዘጠኝ ክልላዊ መንግሥታትን በመፍጠር ፌዴራላዊ መንግሥቱን መሠረተ፡፡ በወቅቱ (ምናልባት እስከ ዛሬም ድረስ) በካፒታሊዝምና በሶሻሊዝም መካከል የሚዋልለው የፖለቲካ አመለካከቱን ያንፀባረቀበትንም ሕገ መንግሥት እነኋችሁ ብሎ ካበረከተልን በኋላ፣ አገሪቱን በተጻፈም ባልተጻፈም ሕግ እያስተዳደረ ለ27 ዓመታት ቀጥሎ ኖሯል፡፡ ይኼው እስከ ዛሬም ድረስ በዋነኛነት የምንተዳደርበትንና እንደ ተሰባሪ እንቁላል ስናሽሞነሙነው የቆየነውን ይህንኑ ዋነኛ ሕግ ዛሬ ለፍርድ እናቀርበው ዘንድ፣ በዚህ ጽሑፌ እንከኖቹን ያለ ርህራሔ ለመተቸት ተነስቻለሁ፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያውያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘመን ተሻጋሪ የሚሆንና እኛንም ወደ እውነተኛ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና የሚያሸጋግረንን ሕገ መንግሥት እናገኝ ዘንድ በውሳኔ ሕዝብ (Referendum) እንዲዳኝ ይኼንን ሐሳቤን አቅርቤያለሁ፡፡

በርካታ ሰዎች የአገሪቱ ፌዴራሊዝም ቋንቋን መሠረት ያደረገ ነው ቢሉም፣ ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባትን አገር ዘጠኝ ቦታ ለመከፋፈል ቋንቋን በመሠረታዊ መሥፈርትነት መጠቀም ካላዋቂነትም ከፍ ያለ ድንቁርና ነው እላለሁ፡፡ ክልሎችን በፌዴራል መንግሥቱ አባልነት ያስተሳሰረው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 47 ቁጥር 2 ላይ እነዚህኑ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሎ የጠራቸውን ማኅበረሰብ ‹‹በማናቸውም ጊዜ›› የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት እንደሰጣቸው ስናስብ፣ ነገ 80 ብሔራዊ የክልል መንግሥታት እንዲኖሩን የአረንጓዴ መብራትን ያህል ምልክት ማስቀመጡን እንረዳለን፡፡ ዛሬ ብቅ ያለችውን የዴሞክራሲ ጭላንጭል ተመልክተውም ስንቶቹ ዞንና ወረዳ የተባሉ መስተዳድሮች የክልልነት ጥያቄያቸውን እንዳቀረቡ እያየን ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥቱ ዋነኛ ሕግ አንቀጽ 46 ቁጥር 2 ላይ፣ ‹‹ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው፤›› ይላል፡፡ እነዚህኑ የተጠቀሱትን አራት የክልልነት መመዘኛዎችን ብንወስድ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የትኛውም ክልል ለክልልነት ብቁ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ይሆንልናል፡፡ እንዴት? እያንዳንዱን መመዘኛ ሚዛን ላይ አስቀምጠን እንመልከተው፡፡ የመጀመሪያው መመዘኛ እንዲያው ዝም ብሎ ለማደናገሪያነት የገባ ስለሆነ እንዝለለው፡፡ ለማደናገሪያነት ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ‘የሕዝብ አሰፋፈር’ ምን ማለት ነው? ሕዝብ ያለበት አካባቢ ለማለት ነው? ወይስ ተመሳሳይ ሕዝብ የሰፈረበት አካባቢ ለማለት ነው? ተመሳስሎአቸውስ በምንድነው የሚለየው? በቋንቋ ነው? በሃይማኖት ነው? በመልክ ነው? ሕዝብ ያልሰፈረበት ቦታ ቢገኝስ በክልልነት ላይታቀፍ ነው? ምንም ትርጉም የማይሰጥ ማደናገሪያ ነው ያልኩበት ምክንያትም ይኸው ነው፡፡

ቋንቋ በመጠኑም ቢሆን ትርጉም የሚሰጥ የሕዝብ መለያ ነው፡፡ በመጠኑም ቢሆን ያልኩበት ምክንያት በአንድ አካባቢ የሚገኝ ሕዝብ የግድ አንድ ዓይነት ቋንቋ ላይናገርና ከአንድ በላይ የሆኑ ቋንቋዎችን ለመግባቢያነት መጠቀሙን ለማስታወስ ነው፡፡ ቋንቋ ዋነኛ አገልግሎቱ ለመግባቢያነት ነውና፡፡ ይኼ በመላው ዓለም የሚታይ እውነታ ሲሆን፣ ከአገራችን ምሳሌ ብንነሳ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢ የራሱ ዘዬ ያለው ኦሮሚኛና ሶማሊኛ በእኩል ደረጃ ይነገራል፡፡ በአካባቢው የሚገኙት ነዋሪዎችም ያለ ችግር ይግባቡባቸዋል፣ ወደ ምዕራብ ትግራይና ሰሜን ጎንደርም ብንሄድ ከአማርኛና ትግርኛ በተጨማሪ ዓረብኛ በስፋት ይነገራል (በሌሎቹም የአፍሪካ አገሮች ይህንኑ እውነታ እንመለከታለን)፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ክልል በአካባቢው በሚነገር ቋንቋ ምክንያት ይካለል ቢባል፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሁለትና ከዚያም በላይ የቋንቋ ባለቤቶች መነሳታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከዚያም በመለስ በትልልቆቹ የአገራችን ከተሞች አማርኛ በከፍተኛ ደረጃ የሚነገር ቋንቋ በመሆኑ፣ ዋና ዋና ከተሞቻችንን የአማራ ክልል ናቸው ብለን ልንጠራቸው እንገደድ ይሆናል፡፡ የቋንቋ መመሳሰል ለክልልነት መመዘኛ ከተደረገ ሌላ ምን ማድረግ ይቻላል? በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 27 ዓመታት የተለጠፈብን የብሔር ታርጋ መመዘኛውም እንዲሁ ግልጽ ያለ አይደለምና አብዛኛውን ጊዜ ብሔር ሲባል ሰው የሚናገረውን ቋንቋ መሠረት ያደረገ መልስ ነው የሚሰጠው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ከደቡብ ክልሎች ውስጥ ከአንዱ ቦታ ከመጡ ወላጆች ብወለድና የምናገረው ቋንቋ ግን አማርኛ ብቻ ከሆነ፣ ብሔሬን አማራ ብዬ ከማስመዝገብ ውጪ ምን አማራጭ አለኝ?

ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬም የዘለቁት የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎችም መነሻ፣ ይኼው ክልሎችና ብሔሮች የሚዋቀሩበት ዋነኛ መመዘኛ ግልጽ ባለመሆኑ ምክንያት በተፈጠረ ጦስ ነው፡፡ ለሁሉም ጥያቄ በመሣሪያ አፈሙዝ መልስ የሚሰጥ መንግሥት እስካለ ድረስ በፍርኃት ተስማምቶ መኖር ይቻል ይሆናል፡፡ በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ዘመን ግን ቋንቋን መሠረት ያደረገ የድንበር ወሰን መጨረሻው ግጭት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ የቋንቋን አከላለል አንድም አስቂኝ የሚያደርገው ሊተገበር የማይችል እውነታም ስለሆነ ነው፡፡ አንድን ቋንቋ 50 ሚሊዮን ሕዝብ ሊናገረው የመቻሉን ያህል፣ በጥቂት ሺሕ ወይም መቶ ሰዎች የሚነገር ቋንቋም ሊኖር ይችላልና አንተ ክልል ሁን፣ አንተ ግን ለመሆን አትችልም ብለን ወደኋላ መመለስ አንችልም፡፡ በሥልጣን ዘመኑ መጀመሪያ አካባቢ ሕወሓት ዛሬ ደቡብ በተባለው ክልል ውስጥም ወደ አራት የሚጠጉ ብሔረሰቦችን በማጠጋጋት አንድ ቋንቋ ለመፍጠር የሄደበትም መንገድ የሚረሳ አይደለም፡፡ የሳምንቱን ቀናት ከሰባት ወደ አምስት የመቀየርን ያህል አወዛጋቢና ውስብስብ ሲሆን እንዲቀር ተደረገ እንጂ፡፡

በዚሁ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 መሠረት ሌላው የክልልነት መመዘኛ በፈቃድ ላይ የተመሠረተ ይሆናል መባሉ ነው (በነገራችን ላይ የእንግሊዝኛው ትርጉም ነው እንጂ በሕዝቦች ፈቃድ መሆኑን የሚገልጸው፣ አማርኛውማ ማን ፈቃጅ ማን አስፈቃጅ እንደሆነ እንኳን ለመግለጽ ከብዶት ይታያል)፡፡ ይኼኛውም መመዘኛ ባያስቅም እንኳን ፈገግ እንድንል የሚያደርገን ነው፡፡ እንዲያው ለመሆኑ የየትኛው ክልል ሕዝብ ነው እኔ መካለል የምፈልገው በዚህኛው ክልል ነው ብሎ ድምፁን የሰጠው? በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ሕወሓት 14 ይሁን ሲል እሺ፣ አይ አልተመቸኝም ዘጠኝ መሆን አለባችሁ ሲለንም እሺ እያልን ነው ዛሬ ላይ የደረስነው፡፡ ሕወሓት በወቅቱ አንድነቷን ጠብቃ በኅብረት ከቆመች ኢትዮጵያ ይልቅ እንደ ባቢሎን በቋንቋ የተደበላለቀና እርስ በርሱ የማይግባባ ሕዝብን ለማስተዳደር እንደማይቸግረው በመረዳቱ፣ ይኼንንም መደነቋቆር መሠረት በማድረግ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመዳኘት ራሱን ብቸኛው ነፍጥ ያነገበ ጉልበተኛ በማድረግ ለዘለዓለም የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ለመግዛት ዕቅድ እንደነበረው፣ ነገሮቹ ግልጽ እየሆኑ ሲመጡ የተረዳነው ጉዳይ  ነው የሆነው፡፡  

ከዚህ በላይ የተመለከትነው ኢትዮጵያ እንዴት በስመ ክልል እንደተሸነሸነች ሲሆን፣ ዜጎቿንም እንዴት እንደከፋፈላቸው ለማወቅ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ መልስ ለማግኘት መሞከር ከሌላ የማይመለስ ጥያቄ ጋር መፋጠጥ መሆኑን ለመረዳት ተጨማሪ ትርጉሞችን እንመልከት፡፡ ይኸው ሕገ መንግሥት መግቢያውን የሚጀምረው ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች›› በማለት ስለሆነ እነዚህ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እነማን ናቸው? ከየትስ መጡ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ብዙ ደክመን በአጨቃጫቂው አንቀጽ 39 የመጨረሻው ቁጥር ላይ እናገኘዋለን፣ እናም እንዲህ ሲል ይተነትነዋል፡፡ ‹‹ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው፡፡›› ይኼንን ትርጉም፣ ትርጉም ነው ብሎ የጻፈውም ሆነ አንብቦ ትርጉም ነው ብሎ የተቀበለ ሰው ምንም ዓይነት የቋንቋ ዕውቀት የሌለው፣ ወይም ሆን ብሎ ነገሮችን በማድበስበስ ለማለፍ የፈለገ መሆን አለበት፡፡ ፈረንጆቹ “If you can’t convince Him, confuse him” እንደሚሉት ማለት ነው፡፡

እስቲ በደፈናው ተሳደብክ እንዳልባል ዘርዘር አድርጌ ልግለጸው፡፡ ሲጀምር ለሦስቱም የተለያዩ ቃላት (ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች) አንድ ዓይነት ትርጉም መስጠት አይቻልም፡፡ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ለየራሳቸው ግልጽ ያለ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል እንጂ፣ አንድ ላይ አጃምለን እንዲህ ናቸው ልንላቸው አይገባም (ነው ወይስ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች አንድና አንድ ናቸው?)፡፡ በማስከተልም የተሰጠው ትርጉም ከአሻሚነቱም ባሻገር በጣም ሰፊና ራሱም ትርጉም የሚያሻው ሆኖ ነው የቀረበው፡፡ ‘የተዛመደ ህልውና’፣ ‘የሥነ ልቦና አንድነት’፣ ‘የጋራ ጠባይ’ የሚሰኙት ግሶች ራሱን የቻለ ትርጉም ካልቀረበላቸው ማንም እንዳሻው እየጠመዘዛቸው የየራሱን ሕግ ሊቀርፅባቸው ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ መመዘኛው ሁሉንም በአንድ ላይ የሚያጠቃልሉትን ነው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የሚላቸው? ወይስ ከተዘረዘሩት መሥፈርቶች አንዱንም ቢሆን ያሟላውን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች ብለን መጥራት እንችላለን? ማንም እንዳይመልሰው ተደርጎ የተሸፋፈነ ትርጉም ነው፡፡ ሌላስ ‘ሰፋ ያለ’ ሲል ምን ማለቱ ነው? በምን መልኩና በምን ያህል መጠን ነው የሚሰፋውና የሚጠበው? ‘ተመሳሳይ ልምዶች’ ምንድናቸው? ኢትዮጵያ ውስጥ ከጫፍ እስከ ጫፍ የምንታወቅባቸው ልምዶች ካሉን (በእርግጥም ይኖሩናል ብዬ አስባለሁ) እንደ አንድ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች ሊያስቆጥሩን ይችላሉ ወይ? የቋንቋውን ጉዳይ ቀደም ሲል በክልል አወሳሰን ላይ በስፋት የተመለከትነው ቢሆንም፣ ከምንካለልበት ቦታም አልፎ ምን ዓይነት ኢትዮጵያውያን መሆናችችን እንዲወስንልን የተቀመጠ መመዘኛም ሆኖ፣ በመቀመጡ ደግመን ስንመለከተው አሁንም ግራ አጋቢነቱ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥት አተያይ ተመሳሳይ ቋንቋን መናገር ብሔር ያስብላል? ወይስ ብሔረሰብ? እንበልና አንድ ግለሰብ ሦስት ቋንቋዎችን መናገር ቢችል ወደ የትኛው ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ይጠቃለላል? በሌላም አንፃር የትኛውንም የአገር ውስጥ ቋንቋ ባይናገር (በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቢወለድ) በየትኛው ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ውስጥ ይካተታል? አንድ ዜጋስ ቋንቋውን (ተምሮም ቢሆን) መናገር ነው የሚጠበቅበት? ወይስ ቋንቋውን ከሚናገሩ ወላጆች መወለዱ ብቻ በቂው ነው? ከቋንቋው ተናጋሪዎች መወለዱ ብቻ በቂው ከሆነስ የሚቆጠርለት የእናቱ ነው ወይስ የአባቱ?

በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን ‘ሕገ መንግሥታችን’ ከሚመልሳቸው ጥያቄዎች በበለጠ የሚጭራቸው ክብሪቶች እየበረከቱ፣ አገሪቱን ወደ ማትወጣበት አዘቅት ውስጥ ከመክተታቸው በፊት አንድ ሊባል የሚገባው ነው፡፡ ልናስተውለው ከፈቀድንም ዛሬ በትክክል እየሆነ ያለውና ላለፉት 27 ዓመታት እንዲሆን የተፈለገውም ይኸው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በፊት እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች ስንመልስ የከረምነው የአገሪቱ ዋነኛ የሕግ መፍቻ ከሆነው ሕገ መንግሥታችን ተነስተን ሳይሆን፣ እንዲሁ በመሰለኝና በደስ አለኝ ስለነበር ወደፊት ጠያቂ ትውልድ ሲመጣ (አንዳንዶች ተፈጥሯል ይላሉ) መደነባበራችን አይቀሬ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም በሕገ መንግሥቱ ላይ ደፍሮ ጥያቄ የሚያነሳ ባለመኖሩ (የእምቧይ ካብ የሆነን ያህል ሕገ መንግሥቱን ለመናድ በማሰብ ተብለው በየእስር ቤቱ ተወርውረው የሰነበቱት ኢትዮጵያውያን፣ ጥፋታቸው ይህንኑ ሕገ መንግሥት በመተቸታቸውና ሊተገበርም የማይችል መሆኑን በማሳየታቸው ነበር) የመንደራችን ካድሬዎች የሚሉንን በመቀበል ብቻ ሕገ መንግሥታዊ ነው አይደለም የሚለውን ጥያቄ ስንፈታው ከርመናል፡፡ የኮልኮሌ ካድሬዎች ዘመን በማብቃቱ በቀደመው ሁኔታ ለመቀጠል መቻላችን ያበቃለት ጉዳይ ይመስላልና ዘላቂውን መፍትሔ ከአሁኑ ልናዘጋጅለት ግድ ይለናል፡፡

አንዳንድ የዋሆች ሕገ መንግሥት ሁሉንም ጥያቄ ለመፍታት አይችልም የሚል አመንክዮ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አንደኛ በጣም መሠረታዊ የሆኑትንና ከላይ የጠቀስኳቸውን የማንነትና የየትነት ጥያቄዎች ያለ ምንም ማምታታት መመለስ የሚገባው ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃም ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችንም የምናይባቸው ሕጎች ሲመነጩ ከሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ መውጣት ስለሌለባቸው በአንድ ወይም በሌላ በሕገ መንግሥቱ ሊጠቀሱ ይገባል፡፡ ለምሳሌም ያህል ሕገ መንግሥቱ የፕሬስ ቅድመ ምርመራን ‘በማንኛውም’ መንገድ የከለከለ ከሆነ ምንም ዓይነት ዝርዝር ሕግ አውጥተን የፕሬስ ቅድመ ምርመራን ተግባራዊ ለማድረግ እንዳንችል ያደርገናል፡፡ እናም ዝርዝር ሕጎቹም ቢሆኑ የሚመነጩት ከሕገ መንግሥቱ እንጂ ከሌላ ከየትም አይደለም ለማለት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹን ግራ መጋባቶች ለማስቀረት ይምስላል በዘንድሮው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ወቅት ማንኛውም ሰው ካላስፈለገው ወይም ካላወቀው ወይም እንደ እኔ ግራ ከገባው፣ ብሔሩን ሳይገልጽ ለማለፍ የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱን ለመረዳት ችለናል፡፡ በእርግጥ ይኼኛውም አካሄድ የራሱ ችግሮች ቢኖሩትም፣ ሕገ መንግሥቱ ለፈጠረው ግራ መጋባት የተሰጠ ጊዜያዊ መፍትሔ በመሆኑ ሊደነቅ ይገባል፡፡ ነገር ግን ዘላቂና ቋሚ ሊሆን የሚችልበት የመፍትሔ አሠራር መፈጠር አለበት፡፡

በመሠረቱ ሕገ መንግሥቱ እውነተኛ የፌዴራል መዋቅር ለመትከል አስችሎ ቢሆን ኖሮ፣ እነዚህ ሁሉ የክልል እንሁንና ከክልል እንውጣ ጥያቄዎች እንደ አሸን ባልፈሉም ነበር፡፡ እንዲያውም በእውነተኛ የፌዴራል የመንግሥት መዋቅር ውስጥ በዝቅተኛው የክልል መዋቅር ላይ መገኘት ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር የሚያጎድለው ምንም ነገር ባለመኖሩ፣ ዞን ካልሆነም ወረዳ መሆን እንደ ጉድለት ተቆጥሮ ጥያቄ የሚቀርብበት ጉዳይ አልነበረም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ስም ብቻ በሚሆንበት ጊዜ ግን በታችኛው የመዋቅር ደረጃ ላይ መገኘት፣ የማዕከልን ትዕዛዝንና መመርያዎችን ያላንዳች ጥያቄ መቀበልን የሚያስከትል በመሆኑ ማንንም ሊያስደስት አይችልም፡፡ በዚህም ምክንያት ቢቻል ከፍተኛውን የክልል መዋቅር፣ ካልተቻለም አንድ እርከንም ቢሆን ወደ ላይ ከፍ በማለት ትኩሱን ድንች ከመቀበል ወደ መወርወር መሸጋገርን መፈለግ፣ በእንዲህ ዓይነት የከሸፈ ፌዴራሊዝም የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የበላዮቻቸውን እየተመለከቱ ምራቃቸውን ሲውጡበት የነበረውን የመንግሥትነት ሥልጣንን ያላንዳች ተቆጪና ሃይ ባይ እንዳሻቸው ሊፈነጩበት የቋመጡ ካድሬዎች፣ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ ሕዝቡን በማያውቀውና በማይገባው የጎሳ የፖለቲካ ጥያቄ እያደናገሩ ከፊት ያሠልፉታል እንጂ፣ ነገ ተነስቶ ክልል ልሁን ወይም አንቀጽ 39ን ጠቅሶ ልገንጠል ቢል አይደለም በአንድ የደቡብ ክልል ለሚገኝ ሕዝብ፣ ለትልቁ የኦሮሚያ ክልልም የሚኖረው ፈተና ቀላል አይሆንም፡፡ ለመገንጠሉማ ኤርትራም ከአንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚልቅ የባህር በርና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንኳን ስትራቴጂካዊ የሆነ መልክዓ ምድር ይዛ ተገንጥላስ አልነበር? እስካሁን ድረስ እንደተረዳሁት ኢትዮጵያዊነቱን የጠላ ወይም ኢትዮጵያዊ ተብሎ መጠራት የማይፈልግ፣ ብሔርም ይሁን ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ መኖሩን አላውቅም፡፡ ድምፃቸው በየማኅበራዊ ሚዲያው ጎልቶ የሚሰሙትን አጭበርባሪ ካድሬና አክቲቪስት ተብዬዎችን ሳይጨምር ማለት ነው (ለነገሩ እነሱም ቢሆኑ ተከታዮቻቸውን በጥቃቅኑ ጥያቄ ሁላ ሲያደናግሩ እንጂ፣ ዜግነትን በተመለከተ የትኛውንም ሕዝብ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ሲያሰኙት አጋጥሞኝ አያውቅም)፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ ሕዝበ ውሳኔ ያስፈልጋል ስል በመሠረታዊነት እነዚህን የማንነት ጉዳዮች አነሳሁኝ እንጂ፣ ሁሉንም አወዛጋቢ ጉዳዮች እንያቸው ካልን አንድ ራሱን የቻለ የጥናት ወረቀት ሊወጣው ይችላል፡፡ እንደ ምሳሌም ሕገ መንግሥቱ በግልጽ መልሶታል የተባለው የመሬት ጥያቄን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 40 ቁጥር 3 ላይ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው ካለ በኋላ፣ ተመልሶ ‹‹መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው፤›› ይላል፡፡ በዚህስ መሠረት መሬት የመንግሥት ነው? ወይስ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች? መሬት ‘የኢትዮጵያውያን የጋራ’ ንብረት ነው ከተባለ አንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ተነስቶ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ በየትኛውም መሬት ላይ የመወሰንና የይገባኛል ጥያቄ የማንሳትስ መብት አለው ወይ? አርሶ አደሩስ ከመሬት ያለ መነቀል መብቱ የተከበረ ነው ተብሎ ሲያበቃ፣ በምን መመርያና አዋጅ ነው ሲፈናቀል የነበረው? ከዚህ ሁሉ ጥያቄ በኋላ እውነታው እንደሚያስረዳን ግን መሬት የማንም ሳይሆን፣ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የሚገኙት ዝባዝንኬዎች ጉዳዩን ለማምታታት የቀረቡ መሆናቸውን ማንም አሌ ሊለው አይችልም፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬ በወሳኝ የፖለቲካ ሽግግር ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህም መሠረት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ዜጎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚሰይሙትን መንግሥት ለመቀበል ተዘጋጅታለች፡፡ ከዚህ በማስቀደም ግን ታላቁ መጽሐፍ እንደሚነግረን አባጣ ጎርባጣው መንገድ መደልደል አለበት፡፡ ጠማማውም መንገድ ሊቀና ግድ ይለዋል፡፡ ነገ የአገሪቱን ሥልጣን የሚጨብጠው ፓርቲ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ሊበራልም ይሁን ሶሻል ዴሞክራሲ ወይም ሌላ፣ ሁሉንም በእኩልነት ሊያሠራ የሚችል ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት አብልጦ የሚመለከት ሕገ መንግሥት ማግኘታችን፣ ለቋሚ የዴሞክራሲ ሥርዓታችን ዋስትና ሊሆነን ይችላልና ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ካልሆነም ሕዝቡ በውሳኔው አሁን በሥራ ላይ የሚገኘውን ሕገ መንግሥት ‘እፈልገዋለሁ አይነካብኝ’ ካለም፣ በዚሁ ሕዝበ ውሳኔ ፍላጎቱን ገልጾ ሲያበቃ የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል ራሱን እንዲያዘጋጅ ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...