Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አዲሱን የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ደንብ ማስፈጸሚያ መመርያ አስተያየት...

ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አዲሱን የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ደንብ ማስፈጸሚያ መመርያ አስተያየት እንዲሰጥበት ለተቋማት ላከ

ቀን:

ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀውን የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ደንብ ማስፈጸሚያ መመርያ አርቅቆ፣ ለክልሎችና ለተለያዩ ተቋማት አስተያየት እንዲሰጡበት አሠራጨ፡፡

ከአሁን ቀደም ከ40 ዓመታት በላይ ሲሠራበት የቆየውን የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ከዘጠኝ ደረጃዎችና ከአሥራ ሁለት እርከኖች ወደ ሃያ ሁለት ደረጃዎች ብቻ በመወሰን፣ እያንዳንዱ ደረጃ ከአንድ እስከ 12 የሚደርሱ መደቦችን እንዲይዝ የሚያደርገውን ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው ከሳምንት በፊት ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መመርያው ከአሁን ቀደም በመንግሥት ተወስነው ይሠራባቸው የነበሩ ከ70 በላይ የደመወዝ ስኬሎችን ወደ አንድ ስኬል የሚቀይር ሲሆን፣ ቀድሞ የነበረው ስኬል ይሠራበታል ቢባልም በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተለያዩ ስኬሎች በመኖራቸው፣ ከ150 በላይ እንዲሆኑ ያደረገውን አሠራርም ይለውጣል፡፡

በዚህም መሠረት በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ለተመሳሳይ ሥራዎች የተለያዩ ክፍያዎች ይፈጸሙ ስለነበር፣ የክፍያ ኢፍትሐዊነት እንዲንሰራፋ በማድረጉና ለእኩል ሥራዎች እኩል ክፍያ የሚያጎናጽፈውን ሕጋዊ መብት ወደ ጎን ያለ አሠራር ነበር ተብሎ የቀድሞው ይተቻል፡፡ አዲሱ የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን በአገር አቀፍ ደረጃ  ሥራዎችን በመስፈርት በመመዘን፣ እኩል የሆኑ ሥራዎች እኩል ክፍያ እንዲያገኙ ያስችላልም ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት ሠራተኞች የተሻለ ክፍያ ለማግኘት ያለ መደብና ደረጃ ለውጥ ከአንድ መሥሪያ ቤት ወደ ሌላው መሥሪያ በት ይዘዋወሩ እንደነበር ለሪፖርተር የገለጹት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ፣ አሁን ግን በደመወዝ ምክንያት የሠራተኞችን ከመሥሪያ ቤት መሥሪያ ቤት መቀየር ያስቀራል ብለዋል፡፡

‹‹አንዱ መሥሪያ ቤት ልምድ ያለው ሠራተኛ ስለሚፈልግ ከሌላው መሥሪያ ቤት ሠራተኛው በመልቀቅ ነው ወደ አንዱ የሚሄደው፡፡ ምክንያቱም ጥቂት የተሻለ ክፍያ ለማግኘት፡፡ በዚህም ሳቢያ ያለውን ሠራተኛ እየተፈራረቁ ከመጠቀም በዘለለ አዲስ ኃይልና ሠራተኛ እንዲገባ ዕድል የለም ነበር፡፡ አሁን ግን የሥራ ቦታ ምቾትና ሌሎች ምክንያቶች ገፍተውት ካልሆነ በስተቀር፣ ሠራተኛ በደመወዝ ምክንያት መሥሪያ ቤት አይቀይርም፤›› ሲሉም አቶ በዛብህ አስረድተዋል፡፡

ለአዲሱ ደንብ ተግባራዊነት የሚረዳ የምዘናና ምደባ ሰንጠረዥ ተዘጋጅቶ ለመሥሪያ ቤቶች የሚበተን ሲሆን፣ ይኼ ሰንጠረዥ ያልደረሰው ተቋም ምደባ ማከናወን አይችልም ተብሏል፡፡

ከአሁን በኋላ መሥሪያ ቤቶች ልዩ ስኬል መጠየቅ እንዳይችሉ በደንቡ ሲታገዱ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ሠራተኞች ስኬል ግን ከአሁን ቀደም እንደነበረው በልዩነቱ ይዘልቃል፡፡

በበፊቱ አሠራር ግድፈቶች ሳቢያ በመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ የተደነገገው በውጤት ላይ የተመሠረተውና በየሁለት ዓመቱ እንዲሰጥ በተቀመጠው የደመወዝ እርከን ዕድገት ሳይሰጥ የቆየ ሲሆን፣ አዲሱ ደንብ ግን ይኼ ዕድገት በየሁለት ዓመቱ እንዲሰጥና እንዳይቋረጥ ያደርጋልም ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...