Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሁለት የፖሊስ ባልደረቦች በፈጸሙት ሕገወጥ ድርጊት ፖሊስ ኮሚሽን ይቅርታ ጠየቀ

ሁለት የፖሊስ ባልደረቦች በፈጸሙት ሕገወጥ ድርጊት ፖሊስ ኮሚሽን ይቅርታ ጠየቀ

ቀን:

ድርጊቱ በአሥር ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ተጠቁሟል

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ሁለት የፖሊስ አባላት ጎፋ ቄራ ማዞሪያ አካባቢ ባደረሱት ሕገወጥ ድብደባና የጥይት ተኩስ ምክንያት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሚሽን የአካባቢውንና የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ይቅርታ ጠየቀ፡፡

ነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ልዩ ቦታው ጎፋ ቄራ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ የፖሊስ ባልደረባ በቁጥጥር ሥር ያዋለውን ግለሰብ ሲደበድብ፣ ሌላው ባልደረባው ደግሞ በያዘው ጠብመንጃ ወደ ላይ ሲተኩስ የሚያሳይ የቪዲዮ ምሥል በማኅበራዊ ትስስር ተለቆ  ነበር፡፡

በቪዲዮው ላይ እንደታየው አንደኛው ፖሊስ የቆመ ተሽከርካሪ ሥር እጆቹን በካቴና የታሰረን ግለሰብ ደጋግሞ በቡጢ ሲደበድብ፣ ድብደባውን በመቃወም ሲከላከሉ የነበሩ እናትን ሲገፈትራቸው ተስተውሏል፡፡

ድርጊቱን በሚመለከት በርካታ የማኅበራዊ ትስስር ተጠቃሚዎች በተለይ ከፖሊስ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ተቋሙን ሲወቅሱ ተስተውሏል፡፡ ፖሊስ ከሕዝቡ ጋር ተባብሮና አንድ ሆኖ የከተማውን ሰላምና ፀጥታ ከተለያዩ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎች መቆጣጠርና ነዋሪዎች ያለ ፍርኃትና መሳቀቅ ወጥተው እንዲገቡ ማድረግ ሲገባው፣ ድብደባ መፈጸሙና ጥይት መተኮሱ ነውርና ተገቢ ያልሆነ ድርጊት መሆኑን በርካታዎች አስተያየት እየሰጡበት ነው፡፡

ፖሊሶቹ ፈጽመውታል የተባለው የድብደባ ድርጊትና የጠመንጃ ተኩስ በተመለከተ ጥያቄ የቀረበለት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሰጠው ምላሽ ይቅርታ ጠይቋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ እንደገለጹት፣ ድርጊቱን የፈጸሙት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ አባላት ናቸው፡፡ ኮንስታብል ቴዎድሮስ መላኩና ኮንስታብል ያሲን ሁሴን እንደሚባሉም ገልጸዋል፡፡ ፖሊሶቹ በአካባቢው ወረዳ ስድስት ጎፋ ቄራ ማዞሪያ በሚባለው አካባቢ ተመድበው እየሠሩ እያለ፣ በአካባቢው የሚኖሩና ለንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች በኮሚሽን ምክንያት መጣላታቸውን ገልጸዋል፡፡

ነጋዴዎቹ ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተው ግብር እየገበሩ የሚሠሩ የአካባቢው ነዋሪ መሆናቸውን በመግለጽ ብቻ፣ ሌሎች በኮሚሽን የሚሠሩትን እንዳይሠሩ ለመከላከል ሲሞክሩ፣ አለመግባባቱ ተካሮ ፀብ መነሳቱን ኮማንደር ፋሲካ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ፖሊሶቹ ‹‹የማትግባቡ ከሆነ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መሄድ አለባችሁ›› ሲሉ፣ በሥፍራው የነበሩትን ሴት ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪ መሆናቸውን የሚገልጹ ግለሰቦች፣ ‹‹ለፖሊስ አንታዘዝም›› በማለታቸው ከፖሊሶቹ ጋር መጋጨታቸውን አስረድተዋል፡፡

ፖሊሶቹ ማድረግ የሌለባቸውን ድርጊት በስሜታዊነት መፈጸማቸውን የጠቆሙት ኮማንደር ፋሲካ፣ ይህ በፍፁም መሆን ስላልነበረበት ኮሚሽኑ ይቅርታ መጠየቁንም ገልጸዋል፡፡ ፖሊሶቹም በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡

ተቀርፆ የተለቀቀው ምሥል ሙሉ በሙሉ የድርጊቱን መነሻ እንደማያሳይና መጨረሻ አካባቢ ያለውን ድርጊት ብቻ የሚያሳይ በመሆኑ፣ ጥፋቱ ሙሉ በሙሉ የፖሊሶቹ አስመስለው እንጂ ሙሉው ተቀርፆ ቢተላለፍ ኖሮ ሕዝቡም በቀላሉ ሊፈርድ ይችል እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ምንም ይሁን ምንም የፖሊስ አባላቱ ግን እንደዚያ ዓይነት ተግባር መፈጸም እንዳልነበረባቸውና ስህተት መሆኑን ኮማንደር ፋሲካ  አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ኮሚሽኑ ይቅርታ መጠየቁን አክለዋል፡፡

ፖሊሶቹ በ2010 ዓ.ም. እና በ2011 ዓ.ም. ከተመረቁ መካከል በመሆናቸው ከሕዝቡ ጋር እንዴት ተባብረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ልምድ እንደሚያንሳቸው አንድ አስተያየት ሰጪ ለሪፖርተር ጠቁመው፣ በዚሁ ከቀጠሉ የሰው ሕይወት ላይም አደጋ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ አንድ ፖሊስ የሚጠበቅበትን ዲሲፕሊን እንዴት ሊከተሉ እንደሚገባ በቂ ሥልጠና ልምድ ባካበቱ ፖሊሶች መሰጠት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አደይ አበባ ድርና ማግ ፋብሪካ አካባቢ አቶ ኢሳያስ መኩሪያ የተባለ ጋዜጠኛ፣ የባቡር ሐዲድ በማቋረጥ ላይ እያለ አንድ የፖሊስ አባል በመሣሪያ ጉዳት ሊያደርስበት ሲል ሌላ የፖሊስ አባል እንዳዳነውና ይህንን ድርጊት ለከተማው ምክትል ከንቲባና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በማሳወቁ፣ ኮሚሽኑ ድርጊቱን ኮንኖ ይቅርታ እንደጠየቀው ተናግሯል፡፡ ጉዳት ሊያደርስበት የነበረው የፖሊስ አባልም በኮሚሽኑ ኃላፊዎች እንዲቀርብ ተደርጎ አቶ ኢሳያስን ይቅርታ እንደጠየቀውና የኮሚሽኑም ጅምር ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ ምሥጋናውን ማቅረቡን አቶ ኢሳያስ አስረድቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...