Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትወጣቶች ስለብሩሁ ዕጣችን ብለን በዴሞክራሲያዊት ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ ዙሪያ እንቁም!!!

ወጣቶች ስለብሩሁ ዕጣችን ብለን በዴሞክራሲያዊት ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ ዙሪያ እንቁም!!!

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

የትናንትናና የዛሬ ወጣትነት

ሀ) እኔ ወጣት በነበርኩበት በ1960ዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ዋና ችግር ባረጀ የምዝበራና የጭቆና ሥርዓት መቀፍደዷ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ወጣትነቴ፣ የጭሰኛነትን/የገባርነትንና የአገልግሎት ባርነትን ምንነት ከመጽሐፍ ሳይሆን በቀጥተኛ ገጠመኝ የማወቅ ዕድል ነበር፡፡ ከገጠር ርስት እህል ቅቤና ማር እያስመጡ፣ ከከተማ ርስት ልዩ ልዩ ገቢ እየሰበሰቡ በመርሰዲስ የሚፈሱ፣ በላንድሮቨር የሚጀነኑ እንደነበሩ ሁሉ፣ ጥላና ካፖርት በአሽከር አስይዘው በእግር የሚኳትኑና በበቅሎ የሚንገታገቱ፣ ግን ከቁርበትና ከባና ኑሮ ፈቀቅ ያላሉ ጌቶችና እሜቴዎችም ነበሩ፡፡ የአገራችን ሁነኛ ማፈሪያም ይኸው ከገጠር እስከ ከተማ የተንስራፋ ቡትቶ ሥርዓት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ዋና ትኩረትም ይህንኑ ሥርዓት በመቀየር ላይ ነበር፡፡

የሌሎች አገሮች አብዮታዊ የለውጥ ልምዶች፣ የጭቆናና የምዝበራ ትንታኔዎች፣ ነቅናቂ ዲስኩሮች በኢትዮጵያ ተማሪዎች ውስጥ ከፍተኛ የስሜት ንካት መፍጠር ችለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች የኢትዮጵያን ገባር መከራና በደል ይበልጥ እንዲያስተውሉ፣ ተቆርቋሪነታቸው እንዲንር ነዳጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በተለይ ከ1966 ዓ.ም. አብዮት መፈንዳት ወዲህ ከማርክሳዊ ነክ ሥነ ጽሑፍ ጋር ሰፊ ንክኪ መፈጠሩ ያስከተለው ለውጥ ፈርጀ ብዙና ዕፁብ ነበር፡፡ መሸቀርቀርንና መቀናጣትን ዓለሜ ይል የነበረውን፣ የቀለም ዕውቀት ከመምጠጥ ውጪ ሌላ ነገር የማያውቀውን፣ ሻይ ቤት ውስጥ ጫትና በራድ ሻይ ታቅፎ በትርኪምርኪ ወሬ ጊዜ ይገፋ የነበረውን፣ የመንገድና የተቋማት አያ መንትፌ የነበረውን ሁሉ ሰብዕናውን አናውጦና ከልሽቀት ውስጥ መንጭቆ እያወጣ፣ ንቁ አንባቢና ንቁ ተወያይ፣ የምዝበራና የጭቆና ብርቱ ተቃዋሚ፣ በአገሩ ውስጥና በዙሪያ ዓለሙ ስላለ ጭቆናና ምዝበራ አንብቦ ለማወቅ ዓይኑን የከፈተ፣ በአገሩ ውስጥ ያለውን ግፍ ሲያስብ እንባውን መቆጣጠር እስኪሳነው ድረስ የሚብሰከሰክ፣ ለአዲስ ሕይወት ትግል ወጣትነቱን ለመስጠት የቆረጠ ብዙ ትንታግ ፈጥሮ ነበር፡፡ ጆሊነቱንም፣ ፓርቲ ጭፍፈራውንም፣ ከጫትና ከሲጋራ ሱስ እስከ ዱርየነት የደረሰ ውመናን ካሰናበቱና በአብዮታዊ ሥነ ጽሑፎች ተመንጭቀው ወደ ትግል ከገቡት ውስጥ አንድ ምሳሌ እኔው ነኝ፡፡ ከጭፍራነት ብዙም ያልዘለለ የታጋይነት ቅርስ ያሳረፈብኝ አሻራ ይኸው እስካሁን ያግደረድረኛል፡፡ አንዳርጋቸው ጽጌን ከዓይን አፋርነት አውጥቶ ያሰላው ታጋይነትም፣ ይኸው የዓይኑ ሽፋል እስኪሸብት ድረስ ብዙ አሳር አስቆጥሮታል፡፡ ሁለታችንም የአንድ ዘመን ሰዎች ነበርን፡፡

በጊዜያችን በአብዮታዊነት በሰልን፣ ላቅን ያሉ ወጣት ታላላቆቻችን፣ ከተማሪ ትግል ወደ ተደራጀ እንቅስቃሴ ባደረጉት ሽግግር ሁሉም ማርክሳዊነት፣ ሌኒናዊነትና ማኦ ቀመስ ሆነው የተለያዩ ድርጅቶች ቢፈጥሩም፣ በደርግ ላይ በወሰዱት አቋምና በመፈክሮቻቸው ላይ እየተለያዩ ቢመጡም፣ መበላላትን ተገቢና ልክ የሚያደርግ አንዳችም ምክንያት አልነበራቸውም፡፡ ግን አብዮታዊነት፣ ከእኔ በላይ ላሳር ባይነትና ይህንኑ የተመረኮዘ የሥልጣን መሽቀዳደም እያነቃቀፈ/እያዘላለፈ ወደዚያ ወሰዳቸው፡፡ ያ ሁሉ የወጣት ትንታግነት፣ ቁርጠኛነትና የወኔ ሙላት አይሆኑ ሆኖ ሊባክን ቻለ፡፡ በድርጅታዊና በአብዮታዊ ጋዜጣ እንቅስቃሴ ቀድሞ ብቅ በማለት ወጣቱን ማፈስ የቀለለው የኢሕአፓ ቡድን፣ የፖለቲካ ሜዳውን የእኔ ብቻ ብሎ ከመሰሰት አንስቶ ቅራኔን አግርሮ ደርግንና ከደርግ የተጠጉትን “የአብዮተኛነት” ባልደረቦቹን አውሬያቸውን በማውጣት ዋናውን ሚና ተጫውቷል፡፡ ወደ ደርግ የተጠጉትን ባንዳ/ከሃዲ ማለቱ፣ አፋኙን ደርግ ፋሽስት ብሎ ከመፈረጅም በላይ ከፋሽስት ንቃት ጀርባ የ“ባንዳዎች”ን አስጠቂነት በማሰብ በግድያ ወደ መቅጣት ማምራቱም የዚሁ ምስክሮች ናቸው፡፡

አንዳርጋቸው ጽጌ ‹‹ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር›› በሚል ርዕስ በቅርብ ያወጣው ቀጥተኛ ገጠመኙን የተመረኮዘ ትረካም ይህንኑ ይበልጥ ያረጋገጠ ነው፡፡ ኢሕአፓዎች እነ መኢሶንን በጨካኝነትና በመሰሪነት የሚበልጡ ሆኖ እንደተሰማው ደፍሮ ነግሮናል፡፡ አንዳርጋቸው በጭንቁ ሰዓት “ባንዳዎች” ዘንድ ተደብቆ እንኳ እነዚያን ባለውለታዎቹን በተመለከተ መመታት ነበረባቸው የሚል ስሜት በጊዜው እንደነበረው ሳይሸሸግ ገልጾልናል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳርጋቸው በስሜትና በድርጅታዊ አምልኮ የተጨፈነም ወጣት አልነበረም፡፡ “በኢንተር ዞን” የኢሕአፓ አመራር አካባቢ በግንዛቤም፣ በስሜትም፣ በዲሲፕሊንም ያልበሰሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጭምር እንደነበሩበትና በዚህም ምክንያት የተነሳ ይግፈለፈሉ የነበሩ የጀብደኛ ሥራዎች ትዝብቱን አጋርቶናል፡፡ የከተማ ትጥቅ ትግል ጠንቀኝነት አዕምሮውን እያጉላለው፣ መሪዎችን የማጓጓዝ ሥራው በፈጠረለት አጋጣሚ ለመሪዎች ከአንዴም ሁለቴ ጥያቄ ወርውሯል፡፡ እሱን ያጉላላውና በተግባርም ብዙ ወጣቶችን በአፀፋ ሲያስመታ የነበረው ሥልት ስህተተኝነት ግን ሥልቱን ላጠበቁት መሪዎች አልታያቸውም ነበር፡፡ እንኳን “ባንዳዎች” ከ”ባንዳዎች” ጋር አብረው የሚታዩ በ‹ሰይብል ባንከረባብት› ዘይቤ የሚመቱበት ሁሉ ሁኔታ ነበር፡፡ የራሱ የኢሕአፓ ሰዎችም በ“ስህተት” ተመትተዋል፡፡ አንዳርጋቸውም ለዚህ ዓይነት አደጋ የተጋለጠበት ጊዜ ነበር፡፡ የጓድ ”ሀ” ና “ለ” (የብርሃነ መስቀል ረዳና የጌታቸው ማሩ) የእርምት አቋም መበላላትን የሚያስተነፍስና ብዙ ውድ የኢትዮጵያ ልጆችን የሚያተርፍ ሆኖ ሳለ፣ አቋማቸው ከፋሽስቶች ጋር የመወገን የክህደት አቋም ተደርጎ ቅስቀሳ የተደረገበት መሆኑ፣ እየገደሉ ማስጨፍጨፍ የፖለቲካ ባለሙያነት ሆኖ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ መቀጠሉ ዛሬም ሲወሳ ያንገበግባል፡፡ የ1969 ዓ.ም. የላብአደር ቀን መንግሥታዊ አካባባር ለማስሳጣትና ኢሕአፓ ወዛደሩን እየመራ ነው የሚያሰኝ ግብዝነትን በሚያረካ መልክ ለማክበር ዝግጅት ይደረግ በነበረበት ወቅት፣ በመንግሥት ወገን በኩል የጨከነ የድምሰሳ ዝግጅት ስለመደረጉ (አንዳርጋቸው የዓይን ምስክር በነበረበት አኳኋን) ለግርማቸው ለማ መረጃ ደርሶት ነበር፡፡ መረጃው ታፍኖ ቀርቶም ይሁን ሰሚ አጥቶ የማይረሳው ጭፍጨፋና የገፍ እስራት ተካሄደ፡፡ ኢሕአፓ በየመንገዱ በጥይት እየቀነደበና እያስረፈረፈ ከሞተ ወዲያ፣ ተራ በተራ የተከተለው መቀርጠፍም እሰይ የሚያሰኝ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውድ ልጀቿን የማጣቷ ሌላ ፈርጅ ነበር፡፡ የሚያስቆጭ፣ የሚያሳዝን፡፡

በእነዚያ ከ1968 እስከ 1971 ዓ.ም. በነበሩ ዓመታት በየትኛውም ቡድንና የመዋቅር ደረጃ ከነበርነው ወጣት “አብዮተኞች” በዚህ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ክስረት ፊት ስንቆም፣ ከምንኮራበት የምናፍርበት ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ጥፋታችን አመዝኖ ይሰማኛል፡፡ ወዲህና ወዲያ ከምንገፋው ስህተትና ጥፋት ይልቅ፣ የምንጋራው የሚያይል ይመስለኛል፡፡ እኛ እየተበላላንና ራሳችንን እያስበላን ውድ ሕይወታችንንና ቆራጥነታችንን ትቢያ ስንቀላቅል፣ ወላጆቻችን በተለይም እናቶቻችን እኛን ለማትረፍ ወደ ወጣንበት ማህፀን መመለስ ቀረሽ አቃስተዋል፣ ተንከውክወዋል፡፡ ልጄ አናርኪስት ሆኖ እንዳይሞት ይታሰርልኝ ብላ ሹም ደጅ ጠንታ አሳስራ ያተረፈች እናት አውቃለሁ፡፡ የስንት እናቶች ያልተነገረ ታሪክ እየተቆፈረ ቢወጣ በአርቆ አስተዋይነት የዚያን ጊዜ ታጋዮችን እናቶቻችን እንደሚያጣጥፉን፣ እንደሚያስከነዱን ይታይ ነበር፡፡

በእኔ ዓይን በጥሬዬ ቆርጥሙኝ የማይል መጽሐፍ መጻፍ ገና አሁን ጀመረ የምለው አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ስለእናቱ ስለአልታየ ተሰማ በሰፊው ስላወሳን እግዜር ይስጠው! አልታየ የአንዳርጋቸው እናት ብቻ ሳይሆኑ፣ የዚያን ጊዜዋ ኢትዮጵያም መፅናኛና መኩሪያ ናቸው፡፡ ያኔ ከነበሩ ቡድኖች ሁሉ የላቁና የሁላችንንም ኪሳራነት፣ ጠባብነትና እየተኳረፉ መመራረዝ በተግባራቸው ያጋለጡና ያሳፈሩ ተምሳሌታዊ “ፓርቲ” ናቸው፡፡ አልታየ ምንም ችግር የማይበግራቸው፣ ተስፋ የማይቆርጡ፣ ልጆቻቸውን በትክክል እንዳሉት እንደ ድመት በአፋቸው አንጠልጥለው ያሳደጉ፣ ባለቻቸው አቅም ከሐረርጌ ድረስ ሳይቀር አምጥተው ያሳደጉ፣ ለማንም የቤትና የቅንነት ማጀታቸውን የማይሰስቱ (ለተቸገሩ፣ ምክር ለሚሹ፣ ለተደፈሩ፣ ለፀነሱ፣ ወዘተ መፍትሔ ሰጪነታቸውን በተግባር ያስመስከሩ)፣ ከጎረቤትና ከመሥሪያ ቤት ባልደረቦቻቸው ጋር፣ ከባለቤታቸው ዘመዶች ጋር፣ ከተማሪዎቻቸውና አስቤዛ ከሚገዙባቸው ደንበኞቻቸው ጋር ሁሉ ዕድሜ ያለው ባልንጀራዊ ግንኙነት መፍጠር የሚችሉ፣ በዚሁ ሰው አፍቃሪና ተፈቃሪነታቸው ምክንያት ከሐረርጌ እስከ ኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ እስከ ውጭ አገር ድረስ የሰው መረብ ማበጀት የቻሉ፣ በዚህም የሰው ትስስራቸው ውስጥ እኛ ባንዳና አናርኪስት እየተባባልን የተጠማመድነው ሁሉ ከቤተሰብ እስከ ውላጅ ድረስ ብንወድም ባንወድም ማቆጣጠር የቻሉ ነበሩ፡፡ ከዚህ በላይ “ፓርቲ” ግንባታ ምን አለ?!! ለአፍላዎች የፖለቲካ መጠማመድ ያልተሸነፈ የመዛመድ መረባቸው የእነ አንዳርጋቸውን አመለካከት በመረረ ጥላቻ እንዳይታወር ታግሏል፡፡ ከሞት መንጋጋ ለማትረፍም አገልግሏል፡፡ ውለታቸው፣ ልፋታቸው፣ ርህራሔያቸው፣ እንባቸው መላ የኢትዮጵያ ሕዝብን የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡ ሕዝብ ባንዳና አናርኪስት ብሎ ዕድር አልለየም፣ ድንኳን አልለየም፣ ባንዳና አናርኪስት ብሎ ለእንባና ለቅሶው ጎራ አልፈጠረም፡፡

ለ) በ1960ዎችና ዛሬ ባለንበት ጊዜ መሀል ወደ 50 የተጠጋ የዓመታት ርቀት አለ፡፡ ያኔ የነበርነውን ወጣቶች አብዛኛው ዕድሜ በ18 እና በ25 ዓመት ውስጥ ብንገምት፣ ከዚያ ትውልድ የተረፍነው የ70 ዓመት ዕድሜን ተጠግተናል ወይም ጀማምረነዋል፡፡ ዕድሜ ካገኘነው መሀልም ብዙዎቻችን ወልዶ ማሳደግንና ለልጅ መጨነቅን የቀመስነው ይመስለኛል፡፡ ያለፈውን የእኛን ዘመን ትውልድ ብርታትና ስብራት በሆዳችን ይዘን በአገር ውስጥና በውጭ በተለያየ ሙያ ተሰማርተን ቆይተናል፡፡ በጡረታም የተገለልን አለን፡፡ የዛሬ ፖለቲካ ውስጥ በቀጥታ ባይገቡም የእኛ የጀብደኝነትና የመጠማመድ ጥፋቶች እንዳይደገሙ ከእኛ ተማሩ ያሉ ከመሀላችንም አልታጡም፡፡ የሚያሳዝነው ግን ከዚያ ትውልድ በደም የጨቀየ የፖለቲካ ልምድ በቅጡ ሳይማሩ፣ ዕድሜም ሳይበግራቸው፣ የትናንትናውን የእኛን የተባበረ ትግል ድህነት፣ የመጠማመድ ፖለቲካ ቅርሳችንን፣ ለወጥ ባለ (በብሔርተኛ ፖለቲካ) መልክ ለአዲስ በቀሉ ትውልድ ያወረሱ፣ ዕይታውን/አስተሳሰቡንና ኑሮውን አጣቦ የመከታተፉን ምህንድስና ያካሄዱት የእኛው ትውልድ ሰዎች መሆናቸው ነው፡፡ ከብሔርተኛ ፖለቲካ በብሔረሰባዊ ማንነት መኩራትን ብናተርፍም፣ ከአምባገነንት ጋር ብሔርተኛ ገዥነት ተሻርኮ ያደረሰብን የክፍልፋይነትና የመሸካከር ክስረት ይበልጣል፡፡ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ፈላጭ ቆራጭነት ከነገሠበት ጊዜ አንስቶ በተለይ በአዲስ መጡ ትውልድ ላይ የደረሰው የሰብዕና እልቀት ከዚህ እስከዚህ የሚባል አይደለም፡፡ ለአጨብጭቢነት በመዳረግ፣ በፕሮፓጋንዳ ቀለብተኝነት በመቀጥቀጥ፣ በአገር ጉዳይ ከመወያየት በማራቅ፣ የጠያቂ አስተሳሰብ ልምምድን ነፍጎ በአፋኝ ዝምታ በማድቀቅ፣ እንዲሁም በሀሳዊና ግልብ ትምህርት፣ በኩረጃና ነጥብ እየጨመሩ ክፍል እንዲቆጥር በማድረግም ሆነ ለሐሰተኛ የትምህርት ምስክር ወረቀት ሸቃጭነት በማጋለጥ፣ ወዘተ ድምር ውጤት የደረሰው የእነፃ ስንኩልነት (ዲፎርሜሽን) ከባድ ነው፡፡ የክፍልፋይ ብሔርተኛነት የአዕምሮ አጠባው የተካሄደው ይህንን ሁሉ ጉዳት ሀብቱ አድርጎ ነው፡፡

በውስን ቁሳዊ ልማትና “ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት” በሚሉ ወገኝነት በተቀሸረ መከፋፈል 27 ዓመታት ያህል ከተደቆስን በኋላ፣ እስከ ዛሬ ለብዙ ጊዜ የታጣውን የዴሞክራሲ ነፃነት ከአገራዊ አንድነትና ከቀጣናዊ የትብብር ትልም ጋር አዛምደን ለመጨበጥ ስንነሳ፣ የክፍልፋይ ፍላጎቶች ንቁሪያዎችና ግጭቶች እጅጉን ሊያብጡን የቻሉትም አጠማምዶ የመግዛትና የመዝረፍ ርዝራዦች አሳቢ መሰለው የተለያዩ መርዝ እየረጩና የማፋጀት ሻጥር እየሠሩ የለውጥ ዕርምጃችንን ሊያንገላቱ የቻሉት፣ የገዥነት አጀንዳቸው ያከተመ ሲመስላቸውም በመበታተን አጀንዳ ሊያምሱን የደፈሩት፣ ይህንንም መሰሪነት ማክሸፍ ቀላል የማይሆነው በጊዜያት ውስጥ የደረሰብን የግለኝነት፣ የሰፊና የሩቅ ዕይታ ድህነት፣ የተጠራጣሪነትና የክፍልፋይነት ጉዳት ከባድ ስለሆነ ነው፡፡

ስለለውጥ ተብሎ የተካሄደው የእኛ የ1960ዎች ትውልድ ትግል በሥልጣን እሽቅድምድምና በእልህ አቅጣጫ ስቶ መበላላት ውስጥ ሲወድቅ ከማንም በላይ በጭካኔያችንና በበቀላችን የረገፍነው እኛው የዚያን ዘመን ወጣቶች ነበርን፡፡ ወላጆቻችን ላይ ያደረስነው ጉዳት ደግሞ በእኛ ዳፋ እነሱም ለእስር ቤት ግርፋትና አብዮታዊ ዕርምጃ መዳረግ፣ እኛን ባጣ የሐዘን ስብራት የዕድሜያቸው መሸሽ፣ በታፈነ እህህታ ጨርቅን መጣል፣ የልጅ ዓለምንና ጧሪነት ዓይቶ የማለፍ ተስፋ በነኮተበት ኑሮ መቆራመድ ነበር፡፡ በዛሬው ትግልና ውመናን መለየት በተሳነው የወጣቶች ጭካኔና በቀል ራሳቸው ወጣቶች እርስ በርስ መቀረጣጠፋቸው ባይቀርም፣ ዋናዎቹ የጀብደኛ ቅጣት ማረፊያ ሆነው የቆዩት (በግድያ በእሳትና በዘረፋ ንብረትን አጥቶ በመፈናቀልና በገዛ አገር ስደተኛ በመሆን ስቃይ ያዩት) ወላጆች፣ አዛውንትና ሕፃናት ናቸው፡፡ እጅግ አስከፊው የጥቃት ማመካኛ ደግሞ፣ አንዳችም የፍትሕና ለሕዝብ የመቆርቆር ይዘት የሌለበት፣ ሰዎችን ነባርና መጤ ከሚሉ አንጓላይነት የሚነሳ መሆኑ!! አሁን በቅርቡ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. አካባቢ የሲዳማ ክልል የመሆን ሪፈራንደም በሴራ ተጓጉሏል ለሚል ብስጭት እልህ መወጫ ጥቃት የተካሄደው፣ መጤ በተባሉና ክልል የመሆን ጥያቄን አይደግፉም ተብለው በታሰቡ ሰዎች ላይ ነበር፡፡ ሰው ሲናደድ እልሁን በገዛ ዕቃው ላይ ቢወጣ አያስገርምም፡፡ ዛሬ ግን ሰዎችና ኑሯቸው እልህ መወጫ ሲሆኑ ማየት ከጀመርን ሰንብተናል፡፡

የድቀታችንም ርዝማኔና ስፋት የርህራሔና የመተሳሰብ ድርና ማጎቻችንን እስከ ማንተብ፣ ለአጋጣሚ ጥቅመኝነትና ለታወረ ራስ ወዳድነት ባሪያ እስከ መሆን ድረስ የበረታ ነው፡፡ የኖርንበት ከፋፋይ የአፈና ሥርዓት በራሱ የሚያመነጫቸው ችግሮች ከድቀታችን ጋር ይመጋገባሉ፡፡ እነዚህን ተመጋጋቢ ችግሮች ደግሞ የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎቶች እያማሰሉ መጠቀሚያ ያደርጓቸዋል፡፡ የለውጡን ጅምር ለማጨናገፍም ይሁን ለሌላ ዓላማ፣ በሰዎችና በኑሯቸው ላይ ጥቃት የመፈጸም ርህራሔ ቢስነትን እንደ ታክቲክ ወይም ብስጭትን እንደ መወጫ አድርጎ መጠቀም እጅግ የከፋ ውድቀት ነው፡፡ በዚህ የውድቀት “ዘዴ” ውስጥ ለብሔሬ ጥቅም እሞታለሁ ባዩም፣ ጥያቄ አለኝ ባዩም፣ የደቦ ፍርድ ሰጪውም፣ ቀልባሹ ሁሉ ሲንሸራሸር ቆይቷል፡፡ መቶ አሥራ (ምናምን) አልፏል ከሚባለው የፓርቲዎች ብዛት ውስጥ ይህን መሰሉ (ቤት ለኩሶ ውስጡ ከመቀመጥ የማይሻል) ጥፋት መመላለሱ አስደንግጦት ሁኔታውን ለመቀየር የሚጥር የተባበረ እንቅስቃሴ ማነሳሳት ይቅርና፣ በአንዳርጋቸው ጽጌ መጽሐፍ የተዋወቅናቸውን የአልታዬ ተሰማን ያህል አሳቢነትን፣ ፍቅርንና ቅንነትን ይዞ የሚንከወከው እንኳ አልታየም፡፡

በሽርፍራፊ ዓላማ መወሰን፣ የትንንሽ ድርጅታዊ ሥልጣን ምርኮኛ መሆን፣ ኪዩስክ ከፍቶ ገዥ እንደ መጠበቅ አድርጎ የፖለቲካ ሥራን ማሰብ፣ የቡድንነትንና የፓርቲነትን ልዩነት አለማወቅ፣ በፖለቲካ ድህነት ተሞልቶ ፓርቲ ለመሆን መከጀል በእኛ አገር ኃፍረት የሚነካካ ነገር አይደለም፡፡ የሚደንቀው ደግሞ የ“ፓርቲነት” ወጉን ከሚከጅሉት ይልቅ፣ የፖለቲካ አየሩን እዚህም እዚያም በማራገብ የሚበልጡት ግለሰብ ቦትላኪዎች መሆናቸው ነው!

 አገሪቱን እያስተዳደረ ነው በሚባለው ኢሕአዴግ ውስጥ የሚታየው መፈናገጥ ራሱ አጀብ የሚያሰኝ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ምክር ቤትም በሥራ አስፈጻሚም ተሰብሰቦ ውሳኔ አብሮ ወሰነ የሚባልለት ሕወሓት፣ በሌላ ፈርጁ የፌዴራል መንግሥቱን አካሄድ የሚቃረንና የሚተናነቅ በሚገዛት ትግራይ ውስጥ ካለኔ ማናለብኝ ባይ ነው፡፡ አማራ ክልልን ከሚገዛው አዴፓ ጋር ጋር ያለው ፍጥጫ የአገሪቱ ቁርጠትና የቀውስ መፍለቂያ ሆኖ መቆየቱ በሕፃናት አዕምሮ ሳይቀር ልብ ተብሏል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ “ንቁ ታጋይ አታጋይ” የሚባሉ ግለሰቦችን፣ እዚያም እዚያም የሚፎልሉ የደቦ ጀብደኞችን፣ ለማገናዘብ ለማጣራት ጊዜ የሌላቸውን የአሉባልታ ቡትለካ ሱሰኞችን ሁሉ አንድ ላይ ከወሰድን፣ በኢትዮጵያ ያሉት “ፓርቲዎች” መቶ ምናምን ሳይሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲን አሳክተውና ሰላምን ተጎናፅፈው በኢኮኖሚ ግስጋሴ ውስጥ የመጓዛቸውን ዕድል እጅግ ከባድ ፈተና ያደረገውም ይህ ሁሉ ገመና ተደማምሮ ነው፡፡

ወከባና ግዝገዛ

ሐ) ሳይበታተኑ በግስጋሴ የመቀጠል ዕድላችን ከዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ግንባታ ጋር የተያያዘ መሆኑ የሰላምታ ያህል ነጋ ጠባ ይነገራል፡፡ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታም ተልዕኳችንን የማቃናት ተግባር፣ ያለውን መንግሥት የለውጥ ጥረት አቅፎ ሲያንቀላፋ እየቀሰቀሱ፣ መንገድ  ሲስት እየመለሱና ጉድለቱን እየሞሉ ወደፊት ከማስኬድ ርብርብ የተሻለ አማራጭ የሌለን መሆኑም ጆሮ ያሰለቸ ጉዳይ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ የለውጡ ጅምር ብዙ የሚያወለካክፉ፣ ዕይታን የሚያጥበረብሩና ሐሞትን የሚፈታተኑ ወከባና ጉንተላዎች የተደራረቡበት ነው፡፡ የእንግልታችን ድርብርብነት ያልታወቀው ይኖራልና አብረን እንዳስሰው፡፡

የዚህ ለውጥ መጨናገፍም ሆነ መሳካት ከማንም በላይ የወጣቱን መፃኢ ዕድል የሚመለከት ነው፡፡ ቢከሽፍና በአገሪቱ ውስጥ የመጨፋጨፍ እሳት ቢቀጣጠል በዋናነት የእሳት ራት የሚሆነውና ከአገር ማጣት ጋር ጨለማ የሚገባው ወጣቱ ነው፡፡ ቢሳካ ደግሞ ኢትዮጵያን በማደስ ውስጥ የድቀት ገጾቹን አራግፎ የበለፀገ ሰብዕና፣ አዲስ ባህልና አዲስ ሕይወት ውስጥ የመግባት ዋና ባለቤቱ እሱ ነው፡፡ ይህንን ያህል ዕጣውን የሚወስን የለውጥ እንቅስቃሴ ተጀምሮ በመቀልበስና ባለመቀልበስ ትንንቅ ውስጥ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ለውጠኛ ወጣቶች በየዩኒቪርሲቲዎችና በየክልሎች በሥራና በመኖሪያ አካባቢዎች ውስጥ የመከፋፋልና የመፈራራት ካቴናቸውን እየበጣጠሱ በትንንሽ የውይይት ህዋሶች፣ በትልልቅ ስብሰባዎች ራሳቸውን እያነፁ ለውጡን ወደፊት የሚያራምዱና በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚያዛምቱ፣ የነፃ እንቅስቃሴ/የነፃ ማኅበር ፈር ቀዳጆች መሆን ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ፈንታ የተሻለ የመናገርና የመደራጀት ዕድል በተከፈተበት በአሁኑ ሁኔታ፣ አብዛኛው ወጣት በተለይ ምሳሌ መሆን የሚገባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች በኖሩበት የመፈራራት፣ የመሸካከርና በየአስባቡ እየተጫረ ብሔረሰባዊ ረድፍ በሚሠራ የፀብ እስረኝነት ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡

ወጣት አቀፍ ትግል ተከሰተ ቢባል፣ የታየው የዕውቀትና የሙያ ጎስቋሎች ያደረጋቸውን የነካ ነካ ትምህርት፣ ኩረጃን፣ የውሸት ነጥብ አሳጣጥንና የመሳሰሉትን ብልሽቶችን በመቃወም ወይም የየትኛውንም አካባቢ ግጭት አመጣሽ ውድመትንና መፈናቀልን በመፃረር ረገድ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ያየነው አገሪቱ ሕግና ሥርዓትን ማስፈን እንደ ዳገት በከበዳትና ኢኮኖሚዋ በመጨራመት አደጋ ውስጥ በነበረበት የአጣብቂኝ ሰዓት፣ በአያሌው የደመወዝ ጭማሪ ላይ ያተኮረ ጥያቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰጠው የሕክምና ባለሙያዎች ደመወዝ ከእነ ኬንያ ጋር እየተነፃፀረና ቤት/መኪና ቶሎ ለመግዛት የማያወላዳ መሆኑ በወጣት የትግሉ ተወካዮች ሲተችም በቴሌቪዥን ታዝበናል፡፡ በዚያ ቀውስ በተበራከተበት ወቅት መንግሥት ለጥያቄውና ለአድማው ባይሸነፍ ኖሮ፣ የበለጠ ሊከተል የሚችለው ነገር አጠቃላይ የኅብረተሰብ ኪሳራ ሊሆን በቻለ ነበር፡፡

ከደመወዝ ጋር ተዳብለው የመጡት የሕክምና ባለሟያዎችን ደኅንነት የተመለከቱና የተስተካከለ አገልግሎት ለሕዝብ ለመስጠት የማያስችሉ ጉድለቶችና አሠራሮች እንዲወገዱ ትግል መደረጉ አከራካሪ አደለም፡፡ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትግል ታሪክ ውስጥ በአፍላ የለውጥ ትግል ጊዜ የደመወዝ ጥያቄን ማንሳት ግን አዲስ ሪኮርድ ነው፡፡ ከኅብረተሰባችን በስተግርጌ በውዳቂ ገቢና በኑሮ ውድነት ተስንጎ ያለውን ብዙኃን አለኁ አትበል በሚል ምፀት የሚቀረደድ ነው፡፡ ዛሬ በአማቃቂ (ከፊል) ረሃብ ውስጥ ከመኖር በማይሻል ኑሮ ውስጥ ያለ ብዙ ሰው በምሬትና በቁጣ ቱግ ብሎ አደባባይ ከመውጣት የተቆጠበውም ቅድሚያ መቀመጫ አገሩን ከትርምስ ማትረፍ በልጦበት ይመስለኛል፡፡

በተጓደለ ሥልጠና ውስጥ ማለፍ የተጓደለ “ሙያተኛነት” ላይ ነው የሚያደርሰው፡፡ የተጓደለ ብቃት ሕክምናን በመሰሉ ከሰው ልጅ ጋር በቀጥታ በሚገናኙ አገልግሎቶች ውስጥ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ደግሞ እንደ ማንኛውም ጉዳት የሚታይ አይደለም፡፡ ለሕዝብ ከሚቆረቆር ለውጠኛነት አኳያ፣ በሥልጠናውም በኩል ሆነ በአገልግሎቱ ውስጥ ያሉ የመሣሪያና የግብዓትም ሆነ የሥነ ምግባር ጉድሎቶችን  በተመለከተ፣ ትግል መቀጣጠል የነበረበት ገና በፊት ከደመወዝ ቀድሞ ነበር፡፡ ትግል ሲባልም ለመንግሥት ጥያቄ ከማቅረብ ባሻገር በራስ አቅም ተቋማዊ አገልግሎትን የቀለጠፈና ፍትሐዊ ለማድረግ የሚያስችሉ (የበጀት መድፋፋትንና የግብዓት ብክነትን የሚቀንሱ፣ የብቃትና የሥነ ምግባር ማነስን የሚጠግኑ መፍትሔዎች በመሻት ረገድ ሁሉ) ፈጠራዊ አስተዋጽኦዎችን ማድረግ ነው፡፡ አሁንም ለውጠኛ እንቅስቃሴ ካለ በዚህ ዓይነቱ መሻሻል መንግሥትንም አትግቶ ሕዝብ ላይ ዕርካታ በመፍጠር ያላንዳች ስሞታ በሕክምና ባለሟያዎች ላይ የተባዛውን አሉታዊ ስሜት በሕዝብ አክብሮትና ፍቅር መተካት ከባድ አይሆንም፡፡

የወጣት “ለውጠኝነት” መንገድ የሳተበትና ለቅብጥብጥ የሥልጣን ጥቅመኞች መሣሪያ የሆነበት ሌላው ጉዳይ ክልል ልሁን ባይነት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ብዙኃናዊ ፍላጎት የሚረጋገጥበት እንጂ፣ የጥቂቶች ሴራ የሕዝብ ፍላጎት ነው ተብሎ የሚጫንበት አይደለም፡፡ ክልል መሆን መብት ነው የሚለው ሕገ መንግሥትም አልተነካም፡፡ የፌዴራል አወቃቀራችን ምን ቢጠና በትልልቅ ግቢዎች ውስጥ የተካተቱ በርካታ የራስ በራስ አስተዳደሮችን፣ ወይም በርካታዎቹ አስተዳደሮች የፌዴሬሽናችን አካላት የሚሆኑበትን ሐሳብ ለውይይት ከማቅረብ አያመልጥም፡፡ ጥናቱ የትኛውንም መልክ ይዞ ቢመጣ፣ ሳያናጭ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲፈይድ ምሑራንና ሕዝብ በደንብና በእርጋታ እየተወያዩበት መፈተጉና ሰፊ ስምምትን መጠየቁ አይቀርም፡፡

የዴሞክራሲ ለውጥ እየሰመረ መሄድ፣ የራስ በራስ አስተዳደርንም ፍትሐዊነትንም የበለጠ የሚያቀርብ ብሩህ ዕድል ሆኖ ሳለ፣ ለውጡ በሚውተረተርበት በዚህ ጊዜ ክልል ካልሆንን በሚል ጥድፊያና ግርግር ማዋከብ ለውጡን ለስብራት ማጋለጥ ነው፡፡ በቅልበሳ ፈተና፣ በፀጥታ መዝረክረክና በኢኮኖሚ መጎሳቆል ላለመሰልቀጥ ለውጡ ጉዞውን ማፍጠን አለበት፡፡ ብዙ ጣጣ ያለበት አዲስ ክልል የማዋቀር ሥራ ፍጥነትንም፣ ትኩረትንም፣ ጥሪትንም ይሻማል፡፡ በጠያቂዎች መቻኮል ውስጥ የሚታይ ንጭንጭና ሰዎችንና ንብረቶች እስከ ማጥቃት የሚሄድ ቁጣ ቀልባሾች የሚሹትን የቀውስ ድግስ ያፈልቃል፡፡ ውሳኔ ሕዝብ በጊዜ አልተካሄደም ብሎ ክልልነትን ለማወጅ መቃጣት መብትን ማረጋገጥ ሳይሆን ሥርዓተ አልባነትን ማነሳሳት ነው፡፡ ምክንያቱም ውሳኔ ሕዝብ ተካሂዶ መቶ በመቶ አዲስ ክልል ልሁን የሚል ድምፅ ቢገኝ እንኳ፣ አዲስ ክልልነቱ አቶማቲክ ዕውቅና የሚያገኘው ክልሉ ለአዲስ ጎጆ ወጪው ክልል ሥልጣን ሲያስረክብ እንደሆነ ነው ሕገ መንግሥቱ የሚናገረው፡፡ ሥልጣን እስከ ማስረከብ ድረስ ደግሞ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ያውም ዝርዝር ሕግ የሌላቸው፡፡ እናም አሁን ያለው ክልል ለመሆን መቁነጥነጥ የክልልነት ውጤት ላይ ወዲያውኑ የሚያደርስ አይደለም፡፡

ምንም ተባለ ምን፣ ምንም ይፈጠር ምን የያዝኳትን ክልል የመሆን የየብቻ ሩጫን አልለቅም፣ መታገስም አልችልም ከተባለ፣ ዴሞክራሲን የማስተማመኑ ተግባር ተቀዳሚ መሆኑን መሳት ነው፡፡ አገር አቀፍ ለውጡ ተጓጉሎ ለሁላችንም በነፃነት የመኖር ዋስትና የሚሆነው ዴሞክራሲ ከራቀን በኋላ፣ ክልል መሆን የሚሻ ሁሉ ተፈቅዶለታል ቢባል፣ የነፃነት ፀሐይ የየክልል ሰማይ ፈጥሮ በየተናጠል አያበራም፡፡ ጨለማው ለሁላችንም መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ጉዳያችን በፍትሐዊነት በእኩልነትና በዴሞክራሲ ውስጥ መኖር ከሆነ ተረባርቦ ይህንን ለወጥ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ከማድረስ የሚቀድም ተግባር የለም፡፡ እናም በሕዝብ መብትና ጥቅም ስም በሚደረግ መቅበጥበጥ ዙሪያ ያለውን ተውኔት ሁሉ በቅጡ መመርመራችን የሚቦዘንበት አይደለም፡፡ በቴሌቪዝን ላይ፣ “ዓላማችን ኅብረ ብሔራዊ ነው . . . የአካባቢያችን ሕዝብ አንዱን ይዞ አንዱ ጥሎ የሚሄድ ሳይሆን ሁሉን አቃፊ ነው. . .” ሲሉ የነበሩ “ንቁ” ግለሰቦች፣ ሰዎችን የለየ ግድያና የንብረት ውድመት ከመድረሱ በፊት አደጋ ለማስወገድ ምነው ሳይቻላቸው ቀረ? ያ ሁሉ ጥፋት ሲፈጸም የደቡብ ክልል ፖሊስ የት ነበር? በሰዎችና በንብረታቸው ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ “አዝነናል ሰርጎ ገቦች በውስጣችን ገብተው እንደሆነ እንጂ፣ የእኛ ሰው እንዲህ ያለ ሥራ የሚሠራ አይደለም፤” ብሎ ማለት. ራስን ከማታለል በቀር ምን ይፈይዳል? ይህ የጥያቄዎች አንድ መስመር ነው፡፡

ሕወሓቶች መቀሌ ላይ ኮንፈረንስ/ምክክር እያዘጋጁና በቴሌቪዥንም በኩል ያሁኑን ክልል የመሆን ሩጫ አይዞህ ባይ የሆኑት ምን ፈልገው ነው? ትናንትና እነሱ በገዥነቱ ቁንጮ ላይ በነበሩበት ጊዜ የሰቀዙትን መብት ዛሬ በሽግግር ምጥ ላይ ግፋ በለው ባይ የሆኑት ስለምን? ድጋፋቸው በታምር ከእውነተኛ የመብት ተቆርቋሪነት የፈለቀ ከሆነ፣ በሚገዙት ክልል ውስጥ ስለምን ቀጋ ሆኑ? ትግራይ ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦች ፍላጎታቸውን ያለ ፍርኃትና ያለ መሳደድ እንዲያንሸራሸሩ ለምን አላደረጉም? ዛሬ ድረስ ሕወሓቶች ያልወደዱትን አቋምና እንቅስቃሴ በተለያየ የአፈና ሥልት የሚያዳፉበት ሁኔታ ስለምን ደራ? ይህም የጥያቄ ሌላ ፈር ነው፡፡

ጥያቄው በዚህ አያበቃም፡፡ የዓብይን መንግሥት ስህተት እያሳዩ እንዲታረም ከመጣር ባሻገር ለውጥ የለም እያሉ ለማውገዝና ለማስወገዝ የሚደረግ መክለፍለፍ ያስተዛዝባል፡፡ ሕግና ሥርዓት ይከበር እየተባለ ሲወተውት እንዳልነበረ፣ ዕርምጃ ወደ መውሰድ ሲገባ፣ በመደበኛ ሁኔታና በቀውጢ ጊዜ መሀል ያለውን ልዩነት ግንዛቤ ውስጥ ሳይከቱ (ቀውስ አላኳሽ ብልጭታዎችንና ግርግሮችን የመቆጣጠር አጣዳፊነት፣ የጥርጣሬ ምልክቶችን ተመርኩዞ ከያዙ በኋላ እያንጓላሉ ከመፍታት ውጪ አጥፊን እያጣሩ ለማሰር ጊዜ እንደማይሰጥ የማገናዝብ አዕምሮን ዘግቶ) “ሳናጣራ አናስርም የተባለው የታለ? ከድሮው የተለየ አዲስ ነገር የለም . . . ትናንትናም ዛሬም ከሕግ ውጪ ይታሰራል፣ ዛሬም እንደ ትናንቱ የፖለቲካ እስር ይካሄዳል . . .” እያሉ አሁናችን በትናንትናችን ዓይን እንዲታይ መልፋት (ከጋዜጠኛም ይምጣ፣ ከ”ፓርቲዎች” አካባቢም ይምጣ፣ ልሂቅ ከሚባል ሰውም ይምጣ ወይም ከማኅበራዊ ሚዲያ ሱሰኛ) ለውጡን በዚህም በዚያ ወግሮና ድጋፍ አሳጥቶ ለመድፋት ከሚደረግ ርብርብ ጋር ከመግጠም በምንም አይተናነስም፡፡ ወገራው ሞቆና ክልል ካልሆንን ባይነት በአፈና ተተርጉሞ ድብልቅልቅ ያለ ቁጣ ቢከተል ብለው የሚጠባበቁ፣ ረመጥ እንዳይከስም ፍግ ነስነስ የሚያደርጉ የቅልበሳና የማፈንገጥ ሸንተረሮች በውስጣችን ስለመኖራቸው ለመሆኑ ልብ ተብሏል? ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያን ገላግሎ በማትረፍ ስም ብቅ የሚሉ. . . የርዕዮተ ዓለም መደበላለቅንና “የፀረ ሰላሞችን” መፈንጨት ድባቅ መትቶ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ”ን የሚያነግስ . . . አዳሜ እርስ በርሱ ሲራኮት ዘወር ለማለት የሚያደባ. . . ይህ ሁሉ የእኔ ሟርት ወይም የቅዠቴ ውጤት አይደለም፡፡

የዓብይን መንግሥት ከፋሽዝም ጋር ያዛመዱ ሰዎችን የያዘው “ባይቶና” የሚባል ቡድንና “ሳልሳዊ ወያነ” (ሁለቱም የኮንፌዴሬሽን ፍላጎት ላይ የሚገናኙ) ያለ ሐሳብ ትግራይ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን እንደ ቻለ ስናስብ፣ አንዱ አማራጭ ወይ እነዚህ ቡድኖች ሰፊ የወጣት ድጋፍ አግኝተው ሕወሓት እንዳያፍናቸውም ማዕበል ፈርቶ፣ ዝም ብሏቸው በታወቀና በደረቀ አቋሙ እንዳይቀጥልም በእነዚህ ፅንፍ በወጡ ቡድኖች ተበልጦ የመውደቅ ሥጋት ውስጥ ገብቶ፣ ከዚህ ለማምለጥ ከእነሱ ጋር እየተሻሸ መቆየትን ዘዴ ብሎታል የሚል መላምት ሊመጣብን ይችላል፡፡ ወይም ከዚህ አጣብቂኝ ባሻገር፣ ከዋና የኢትዮጵያ ገዥነት መንሸራተቱና ከአዴፓና ከአማራ ክልል ጋር ያለው ፍጥጫው ገፍተውት የእነ ‹ሳልሳዊ ወያኔ›ን አቋም (ቢያንስ በሽፍንፍን) ተቋድሷል፡፡ ወይስ የሕወሓት አሮጌና የኋለኛ ቁንጮዎች ከኢትዮጵያ የገዥነት ብርንዶ ከራቅን ምን ቀረን ከእንግዲህ ብለው፣ ከክልልነት ወደ አገርነት ለመሸጋገር የሚያስችል የፖለቲካ ጨዋታ በብዙ መልክ ለማካሄድ እነ ‹ሳልሳዊ ወያኔ›ን ወልደው ይሆን? እውነቱ ያለው የትኛው ምናልባት ጋር እንደሆነ ባይታወቅም፣ በገዥው ኢሕአዴግ ግንባር ውስጥ ሆነው፣ የጎጥ አገር የመሆን ያህል ማናለብኝ ባይ ባህርይ ማሳየታቸው ይከነክናል፡፡ ለእነ ‹ባይቶና› ቡድን ተመችቶ፣ በተቃራኒው ግን እነ አረና ትግራይየትግራይ  ዴሞክራሲያዊ ትብብር በትግራይ ውስጥ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ አለማስቻላቸው (በከሃዲነት እንዲዋከቡ መፍቀዳቸው) ስለምን ያሰኛል፡፡

ያም ሆነ ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ ዓብይ አህመድ የሚመራትን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጥያቄዎችና ግጭቶች እንዲዋከብ በሥውርና በሩቅ ጣቶች ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ለሕገ መንግሥታዊ የብሔረሰቦች መብት ታማኝና ደጋፊ በመሆን መልክ/ስም፣ ከተለያዩ የብሔርተኛ ቡድኖችና በኢሕአዴግ አባልነትም ሆነ በአጋርነት ካሉት ቡድኖች ውስጥ የሚቻለውን ያህል ደጋፊ ቦጭቆ ሸሪክ ለማበጀትም ይሞካክራል፡፡ እንዲህ ያለው ሙከራ ለየዋሆች የአንድ ሰሞን ወረት ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን በሥጋቶችና በግርግሮች እየነገዱ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ መቀላቀል የሌለባቸውን “የልማታዊ ዴሞክራሲ ወገኖች”ን የማሰባሰብ ሥውር ድር የማድራት ዕድል አለ፡፡ ድሩ በኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውስጥ በመሹለክለክ ብቻ ሳይወሰን፣ ከፌዴራልና ከክልል መንግሥት ጋር ፍትጊያ ያላቸውን እስከማባበል፣ ከፓርቲና ከሹሙት የተገለሉ ሀቀኛ “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ” በልቶ አብሊዎችን እስከ ማሰባሰብ ሊሄድ ይችላል፡፡ በዚህ አኳኋን የሚፈጠር ፍንካች፣ በቅርብ ርቀት ተልዕኮ የእነ ኦዴፓን ትልቅና ውህድ ፓርቲ የመፍጠር ጥረት የማጨናገፍ፣ የማሳሳትና በተቀናቃኝ የመመከት አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል፡፡ በዚህ የተጀመረ ስብስብን አሁንም መብትን ማዕዘኑ ባደረገ ውስወሳ የልል ፌዴራሊዚም (ኮንፌዴሬሽን) አቋም ተሸካሚና አባዢ አድርጎ መቃኘት ከባድ አይሆንም (የክልል ካርታ ሳይጎድል በጦርነት መጨፋጨፍ ውስጥ “ሳይገቡ” [??] አገርነትን ለመቀዳጀት መላ ኢትዮጵያን በስምምነት በጎጦች ኮንፌደራላዊነት ቆራርጦ የመካፈል ምህንድስና አነሳስና ጉዞው ይህንን መሳይ ንድፍ አይኖረውም አይባልም)፡፡

በዚህ ረገድ በአሁኑ ጊዜ ያዋጣኛል ተብሎ የተያዘው አንዱ ዘዴ የዓብይን መንግሥትና የ‹ኦዴፓ› እና የ‹አዴፓ›ን ዝምድና የርዕዮተ ዓለም መሳከር የደረሰበት “ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት”ን ከትምክህት ጋር ያደበላለቀ አድርጎ ማራገብ ነው፡፡ የሰኔ 15 የእነ ጀኔራል ሰዓረ መኮንንና የእነ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ግድያ በትምክህተኞች (ነፍጠኞች) ሴራ መተርጎሙ አንድ ምሳሌ ነው፡፡ ዋል አደር ብሎ የሕወሓት መሪዎች ባወጡት መግለጫ፣ አዴፓ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አፈንግጦ (ከትምክህተኞች በመደበላለቁ) ነውና እንዲያ ያለ ጥቃት የመጣው፣ ይቅርታ ካልጠየቀና ካልፀዳ አብሮ ለመቀጠል ያስቸግራል የሚል መንፈስ ያለው ግንዛቤ መለቀቁም በዚሁ ታክቲክ ፈርጀ ብዙ ውጤትን ለማግኘት ታልሞ ነበር፡፡ ከሁሉ በፊት ከአዴፓ ጋር የተያያዘው የሰኔ 15 የግድያ ጣጣ በኢሕአዴግ አባል አጋር ድርጅቶች ውስጥ በፈጠረው ድንጋጤ ላይ፣ የትምክተኞች ጦሰኝነት ሲታከልበት በድርጅቶቹ ግንባርነትም ውስጥም ሆነ በየድርጅቶቹ የአባላት ጥንቅር ውስጥ ጥርጣሬ ይጭራል፡፡ የጥርጣሬ ስርሰራ ደግሞ መከፋፈልና መፍረክረክን ያመጣል፡፡ ይህ ውጤት ደግሞ ወደ አዴፓና ኦዴፓ “ሽርክና” ክሽፈትና ትልቅ አገራዊ ፓርቲ የመገንባት ዕቅዳቸው መተጓጎል ይወስደናል፡፡ ይህ ሆነ ማለት የዓብይ መንግሥት ራቁቱን ቀረ ማለት ነው፡፡

የስርሰራው መሳካትና አለመሳካት ከአዴፓና ከኦዴፓ የነገሮች አያያዝ ጋር በጣሙን ይገናኛል፡፡ ለምሳሌ አዴፓ ከሕወሓት መሪዎች ለተወረወረበት መግለጫ ድንፋታና አፍ እላፊ ውስጥ የገባ ምላሽ ከሰጠና ፀበኝነት ካከረረ እሰየው፣ የትምክህተኛነት ጥርጣሬ ሕይወት ሳያጣ ይቆያል፡፡ ይኸዋ የትምክህትና የጥላቻ ኃይሎች እንዲህ ብለው ዘለፉህ/ሊበሉህ እያቅራሩ ነው እያሉ የትግራይን ሕዝብ በጎጠኛ ጎሬ ውስጥ የማጠናቀቅ ፍላጎትም የአስቤዛ ችግር አይገጥመውም፡፡ አዴፓ ከይቅርታ ጥያቄ ጋር የርዕዮተ ዓለም ጥራቴን ከእንግዲህ . . . የሚል ምላሽ ሰጥቶ ቢሆን ኖሮም ለመሰሪዎች ሌላ ፌሽታ፣ ለአዴፓ እርስ በርሱ ተከፋፍሎና በአማራ ክልል ሕዝብ ተተፍቶ የመውደቅ ቁልቁለት ይሆን ነበር፡፡ አዴፓ ሲወድቅ የሚተካው በእነ ቴዎድሮስና በእነ ምኒሊክ ቆሌ የሚሰግርና ጎራዴ የሚስል ከሆነም ድርብ ዕልልታ ነው፡፡ የትምክህተኛነት ክስ ገበያ ይደራለታል፡፡ አዴፓና ዓብይም በመለዘብና ባለመለዘብ (በብሔረተኛ ጉድጓድ ውስጥ በመግባትና ባለመግባት) አጣብቂኝ መለዝለዛቸው ይበረታል፡፡ ልብ በሉ! ይህንን መሳዩን መከፋፈልና የለውጥን መጨንገፍ የሚናፍቁ ወገኖች በአማራ ክልል ጦርነት አቅራሪ ቡድን ሥልጣን ላይ መውጣቱን (ለሚሹት ውጤት ሲሉ) እንደሚወዱት ከገባን፣ የእነ ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ ፍላጎት የአዴፓን አመራር ሳይቆጣጠር መክሸፉ የሚያስቆጫቸው መሆኑም ይገባናል፡፡ ለዴሞክራሲ ለውጥ የተያዘውን ፖለቲካዊ መተባበር በዚህ ዓይነቱ የ‹ትምክህት› ክስ ሰርስሮ መበታተን አንዱ ትልቅ ተረተር ነው፡፡

ከዚህ ጋር በጎን የሚገናኝና በብዙ ነገር የሚጣጣም አንድ ላይ ፈስሶ ቡድኖችንና ብሔረሰቦችን በተለይም ኦሮሞነትን፣ ትግሬነትንና አማራነትን በጥላቻዊ ዘለፋና ብሽሽቅ አንጨርጭሮና ተስፋ አስቆርጦ “አገሬ ብሔሬ ብቻ” የሚል ጉድጓድ ውስጥ እንዲንከባለሉ በማድረግ ላይ የሚተጋ ሌላ ትልቅ ተረተር አለ፡፡ በዚህ ተረተር ውስጥ ምን ምን ይንቆረቆራል?

አዴፓ የኦዴፓ ተላላኪ/ዓብይ መሪውን የሚሾምለት፣ የሥልጣን ተቁለጭላጭና የአማራ አስጠቂ ተደርጎ እንዲታይ ማድረግ፣

የትኛውም የአማራ ድርጅት ትምክህተኛነት/ነፍጠኛነት አይፀዳው ተድርጎ በተለይ በኦሮሞ ዘንድ እንዳይታመን ማድረግ፣

አማራው ኦሮሞውንና ኦዴፓን ለራሱ ሥልጣን ያግበሰበሰ፣ ያው ሕወሓት ይሠራ የነበረውን የሚሠራ፣ ብሔርተኛ አድሎኛነትና ፀረ አማራ ጥላቻ አይጠራው አድርጎ እንዲያስብ ማድረግ፣

ከዚሁ ጋር በአማራ ክልል ውስጥ ብሔረሰባዊና ጎጣዊ ጥቅሜ ተጎዳ የሚል ክፍፍል እንዲተባ ማድረግ፣

ሕወሓት ላይ ያለ የሌለ የጥላቻ ወገራ ማሞቅ፣ ሕወሓትንና ትግራይን አንድ አድርጎ በሕወሓት ላይ የደረሰውን መገፋት በሕወሓት ላይ የሚካሄደውን ወገራ ሁሉ በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚካሄድ የጥቃት ዘመቻ ማድረግ፣

የትግራይ ሕዝብ በዚሁ ተንገፍግፎ ትግራይን የኢትዮጵያ አገሩ አንድ አካል አድርጎ ከማየት እንዲወጣ ማድረግ፣

ሕወሓትን በበደል የሚነቅፉ ትግራዊ ቡድኖች የትግራይን ሕዝብ የካዱ ተደርገው እንዲታዩ (የትግራይ ሕዝብ የፖለቲካ አማራጭ አድርጎ እንዳያያቸው) ማድረግ፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያን እንደ አንድ አገር ሊያቆሙ የሚያስችሉ ክሮችን መበጣጠስ ሁሉንም ተረተሮች የሚያገናኝ መነሻ ነው፡፡ ይህን ቡድንና ብሔረሰብ የሚተናኮለው እንቶኔ ነው፣ ያኛውን የሥራ ድርሻ የተያያዘው እከሌ ነው ብሎም መለየት አይቻልም፡፡ አንዱ የሌላውን ሌላውም የዚያኛው ሥራ ይሠራል፡፡ አንድ ሰው ለትግሬም፣ ለኦሮሞም፣ ለአማራም አሳቢ መስሎ ቁስል የምታሳድግ፣ ጥላቻና ጥርጣሬን የምታጠልቅ ነገረ ሊሠራ ይችላል፡፡ ዋናው መርዘኛ ሥራ የሚካሄደው በጥቂት ነገር ሠሪዎችና ቅጥረኞቻቸው ነው፡፡ ዋና መድረካቸው ደግሞ በሐሰት ስምና አድራሻ ማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም ነው፡፡ ጥቂቶቹ ሴረኞች ማር የተቀባችና ተቆርቋሪ መስላ የምትማርክ ወይም ብሔሬ ወገኔ ተዘለፈ/ተዋረደ አስኝታ የምታቃጥል መርዝ ጣል ያደርጋሉ፡፡ አልነቄዎች እያፈሱ ይውጣሉ፣ ያዛምታሉ፡፡

በዚህ ጥቃት ውስጥ ዋናዎቹ ሰለባዎች ደግሞ በመላ ኢትዮጵያ ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት ከዓለም ሥልጣኔ የመቀላቀል ምኞት ሟሟያ ሆኗቸው፣ በዚህ አመለኛታቸው የሚኮሩና የሚረኩ፣ ጆሯቸው ላይ መድፍ ቢተኮስ ለመስማት የማይፈቅዱ፣ ማኅበራዊ ማህፀናችን ሰብዕናቸውን ወሸከሬ አድርጎ ያጎሳቆላቸው ወጣቶቻችን ናቸው፡፡ የማነበው ሐሰት ነው አይደለም? መርዘኛ ነው ጤናማ ነው? ላወራው/ላጋራው የሚገባ ነው አይደለም? ብሎ መቆጠብ የለም፡፡ መርዘኛ የብሽሽቅ መድረክን አኩርፌ ላምክን የሚል ጥንካሬ የለም፡፡ መርዘኛ ፍተላና ስድብን አፍሶ በንዴት እየጦፉ ወይም በሳቅ እየተንከተከቱ ያዛምታሉ፡፡ በአፀፋ ደሞ የራሳቸውን ፍተላና ስድብ እያዋጡ ይለጥፋሉ፡፡ በዚህም ሳቅ ያዋጡ፣ የብሔር ወገናቸውን የጠቀሙ/በቀሉን የተበቀሉ እየመሰላቸው አንጀታቸውን ቅቤ ያጣጠሉ፡፡ በተግባር ግን ለጥቂት መሠሪዎች ሥውር ጣትና አፍ ሆነው ማገልገላቸውን አይረዱትም፡፡ የአገራችን ጣጣ እዚህ ድረስ ደርሷል፡፡

የአገር መበጣጠስ፣ የሕዝቦች መበታተንና የደም አበላ የሚጀምረው በጥይትና በገጀራ በመከታከት አይደለም፡፡ ‹ሀ› ብሎ የሚጀምረው ጥርጣሬን፣ መናናቅን፣ ጥላቻንና በቀልን በሚወራወር አሉባታ በመከታከት ነው፡፡ ለዚህ ነው ሳንበላላ በቶሎ መባነን ያለብን!!!

     ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...