ዳንኪራ የተሰኘውን አዲስ ምርት አስተዋወቀ
በኢትዮጵያ አንጋፋ የወይን ጠጅ ጠማቂ የሆነው አዋሽ ወይን ጠጅ አክሲዮን ማኅበር በአዲስ አበባ መካኒሳ በሚገኘው ፋብሪካው በሁለት ሚሊዮን ዶላር ያስገነባውን የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ አስጀመረ፡፡
የኩባንያው ኃላፊዎች ማክሰኞ ነሐሴ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሁለት ዓመት የፈጀው የአዲስ ፋብሪካ ግንባታ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደወጣበትና የፋብሪካውን የማምረት አቅም በሦስት እጥፍ እንደሚያሳድግ አስታውቀዋል፡፡
የአዋሽ ወይን ኮሜርሻል ዳይሬክተር ኔል ካምፎርድ ኩባንያው በፋብሪካውና በምርቶቹ ላይ ኢንቨስት እያደረገ እንደሆነ ገልጸው፣ የማኅበረሰቡን ሕይወት ለማሻሻል ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አዲስ የተገነባው ፋብሪካ ማሽኖች ከጀርመን፣ ከጣሊያንና ቻይና እንደመጡ ገልጸው፣ በአጠቃላይ የማስፋፊያ ሥራው የፋብሪካውን የማምረት አቅም በሦስት እጥፍ ለማሳደግ እንዳስቻለ ገልጸዋል፡፡ የፋብሪካው የወይን እርሻ በሚገኝበት አርሲ ዞን መርቲ ወረዳ ለሚገኘው ማኅበረሰብ በምግብ ዋስትና፣ በጤናና በንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት በማገዝ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1956 የተቋቋመው አዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካ በመካኒሳና በልደታ ሁለት ፋብሪካዎች ሲኖሩት፣ በአርሲ ዞን መርቲ አካባቢ 517 ሔክታር የወይን እርሻ ባለቤት ነው፡፡ በመካኒሳ በሚገኘው ፋብሪካ የተካሄደው የማስፋፊያ ፕሮጀክት አዲስ የማምረቻ መስመር፣ የጠርሙስ ማጠቢያ፣ መሙያና የቆርኪ መክደኛ ማሽኖች አካቶ የያዘ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የመካኒሳ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ እዮብ አሳምነው አዲስ የተገነባው የማምረቻ መስመር ከጀርመን፣ ከጣሊያንና ከቻይና በተገዙ ዘመናዊ ማሽኖች መገንባቱን ገልጸው፣ ፋብሪካው በ750 ሚሊ ሊትር በሰዓት 9,000 ጠርሙሶች፣ በ330 ሚሊ ሊትር 11,000 ጠርሙሶች እንደሚያመርት ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው በቀጣይ የማስፋፊያ ሥራዎች እንደሚያከናውን የገለጹት አቶ እዮብ፣ በዚህ ዓመት ለሚካሄዱ የማስፋፊያ ሥራዎች 70 ሚሊዮን ብር በጀት እንደተያዘ ጠቁመዋል፡፡ አዋሽ ወይን ጠጅ ቀደም ሲል የኤክስፖርት ሥራ ልምድ እንደነበረውና ላለፉት ጥቂት ዓመታት ምርቱን ወደ ውጭ መላክ አቋርጦ እንደነበር ገልጸው፣ ምርቶቹን እንደ አዲስ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የገበያ ጥናት በማካሄድ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የአዋሽ ወይን ጠጅ አክሲዮን ማኅበር እ.ኤ.አ. በ2013 ወደ ግል ከዞረ በኋላ ኩባንያው መርቲ በሚገኘው 517 ሔክታር የወይን እርሻ ላይ የማስፋፊያ ሥራዎች ማከናወኑን፣ አዲስ አበባ መካኒሳና ልደታ በሚገኙት ሁለት ፋብሪካዎች የወይን መጥመቂያ፣ ማጣሪያና ማጠራቀሚያ ማሽኖች በመትከል የወይን ጠጅ የማምረት አቅሙን በዓመት ከስድስት ሚሊዮን ሊትር ወደ 30 ሚሊዮን ሊትር እንዳሳደገ ተገልጿል፡፡ ኩባንያው በሁለቱም ፋብሪካዎች የፍሳሽ ማጣሪያ በማስገንባት ላይ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በዕለቱ ኩባንያው አምርቶ ለገበያ ያቀረበውን ዳንኪራ የተሰኘ አዲስ የወይን ምርት ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች አስተዋውቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ለገበያ የቀረበው አዲስ የወይን ምርት ዳንኪራ የወይን ኮክቴል በመባል ይታወቃል፡፡ በ330 ሚሊ ሊትር ጠርሙስ በቆርኪ ክዳን ታሽጎ የቀረበው የወይን ኮክቴል ሁለት ዓይነት ጣዕሞች አሉት፡፡
የካታጎሪ፣ ኢኖቬሽንና ብራንድ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ብርሃን መንግሥቱ ስትሮቤሪ ማርጋሪታና ፒች ቮድካ በሚል ስያሜ የቀረበው ዳንኪራ የወይን ኮክቴል ምርት፣ የደረቅ ወይንና የተፈጥሮ ፍራፍሬ ጣዕም እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ስድስት በመቶ የአልኮል ይዘት ያለው ዳንኪራ የወይን ኮክቴል ጋዝ ያለው ለስለስ ያለ የአልኮል መጠጥ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከሁለት ዓመት በፊት ባካሄድነው ጥናት ደንበኞቻችንን ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ጠይቀናቸው ባገኘነው ምላሽ መሠረት ያመረትነው አነስተኛ የአልኮል ይዘት ያለው ለስለስ ያለ የአልኮል መጠጥ ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ ብርሃን፣ ምርቱ ወደ ገበያ ከገባ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከተጠቃሚዎች ጥሩ ግብረ መልስ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
የ75 ዓመታት ዕድሜ ያለው የአዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካ በታዋቂው የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝና በግብረ ሰናይ ተግባሩ የሚታወቀው ቦብ ጌልዶፍ የሚመራው ኤይት ማይልስ የተሰኘው ኩባንያ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያዊው ባለሀብት አቶ ሙሉጌታ ተስፋ ኪሮስ ኩባንያው የሆነው ብሉናይል ኢንቨስትመንት በጋራ በ470 ሚሊዮን ብር እንደገዙት ይታወሳል፡፡