በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በተለይ በዳኝነት ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ ከበቁት ጥቂቶች አንዱ ነበሩ። አቶ ተስፋዬ ገብረ ኢየሱስ ከሌሎቹ ለየት የሚያደርጋቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት መምራታቸው ነው፡፡ አልፎም የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) ፕሬዚዳንትም ነበሩ፡፡
አቶ ተስፋዬ በአፍሪካ እግር ኳስ የላቀ ስም ያሰጣቸው ሰባት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን፣ የዓለም ዋንጫንና የዓለም ወጣቶች ዋንጫ፣ እንዲሁም በሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ በዳኝነት መሥራታቸው ነው። አቶ ተስፋዬ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ራሷን የቻለች አገር ከሆነች በኋላ ብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽኗን በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡
ከዳኝነት በኋላ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እና የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ኢንስትራክተር በመሆን በርካታ ሙያተኞችን በማፍራት የሚታወቁት አቶ ተስፋዬ የተወለዱት በ1932 ዓ.ም. ሲሆን፣ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በ79 ዓመታቸው ነሐሴ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. አርፈው በማግስቱ ሥርዓተ ቀብራቸው በአስመራ መፈጸሙ ታውቋል፡፡ ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ሴካፋና ካፍ ሐዘናቸውን ገልጸዋል።