የክረምቱ መገባደጃ ብሔራዊ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨምሮ ክለቦችና በየደረጃው የሚገኙ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ባለፈው የነበረው ጠንካራና ደካማ ጎን ምን እንደሚመስል ውይይት አድርገው የሚዘጋጁበት ነው፡፡
ይሁን እንጂ ያ ሳይሆን ቀርቶ ከስፖርታዊ ጨዋነትና ከጊዜ ወደ ጊዜ ባልተጠበቀ ፍጥነት እየናረ ከመጣው የክለቦች በጀት ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ክለቦች ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ የክልል ክለቦች ደግሞ ከተጨዋቾች ወርኃዊ ክፍያ ጋር በተያያዘ አለመግባባቱ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
የ2012 ውድድር ዓመት እየመጣ ነው፣ የፕሪሚየር ሊጉ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ እንዴትና በምን ስሪት እንደሚቀጥል ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ከፌዴሬሽኑም ሆነ ከክለቦች የሚነገር አንዳች ነገር የለም፡፡ ሪፖርተር በዚህ ጉዳይ ያነጋገራቸውና በተለይም ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር ባለመግባባት የቀጠሉት የአዲስ አበባ ክለቦች እንደሚናገሩት ከሆነ፣ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አካሄድ አሁንም ደስተኛ እንዳልሆኑ ነው፡፡
በሌላ በኩል የክልልም ሆነ የአዲስ አበባ ክለቦች ምንም እንኳን ተጫዋቾች በወርኃዊ ክፍያቸው ጉዳይ ላይ ከቀጣሪዎቻቸው ጋር የደረሱበት የመፍትሔ አቅጣጫ ባይኖርም፣ አንዳንድ ክለቦች ተጨዋቾችን እንደተለመደው የፊርማና መሰል ጥቅማ ጥቅሞችን በመስጠት በዝውውር ገበያው እንደተጠመዱ ይነገራል።
ይሁንና ዝውውርን በሚመለከት ፌዴሬሽኑ አዲስ በፈጠረው አሠራር መሠረት ይህ የክለቦችና የተጫዋቾች ውል ሕጋዊ የሚሆነው በአዲሱ የተጫዋቾች የዝውውር መመሪያ መሠረት ፌዴሬሽኑ ሲያውቀው ብቻ ነው።