Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርፖለቲካን እንደ ቤተሰብ

ፖለቲካን እንደ ቤተሰብ

ቀን:

(ክፍል አንድ – አባት)

በሰለሞን መለሰ ታምራት

በርካታ ሰዎች ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር ወይም ሲገዛ የነበረው ኢሕአዴግ እንደሆነ ሲናገሩ ይገርመኛል፡፡ ኢሕአዴግ ተብለው የተደራጁት ሦስቱንም ፓርቲዎች እንዲመሠርቱ ሐሳቡን ያመጣው፣ ያደራጃቸውና የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ከመጻፍም በላይ ስማቸውንና መለያ ዓርማቸውን ሳይቀር መድቦላቸው አቅፎና ሰብስቦ የያዛቸው ሕወሓት አልነበረም እንዴ? አጋር ተብዬ ድርጅቶቹን ትተን እነዚሁ በኢሕአዴግ ጥላ ሥር የተመደቡት ሦስት ድርጅቶች ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴን (የከሰመውን ኢዴመአንን ጨምሮ) ሕወሓት የወደደውን ከሕወሓት በላይ ሲወዱ፣ ሕወሓት የጠላውንም ከሕወሓት በላይ ሲጠሉ አይደለም የከረሙት? ቁጭ በሉ ሲባሉ መቀመጥ፣ ተነሱ ሲባሉ ከመቆም ሌላ ምንም የሚሠሩት ነገር አልነበራቸውም፡፡ ድርሻችሁ ይኼ ነው ሲባሉ እጅ ስመው ከመቀበልና ከበሉት በላይ ዝቅ ብለው በማመሥገን ጀርባቸው የጎበጠ መከረኞች፣ የአባታቸው ፊት የጠቆረባቸው ቀን የሚከተለውን ስለሚያውቁ በወጡበት የሚቀሩ ነበሩ፡፡ ወለም ዘለም ሳይሉ ሕወሓት አድርጉ/በሉ ያላቸውን ሁሉ ያለምንም ይሉኝታና ኃፍረት ሲያስተጋቡ የኖሩ አቅመ ቢሶች እንደነበሩ፣ አይደለም እኛ መላው ዓለም የሚያውቀው ጥሬ እውነት ነው:: ልክ ዘመናትን የተሻገረ ታሪክ አስመስለን ልንረሳው ካልዳዳን በስተቀር፡፡

አንድ ሰው የወለዳቸው ልጆቹ ከትዕዛዙና ከፈቃዱ በማይወጡበት ሁኔታ ወይም ዕድሜ ውስጥ እያሉ ‹‹ነፃ ናችሁ እኮ፣ ካስፈለገም የራሳችሁን ዕድል በራሳችሁ የምትወስኑበትን ሁኔታ ፈቅጄላችኋለሁ፤›› ቢላቸው የት ይደርሳሉ? በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ የሆነውም ይኼው ነው፣ ሕወሓት ሦስት ልጆችን ወልዶ “ኢሕአዴግ” የሚል ካባ አለበሳቸውና ላለፉት 27 ዓመታት በአገሪቱ ላይ እንዳሻው ሲፈነጭ ሰነበተ፡፡ ማደግ አይቀርምና እነዚሁ ጉዶዮች ዕድሜያቸው ደርሶ የአባታቸውን ጫማ መለካት ሲጀምሩ ችግር ተፈጠረ፡፡ እንደ ጎልማሳ አባት ከሦስት ጎረምሳ ልጆቹ ጋር ተጣልቶ ሊያሸንፍ የሚችልበት ምንም ዓይነት ተዓምር ባለመኖሩ፣ ጥጉን ይዞ ከማስፈራራት የበለጠ አቅም አላገኘም፡፡ በእርግጥ ልጆቹ አባትነቱ በይሉኝታ ጠፍሯቸው እንጂ፣ ከዚህም የከፋ ጉዳት ሊያደርሱበት የሚችሉበት አቅም እንደሚኖራቸው ሳይታለም የተፈታ ህልም ነው፡፡ በተደጋጋሚ የምንሰማው ‹‹በጠላት ተከበናል፣ ልብ አድርጉልን ልንወረር ነው፤›› ጩኸቶች ከየትም የመጡ ሳይሆን፣ የዚሁ አቅም ማጣት የወለዳቸው የጣር ድምፆች ናቸው፡፡ አረረም መረረ እውነታው እንግዲህ ይኼው ነው፡፡

አባት በዚህን ጊዜ ሁለት አማራጮች ይኖሩታል፡፡ አንደኛው በልጆቹ ዘንድ ያልተወደደለትን ያለፈውን የመከራ ጊዜያት አስታውሶ በመፀፀትና ዳግም በዚህ ሁኔታ ለመቀጠል እንደማይፈልግ ማረጋገጫ በማቅረብ፣ ከልጆቹ ጋር ታርቆና አቅሙን አውቆ መኖር ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ምንም እንኳን ጉልበት ቢደክምም ልብ አይሞትምና በማንኛውም መንገድ የቆየ ክብሩንና ማንነቱን በማስጠበቅ ዳግም የአባትነት “ቆራጥ” አመራሩን ማስቀጠልና ልጆቹንም አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት፣ ለእነሱም ሆነ ለቀጣዩ ትውልድ የማይደፈርና ተቀናቃኝ የሌለውን ሥርዓት አስቀምጦ ማለፍ ይሆናል፡፡ በአጭሩ ለውጡን መቀበል ወይም በተገኘው መንገድ የተፈጠረውን አዲስ ሁኔታ ቀልብሶ ሁኔታዎችን በነበሩበት መንገድ ማስኬድ፣ ይኼው ነው፡፡

የአባትና የልጅ ትርክቱን ለቀደመ ጉዳያችን ማጠናከሪያነት ስናመጣው፣  ሕወሓት በአምሳሉ ቀርፆ የሠራቸው የግንባሩ አባላት ለዝንተ ዓለም በዚሁ የጌታና ሎሌ መንገድ መጓዛቸውን ስላልወደዱትና እንዲወክሉት በአደራ የተሰጣቸውም ማኅበረሰብ (በዘመኑ ቋንቋ ብሔር) ካደረሰባቸው ጫና በመነሳት፣ ኢትዮጵያን የሁሉም ኢትዮጵያዊ አገር እንድትሆንና ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እኩል ተጠያቂነትና ተጠቃሚነትም ጭምር ሊኖረን ይገባል ባሉት መሠረት የተፈጠረ የለውጥ ዕርምጃ ነው ዛሬ እዚህ ሊደርስ የቻለው፡፡ የሕወሓት አመራሮች የፈጠሩት እልህ መጋባት ጉዳዩን ከታሰበው በላይ አጦዘው እንጂ፣ በመሠረቱ የተከሰተው የለውጥ ፍላጎትና የተነሱትም የመብት ጥያቄዎች ተፈጥሯዊ በመሆናቸው፣ ከግንባሩ ውጪ ምንም ነገር ኮሽ ሳይል ሊፈታ የሚችል ተራ የዕለት ከዕለት ሥራ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ከሕወሓት ውጪ ባሉት ድርጅቶች መካከል የታየው መናበብና ወክለነዋል የሚሉት ሕዝባቸውም ያለማቋረጥ ባደረገው የሞት ሽረት ትግል ሕወሓት ወደ ጠርዝ እየተገፋ ከመምጣቱም በላይ፣ የተነሳውን ፍፁም ሰላማዊ ጥያቄ በጉልበት ለማፈን የሄደበት የጭካኔ ደረጃ ጉዳዩን ወዳልተጠበቀ የቀውስ አቅጣጫ ሊወስደው ችሏል፡፡

እንግዲህ በባሌም ተባለ በቦሌ የተጠበቀው ለውጥ ዕውን ሲሆን ነገሮች ባሉበት ሁኔታ መቀጠላቸው ያበቃል ማለት ነው፡፡ ለውጥ ማለት በአጭሩ አዲስ ነገር ማለት ነውና፡፡ ከእዚያም ባለፈ ባለፉት 27 የአገዛዝ ዘመናት የተፈጠሩ ሰብዓዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስህተቶች መታረም የሚኖርባቸው ሲሆን፣ ፈር ለቀው የወጡት የሕግና የሞራል ጥሰቶች ደግሞ ለወደፊቱም አስተማሪ ሊሆን በሚችል መልኩ በፍትሕ አደባባይ ሊታዩ የግድ ሆኗል፡፡ ሕወሓት ሁለተኛው ስህተቱን የሠራው እዚህ ላይ ነው፡፡ በቅድሚያ የመጣውን ለውጥ በጣም በቀላሉና ያለ ምንም መገዳደር ተቀብሎ ቢቻል፣ ሊታየው ያልቻለውን ጥፋት ያሳዩትን አጋር (ተቀፅላ) ድርጅቶቹን አመሥግኖ የለውጡም ሐዋርያ ሆኖ መቀጠል ይችል ነበር፣ ግን አልሆነም፡፡ በማስከተልም ያበጠው ለውጥ ፈንድቶ ሊደርስ የማይገባው ጥፋት ከደረሰ በኋላም ቢሆን፣ ሁኔታውን እንደ አመጣጡ ከመቀበልና የተፈጠረውንም ጠባሳ እንዲሽር ለማድረግ የራሱን ከፍተኛ ድርሻ ሊወጣ ሲገባ፣ ሊሆን የማይችለውን የ”ወደኋላ እንመለስ” ጥሪ ማቅረብና ያንን ያልተወደደ ዘመን መናፈቅ/መጋበዝ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደ መጥራት ነው፡፡

በአባትና ልጆች ምሳሌ ላሳየው የፈለግኩት ቁምነገርም የሚያሳየን ነገር ይህንኑ ነው፡፡ ሕወሓት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡበት ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለውጡን ቢቻል ለመቀልበስ፣ ካልተቻለም አንዳች ቀውስ ተፈጥሮ ነገሮች (አገሪቱም ብትሆን) እንዳልነበሩ የሚሆኑበትን አጋጣሚ ለመፍጠር በትጋት እየሠራ ይገኛል፡፡ ከላይ ልገልጸው የፈለግኩት አባት አቅመ ቢስነቱን ለመሸፈን የሚያሰማው የጣር ድምፅ ልጆቹን ለማስፈራራት ከሚጠቅመው ባሻገር፣ ሊረዱት የሚችሉ አካላት ከተገኙም አትኩሮታቸውን እንዲስብበት ያስችለዋል፡፡ በእርግጥም የሕወሓት የጩኸት ጥሪ በከንቱ አልቀረም፡፡ ከማንም ቀድሞ የደረሰለት ባለፉት 27 የሥልጣን ዓመታትና ከእዚያም ቀደም ሲል በነበሩት የትግል ወቅቶች፣ በጥብቅ ድርጅታዊ ዲሲፕሊን ተወጥሮ/ተጠፍሮ አንድ ዓይነት አመለካከት ብቻ እንዲኖረው በጥብቅ ሲሠራበት የነበረው የትግራይ ሕዝብ ነው፡፡ በበርካታ ምክንያቶች የትግራይ ሕዝብ ሕወሓትን አሳልፎ ሊሰጠው እንዳልፈቀደ የታየው ገና የለውጡ ንፋስ ሲነፍስ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚሰደዱ የክልሉ ተወላጆች ምክንያት የሚያሰማው ቁጣ በቀጥታ ያነጣጠረው፣ በለውጡ ደጋፊ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ላይ በመሆኑ ነው፡፡ የለውጡ አዝማሚያ ያላማራቸውና ሁኔታው ያሠጋቸው የሕወሓት አመራሮች ላለፉት በርካታ ዓመታት ለስብሰባ ሲሆን ብቻ ወደሚናፍቋት መቀሌ አንድ በአንድ መሰባሰብ ሲጀምሩ የሰጡት ምክንያት፣ ባለፉት ዘመናት የረሳነውን የትግራይ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ልናገለግለውና ልንክሰው ቆርጠን ተነስተናል የሚል ሆነ፡፡ ሕወሓት ይህንኑ ሰበብ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በማቅረብ ከወዳጅም ከጠላትም ታርቆ በሰላም መኖር ይችልበት የነበረው ዕድል እንዳመለጠው ቀደም ባለው አንቀጽ ላይ ጠቅሻለሁ፡፡ ምን ዓይነት ሞኝነት ነው ‹ዶሮዋን ትቶ እንቁላሉን ለማግኘት› የሚደረግ ሩጫ?

‘መጀመርያ የመቀመጫዬን’ አለች እንደተባለችው እንስሳ ማረፊያውን ያደላደለው ሕወሓት ወደ ቀጣዩ አስቸኳይና አጣዳፊ ሥራው ተሸጋግሯል፡፡ አዲሱን የለውጥ አስተዳደር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ዕረፍት ማሳጣት፡፡ ሕወሓትን በሊቀመንበርነት ይመሩ ከነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጀምሮ በተዋረድ ሲገለጹ ከነበሩት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው፣ ኢሕአዴግ/ሕወሓት ከሌለ ኢትዮጵያ የመበታተኗ ትርክት ዋነኛው በመሆኑ፣ ዛሬ ሕወሓት ገለል በተደረገበት ወቅት ይህች አገር ተረጋግታ ከተቀመጠች ለእስከ ዛሬው ችግር ሁሉ በምክንያትነት መጠርጠራቸው ያሠጋቸው የመቀሌዎቹ አዲስ ቤት ሠሪዎች፣ በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ከፍተኛ ቀውስ ለማራገብ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ሱማሌ ተብሎ የሚጠራውን ክልል እንዲመራ በጣም ዝቅተኛ ከሆነ የሥራ መደብ ተነስቶ የተመደበው ግለሰብ ለሕወሓት ከነበረው ከፍተኛ ቅርበትና የውለታ መላሽነት ጥማት የተነሳ፣ ለሕወሓት ከፍተኛ አመራሮችና ደጋፊዎቻቸው ወክሎናል ከሚሉት ከትግራይ ክልል በበለጠ የሚተማመኑበት፣ ከእዚያም አልፎ እንዳሻቸው የሚወጡበትና የሚገቡበት መደላድል ፈጥሮላቸው ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚም ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ እንደልቡ ይፈነጭ የነበረውንና በኋላም በአሸባሪነት የተፈረጀው ኦብነግን እንዲከላከል ታስቦ በከፍተኛ ደረጃ የታጠቀውን ‹‹ልዩ ኃይል›› የተባለ እጅግ በጣም አደገኛ ቡድንን ለመቆጣጠር ዕድሉን አግኝቷል፡፡ ይኼው የሶማሌ ልዩ ኃይል ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ የሕዝባዊ ትግሉ ዋነኛ መነሻ የሆነው የኦሮሚያ ክልልን ዕረፍት ለመንሳት በከፍተኛ ደረጃ ይንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን (ልክ ኢትዮጵያ በ60ዎቹ መጨረሻ ላይ በለውጥ ስትናጥ ዚያድ ባሬ አጋጣሚውን ለመጠቀም ካደረገው ሙከራ ጋር የሚመሳሰልና ከክልሉም አልፎ ቀጣናውን የማተራመስ ዕቅድ በሚመስል መልኩ)፣ ለውጡ ዕውን መሆኑ ሲታወቅ ሁለቱ ክልሎች ወደለየለት ጦርነት እንዲገቡ የተፈለገ በሚያስመስል ሁኔታ ግጭቶቹ ተባብሰው ቀጠሉ፡፡ ደግነቱ ለወትሮው ለሱማሌው ልዩ ኃይል ደጀን በመሆን ሲጠቃ የሚያስጥለውና ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ድጋፍ ሲቸረው የነበረው ኃይል በራሱ ጊዜ ጥጉን ይዞ ስለነበር፣ በዚህ ወቅት የሚደርስለት አጋር አልነበረውም፡፡ በኦሮሚያ ግንባር ያሰበው ያልተሳካለት የሶማሌ ልዩ ኃይል በቀጥታ ፊቱን ያዞረው በክልሉ ውስጥ ወደሚኖሩት የሌላ ክልል ተወላጆች ላይ ሲሆን፣ በተለያዩ ከተማዎች በሚገኙ ንፁኃን ዜጎችና የእምነት ተቋማት ላይ በመዝመት ዛሬ ዛሬ እየለመድነው የመጣነውን የሞትና የንብረት መጥፋት ዜና ሊያረዳን ቀዳሚው በመሆን ድርሻውን ተወጥቷል፡፡ በማዕከላዊው መንግሥት ጣልቃ ገብነት ሁኔታው ባይከሽፍ ኖሮ በወቅቱ ይሰማ እንደነበረው አካሄዱ ክልሉን እስከ መጨረሻው ከኢትዮጵያ ለመነጠል ያሰበ መሆኑም ብቻ ሳይሆን፣ በወቅቱ የደረሰው ጥፋትም እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡

ሕወሓት ከዚህ ሁሉ ግርግር ጀርባ እንዳለበት የሚያሳብቅ ሁኔታ የተፈጠረው የሶማሌ ክልል በፌዴራል መንግሥቱ የመከላከያ ኃይል ጣልቃ ገብነት ወደ ቀደመው ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ ተደርጎ፣ የነውጡ ዋነኛ አስተባባሪ ነው ተብሎ የተጠረጠረው የክልሉ ፕሬዚዳንት በቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት ‘ዲጂታል ወያኔ’ ተብለው በድርጅቱ በይፋ ዕውቅና ካገኙት የፕሮፓጋንዳ ክንፍ አባላቱ ዘንድ የታየው ጫጫታና የሕገ መንግሥት ተጣሰ “ክስ” ሲመጣ ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር ሕወሓት አገሪቱን በሚያስተዳድራት ዘመን አንድ የክልል አመራር የዚህን ያህል ርቀት በተቃውሞ ሊጓዝ ቀርቶ፣ በጣም በተራ ምክንያት ሊቆጥር የሚችለውን ፍዳ ቀደም ሲል በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በደቡብ ክልሎች ውስጥ በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ በነበሩት ግለሰቦች ላይ የደረሰባቸውን ዓይቶ መገመት ከባድ አይሆንም፡፡ ሕወሓት በሥልጣን ላይ ከሌለ ግን በአገርና በሕዝብ ላይ እንዲህ ዓይነት መከራ መጋበዝ እንኳን እንደ መብት የሚቆጠርበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በክልሉ ሕዝብ ላይ ለዘመናት ሲፈጸምበት የኖረው ሰቆቃም በተከታታይ በሰማናቸው የ“ጄል ኦጋዴን” ታሪኮች ይፋ ለመሆን ችለዋል፡፡

የደቡብ ምሥራቁ ግንባር ያደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ጠባሳው ለረጅም ጊዜ መሰንበቱ እንደተጠበቀ ቢሆንም፣ ይዞት የመጣው እጅግ የከፋ ጥፋት ዳግም እንዳይመለስ ተወግዶ ቀጣናው ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሁኔታው መመለስ በጀመረበት ወቅት ሕወሓት ሌላ ሲሳይ ዘነበለት፡፡ አዲሱ የለውጥ መንግሥት ቀደም ሲል በአገሪቱ ፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጁትን ጨምሮ ለሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች ባቀረበው የሰላም ጥሪ መሠረት፣ ፓርላማው በ2003 ዓ.ም. በተመሳሳይ ወቅት ያሳለፈውን የአሸባሪነት ፍረጃ በሰባተኛው ዓመቱ አነሳው፡፡ በዚህም መሠረት ኦነግ የተሰኘው ላለፉት 50 ዓመታት እወክለዋለሁ ለሚለው ሕዝብ በስሙ ምክንያት ከሚደርስበት መከራ ውጪ አንዳች ጠብ የሚል ፋይዳ ያልፈጠረለት ቡድን፣ ሕወሓት በሚቆጣጠረው በመቀሌ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ወሰነ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከኦነግ ባንዲራ አጠገብ ቆማችሁ ፎቶግራፍ ተነስታችኋል ተብለው ሰዎች በአሸባሪነት እንዳልተከሰሱ፣ ዛሬ የሕወሓት ትልቁ ሰውዬ የኦነግን ባንዲራ እያውለበለቡ የእንኳን ደህና መጣችሁ የምሳ ግብዣ ላይ ተገኙ፡፡

ኦነግ እንደ ሌሎቹ የቀድሞ “አሸባሪ” ድርጅቶች እግሩ ኢትዮጵያን በረገጠበት ሰሞን በአዲስ አበባና በቡራዩ የተፈጠሩትን ግርግሮች እንደ ክፉ አጋጣሚ ብንወስዳቸው፣ በቀጣዮቹ ወራት ላይ ያሳየውን አጉራ ጠናኝነት ግን እንዲሁ እንደ ዋዛ ልናልፈው አያስችለንም፡፡ በእርግጥ የለውጡ ኃይል ለሁሉም የተቃዋሚ ድርጅቶችና የፖለቲካ እስረኞች ያቀረበው የሰላም ጥሪ የቅድመ ሁኔታዎች ችግር ያለበትና ግልጽነት የጎደለው ቢሆንም፣ ሁሉም ቡድን ሰላምን የሚያይበት መነጽር የተለያየ በመሆኑ የተሰጣቸውን ዕድል የባለጉበት (Abuse) ጥቂት የማይባሉ ናቸው፡፡ ኦነግም በአገር ውስጥ ያሉ አባላቶቱን ትጥቅ እንዲያስፈታ ሲጠየቅ ‹‹ትጥቅ ፈቺም አስፈቺም የለም›› ከሚለው የንቀት መልስ ጀምሮ የራሳችን የሆነ ነፃ መሬት አለን እስከ ማለት ደርሶ ነበር፡፡ አንዳንድ ወዳጆቹም በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት መንግሥት ነው ያለው በማለት በይፋ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የደቡብ ምዕራቡ የአገራችን ክፍል ፍፁም አደገኛ ቀጣና (No-go Zone) ሊሆን በቅቷል:: በደቡብ ኢትዮጵያም የተለያዩ አካባቢዎች በተከታታይ የተከናወኑት ሕዝብን የማፈናቀል እንቅስቃሴዎች ለውጡን በሙሉ ልባቸው የደገፉትን ኃይሎች ሳይቀር አንገት ያስደፋ ክስተት ለመሆን ችሏል፡፡ ‹‹ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ውጪ ታሳድራለች›› እንደተባለው፣ ኦነግ ፈጽሞ አቅም ያጣ በመሰለው አዲሱ የለውጥ ኃይል ለሚያቀርብለት የ“አደብ ግዙ” ጥያቄ የሚሰጠው መልስ በጣም አስደንጋጭና ከመስመር የወጣ እየሆነ ቀጠለ፡፡ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ግራ መጋባት ያደረበት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ላወጣው መግለጫ ኦነግ ታኅሳስ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ያወጣው የአፀፋ ምላሽ የቅርብ ጊዜውን የሕወሓትና የአዴፓን የቃላት ጦርነት የሚያስንቅ ነበር፡፡ ይህንኑ ውዝግብና የኦነግን በድል ላይ ድል መንበሽበሽ የተመለከቱት የሕወሓት ቀኝ እጅ በመሆን የሚያገለግሉት የዲጂታል ወያኔ አባላትም፣ ኦነግ ከአዲስ አበባ በ70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝና በሦስት ወራት ውስጥ ሥልጣኑን እንደሚረከብ ለመተንበይ አስችሏቸዋል፡፡

ኦነግ በረጅም ጊዜ የትግል ታሪኩ ራሱን ችሎ ያመጣቸው ተጨባጭ ውጤቶች ካለመኖራቸውም በላይ፣ ዘወትር ጊዜ የሰጣቸውን ቡድኖች ተጠግቶ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ በብልኃት ሳይጠቀምበት እየቀረ በተደጋጋሚ ሲወድቅና ሲነሳ የከረመ ድርጅት ነው፡፡ ወር ተረኛ ነው ብሎ በሚያስበው ቡድን ጉያ በመሸጎጥ ዕድሜውን ሲገፋ የከረመ ድርጅት በመሆኑ፣ ገና እግሩን እንኳን በቅጡ ወደ አገር ውስጥ ሳያስገባ ደመኛ ጠላቱ በሆነው የኦሕዴድ ኃይል ላይ ብትሩን ለማሳረፍ በቂ የሞራል ስንቅ ከየት እንዳገኘ ሁኔታውን በአንክሮ ለሚመለከተው ሰው ግልጽ ነበር፡፡ በዝሆኑ ጀርባ ላይ የተሳፈረችው ዲምቢጥ ‹‹ድልድዩን አንቀጠቀጥነው›› አለች እንደተባለው፡፡ ውሎ አድሮ ኦነግን እሹሩሩ ማለቱ ከአቅሙ በላይ የሆነበት ማዕከላዊ መንግሥት ጠንከር ያለ ዕርምጃ መውሰድ ሲጀምር፣ በሽምግልና ብርታት ኦነግ አደብ ሊገዛ ችሏል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ አገሪቱን በአራቱም አቅጣጫ የማተራመስ ሩጫ በኋላ በቅርቡ እንደታየው ከኦነግ ጋር ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸውን የኦሮሞ ምሁራንን ወደ መቀሌ በመጋበዝ፣ የራሳቸውን ጠባብ አጀንዳ እንዲያራግቡ ዕድል ተከፍቶላቸዋል፡፡

ሕወሓት ከዚህ የለውጥ ሒደት የተማረው ትልቁ ቁምነገር በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙት ሁለቱ ታላላቅ ብሔረሰቦች መካከል ልዩነት እስካልተፈጠረ ድረስ ዳግም ወደነበረበት የሥልጣን መንበሩ ሊመለስ እንደማይችል መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ውሎ ሲያድር የትግራይ ሕዝብም ሊሰላችና ጠንካራ ድጋፉን ሊነፍጋቸው የሚችልበት ዕድል ሰፊ መኖሩን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለአማራው ሕዝብ ያላቸውን ከገደብ ያለፈ ምሬት (Resentments) በማንፀባረቅ የሚታወቁ የኦሮሞ ልሂቃንን በመቀሌ በማሰባሰብ፣ የማኅበራዊ ሚዲያውን ለማደናገር የሚሆን መጠነኛ የአጀንዳ ግብዓት አቅርበውና ለሕወሓት ደጋፊዎችም ከጎናችሁ ነን፣ አለንላችሁ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ዕድሉን እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በኦሮሚያ ብቻም ሳይሆን በቅርቡ በሲዳማ የክልል እንሁን ጥያቄ ላይም ሕወሓት ከጎናችሁ ነን መብታችሁ ሊከበርላችሁ ይገባል ከማለቱም በላይ፣ ላለፉት 20 ዓመታት ለጥያቄያቸው በጥይት መልስ ሲሰጣቸው የነበረው ኃይል ዛሬ አለሁላችሁ ከጎናችሁ ነኝ ማለቱ ከቀልድ ባለፈ ሊታይ የሚገባው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በ1994 ዓ.ም. የቀረበው የሲዳማ የክልልነት ጥያቄና ዛሬ የቀረበውን የሚለያቸው አንድና አንድ ምክንያት፣ ዛሬ ሕወሓት ከማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ተገፍቶ ወደ ዳር መውጣቱ ብቻ ነው፡፡ እናም ትናንት ፈፅሞ ሊሰማው የማይፈልገውን የክልል እንሁን ጥያቄ ዛሬ ዋነኛ የመብት ጉዳይ አድርጎ ከቆጠረው፣ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› ካለችው እንስሳ አነጋገር ተለይቶ እንዴት ይታያል?

ስናጠቃልለው ሕወሓት እንደ አባት ለቤተሰቡ (ለልጆቹ) ሊሰጣቸው ይገባ የነበረውን መብታቸውን እያፈነና የአባትነት ፍቅርና ወጉን ሳያሳያቸው ለዘመናት ሰንብቶ፣ ዛሬም ፅዋው ሞልቶ በሚፈስበት ሰዓት ላይ የቀረችውን እንጥፍጣፊ ዕድል በመጠቀም ፈንታ አጥፍቼ እጠፋለሁ በሚል ሥሌት አካሄዱን እንደ ቀጠለ በግልጽ ይታያል፡፡ ካልጠፋ ምርጫ የመጨረሻ ፍላጎቱ ይኼ ከሆነ ምን ይደረጋል? ታላቁ ባለ ራዕይ መሪው በአንድ ወቅት እንዳሉት ‘መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ’ ከማለት ውጪ፡፡ ከዚህ ሁሉ የሞት የሽረት ትግል ጀርባ ግን የሰው ሕይወትና የአገር ሀብት ያላግባብ እንዳይጠፋ፣ አዲሱ የለውጥ አመራር አተኩሮ ሊሠራ ይገባዋል፡፡ ሕወሓት እንደሆነ በተደጋጋሚ (ቢያንስ ለአራት ጊዜያት ከ1967 ዓ.ም. 1969 ዓ.ም. ከ1977 እና በ1993 ዓ.ም.) አበቃለት ሲባል አፈር እየላሰ ደጋግሞ መነሳትን የተማረ ድርጅት ነው፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ እንደታየውም የግርግሩ መንስዔ ሥልጣንን ከመሻት የሚመነጭ እንጂ፣ የተሻለ አስተሳሰብና ርዕዮተ ዓለም ይዞ ለመምጣት አይደለም፡፡ ላለፉት አርባ ዓመታት በላይ ያለ ዕረፍት በመቆየቱ የተዳከመው ድርጅትና አዛውንት አመራሮቹ ዛሬም ክፉኛ የአካልና የአዕምሮ መዳከም ቢታይባቸውም ትግላቸውን ቀጥለዋል፡፡ የአሁኑ ግን የተለየ ነው፡፡ ከሥልጣን ባለፈ እንደ ሰማይና ምድር የተራራቀ የአስተሳሰብ ልዩነት ይዞ በመጣና ከአብራኩ በተገኘ ኃይል ነው ክፉኛ በትር ያረፈበት፣ እናም የአባ ወራውን መጨረሻ የምናይበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...