Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ቁማር መጫወት ክልክል ነው!

  ኢትዮጵያን ሁሌም ወደኋላ የሚጎትታት ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ የተሳነው አስተሳሰብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ ብትሆንም፣ የዘመኑ ሥልጣኔ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ እጅግ በጣም የወረደ እርከን ላይ ናት፡፡ ትምህርት የሥልጣኔ መግቢያ በር ቁልፍ መሆኑ ቢታመንበትም፣ በኢትዮጵያ ግን ከቋንቋና መሰል ችግሮች ጋር በተያያዘ የልዩነት ማዕዘን ድንጋይ እንዲሆን እየተደረገ ነው፡፡ ትምህርት ከየትኛውም ዓይነት የፖለቲካ ጫና ውጪ በነፃነት መመራት ሲገባው፣ የብሽሽቅ ፖለቲካ ሰለባ ሲሆን ማየት ያሳዝናልም፣ ያሳፍራልም፡፡ የዘመኑን ፈጣን የቴክኖሎጂ ግስጋሴ በመጠቀም አትራፊ መሆን የሚቻልባቸውን አማራጮች ማየት ሲገባ፣ አክሳሪ ድርጊቶች ውስጥ መገኘት ያሳፍራል፡፡ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በደቡብ ኮሪያ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ደቡብ ኮሪያ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ግዙፍ የሆነው የሳምሰንግ ሞባይልና የኤሌክትሮኒክስ አምራች ድርጅት ባለቤት ናት፡፡ በትልልቅ የኢንዱስትሪ ምርቶች ታዋቂ ናት፡፡ በሥልጣኔ ወደፊት የተራመደች በመሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ሥፍራ አላት፡፡ ከዛሬ 68 ዓመታት በፊት ሁለቱ ኮሪያዎች ጦርነት ሲጀምሩ፣ ከአፍሪካ ብቸኛው የሰላም አስከባሪ ኃይል የተሰማራው ከኢትዮጵያ ነበር፡፡ ለአምስት ዓመታት 6,037 ወታደሮችን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር በሰላም አስከባሪነት ያሠለፈችው ኢትዮጵያ፣ ወታደሮቿ ወደር በሌለው ጀግንነት ለከፈሉት መስዋዕትነት በኮሪያ የመታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ እንኳን በሕይወት ያለ አስከሬን ያልተማረከባት ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ እንደነበረች ዓለም ያውቀዋል፡፡ ይህች ታላቅ አገር ኢትዮጵያ ዛሬ ከኮሪያ ጋር ስትነፃፀር ያለችበት ደረጃ ያሳዝናል፡፡ ከማሳዘን አልፎ ያንገበግባል፡፡

  ኮሪያ በጦርነቱ ከመውደሟ በፊት ምንም ያልነበራት አገር ብትሆንም፣ ከዚያ በኋላ ከጦርነቱ አመድ ውስጥ ወጥታ ታሪክ ለመሥራት ግን አልቸገራትም፡፡ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ክብር ያላቸው ኮሪያውያን፣ የዚያን ዘመን ውለታ ለመመለስ ብዙ ነገሮች ለማድረግ ሲጥሩ ይታያሉ፡፡ ቢያንስ የኢትዮጵያ ሁኔታ እያሳዘናቸው ሊደግፉን ይሞክራሉ፡፡ እኛስ ምን እያደረግን ነው? የኮሪያን ትውስታ ስናነሳ ራሳችንን መመርመር አለብን፡፡ ለዘመናት ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች እናት አገራቸውን ሲጠብቁ የኖሩትን አያት ቅድመ አያቶቻችንን እያሰብን፣ እኛም በዚህ ዘመን ድህነትን ድል በመንሳት የዘመኑን ሥልጣኔ መቋደስ ሲገባን፣ ዕርግማን ያለብን ይመስል በማይረቡ ነገሮች ለምን እንነታረካለን መባል አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆኖ በድህነት አለንጋ እየተገረፈ፣ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ዳተኛ ሆነን እንቀናጣለን፡፡ ልዩነቶቻችንን በሠለጠነ መንገድ መፍታት ሲገባን፣ የነገር ጅራፍ እያወናጨፍን እንደ ደመኛ ጠላት እንዛዛታለን፡፡ ዓለም በሥልጣኔ ጥሎን እየነጎደ እኛ በኋላቀር አስተሳሰብ ተዘፍቀን አገራችንን መቅኖ ቢስ እናደርጋለን፡፡ የኮሪያን ጉዳይ ከሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ጋር በምሳሌ አነሳን እንጂ ከጎረቤቶቻችን ሱዳን፣ ኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ወዘተ. ጋር ስንነፃፀር በርካታ ጉድለቶች አሉብን፡፡ እኛ የማይበላንን እያከክን አገራችንን እናደማታለን፡፡ እንኳን ለመጪው ትውልድ ቅርስ ልንተው ለዘመኑ ታዳጊዎች ምሳሌ መሆን እንደማንችል በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ያሳፍራል፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ ክፉና ደጉን አብሮ በማሳለፍ ለረዥም ዘመናት አኩሪ የሆነ ታሪክ አለው፡፡ ይህንን የመሰለ ፀጋ ባለቤት የሆነን ሕዝብን በአልባሌ ነገሮች በመከፋፈል፣ የድህነትና የኋላቀርነት መዘባበቻ ማድረግ ነውር ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የብልፅግና ማማ ማድረግ እየተቻለ፣ ይህንን ምስኪን ሕዝብ ሁልጊዜ ችግር ውስጥ መክተት ወንጀል ነው፡፡ ፖለቲከኞችና በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ስም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችም ሆኑ ሌሎች፣ የየዕለቱን ድርጊታቸውን ሊያስተውሉ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ አካሄዷ ካልተስተካከለ በርካታ ችግሮች እየተጋረጡ ነው፡፡ እንኳንስ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የአገር ህልውና አጠራጣሪ እየሆነ ነው፡፡ አገርን በወጉ መምራት የተሳናቸው ወገኖች፣ ዛሬ ተነስተው በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና በፌዴራሊዝም ስም ሲማማሉ ይገርማል፡፡ ከአገር ህልውና በላይ ለሥልጣናቸው ሲሟሟቱ እንዳልነበር፣ ዛሬ ተነስተው የአዞ እንባ ሲያፈሱ እንቆቅልሽ ይሆናሉ፡፡ ለሰላምና መረጋጋት መጥፋት እጃቸውን አስረዝመው የሚተጉ ኃይሎች፣ ራሳቸውን ከደሙ ንፁህ በማድረግ ሲቅበጠበጡ ያስደምማሉ፡፡ መሆን የነበረበት ግን ጥፋትን አምኖ መታረምና ለሕግ የበላይነት ተቆርቋሪ መሆን ነበር፡፡ አሁንም ጊዜው አልረፈደምና ራስን ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ለአገር ፋይዳ የላቸውም፡፡

  በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ምድር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ሊኖራቸው ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ፣ አሁን ተገልብጠው የቅራኔና የግጭት መንስዔ መሆናቸው ያስተዛዝባል፡፡ ለአገር አንዳችም የሚረባ አጀንዳ ሳይኖራቸው በእያንዳንዱ ጉዳይ ውስጥ እንደ እርጎ ዝንብ እየገቡ፣ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚተጉ ነውጠኞች እየተበራከቱ ነው፡፡ የሌሎች አገሮችን ፓስፖርት በመያዛቸው የከፋ ነገር ቢያጋጥም ወላፈኑ የማይነካቸው፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ህልውና ላይ ይቆምራሉ፡፡ ይህንን በአኩሪ መስተጋብሩ ዘመናትን የተሻገረ ሕዝብ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በእምነትና በመሳሰሉ ልዩነቶች ይፈታተኑታል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እየተፀየፉ ሕዝቡን እርስ በርስ ሊያባሉት ያሰፈስፋሉ፡፡ ከእነሱ ፍላጎት በላይ ለዘመናት በልጆቿ መስዋዕትነት እዚህ የደረሰች አገር እንዳለች እያወቁ፣ በሐሰተኛ ታሪኮችና የበደል ትርክቶች ንትርክና ግጭት ሲቀፈቅፉ ውለው ያድራሉ፡፡ አልተማሩም እንዳይባሉ የከፍተኛ ትምህርት ማስረጃዎችን ይዘዋል፡፡ ተምረዋል እንዳይባሉ ካልተማሩ ሰዎች በታች ነው የሚያስቡት፡፡ በዘቀጠ ሰብዕናቸው እንኳን ኢትዮጵያን ወደ ሥልጣኔ ሊወስዱ፣ እነሱም ሥልጣኔ ምን እንደሆነ አልገባቸውም፡፡ አሁን ወሳኝ ጊዜ ላይ ስለሆንን ግልጹን መነጋገር ይገባል፡፡ ኢትዮጵያና ሕዝቧን መታደግ የግድ ይሆናል፡፡ ለዚህም ሲባል የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡

  ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት፡፡ እነዚህን ችግሮች ለዓመታት የታቀፈች አገር ዘመኑን በሚመጥኑ መፍትሔዎች ካለችበት አረንቋ ውስጥ ማውጣት የግድ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ፋይዳ የሌላቸውና ለሕዝብ ዕድገት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ የማያመጡ ትርኪምርኪ ነገሮች ላይ ጊዜ ማጥፋት ለወቀሳ ይዳርጋል፡፡ ችግሮችን በመመካከርና በወንድማማችነት መንፈስ ለመፍታት አብሮ መሥራት ያስከብራል፡፡ ልዩነቶች ሲያጋጥሙም በሠለጠነ መንገድ መፍትሔ መፈለግ የሥልጣኔ ምልክት ነው፡፡ ችግር ባጋጠመ ቁጥር ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ አንደራደርም›› ማለት ያስተዛዝባል፡፡ በዚህ ምድር ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ቢኖር የአገር ህልውና ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉ ችግሮች በሙሉ የሚፈቱት በድርድር ነው፡፡ ድርድር የጠቢብ ፖለቲከኞች መሣሪያ ነው፡፡ የተዋጣላቸው የንግድና የኢንቨስትመንት ሰዎች ውጤታማ የሚሆኑት በድርድር ነው፡፡ ድርድር ከሌለ የሚከተለው ኪሳራ ነው፡፡ በፖለቲካ መስክ ደግሞ ግጭት ነው፡፡ በሕግ የበላይነት የሚመራ ሥርዓት ማቆም የሚቻለው በድርድር ምኅዳሩን ማስከፈት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የጉልበተኞችን መንገድ መምረጥ ሕገወጥነት ነው፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በድርድር የሚገነባ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ብቻ ነው፡፡ ከድህነትና ከኋላቀርነት ውስጥ ተምዘግዝጋ መውጣት ያለባትም በዚህ መንገድ ነው፡፡ ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አይቆመር የሚባለው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

  ‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...